ሊግ:- የጥሎ ማለፉ ዋንጫ ላይ ወጥራችኋል የሚል መረጃ ደረሰኝ… እውነት ነው …?
በረከት:- ያው ዋንጫ እስከሆነ ውድድር እስከሆነ ድረስ እንዴት አናቅድም እንዴትስ አንወጥረም…? ሀገር የምትወክልበት እስከሆነ ድረስ መታቀዱ አይቀርም… በተከታታይ ሁለት ጨዋታ አድርገን በጥሩ ሁኔታ እየተጓዝን ነውና ውድድሩ አንዱ እቅዳችን ነው ለዚህ ትኩረት ሰጥተን መጫወታችን ጥርጥር የለውም…
ሊግ:- ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ውጤታማ ናችሁ ማለት ይቻላል በምትፈልገው መንገድስ እየተጓዘ ነው …?
በረከት:- ፕሪሚየር ሊጉ ላይ እንደምጠብቀው አይደለም ለማለት ይከብዳል… ገና ቀሪ 23 ጨዋታ አሉ… የውጤት መንገራገጭ ቢኖርም ነጥቦቹ ባለመራራቃቸው አስከፊ ደረጃ ላይ ነን ብዬ አላምንም… በርግጥ የሚስተካከሉ ነገሮች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ በቀጣይ ጨዋታዎች እየተስተካከለ ግን ወደምንፈልገው ደረጃ እንመጣለን ብለን እናስባለን እንደምንሻሻል የቡድኑ አባላት እምነት ነው፡፡ ለዚህም ጠንክረን እየሰራን ነው…
ሊግ:- አምበል እንደመሆንህ አሁን ያለው የክለቡ ሁኔታ እንደ አምበልነትህ ከብዶሃል..?
በረከት:- እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ክለብ እንደመሆኑ የዚህ ክለብ አምበል መሆኔ ያኮራኛል፡፡ ክለቡ ትልቅ እንደመሆኑ እንደ አምበልነት ትልቅ ስራ ይኖርብኛል፡፡ የበረኝነትም የአምበልነትም ሃላፊነት አለብኝ፡፡ ያም ቢሆን ውጤቱ ላይ ደከም ስትል የሚኖር ጫና አይጠፋም.. ነገር ግን ከዲሲፕሊን ከልምምድ፣ ከመልበሻ ቤት ስነስርዓት ጋር ተያይዞ አምበል ማድረግ ያለበትን ከማድረግ አንጻር እስካሁን አልተቸገርኩም፡፡ ተጨዋቾቹም ጥሩ ናቸው፡፡ ሁሉን ነገር ተጋግዘን ስለምናደርግ አልተቸገርኩም ወደፊትም ይከብደኛል ብዬ አላስብም ነገር ግን ውጤት ሲጠፋ አምበል ላይ ያለው ጫና እንደሚከብድ አውቃለሁ….
ሊግ:- እንደ አምበል ከደጋፊያችሁ ጋር ጥሩ ናችሁ..?
በረከት:- በጣም ጥሩ ነን፡፡ ደጋፊዎቻችን ብዙ ጊዜ ውጤት ደስታ ይፈልጋሉ፡፡ ይሄ ሲቀር ቅር ይላቸዋል፡፡ እኛም የምንሰራው ደጋፊዎቻችንን ቤተሰቦቻችንን ለማስደሰትና ቀና ብሎ ለመሄድ ጭምር መሆኑ መታወቅ አለበት… አንዳንዴ እንደምንፈልገው አልሆን ሲል ውጤት ሲጠፋ ደጋፊውም ቅር ሊለው ይችላል… ይህን እንረዳለን እኛ ያለነሱ እነሱም ያለ እኛ አይሆንምና መደጋገፍ አለብን እንደ አጠቃላይ ከደጋፊው ጋር ችግር የለብነንም፡፡ ውጤት ሲመጣ ያሉትን ቅሬታዎች ያስወግዳልና ለሱ ጠንክረን እየሰራን ነው።
ሊግ:- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ላለባችሁ ጨዋታ ተዘጋጅታችኋል…?
በረከት:- በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጀንበት ነው፡፡ ጠንክረን ነው የምንመጣው… በሊጉ የተወሰኑ የውጤት ችግሮች ነበሩ፡፡ በጥሎ ማለፉ ከኮልፌዎች ጋር ስንጫወት ጥሩ ነገር አይቼበታለሁ፡፡ በሊጉ ከተጫወትን ስለቆየን ጥሩውንም አቋማችን በሊጉ የምናሳይበት ጨዋታ ይሆናል… ጥሩ ተዘጋጅተን ከበርካታ ቁጥር ካለው ደጋፊ ፊት ስለምንጫወት አስደሳች ውጤት ይመዘገባል ብዬ እጠብቃለሁ።
ሊግ:- ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ የተፈጠረውን ችግሮችን የሚያስወግድ ይሆናል ማለት ይቻላል.!
በረከት:- የደርቢ ጨዋታ እንደመሆኑና የውጤት ክፍተቶች ስለነበሩ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ ብዙ ነገሮችን ያስተካክላል ብዬ አምናለሁ። ደርቢ መሆኑ ከላይ ያሉትም ክለቦችን በነጥብ ለመቀራረብ የምናደርገውን ጥረት ያግዛልና ጨዋታው ተጠባቂ ነው … ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን ተጋጣሚያችን ሌላ ክለብም ቢሆንም ማሸነፋችን ትርጉም አለው ….
ሊግ:– ቅዱስ ጊዮርጊስንም ይሁን ሌላውን ክለብ ስታሸንፉ የሚገኘው 3 ነጥብ ነው… ከሌሎቹ የምታደርጉት ጨዋታ ከጊዮርጊስ ጋር ካለባችሁ ጨዋታ ጋር እኩል ነው ..?
በረከት:– አይሆንም …ትልቅ ጨዋታ ነው እንደሌላው የምታየው አይደለም ከባህርዳርም ይሁን ከሻሸመኔ ከተማ የሚገኘውና የሚታጣው ነጥቡ ተመሳሳይ ቢሆንም ውጤቱ የሚፈጥረው ስሜትና የደጋፊ ፉክክር ብዙ ነገር ስለሚቀይር ጨዋታው ይለያያል… ትልቅ ጨዋታ እንደመሆኑ ለማሸነፍ ጠንክረን እንገባለን።
ሊግ:- አሰልጣኞች መቀያየራቸውስ ቡድኑን አልጎዳውም …?
በረከት:- የተወሰነ ጉዳትና ጫና ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ከአንድ አሰልጣኝ ጋር ይዘነው የመጣነውና የለመድነው አጨዋወት አለ፡፡ ሌላ አሰልጣኝ ሲቀየርና ሌላ አይነት አጨዋወት ሲሆን ትንሽ ሊከብድ ይችላል… ግን በመላው አለም እግር ኳስ ላይ ያለና የሚታይ በመሆኑ ከሁኔታዎች ጋር ቶሎ መላመድ የግድ ይላል… እንደ ተጨዋች ግን ማንም ይምጣ ማንም ስራችን ላይ ትኩረት አድርገን መዘጋጀት አለብን የመጣው አሰልጣኝ የሚለውን መቀበልም የግድ ስለሆነ እስኪስተካከል ጠንክሮ መስራት አማራጭ የለውም፡፡ አሁን ለጨዋታው የተዘጋጀው በምክትል አሰልጣኝ ሲሆን ባለፉት ሁለት አመታት ከእኛ ጋር የቆየ በመሆኑ ብዙ ይከብደናል ብዬ አላስብም፡፡ የቡድናችን ተጨዋቾች ወጣቶችና ቶሎ መቀበል የሚችሉ በመሆናቸውም እንቸገራለን ብዬ አላስብም።
ሊግ:- ጨዋታው ላይ ምንም ውጤት ይመዝገብ ስለ ቅዳሜው ጨዋታ ለደጋፊው ምን መናገር ትፈልጋለህ…?
በረከት:- ደጋፊዎቻችን የራሳቸው ሀሳብና ቅሬታ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባት አልፈልግም፡፡ እንደ ተጨዋችና ደጋፊ ካነሳን እኛም ያለነሱ እነሱም ያለእኛ ስለማይሆን ችግር ተፈጥሮ በዝግ እንዲደረግ ስለማንፈልግ በሰላም ጨዋታው እንደሚጠናቀቅና ከደጋፊው ጋር ውጤታማ እንደምንሆን ተስፋ አደርጋለሁ.. ደጋፊዎቻችን በስፖርታዊ ጨዋነት እንደሚደግፉን እምነቱ አለኝ… እኛም እነሱን አስደስተን የሚፈልጉትን ስለምናደርግ ከደጋፊዎቻችኝ 90 ደቂቃ ሙሉ የተሻለ ድጋፍ እናገኛለን ብዬ አምናለሁ… ።
ሊግ:- ለሰጠኧን ቃለምልልስ አመሰግናለሁ…
በረከት:– እኔም አመሰግናለሁ…