Google search engine

“በአዲሱ አመት አንዱን ሌላኛውን ለመጥለፍ የሚደረጉ ተንኮሎች ሊወገዱ ይገባል” “ስታዲየሞችን የመስራት ሃላፊነት የክለቦችና የመንግስት እንጂ የፌዴሬሽኑ አይደለም” አቶ ባህሩ ጥላሁን /የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ/

ልክ የዛሬ አመት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ምርጫ አድርጎ አቶ ኢሳያስ ጅራን ለቀጣዮቹ አራት አመታት በድጋሚ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ መርጧቸዋል። ከነባር አመራሮች ብቸኛ የሆኑት አቶ ኢሳያስ ከአዲሶቹ ጋር ባለፉት 12 ወራት ሲሰሩ ቆይተዋል። ጽ/ቤቱን እየመራ ያለው ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ባህሩ ጥላሁን ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ያለፉት 12 ወራቶች እንዴት አለፉ፣ የፈረሰኞቹ 1 ሚሊዮን ብር ጉዳይ የት ደረሰ፣ ደመወዝ ባለመክፈላቸው የተነሳ የታገዱ ክለቦች ጉዳይ ምን ይመስላል ፊፋስ ኢትዮጵያን ሊያግድ የሚችልበት ስጋት አለ፣ የጠፉ የፌዴሬሽኑ ሰራተኞች ምክንያት የፌዴሬሽኑ ጫና ይሆን እንዴ…? በሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሽ ሰጥተዋል…

ሊግ:- እንኳን አደረሰህ…. ?

ባህሩ:- እንኳን አብሮ አደረሰን…

ሊግ:- ለመላው ኢትዮጵያዊያንስ ምን መልዕክት አለህ….?

ባህሩ:- ለመላው ኢትዮጵያዊያንም እንኳን አደረሳችሁ አዲሱ አመት የሰላም የጤና አገራችን ሰላም የምትሆንበት ሁሉም በተሰማራበት የስራ ዘርፍ ስኬታማ የሚሆንበት የአገራችን እግር ኳስ ከፍ የሚልበት ሙያተኞች በጋራ ለአንድ አላማ የሚቆሙበት በጋራ መተባበርና መተሳሰብ ለሀገር እድገት የሚተጉበት እንዲሆን እመኛለሁ….

ሊግ:- ዋሊያዎቹ ካይሮ ላይ በግብጽ 1ለ0 ተረተዋል… ጨዋታውን ውጤቱን እንዴት አገኛችሁት…?

ባህሩ:- ቡድኑ ውስጥ የነበረው ጠንካራ ዝግጅትና የማሸነፍ መንፈስ ለዚህ ጨዋታ ለሰጡት ትኩረት ተጨዋቾቹን ማመስገን እፈልጋለሁ። በጣም ዲሲፕሊንድ ሆነው ውጤቱ ለውጥ ባያመጣም የሀገር የክብር ጉዳይ መሆኑን አውቀው ከእግርኳሳዊ ፋይዳው በተጨማሪ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ሂደቱን ተረድተው የኢትዮጵያ ህዝብን ለማስደሰትና ለአዲስ አመት ስጦታ ለማድረግ የተጉበት ሂደት አስደስቶኛል። ጨዋታው ላይ ያየነውም ይህንን ነው፡፡ 1ለ0 ቢሸነፉም ሽንፈቱ ይገባቸዋል ብዬ አላምንም ጎል አስቆጥረን ማሸነፍ ባንችል እንኳ አቻ መሆን ይገባን ነበር ብዬ አምናለሁ። እንደ አጠቃላይ የነበረው የተጨዋቾቹ ዝግጅት የአሰልጣኞቹ መናበብ ጥሩ እንደነበር መናገር እችላለሁ።

ሊግ:- የግብጾቹ አቀባበል ጥሩ ነበር…?

ባህሩ:- ምንም ችግር አልገጠመንም …የሚፈለገውም ይህ ነው፡፡

ሊግ:- እስቲ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንመለስ… ፌዴሬሽኑ ምን ድጋፍ አድርጓል…?

ባህሩ:- የሻምፒየንስ ሊግና የኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር በሜዳችን እንዲደረጉ ፌዴሬሽናችን ጥረት አድርጓል፡፡ እያደረገም ይገኛል… ማሳያውም የባህርዳር ከተማ ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ነው የሚደረገው….ነገር ግን ጨዋታው በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲደረግ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ስለነበሩ በክለብ ላይሰንሰ ማናጀራችን አማካይነት ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል። የመጀመርያው ጨዋታ በአገራችን እንዲካሄድ በማድረጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቁን ሚና ተጫውቷል። የተለያዩ ማቴሪያሎችን ከሟሟላት አንጻር ትልቅ ስራ ተሰርቶ መልበሻ ክፍሉ የተቀያሪ ተጨዋቾች ወንበር የተለየ ገጽታ እንዲኖረው ተደርጓል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ላወጡት ወጪ ፌዴሬሽናችን፣ ባህርዳር ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምንሸፍነው ይሆናል። ፌዴሬሽኑ እያንዳንዱ ስራ ላይ አለ.. የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት አድርገናል። በተጨማሪ መልበሻ ክፍሉ እንዳያንሸራትት ቶክሲ እንዲደረግ ቬንትሌተር፣ ኤር ኮንዲሽነርና ፍሪጅ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ክሊኒክ ሩሙ እንዲሟላ የህክምና ኮሚቴው ሃላፊ ዶ/ር ሳሚ በኩል ውዳሴ ዳይግኖስቲክ ሴንተር በውሰት በማምጣት እንዲሟሉ አድርገን ውድድሩ እዚህ እንዲደረግ የሚያስችል ስራ ሰርተናል። ቅ/ጊዮርጊሶች በተመሳሳይ በራሳቸው መንገድ ስራ ሲሳሩ ቆይተዋል። ፌዴሬሽኑ ከከተማ አስተዳደሩና ከክለቦቹ ጋር በጥምረት ሰርቶ መደረግ ያለበት ተደርጓል። ነገር ግን ከደጋፊ መግባት ጋር ተያይዞ የሚገባውን ደጋፊ ቁጥር የመወሰን ስልጣን ካለው መንግስታዊ ተቋም ጋር ያለውን ሂደት የመወሰን ሃላፊነት ከኛ ጋር ስለሌለ ምንም ልናደርግ አልቻልንም።

ሊግ:- አሁን ግን ጨዋታው ካይሮ ላይ ነው የሚደረገው..?

ባህሩ:- ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁሉንም የሚጠበቀውን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የወጣቶች ስፖርት ሃላፊ በአቶ በላይ ደጀን ፊርማ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጽፎ ለኛ በግልባጭ ደርሶን አይተነዋል፡፡ ደጋፊ መግባት እንደሚችል የሚገልጽ ደብዳቤም አይተናል…. ነገር ግን ካፍ ባስቀመጠው ቀነገደብ ውስጥ የመጣ ምላሽ ነው አይደለም የሚለው ነገር ላይ ልዩነት ሊኖረው ይችላል። እነሱም ጊዜው ሳያልፍ ቀድመው ከአልአህሊ ጋር ካይሮ ላይ ለመጫወት መጨረሳቸውን ሰምተናል። ያለው ሂደት ይሄ ነው …በቀጥታ እኛን አይመለከትም ..

ሊግ:- ወደ አንድ ሚሊዮን ብር አካባቢ ወጪ አድርገን እስካሁን አልተመለሰልንም የሚል ቅሬታ በቅዱስ ጊዮርጊስ የፌስቡክ ፔጅ ላይ አይቻለሁ …ምላሻችሁ ምንድነው..?

ባህሩ:- ሜዳውን እንደ ፌዴሬሽን ስለምንጠቀምበት በወጪ ደረጃ የራሳችን ድርሻ ይኖራል…. ባህርዳር ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊሶች፣ ፌዴሬሽናችንና የከተማ አስተዳደሩ የምናዋጣው ክፍያ ይኖራል፡፡ እኛም የሚደረስብንን ለመክፈል ዝግጁ ነን በዚህ በኩል ችግር የለም… በነገራችን ላይ ሜዳን የማዘጋጀት ሃላፊነት የፌዴሬሽኑ አይደለም አንዳንዴ ክለቦች የራሳቸው ሃላፊነት መሆኑን የመዘንጋት የሚመስሉ ነገሮች ይታያሉ.. ፌዴሬሽኑ በተለያዩ ጨዋታዎች ሲወቀስ ይታያል፡፡ ይሄ ሚናን አለመለየት ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ሜዳ አመቻችቶ የማቅረብ ግዴታ የለበትም ነገር ግን እንደ ሀገር የተሳካ ውድድር እንዲኖር ከማሰብ ተናቦ መስራትን ሲተገብር ኖሯል፡፡ ሀገር ወክለው ለሚሄዱ ክለቦቻችን ተቆርቋሪ ሆኖ መስራት ግዴታችን ነው፡፡ ነገር ግን ስታዲየሞችን የመስራት ሃላፊነት የክለቦችና የመንግስት እንጂ የፌዴሬሽኑ አይደለም። ይሄ የተዘነጋ ይመስላል፡፡ የሜዳ ጉዳይ የኛ ሀላፊነት አይደለም…. የክለቦችን ገቢ ከማጠናከር አንጻር ጨዋታዎችን በተመልካች ፊት ማድረግ አንዱ ስትራቴጂ ነው በርግጥ አንዱ አማራጭ እንጂ የመጨረሻው አይደለም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለያዩ መንገዶች ራሳቸውን በገቢ ለማጠናከር የሚበረታታ ስራ እየሰሩ እንደሆነ ይታወቃል።

ሊግ:- አራት ሰራተኞች ውጪ ሄደው ቀርተዋል….ፌዴሬሽኑ ሰራተኞቹ ላይ ጫና ያደርጋል እንዴ..?

ባህሩ:- በዚህ ጉዳይ የተለየ የምለው ነገር ሊኖር አይችልም… ሁሉም በራሱ ሃሳብ ለውጥ ፈልጎ ይጠቅመኛል ያለውን ይወስናል… ፊዴሬሽኑ ሰራተኞቹ ላይ ጫና የሚያደርግ ወይም የአሰራር ክፍተት ቢኖር ለምን እነዚህን ሰዎች ላከ..? በነሱ ቦታ ሌላ ሰው መላክ ይችል ነበረኮ… አሜሪካ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ተጉዘው ወጌሻውና የትጥቅ ያዡ ቀሩ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ሄደው የቀሩትኮ ፓስፖርት እኛ ጋር ነው በህጋዊ መስመር ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን አበቃ…. የቴክኒክ ዳይሬክተሩ አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ የስልጠና እድል አግኝቶ በራሱ ወጪ አሜሪካ ሄዶ ቀረ….
አልማዝ ደግሞ ሙሉ ወጪዋን ፊፋ ችሏት የሄደች ሰራተኛችን ናት፡፡ አሁንም ቀርታለች የሚለው ላይ ርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ብትቀርም ግን ከኛ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ነገር ነው… እዚህ ላይ የምለው የተለየ ነገር የለኝም። ጽ/ቤቱ ምንም አይነት ጫና አያደርግም፡፡ በአሰራር በተቀመጠ መስመር ስራውን ግን ይመራል። የቀሩት ብቻ ለምን ይወራል.. ? የፌዴሬሽኑ ሜዲካል ዶክተር የሆነው ዶክተር ሳሙኤል ዙሪክ /ስዊዘርላንድ/ ፓሪስ /ፈረንሳይ/ ሄዶ ተመልሷል… የጨዋታ ኮርዲኔተሩ ሚኪ ስዊዘርላንድና ሌሎች ሀገሮች ሄዶ መጥቷል፡፡ አልገባኝም የመረጃዎቹ መነሻ ምንድነው…? ምን ተፈልጎ ነው የተወራው…? በእኛ በኩል ሰራተኞቻችን ላይ ጫና አናሳድርም፡፡ ህግን ተከትለን ነው የምንሰራው… የቀሩት በሙሉ ቢጠየቁ በጫና ነው የቀረነው ይላሉ ብዬ አላምንም… ለቀጣይ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን በደንብ የምናየው ይሆናል… በተቃራኒውኮ የትጥቅ ያዡ አስቀርተን ከቡድኑ ጋር ከሄደው ለአንዱ ደርበህ ስራ ወገሻውን አስቀርተን ደግሞ የቡድኑ ሀኪም ደርቦ ይስራ ብንል ሌላ ጩኸት አይነሳም…? ፌዴሬሽኑ ዝቅተኛ ስራ ለሚሰሩ አይሆንም ግፍ ሰራባቸው ይባልና ሌላ ጩኧት ነበር የሚነሳው… ለማንኛውም ማለት የምችለው ይህንን ብቻ ነው….

ሊግ:- ለተጨዋቾች ደመወዝ ባለመክፈል በፊፋ የታገዱ ክለቦች ጉዳይ የት ደረሰ..?

ባህሩ:- ፊፋ ያገዳቸው ክለቦች ታግደው እንዳሉ ናቸው፡፡ ካልከፈሉ እገዳው ይቀጥላል፤ ለክለቦቹ ማለት የምፈልገው ይህንን ነው ዝውውር ማድረግ አይችሉም፡፡ እገዳው ካልተነሳ ሲስተሙም አይሰራም ይዘጋል… በዚህ አጋጣሚ ከታገዱት ክለቦች መሃል አንዱ የነበረው መቻል የሚጠበቀወን ከፍሎ እገዳው ስለተነሳለት ዝውውሩን አጽድቀንለታል።

ሊግ:- በታሪክ ውስጥ ፊፋ ክለቦች ለተጨዋቾቻቸው ደመወዝ አልከፈሉም ብሎ ክለቦቹ የሚገኙበትን ሀገር አግዶ ያውቃል..?

ባህሩ:- ፌዴሬሽኑ ክለቦቹ ላይ ጫና እንዲያሳድርና እንዲያስከፍል የተለያዩ ቅጣቶች የሚቀጣበት አሰራር ሊኖረው ይችላል፡፡ ፊፋ ራሱን የቻለ ነጻ ተቋም ነው፡፡ ለምሳሌ ፊፍፕሮ ከፊፋ ጋር በጋራ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡ የተለያዩ ነገሮች ሲኖሩ ለፊፋ ያቀርባል ፊፋም ጉዳዩን መርምሮ እርምጃ ይወስዳል። የተጨዋቾች ማህበር ከጅማ አባጅፋርና አዳማ ከተማ ጋር ተያይዞ ለፊፍፕሮ ያቀረበው መረጃ አለ…. ያም ተቋም ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ ፌዴሬሽናችን ኢሜይል ይልካል የመረጃ የደብዳቤ ምልልስ ስናደርግ ቆይተናል…

ሊግ:- ከሰሞኑ አዲስ ደብዳቤ እንደመጣ መረጃው አለና እናንተ ጋር ደርሷል ….ዝርዝር ሃሳቡ ምን ይላል…?

ባህሩ:- አዎ የተላከ ደብዳቤ አለ፡፡ ባስቀመጥነው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በሰባት ቀን ውስጥ የተባለው የደመወዝ ክፍያዎች እንዲፈጸሙ ያ የማይሆን ከሆነ ግን ጉዳዩን ወደ ፊፋ እወስደዋለሁ ብሏል። እኛም እንደፌዴሬሽን ስላለው ሂደት ለሚጠይቀን አካል ለማብራራት ዝግጁ ነን..

ሊግ:- ከተጨዋቾች ደመወዝ አለመከፈል ጋር ተያይዞ ያለው ሂደት ምን ይመስላል..? ከማህበሩ ጋር በጋራ እየሰራችሁ ነው..?

ባህሩ:- የተጨዋቾችን ደመወዝ የሚከፍሉ ክለቦች ናቸው፡፡ የተወሰኑ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች እንዲተገበሩ የማስገደድ ጫና የማድረግ ግዴታ የፌዴሬሽኑ ይሆናል፡፡ በዚህ መሰረት ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን የትኛውም አካል ከሚችለው በላይ አይንጠራራም፡፡ ፌዴሬሽኑ ማድረግ ያለበትን ደረጃውን ጠብቆ ያደርጋል። በአንድ ቀን ከሊግ አያወርድም ሁሉም ሂደት አለው፡፡ ያንን መጠበቅ የግድ ይላል..ጅማና አዳማ ባለመክፈላቸው እግድ ላይ ያሉ ክለቦች ናቸው፡፡ በቀጣይ ምን ይወስናል የሚለው የምናየው ይሆናል… በዚህ አጋጣሚ የተጨዋቾች ማህበር ደመወዝ አልተከፈላቸውም ብሎ ለፊፍፕሮ የላከው ደብዳቤ ያለ ይመስለኛል… ተቋሙ ደግሞ የወልቂጤ ተጨዋቾች ደመወዝ አልተከፈላቸውም ብሎ ለኛ ጽፏል። ተጨዋቾቹ እንዳልተከፈላቸው በተለያየ የመገናኛ ብዙሀን መረጃዎች ሰምተናል፡፡ አንድም ተጨዋች ግን ለፌዴሬሽን አልተከፈለኝም ብሎ ያቀረበው ክስ የለም፡፡ እያየነው ያለ ክስም የለም በተባራሪ ነው የምንሰማው …. እንደ አጠቃላይ ማሳሰብ የምፈልገው ደመወዝ ያልከፈሉ ክለቦችን እያስከፈልን ነው… የፕሪሚየር ሊግ፣ የከፍተኛና የአንደኛ ሊጎች ክለቦች መሃል ያልከፈሉትን እንዲከፍሉ እያደረግን እንገኛለን…. ከዚያ ውጪ የተጨዋቾች ማህበር ለተጨዋቾች መብት መቆም እንዳለበት ይሰማኛል ተገቢም ነው… ሁሉም ደብደቤዎችና ክሶች መነሻቸው ምንድነው የሚለው ግን መታየት ያለበት ይመስለኛል። ክለቦች ናቸው ያልከፈሉት እንጂ ፌዴሬሽኑ መክፈል የለበትም አይችልምም….ይሄ መታወቅ አለበት… ደመወዝ ካልከፈለ ክለብ ጋር ነው ጭቅጭቁ መሆን ያለበት ወይስ ከፌዴሬሽኑ ጋር ነው የሚለው መታየት የሚገባው ይመስለኛል… ማህበሩ የተጨዋቾች ደመወዝ እንዲከፈል ከክለቦቹም ይሁን ከፌዴሬሽኑ ጋር ምን ያህል ርቀት ተጉዟል። ባለፉት 12 ወራት ከተጨዋቾች ማህበር ጋር ቁጭ ብለን ያወራንበት ወቅት የለም ትዝም አይለኝም በጎን ግን የፊፍፕሮ ደብዳቤ ይመጣል…

ሊግ:- ከተቋሙ ጋር ጥሩ ግንኙነት አላችሁ..?

ባህሩ:- በእኛ በኩል ለተቋሙ ክብር አለን፡፡ በቅርብ የምናውቃቸው አመራሮችም አሉ፡፡ የኛ አባልነት ለፊፋ ነው ጉዳዩ ወደ ፊፋ ከተጓዘ ከፊፋ ጋር የምንነጋገር ይሆናል፡፡ እኛ የሄድንበትን ርቀት ማስረጃ ይዘን የምንነጋገር ይሆናል

ሊግ:- የእገዳ ስጋት የለብንም እያልክ ይሆን አቶ ባህሩ..?

ባህሩ:- እንግሊዘኛውን አንብቦ ከመረዳት ጋር ክፍተት ያለ ይመስለኛል፡፡ ለምን እንደሚጦዝም አልገባኝም… ከሰሞኑ የተላከው ደብዳቤ በትህትና በተሞሉ ቃሎች የታጀበ ነው… በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ጠይቀን ነበር ግን ማብራሪያው አልደረሰንም .. ቀነ ገደብ አስቀምጠው በዚህ ጊዜ ውስጥ ካልተፈታ ጉዳዩን ወደ ፊፋ እንወስደዋለን ነው የሚለው አበቃ …. ጉዳዩ ወደ ፊፋ ሲወሰድኮ ምላሽ እንጠየቃለን፡፡ ኢትዮጵያ ከፊፋ አባል ሀገራት መሃል አንዷ ናት፡፡ የራሷ ዋጋና ክብር አላት። ጥያቄ አቅርቦ ምልልስ አድርገን ነው ወደ ውሳኔ የሚገባው.. ጥፋተኛ ከሆንን የሚወስነው ውሳኔ ይኖራል አሁን ግን ምንም አይነት ስጋት የለም…

ሊግ:- ያለፈው ምርጫ ከተካሄደና አዲሱ አመራር ስራ ከጀመረ አመት ሞላው ….አመቱ እንዴት ይገመገማል..?

ባህሩ:- ጥሩ የሚባል 12 ወራት አሳልፈናል ብዬ አምናለሁ። በመተዳደሪያ ደንብ መሰረት እየተገናኘን ስብሰባ እናደርጋለን ስራዎች ይገመገማሉ ውሳኔዎች ይወሰናሉ። ሰላማዊ በሆነ የስራ መንፈስ እየሰራን የተለያዩ ውሳኔዎች እየወሰን በጋራ ተናቦ በመስራት ጥሩ ተግባራት ፈጽመናል ብዬ አምናለሁ፡፡ አመራሮቹ አዲስ ከመሆናቸው የተነሳ ቶሎ ነገሮችን ከመረዳት አንጻር ክፍተት እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ የተወሰኑ ያሉ ነገሮችም ጊዜ እየተወሰደ ሲሰራ የመዋሃድ የመናበብ አቅማችን እየጨመረ እንደሚሄድ አምናለሁ፡፡ አመቱ ግን በጥሩ መግባባት ተጠናቋል ማለት ይቻላል።

ሊግ:- ጨረስኩ …የመጨረሻ ቃል…?

ባህሩ:- አዲስ አመት እንደመሆኑ አዲስ በሆነ የስራ ሂደት ለመነሳት መዘጋጀት አለብን። በቀጣይ የወንዶች የዓለም ዋንጫ፣ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ፣ የኦሎምፒክ ማጣሪያዎች በእድሜ ደረጃ የሚካሄዱ ውድድሮች አሉብንና በጋራ በጥሩ መንፈስ ባለበት የስራ ድርሻ እንዲዘጋጅ ጥሪ አደርጋለሁ። እግርኳስ ውስጥ ያለው እንቅፋት ማበጀት አንዱን ለመጥለፍ የሚደረጉ ተንኮሎች ሊወገዱ ይገባል፡፡ በኔጌቲቭ ኢነርጂ ጊዜያችንን አናቀጥል ሁሉም ዝግጁ ሆኖ ሀገር የሚጠቅም ስራ እንዲሰራ አደራ እላለሁ አገርን በሚጠቅም ጉዳይ ላይ በጋራ እንስራ ማለት እፈልጋለሁ… በድጋሚ ለመላው ኢትዮጵያዊያን መልካም አዲስ አመት እላለሁ

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P