Google search engine

“ፈጣሪ ጤናውን ሰጥቶኝ ከጨረስኩ በርግጠኝነት ኮከብ የማልሆንበት ምክንያት አይኖርም” አስቻለው ታመነ /መቻል/

በመሃል ተከላካይነት ሚና አሁንም ለክለባቸውም ሆነ ለዋሊያዎቹ አይተኬ ከሆኑት ተጨዋቾች መሃል አንዱ ነው  የትኛውም አሰልጣኝ የሚፈልገው አይነት ተከላካይ ነው ሲሉ የሚያቁት ያሞግሱታል… የመቻል አዲሱ ተከላካይ አስቻለው ታመነን….። በቅርብ ጊዜያት ከመገናኛ ብዙሃን መራቁን ፈልጎ መሆኑን የሚናገረውና ከልጅነቱ አሰልጣኝ ገ/ክርስቶስ ቢራራ ጋር መገናኘቱ ያስደሰተው አስቻለው ከሊጉ ባልደረባ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ አዲሱ ክለቡ፣ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ ጀጋፊዎች፣ መቻል የዋንጫ ተፎካካሪ ስለመሆኑና ሌሎች ጥያቄዎች ዙሪያ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል።

ሊግ:- አስቻለው ታመነ ከሚዲያ ጠፋ …በሰላም..?

አስቻለው:- /ሳቅ/ አዎ ጠፋሁ…ብዙ ጊዜ ከሚዲያ ይደወላል ግን ብዙም መታየት አልፈለኩም… መቻል ገና የገባሁት ዘንድሮ በመሆኑና አዲስ በመሆኔ ገና ሁለት ጨዋታ ብቻ በማድረጌ በሚዲያ ለመታየት ገና ስለሆነ ነው የጠፋሁት…

ሊግ:- ዝምታህን ለመስበር እኛን  በመፍቀድህ እናመሰግናለን ../ሳቅ/

አስቻለው:- /ሳቅ በሳቅ/

ሊግ:- መቻሎች ባለ ልምዱንና አቅም ያለውን አስቻለውን አግኝተዋል ማለት ይቻላል ..?

አስቻለው:- አዎ../ሳቅ/ መቻል ትልቅ ክለብ ነው። ከዚህ በፊትም ትልልቅ ተጨዋቾች የሚመጡበት እንደሆነ አስተውያለሁ… ስብስቡም ጥሩ ሆኖ ለሻምፒዮንነት የሚወዳደር በመሆኑ መቻልን መርጫለሁ… በርግጠኝነት ለዋንጫ ስለሚጫወት ለዚህ የሚጠቅመውን ጠንካራውን አስቻለውን አግኝቷል ማለት ይቻላል …ከሲዳማ ሲቲ ካፕ የዋንጫ አሸናፊ ከሆነበት ውድድር  ጀምሮ  ጥሩ አቋምን አሳይቷል። ግብ ሳይቆጠር ነው ሻምፒዮን የሆነው። ለኛ ጥሩ ልምድ ሆኖናል… የሊግ ውድድር ከባድ ቢሆንም ጥሩ ውጤት ይጠበቅብናል

ሊግ:- በቅዱስ ጊዮርጊስና በፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የነበረው ጫና መቻል ላይ ይጠበቃል..?

አስቻለው:- ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ፋሲል ከነማ እያለሁ የደጋፊ ጫና አልነበረብኝም ጀማሪ ተጨዋችም አይደለሁም።   የእኔ ስራ መጫወት ነው። የደጋፊው ደግሞ ገብቶ መደገፍ ነው። ያን ያህል ጫና አያስፈራኝም መቆጣጠር እችላለሁ።  ወደ መቻል ስንመጣ ብዙ የሚደግፉ አሉ። ስታዲየም ባይመጡም ክለቡን ይረዳሉ። ወታደሩ አመራሩም በሀገራዊ ጉዳይ ቢዚ ስለሚሆኑ ባይመጡም አብረውን አሉና እነሱን ለማስደሰት እንሰራለን። በግሌ ግን ይህን ያህል የደጋፊ ጫና አያሰጋኝም። ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ እያለሁ አልረበሸኝም። አሁንም ደጋፊ ኖረ አልኖረ ጉዳዬ ከደጋፊው ጋር አይደለምና አልረበሽም።

ሊግ:- የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ዋንጫ ይፈልጋሉ…እናስ የደጋፊዎቹ ጫና አልነበረም እያልክ ነው …?

አስቻለው:- የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ዋንጫ ስለሚፈልጉ ሁሉንም እንቅስቃሴ ሊከታተሉ ይችላሉ ግን አያዘንም።  እዚህም ያለው ደጋፊም ትንሽ ሆኖም ይጠይቃል። ያም ቢሆን ጥያቄው ወደ አመራሩ እንጂ ወደኛ አይመጣም። እዚህ እንደ ህግ ማንም አይጠይቅህም። ውጤት ቢጠፋም ከስታዲየም በሰላም ነው የምትወጣው። መጠየቅ በሚችሉበት የህግ አግባብ እንጂ ቀጥታ ተጨዋቹ ጋር አይመጡም … ቤቱ የወታደር ቤት ስርዓት ያለው በመሆኑ የወጣ ነገር አይታይም። ደጋፊው ይጠይቃል አመራሩም ይጠይቃል እኛም ዋንጫ ብለን ስላሰብን ለራሳችን ስንል እንጫወታለን እንደ ጥያቄው ግን የሁለቱ  ክለቦች ደጋፊዎች ጫናማ አለው።

ሊግ:- የመጀመሪያውን ጨዋታ አሸንፋችሁ በባህርዳር ከተማ ተሸነፋችሁ… ሽንፈቱ ትምህርት ሰጥቶ አልፏል ማለት ይቻላል ..?

አስቻለው:- አሁን  ሊጉ ገና ተጀመረ ማራቶን በለው። አንድ አሸንፈን አንድ ተሸነፍን እግር ኳስ ውስጥ ያጋጥማል። ዋናው ከሽንፈት መማር ነው። ተምረናል ባሉን ስህተቶች ዙሪያ አሰልጣኞቻችን በሚሰጡን ስልጠና እንማራለን የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም። ወደ ኋላ ሳይሆን ወደፊት ነው የምናስበው። የባህርዳር ከተማ ሽንፈት አስተምሮን አልፏል አሁን ትኩረታችን ለቀጣዩ ነው።

ሊግ:- በቀጣይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ምን ውጤት ይጠበቅ..?

አስቻለው:- ለማንኛውም ጨዋታ ተዘጋጅቶ በመቅረብ  አምናለሁ 11ለ11 ሆነን ወደ ሜዳ እስከገባን ትንሽ ትልቅ የምለው ቡድን የለም። ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ ነው ወደ ሜዳ የምንገባው። ለማሸነፍ በሚያልም ስነልቦና የተሞላ ቡድን ስላለን በርግጠኝነት ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን።

ሊግ:- አሰልጣኝ ገ/ ክርስቶስ ቢራራን እንዴት አገኘሃቸው ..?

አስቻለሁ:- በፕሪሚየር ሊጉ ሲያሰለጥነኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ነገር ግን ትውውቃችን ኳስን ሀ ብዬ ስጀምር ነው… ስለ እግርኳስ ያስተማረኝ አሰልጣኜ ነው። ከ17 አመት በታች አሰልጥኖኛል። ኳስ እንዲህ ነው የሚደረገው ያለኝ የእውቀት አባቴ ነው። በሱ ስር ፕሮጀክት ደቡብ ምርጥ ሱፐር ሊግ ላይ ደግሞ ለዲላ ስጫወት አሰልጥኖኛል። አሁን ደግሞ የእውቀት መነሻዬ ከሆነ አሁን ላለሁበት ደረጃ ለመድረሴ ትልቅ አስተዋጽኦ ካደረገ ግንባር ቀደም አሰልጣኝ  ጋር  በሊጉ ላይ  ዳግም መገናኘቴ ያስደስተኛል።

ሊግ:- የአሁኑ አቋምህን የመጨረሻው ጫፍ ደረሰ ወይስ ገና እንጠብቅ ..?

አስቻለው:- የመጨረሻው ምርጡን አቋሜ አሳይቻለሁ አልልም። ነገር ግን የሲቲ ካፑ  አምስት ጨዋታዎችን ጨምሮ ሁለቱን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር አካቶ ወደ ድሮ ምርጥ አቋሜ 90 በመቶውን አግኝቷል ማለት ይቻላል… መቶ ለመሙላት ጠንክሬ እየሰራሁ ነው። በዘንድሮ ውድድር ምርጥ አቋሜን አሳይቼ ከመቻል ጋር ስኬታሜ እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ።

ሊግ:- ፕሪሚየር ሊጉ ላይ የመቻል ጠንካራ ተፎካካሪ ማን ይሆን ..?

አስቻለው:- በእግር ኳስ በስብስብ ብቻ ዋንጫ ይገኛል ማለት አይቻልም። ሰብስበህ ላይሳካ ይችላል። የኛ ሊግ ላይ መገመት አይቻልም በግሌ ከቡድኔ ጋር የምሰራውን ልምምድና የቡድን ጓደኞቼን አቋም ጠንካራ ሆኖ ስላየሁ ርግጠኛ መሆን የምችለው ስለመቻል ብቻ ነው። ሌላው አያሰጋኝም ቅድሚያ ለራሳችን  ነው የምሰጠው። በሊጉ ግን የምገምተው የለም ከ30ኛ ሳምንት በኋላ እናያለን /ሳቅ/።

ሊግ:- በ2016 የአመቱ ምርጥ ተከላካይ አስቻለው ሊሆን ይችላል ..?

አስቻለው:- መጠራጠር የለብህም። በርግጠኝነት እንደምኖር ቃል እገባለሁ። ከቡድኔ ጋር ውጤታማ ከሆንኩ የማልገባበት ምክንያት የለም። በርትቼ እስራለሁ ፈጣሪ ጤናውን ሰጥቶኝ በጤና ከጨረስኩ በርግጠኝነት ኮከብ የማልሆንበት ምክንያት አይኖርም።

ሊግ:-  ከዋሊያዎቹ  እና ከመቻል ጫናው የማን ይበልጣል ..?

አስቻለው:- ሁለቱም የየራሳቸው ጫና አለባቸው። የብሄራዊ ቡድኑ ግን እንደ ሀገር ከፍ ይላል። መቻልም እንደ ሀገር የሚያስብ ስለሆነ ከባድ ሀላፊነት ነው። ለመቻል ስትጫወት እንደ ሀገር ነው የምታስበው… ብዙውን ለሀገር ለማበርከት የሚሰራ ክለብ በመሆኑ ጫናው ተመሳሳይ ነው። ብሄራዊ ቡድኑ ሀገር ሲወክል መቻልም ከሌሎቹ ክለቦች የሚለየው ለብሄራዊ ቡድን ግብአትነት የሚሆኑ ተጨዋቾችን ነው የሚያፈራው። አመራሮቹን ስታወራቸው የሚነግሩህም ይህንን ነው በአጠቃላይ መቻል ደስ የሚል ቤት ነው።

ሊግ:- ጨረስኩ …የመጨረሻ መልዕክት አለህ ..?

አስቻለው:- ከፈጣሪ ጋርና ከቡድን ጓደኞቼ ጋር በመሆን ክለባችን መቻል የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ እንጥራለን የሚል እምነት አለኝ… ዋናው ሰላም ነውና ኢትዮጵያ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን ማለት እፈልጋለሁ።

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P