“ምርጡ ቡድን ወላይታ ድቻ እንጂ ሌላ ክለብ አይደለም”
ወላይታ ድቻ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ
ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የአንደኛው ዙር ተጠናቋል፤ ስለ እስካሁን ጉዞአችሁ ምን የምትለው ነገር አለ?
አንተነህ፡- የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዙር ጉዞአችን ጥሩ ነው፤ ካሳብነው በላይም ነው እቅዳችንን ለማሳካት የቻልነው፤ በውድድሩ ቆይታችንም ሐዋሳ ላይ በነበረን ተሳትፎ ወደ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አካባቢ መውረዶች ነበረብን፤ ከእረፍት በኋላ ግን ወደ ድሬዳዋ ከተማ ስንመጣ ካደረግናቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ አምስቱን አሸንፈን ዙሩን በጥሩና ስኬታማ በሆነ ውጤትም ልናጠናቅቅ ችለናል፡፡
ሊግ፡- በድሬዳዋ ከተማ በነበራችሁ የውድድር ቆይታ ለወላይታ ድቻ ከስድስት ግጥሚያዎች አምስቱን ማሸነፍ መቻሉ ከባድ አይደለም?
አንተነህ፡- በጣም ከባድ ነው እንጂ! ምክንያቱም ሁሉም ቡድኖች ሐዋሳ ላይ ከነበራቸው የውድድር ቆይታ አኳያ ራሳቸውን አጠናክረው የመጡበት ሁኔታ ስላለ እኛ ራሳችን ባለን ኳሊቲና አሰልጣኛችንም ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በሚሰጠን የጨዋታ ታክቲክ አድርጉ የምንባለውን ነገር ስለምናደርግና መዘናጋቶች ስለሌሉብን፤ ከእዛም ባሻገር እያንዳንዱን ጨዋታዎችምእያንዳንዱ ስፍራ ላይ ትኩረት አድርገን ስለምንጫወትም ለእዛ ነው ከስድስቱ ግጥሚያዎች ውስጥ አምስቱን ለማሸነፍ የቻልነው፡፡
ሊግ፡- ወላይታ ድቻ በውድድር ዘመን ተሳትፎው ምን አይነት ጠንካራና ክፍተት ጎኑን እያስመለከተን ይገኛል?
አንተነህ፡- ጠንካራ ጎናችን ሁሌም እንደ ቡድን ኳሱን መጫወት መቻላችን ነው፤ ከእዛም ጋር በተያያዘ ሁኔታ በግለሰብ ላይ የተንጠለጠለና ጥገኛም የሆነ ቡድን አይደለም ያለን፤ ሌላው ማንም ተጨዋች ከቡድናችን ቢወጣም እነሱን ተክተው የሚጫወቱ ተጨዋቾችም ስላሉን በህብረትም ሆነን እንደ ቡድን ስለምንከላከልና በጋራም ስለምናጠቃ እነዚህ ሁኔታዎች እኛን ይገልፁናል፤ በክፍተት ደረጃ ልገልፀው የምፈልገው ነገር ደግሞ ቶሎ ቶሎ የግብ አጋጣሚዎችን የመፍጠር ችግሮች አሉብን ያን እንደ ደካማ ጎንም ነው የማየው፡፡
ሊግ፡- አንደኛው ዙር አሁን ተጠናቋል፤ ለአዳማው የሁለተኛው ዙር ተሳትፎአችሁ ምንን አሻሽላችሁ የምትመጡ ይሆናል?
አንተነህ፡- እኛ የቡድኑ ተጨዋቾች በእዚህ ጉዳይ ዙሪያ ሁሌም እየተነጋገርንበት ይገኛል፤ ከፊት ለፊት ያሉብንን እያንዳንዱን ጨዋታዎች እንደ ጥሎ ማለፍ በማየትና ግጥሚያዎቹንም በአዳማ ቆይታችን በማሸነፍ አሁን ካለንበት የሁለተኛ ደረጃም ከፍ ለማለትም ነው የምንፈልገውና ለእዛም ዝግጁ ሆነናል፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር እቅዳችሁ ምን ውጤትን ማስመዝገብ ነበር፤ አሁን ላይስ?
አንተነህ፡-አሁን በማስመዝገብ ላይ የምንገኘው ውጤት ከሚፈለገው በላይ ነው፤ ከእዚህ በኋላ በሚኖረን የውድድር ተሳትፎም ቀጣይ ቀጣይ ጨዋታዎቻችንን ድል በማድረግ አጠቃላይ ውጤቱን መጨረሻ ላይ ነው የዋንጫው ባለቤት ሆኖ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ስለመሳተፍ ሊሆን ይችላል፤ አለያም ደግሞ ሁለተኛ ወጥቶም በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ መሳተፍና እነዚህ እንኳን ባይሳኩ ሶስተኛ መውጣትም ሊሆን ይችላልና ይህ ሁሉ ውጤት በኋላ ላይ ይታወቃል፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችሁ ለእናንተ የትኛው ቡድን ፈታኝ ሆነባችሁ?
አንተነህ፡- እስካሁን ያስቸገረንና ፈታኝ የሆነብን ቡድን የለም፤ ሁሉም ተመሳሳይ የሆነ አቋምም ነው ያለው፤ ከዛ ይልቅ ግን በውድድር ዘመኑ እስካሁን ባደረግናቸው ጨዋታዎች ቡድኖች ፈታኝ ሆነውብን ሳይሆን ከእነሱ ጋር ስንጫወት ባልጠበቅነው መልኩ ከእዚህ ቀደም የምንታወቅበትን በፍላጎት ኳስን የምንጫወትበትን አቅም በማጣት የአቋም መውረድ የታየብን ግጥሚያ ከባህርዳር ከተማ ጋርና ከሲዳማ ቡና ጋር ስንጫወት የነበረውን ነው፤ ይህም ማለት የእነሱ ጥንካሬ ሳይሆን የእኛ በፍላጎት ያለመጫወት ችግር ነበር ሊያስቸግረንም የቻለው፡፡
ሊግ፡- የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታችሁን ወልቂጤ ከተማን በማሸነፍ አጠናቅቃችኋል፤ ስለ ጨዋታው ምን ትላለህ? የድል ውጤቱስ ለእናንተ ይገባል…?
አንተነህ፡- በጣም ነው እንጂ የሚገባን! ወላይታ ድቻ በውድድር ዘመን ተሳትፎው የሚታወቀው በጥብቅ መከላከል ነው፤ ከእዛም ውጪ ባገኘው አጋጣሚ ጎል ማግባትም ዋንኛው እቅዱ ነው፤ ያንንም ተግብረነዋል ማለት ይቻላል፤ በአሁኑ ጨዋታ ላይም እንደተመለከትከው ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን ስንፈጥር ነበር፤ ፖልም መልሶብናል፤ ከግብ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተንም ያመከናቸው የግብ እድሎችም አሉ፤ አራት ያህል ንፁህ የግብ እድሎችም ነው ያመለጡን፤ በእነሱ ወገን ስታየው ደግሞ ከበረኛ ጋር ተገናኝተው የሳቱት ምንም አስቆጪ የሚባል የግብ ኳስ ስለሌለ የውጤት ተገቢነቱ ለእኛ ሆኗል፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የደረጃው ሰንጠረዥ አሁን ላይ ከመሪው ቅ/ጊዮርጊስ በሶስት ነጥብ በማነስ በሁለተኛው ስፍራ ላይ ተቀምጣችኋል፤ የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ የሊጉን ዋንጫ ማን ያነሳል? ቅ/ጊዮርጊስ? ወይንስ ወላይታ ድቻ?
አንተነህ፡- አሁን ላይ እኛ ዋንጫውን እናነሳለን ብለን ነው ስራችንን የምንሰራው፤ ለእዛም ስንል ከፊት ለፊት ያሉብንን ጨዋታዎች እያሸነፍንም ለመሄድ ተዘጋጅተናል፤ ሊጉ ገና ቢሆንም ዋንጫውን ለማንሳት ጥረትን እናደርጋለን፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አቡበከር ናስር ዓምና የሊጉ ክስተት ተጨዋች ሆኖ አልፏል፤ በእስካሁኑ የአንደኛው ዙር ጨዋታስ ለአንተ የትኛው ተጨዋች ጎልቶ ወጥቷል?
አንተነህ፡- በአንደኛው ዙር የውድድር ቆይታ ለእኔ ጎልቶ ወጥቷል ብዬ ስሙን የምጠቅሰው ተጨዋች በዋናነት የቅ/ጊዮርጊሱ አቤል ያለውንና የፋሲል ከነማውን በረከት ደስታን ነው፤ ከእነሱ በመቀጠል ደግሞ የቅ/ጊዮርጊሱ አጥቂ ኢስማሄል ጎሮ አጎሮም ሌላው ጎልቶ እየወጣ ያለ ተጨዋች ነው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዙር ተሳትፎ ለአንተ ምርጡ ቡድን ማን ነው?
አንተነህ፡- ምርጡማ የእኛው ወላይታ ድቻ ነዋ! ምክንያቱም ማንም ሰው ሳይጠብቀን ነው በተሻለ ደረጃ ላይ እንድንገኝና ይህንንም ስኬታማ የሚባል ምርጥ ውጤትን እያስመዘገብን እንድንገኝ ያደረገን፡፡
ሊግ፡- በወላይታ ድቻ ክለብ ውስጥ እንደ ደጉ ደበበ አይነት ልምድ ያላቸው /ሲኒየር ተጨዋቾች/ ይገኛሉ፤ የእሱ አስተዋፅኦ የጎላ ነው ማለት ይቻላል?
አንተነህ፡-በጣም እንጂ! የደጉ መኖር ምንም ጥርጥር የለውም በጥሩ ሁኔታ እየጠቀመንም ነው የሚገኘው፤ ከእሱ ውጪ የአዲስ ህንፃም በቡድኑ ውስጥ መገኘት አያጠራጥርምናእነሱ በአሁን ሰዓት ልምዳቸውን እያካፈሉን ነው የሚገኘው፤ ሁለቱ ተጨዋቾች መች ተረጋግተን መጫወት እንዳለብን፤ ከመከላከሉ ወደ ማጥቃቱ ስንሸጋገር መች መቸኮል እንዳለብን፤ መች ኳስ መያዝ እንዳለብን እነሱ ናቸው ሲመሩን /ጋይድ/ ሲያደርጉን የነበሩት፡፡
ሊግ፡- ወላይታ ድቻ ከእዚህ ቀደም ላለመውረድ ነው ሲጫወት የነበረው፤ ዘንድሮ ወደ ስኬታማነት ከመምጣታችሁ አኳያ የአሁኑ የለውጥ ሚስጥር ምንድን ነው?
አንተነህ፡- የለውጥ ሚስጥራችን ብዬ የማስበው መተባበራችንን እና አንድ መሆናችንን ነው፤ እንደዚሁም ደግሞ ያለን የቡድን መንፈስም አሪፍ መሆኑና እንደ ቡድንም መንቀሳቀሳችንና ታክቲካል ዲስፕሊንም ሆነን መጫወታችን እኛን ወደ ለውጥ ሊያመጣን ችሏል፡፡
ሊግ፡- ከወላይታ ሶዶ የወጣችሁ ሶስት ወንድማማቾች ተጨዋቾች በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እየተጫወታችሁ ይገኛል፤ በተወለዳችሁበት ክልል ውስጥም በአባታችሁ ስም “ጉግሳ ፋሚሊ” በሚልም ትልቅ ሆቴልን ገንብታችሁና ከፍታችሁም የንግድ ስራን እየሰራችሁ ይገኛል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ? የእዚህ ሆቴል የመክፈት ሃሳቡን በማመንጨት ከሶስታችሁ ውስጥ ቀዳሚው ተጨዋችስ ማን ነው?
አንተነህ፡- ከሶስታችን ውስጥ ሆቴል የመክፈቱን ሀሳብ በቅድሚያ ያመነጨሁት እኔ ነኝ፤ በሶዶ ከተማ ውስጥ ኳስን እጫወት ስለነበርም ነው ያኔ ይህን ጉዳይ ሳስብም የነበርኩት፤ ወንድሜ ሽመክት ጉግሳ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ነገርን አያውቅም ነበር፤ ጉዳዩን ጀምሬውም ነው ለእሱ ያሳወቅኩትና በጋራ ሆነንም ነው እኛ ወንድማማቾቹ፣ እናታችን፣ አንዷ አለን የምንላት እህታችን እና አሁን አባታችን በህይወት ባይኖርም እሱን ጨምሮ ነው የእኛን ቤተሰብ ለየት የሚያደርገው አንዳችን ለአንዳችን ሁላችንም የምንደባበቀው ምንም ነገር ስለሌለና ክሎዝም ስለሆንን ከእዛም ውጪ ደግሞ አንድ ነገር ስናገኝ ምንም ነገርን ሳንደብቅም ለቤታችን ስለምናውልም በእዚህ መልኩ ነው ጥራቱን የጠበቀ 22 አልጋ፣ ከስር ቆንጆ ባር፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ ከፊት ለፊቱ የሱፐር ማርኬት ያለው ዘመናዊ ሆቴል ነው ለመገንባት የቻልነው፡፡
ሊግ፡- ዘመናዊ ሆቴሉን ከገነባችሁ በኋላ ወላጅ አባታችሁን በሞት አጣችሁ፤ የሀዘን ስሜቱ ምን ይመስል ነበር?
አንተነህ፡- ስለ ሀዘኑ እንደዚህ ብሎ ለመናገር ስሜቱ በጣም ከባድ ነበር፤ ይህንንም ለማወቅ በሜዳ ላይ ከምናሳየው አቋማችን የምትረዳውና የምታውቀው ነገር አለ፤ አሁን አባታችንን በሞት ካጣን ወደ መቶ ቀናት ሊሆነን ነው፤ በእዚህ ጊዜ ውስጥም የሽመክት አቋምን ስታይ በበፊት ሁኔታው ላይ አልነበረም፤ ያን ሰሞን ከአቋሙ ወርዶም ነበር፤ አሁን ላይ ነው ገና ወደ ጥሩ ብቃቱ እየመጣም የሚገኘው፤ ከእሱ ውጪ ለቅ/ጊዮርጊስ የሚጫወተው ቸርነትንም ሆነ እኔን ጨምሮም በሀዘኑ በጣም ተጎድተናልና በሁሉም ነገር ለቤተሰባችን የምናስብ ከመሆናችን አኳያ ወደ ወቅታዊ አቋማችን ለመመለስ የተቸገርንበት አጋጣሚም ነበርና ከባድ ጊዜን ነበር ለማሳለፍ የቻልነው፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ወላይታ ድቻ በሁለተኛው ዙር በምን መልኩ ይቀርባል?
አንተነህ፡-የሁለተኛው ዙር ላይ ባሉን የክፍተት ቦታዎች ቡድናችን የተወሰኑ ተጨዋቾችን ማስፈረሙ የማይቀር ነው፤ ለተጋጣሚ ቡድኖች አስቸጋሪና በጣም ጠንካራ ሆነንም እንቀርባለን፤ ባለን የአሸናፊነት መጠን /ቴምቦ/ እና በፍላጎታችንም የምንቀጥል ስለሚሆንም ብዙ የተለዩ ነገሮችንም ከእኛ አትጠብቁ፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ህይወትህ ደስተኛ ነህ?
አንተነህ፡- በጣም ደስተኛ ነኝ፤ የተከፋሁበትን ጊዜም አላስታውስም፡፡
ሊግ፡- ወላይታ ድቻ በአንተ አንደበት እንዴት ይገለፃል?
አንተነህ፡- እኔ የእዛው አካባቢ ልጅ ስለሆንኩኝ ስለ ቡድናችንና ስለ ደጋፊዎቻችን ሁሉንም ነገር ነው የማውቀው፤ ደጋፊዎቻችን ለእኛ ሁሌም ቢሆን ምርጥ ናቸው፤ የትም ስንሄድ እኛን ተከትለው ይመጣሉ፤ በብዛት ደጋፊዎቻችን ወደ ሜዳ ስለሚገቡና ጥሩ ድጋፋቸውንም በሐዋሳም ሆነ በድሬዳዋ ከተማ ቆይታችን ስለሚሰጡን እኛ ተጠቃሚም ነን፤ ያን ስታይ ያለህን ነገር መስጠት እንዳለብህም ትረዳለህና ወላይታ ድቻን የምገልፀው ከቃላት በላይ አድርጌው ነው፡፡
ሊግ፡- ከአንተ፣ ከወንድሞችህ ሽመክት ጉግሳና ቸርነት ጉግሳ ምርጡ እግር ኳስ ተጨዋች ማን ነው?
አንተነህ፡- /እንደ መሳቅ ብሎ/ ይህ ከባድ ጥያቄ ነው፤ ሶስታችንም የራሳችን የሆነም ኳሊቲም አለን፤ በእርግጥ ሽመክትና ቸርነት በሚጫወቱበት ቦታ የሚገናኙበት አጋጣሚ ቢኖርም ሽመክት ከእኛ አንፃር ይለያል፤ እሱ ለ10 ዓመት ያህል በአንድ አይነት አቋም ነው ሲጫወት የነበረው፤ እንደዚህ አይነት ሰው ማግኘትም ይከብዳል፤ ወጥ የሆነ አቋምንም ነው የሚያሳየው፤ ቸርነትም ትንሽ ልምዱን በደንብ እስኪያገኝ ድረስ እንጂ ወደ ውጪ ሀገር ወጥቶ መጫወት የሚያስችል አቅም እንዳለውም ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡
ሊግ፡- በቤተሰባችሁ ከሚገኙት ተጨዋቾች ውስጥ አኩራፊው ማን ነው?
አንተነህ፡- አኩራፊ ተጨዋች ማንም የለም፤ ከእኛ ቤተሰብ ውስጥ ሽመክትም ሆነ እኔ ተጨዋችና ቀልደኛ ነን፤ ምንአልባት ቸርነት ጉግሳ ነው የአባታችንን ነፍስ ፈጣሪ ይማረውና የእሱ አይነት የጭምተኝነት፤ የዝምተኝነትነ ባህሪህ ያለው እንጂ አኩራፊ አይደለም፡፡
ሊግ፡- ቤትኪንጉንና ራስህን አስብና ወደማጠቃለሉ እናምራ?
አንተነህ፡-ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት ነው፤ በርካታ ክለቦችም በተቀራረበ የነጥብ ልዩነት ላይ ስለሚገኙ ውድድሩን እያደመቁትም ነው፤ የሊጉን ዋንጫ የሚያነሳውን ቡድን ለመለየት ከባድ ሆኗል፤ እንዲሁም ወራጁን ለማወቅ፤ የሁለተኛው ዙርም የበለጠ ጠንካራ ይሆናል፤ ስለ ውድድሩ ይህን ካልኩ ስለ ራሴ ደግሞ አንድ ነገርን ማለት እፈልጋለው፤ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አሁን ላይ ለቡድኔ ሙሉ አቅሜን አውጥቼ አይደለምእየተጫወትኩ የምገኘው፤ ከዛ ይልቅ ገና የራሴንም ሆነ የቡድናችንን ስነ-ልቦና እርስበርስ ከኮቺንግ ስታፉ ጋር በመነጋገርና በማሳደግም ላይ ነው የምገኘው፤ ከላይ እንዳልከው ወላይታ ድቻ ከዚህ ቀደም ላለመውረድ ይጫወት የነበረ ክለብ ነው አሁን ላይ ግን ያንን የአህምሮ አስተሳሰብ ለመቀየርና መጀመሪያምበውጤቱ ላይ ትኩረት ማድረግ ስላለብንም በእዛ መልኩ በመጫወታችን ነው ውጤታማ እየሆነን የምንገኘው፤ ከእዚህ በኋላም እኔም ለእዚህ ቡድን ራሴን አሻሽዬም ለክለቤ ጥሩ ነገሮችን አሰራለው፡፡