ልጅ ሆኜ ስለምወደው እግርኳስ ሳስብ ትልቅ ደረጃ እንደምደደርስ ውስጤ ያምን ነበር… አስመራ እያለሁ በኤርትራ ሊግ ላይ ለአራት አመታት ተጫውቼ አራት ተከታታይ አመታት ዋንጫ አንስቻለሁ… ለሁለት ቡድኖችም ተጫውቻለሁ.. አስመራ ካለው የቀይ ባህር ቡድን ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ … ለኣርትራ ከ20 እና ከ23 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ለዋናውም ቡድን ለሴካፋና ለአለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጫውቻለሁ ሲል ይናገራል …በ12 ግብ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነትን እየመራ ያለው የኤርትራና የሀዋሳ ከተማ ተጨዋቹ አሊ ሱሌይማን….ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታም ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል።
ሊግ:– እንኳን ለበዓሉ አደረሰህ ..?
አሊ:– አመሰግናለሁ …ለመላው የሙስሊም ማህበረሰብ እንኳን አደረሳችሁ…አንተም ለሰጠኧኝ እድል አመሰግናለሁ።
ሊግ:– ጾሙ በሰላም አለፈ..?
አሊ:- አዎ አሪፍ ሆኖ አለፈ ዱአ እያደረግን በጥሩ ሁኔታ አልፏል የድሬዳዋ ጸሃይ ከበድ ብሎኝ ነበረ እንጂ ጾሙ አሪፍ ነበር ደስ ብሎኝ ነው ያለፈው… የመጀመሪያ ቀኑ ጾም ከበድ ብሎ ነበር ጸሃዩ ድካሙ በኋላ ላይ ግን ዝናብ ዘነበና አቀዘቀዘው..እንደ አጠቃላይ አሪፍ የጾም ጊዜ አሳልፌያለሁ… ጥሩ የጾም ጊዜ ነበረን..
ሊግ:- ተጨማሪ 6 ቀን ይጾማል…ቀጠልክ ወይስ..?
አሊ:– አይ አሁን አልጾምኩም። የጨዋታው ጊዜ እየጠነከረ ስለመጣና አገግሜ ለየጨዋታው መዘጋጀት ስላለብኝ 6 ቀኑን አልጾምኩም።
ሊግ:– ሀዋሳ ከተማ ቡድኑ ተመችቶሃል ..?
አሊ:- አዎ በጣም ተመትቶኛል… ከአምና ዘንድሮ ምርጥ ሆኖ ተሻሽሎ እንደ ግልም ጥሩ ሆኜ ቡድኔን ለማገዝ የምሰራበት ጊዜ ሆኖልኛል በቀሪ 9 ጨዋታ የተሻለውን ሀዋሳ ከተማን ለማሳየት የምችለውን እያደረኩ ነው የክለቡ አመራር፣ አሰልጣኞች፣ ተጨዋቾች፣ ደጋፊው ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ
ሊግ:- የሀዋሳ ከተማ ደጋፊን እንዴት አገኘኧው..?
አሊ:– በጣም ምርጥ ደጋፊ ነው …ሁሌ ከቡድኑ ጀርባ ሆኖ ድጋፍ ስለሚሰጠን ማመስገን እፈልጋለሁ..እነሱ የሚፈልጉትን የሚደሰቱበትን ለማድረግ እየጣርን ነው አላህ ይርዳንና እንደምናስደስታቸው ተስፋ አደርጋለሁ በጣም አከብራቸዋለሁ እወዳቸዋለሁ ይህን መግለጽ እፈልጋለሁ…
ሊግ:– በ12 ግብ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆነህ እየመራህ ነው ሀዋሳ ግን በ26 ነጥብና 3 የግብ እዳ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል…ግቦቸ የባከኑ አልመሰለህም ..? / ቃለምልልሱ የተሰራው ባለፈው ማክሰኞ ነው/
አሊ:– ኮከብ ግብ አግቢ ሆነህ ለመጨረስ ከማሰብ በፊትኮ የሚቀድመው የክለቡ ውጤት ነው በድኑን ከፍ የማድረግ ቀዳሚ ሃሳብ ነው ያለው ቀሪ 9 ጨዋታ ስላለ ግብ እያስቆጠርኩ እያሸነፍን ለመሃድ ስለምንጥር ጥሩ ውጤት ይመዘገባል ደረጃችንም ይስተካከላል ብዬ አምናለሁ…በዚህ ላይ ከ23ኛው ሳምንት ጀምሮ ሀዋሳ ላይ ስለሚካሄድ በሜዳችን ከሙሉ ደጋፊ ጋር የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ እኔም ቡድኑንም እንደማግዝ ተስፋ አደርጋለሁ ብዬ አስባለሁ።
ሊግ:- በግል አሪፍ ጊዜ እያሳለፍክ እንደሆነ ይሰማሃል..?
አሊ:– አዎ በግሌ አሪፍ ጊዜ ነው እያሳለፍኩ ያለሁት በዚህም ደስተኛ ነኝ ግን አሪፍ ያደረጉኝ የቡድን ጓደኞቼ ናቸው ያለነሱ አይሆንም እንደ ቡድን ጠንክረን የሚጠበቅብኝን አድርጌ የተሻለ ደረጃ እንደ ግልም እንደ ቡድንም እንደሚኖረኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እስካሁን ያለውም አሪፍ ነው በጥሎማለፉ ግማሽ ፍጻሜ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሚያዚያ 20/2016 የምናደርገውን ጨዋታ አሸንፈን ለፍጻሜ እንደምናልፍ ሙሉ የክለቡን ደጋፊ እንደምናስደስት ተስፋ አደርጋለሁ
ሊግ:– እግርኳስ ላንተ ምን ትርጉም አለው…?
አሊ:– በጣም የምወደው የምኖርበት ሙያ ነው፡፡ ስለምወደውና ስለማከብረው ነው የምጫወተው… የሚጠበቅብኝን ዲሲፕሊን ለማክበርም የበቃሁት የምኖርበትም ህይወታችንን የሚቀይር በመሆኑ ትልቅ ክብር አለኝ …እግርኳስ ህይወቴ ነው ብል ይቀለኛል፡፡
ሊግ:- ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጣህበትን ሂደት እስቲ አስታውሰኝ..?
አሊ:– መጀመሪያ የመለመለኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ነው የሴካፋ ኮከብ ጎል አግቢ ከሆንኩ በኋላ ለባህርዳር ከተማ እንድፈርም አደረገኝ እዚያ ከተጫወትኩ በኋላ አሁን ደግሞ ለሀዋሳ ሁለት አመት ፈርሜያለሁ ሰኔ 30/ 2017 ውሉ ይጠናቀቃል…
ሊግ:- የኮከብነቱ ልምድ አለህ…እዚህም ይቀጥላል ብለህ ታስባለህ..?
አሊ:-/ሳቅ/ ኢንሽሃላ …. እየሞከርኩ ነው ኮከብነቱ የስራ ውጤት በመሆኑ እጥራለሁ…. የሴካፋ ኮከብ ግብ አስቆጣሪነትን በፕሪሚየር ሊጉም ለመድገም እጥራለሁ…
ጠንከሬ እሰራለሁ..ከተሳካ ደስ ይለኛል ፉክክሩ ግን ቀላል አይደለም በጥቂት የግብ ልዩነት እየመራሁ ስለሆነ ጠንካራ ፉክክር ይኖራል ብዬ አምናለሁ ለማሳካትም ጠንክሬ እሰራለሁ።
ሊግ:– በ12 ግብ የኮከብ ግብ አስቆጣሪነትን እየመራህ ነው …ውስጥህ ኮከብ ለመሆን አልጓጓም….?
አሊ:- ውስጤ ይፈልጋል ለዚህም የምችለውን ለማድረግም ተዘጋጅቻለሁ ማንም ግብ ያስቆጥር ቅድሚያ ማሸነፍ ያለበት ክለቡ ነውና በቅድሚያ የምጥረው ለክለቡ ድል ነው.. እኔም ኢንሽሃላ ጥሩ አቋም ለማሳየት እጥራለሁ በርግጥ ለኮከብነት የሚፎካከሩ አጥቂዎች አሉና ጠንካራ ትግል እንደሚኖር አምናለሁ…ሀዋሳ ከተማ ከእኔ ጎል ይጠብቃል.. እኔም የሚጠብቅብኝን ለማድረግ እጥራለሁ።
ሊግ:- አብሬው ብጫወት የምትለው ተጨዋች አለ..?
አሊ:– ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች አሉ ሊጉ ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ያሉበት ነው… ከእነኚህ መሃል ከሽመልስ በቀለ ፣ መስዑድ መሃመድና አቡበከር ናስር ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል።
ሊግ:– ብጫወትለት ብለህ የምትመኘው ክለብ ነበር..?
አሊ:- /ሳቅ በሳቅ/ ሁሉም ክለቦች አሪፍ ናቸው አሁን ያለሁት ሀዋሳ ከተማ ነው በዚያ ደስተኛ ነኝ…
ሊግ:– የድሬዳዋ ሜዳ በጥራት አንድ ለእናቱ ሊባል ነውና ተመቸህ…?
አሊ:- አዎ በጣም አሪፍ ሜዳ ነው ተመችቶኛል ኳሷን ኮንትሮል ለማድረግ ለጓደኛ በትክክል ለማቀበልና የተጋጣሚ ተጨዋችን ለማለፍ ድሪብል ለማድረግ ሜዳው ተመችቶኛል… አሪፍ ሜዳ ነው ዝናብ ሲመጣ ለመቀባበል አልተቸገርንም የአዳማው ሜዳ መጥፎ አይደለም የድሬዳዋው ግን ይሻላል ብዬ አስባለሁ።
ሊግ:- የኛ ተጨዋቾች ጠንካራ ልምምድ አይወዱም ይባላል አንተስ በጠንካራ ልምምድ ታምናለህ ..?
አሊ:- አዎ በደንብ አምናለሁ…በጠንካራ ልምምድ የተሻለ ስራ ስትሰራ ነው የምትፈልገው ደረጃ መድረስ የምትችለውና ልምምድ ወሳኝ ነው ያለ ልምምድ ጠንካራ መሆን አይቻልም ለዚህ ደግሞ ክርስቲያኖ ሮናልዶን መመልከት በቂ ነው,,,, ከመደበኛ የክለብ ልምምድ በፊትና በኋላኮ በግሉ ጠንክሮ ይሰራል ጠንካራ ልምምዱ ጠንካራ ሰው አድርጎታልና ልምምድ የግድ ነው።
ሊግ:- የውጪ እድል ከተሻለ ሊግ ጥያቄ አልመጣም..?
አሊ:- እስካሁን አልመጣም በቀጣይ ግን እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ…ከፍ ባለ ደረጃ መጫወት እፈልጋለሁ..ጠንክሬም እሰራለሁ አሁን ግን እዚህ በመኖሬና እዚሁ በመጫወቴ ደስተኛ ነኝ እድሜና ጤና ከሰጠኝ ከጉዳት ከተረፍኩ ረጅም የመጫወቻ ጊዜ አለኝ።
ሊግ:- በእስካሁኑ 21 ጨዋታ ስታሸንፍ የተደሰትክበት ስትሸነፍ ቅር ያለህ በየትኞቹ ጨዋታ ነው …..?
አሊ:– በየትኛውም ጨዋታ መሸነፍ ያበሳጫል የምናጣው 3 ነጥብ ነው ስናሸንፍም የምናገኘው 3 ነጥብ ነው እንደ ፉክክር ግን ስናሸንፍ ደስ ያለኝ ጥሎ ማለፍ ላይ ሃትሪክ ሰርቼ መቻልን 3ለ0 ስናሸንፍ በጣም ተደስቻለሁ ሽንሸነፍ ደግሞ በጣም ያበሳጨኝ በመጀመሪያ ዙር ኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 ሲያሸንፈን ተበሳጭቻለሁ በፍጹም ቅጣት ምትና በሌላ የበረኛ ስህተት የተገኘ ሽንፈት ነበር በዚያ ላይ አሪፍ ነበርን መጨረሻ ላይ ወሳኝ ኳስ ባለመጠቀሜ በጣም የተበሳጨሁበት ሽንፈት ሆኗል።
ሊግ :- በምርጥ አቋሙ ያስገረመህ ቡድን አለ..?
አሊ:– አዎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተለየ ሆኖብኛል ከታችኛው ሊግ እንደመምጣቱ በዚህ ደረጃ መፎካከሩ አስገርሞኛል
ሊግ:-የዋንጫ እድሉስ ክፍት ነነው…? የሚገመቱ የሉም..?
አሊ:- እድሉ ለሁሉም ክፍት ነው እያንዳንዱ ጨዋታ ከባድ በመሆኑ ገና 9 ጨዋታም ስላለ ተለይቶ እገሌ ይወስደዋል የምትለው ቡድን የለም ብዬ አምናለሁ።
ሊግ:– የውጪ ኳስ ታያለህ ..?
አሊ:- አዎ በደንብ አያለሁ የማን .ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ አመቱን ሙሉ ውጤታማ አልነበርንም ምን ይደረጋል እግርኳስ እንዲህ ነው።
ሊግ:– ውጤት ለመጥፋቱ የአሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሃግ ችግር ..? ወይስ ..?
አሊ:- የማን.ዩናይትድን መረጃ በደንብ እከታተላለሁ ባለኝ መረጃ የአሰልጣኙ ፕሮጀክት ለዩናይትድ የመጠነ አይመስለኝም ብዙ አቅም ያሳየው የዋንጫ ልምድ ያለው እንደ አሰልጣኝ ካርሎ አንቾሎቲ አይነት አሰልጣኝ ነው የሚያስፈልገው ብዬ አምናለሁ…
ሊግ:- በቦታህ ምርጡ ማነው…?
አሊ:- ከሀገር ውስጥ አቡበከር ናስር ከውጪ ደግሞ ክሊያን ምባፔ ምርጫዎቼ ናቸው።
ሊግ:- በመጨረሻም የምትለው አለ..?
አሊ:- በሀዋሳ ከተማ አብረውኝ እየተጫወቱ ያሉ ተጨዋቾች ፣ ሌሎች አብረውኝ የተጫወቱ ጓደኞቼ፣ አሰልጣኞቼን በሙሉ አመሰግናለሁ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኜ አጠናቅቄ ዳግም እንደማገኝህ ተስፋ አደርጋለሁ ለሰጣችሁኝ እድልም አንተንና የሊግ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን ማመስገን እፈልጋለሁ..