Google search engine

“ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፈረመ  አንድም ተጨዋች ስለኮሚቴና ደላላ  ሊያወራልህ አይችልም” “ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድም ኢትዮጰያዊ ተጨዋች በደላላ አላስፈረመም” አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ /ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ/

ፕሪሚየር ሊጉ ላይ የሰራው በምክትል አሰልጣኝነት ደረጃ  ቢሆንም በተቃራኒው በከፍተኛ ሊግ ኢትዮጵያ መድንና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሰልጥኖ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የማደግ  ህልማቸው ጋር አገናኝቷቸዋል …. አሰልጣኝ በጸሎት ልዑል ሰገድ ….. ከንግድ ባንክ ጋር ለ2016 ጠንካራ ልምምድ ላይ የሚገኘው አሰልጣኙ “ከሊግ ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ ዮሴፍ ከፈለኝ” ጋር ባደረገው ቆይታ ካንተ እውቅና ውጪ የፈረመ ተጨዋች የለም ወይ…. ? የ2016 እቅድህ ምንድነው…? እነ ጌቱና ዳግማዊን ያሰናበትክበት መንገድ ተገቢ ነው ወይ…. ? ወጣት በመሆንህ ሲኒየሮቹ አላስቸገሩህም ወይ… ?  የዝውውር ገበያው ላይ አመራሮችና  ኮሚቴዎች እጃቸው አልነበረም ወይ….?  ብዙ ጊዜ ዝውውር ሲደረግ ትክክለኛው የደመወዝ ዋጋ ይደበቃል ንግድ ባንክስ  ይሄ ተግባር ውስጥ እጁ የለበትም….? ሁሉም የፈረሙት ባንተ ፈቃድ ከሆነ ለውጤቱ ሃላፊነቱን ትወስዳለህ… ? ጫና ውስጥ ነህ ወይ…. ? በእናንተ ዝውውር ውስጥ ኤጀንቶች የነበረቸው ሚና ምንድነው…..? በሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ዙሪያ አሰልጣኙ የሰጠውን የፊት ለፊት ምላሽ ይከታተሉት…

 

ሊግ:- ከቀናቶች በኋላ ፕሪሚየር ሊጉ ይጀምራልና ዝግጅታችሁ ምን ይመስላል..?

በጸሎት:– ከነሀሴ 1/2015 ጀምሮ  አዳማ  ከተማ በመግባት የህክምና ምርመራ አድርገን  የመጀመሪያ ወደሆነው አጠቃላይ ዝግጅት የገባነው…አሁን ወደ ዋናው የዝግጅት ጊዜ ገብተን ቡድኑን የመገንባት የማዋሃድ ስራ እየሰራን ነው…አቋማችንን ለመገምገም የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ እየተዘጋጀን እንገኛለን… በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወደ 10 የሚጠጉ ተጨዋቾች  አስፈርመናል…  አንድ ተከላካይ ብቻ  ከአምበሪቾ  ስናስፈርም ዘጠኙ ከፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የፈረሙ  ናቸው…

ሊግ:-  በእስካሁኑ የዝግጅት ጊዜ  የፈረሙትን ተጨዋቾች መቆጣጠርና አለቃ መሆንህን ማሳየት ችለሃል..?

በጸሎት:- አዎ ምንም የተለየ ነገርኮ የለውም ሲኒየር ይሁኑ ልምድ ያላቸው የአሰልጣኙ የስልጠናና የማኔጅመንት አቅም የሚወስነው ነው የሚሆነው እንጂ ልዩነት የለውም…ታችም ሆነህኮ  በትክክል ካልመራህ ያው ነው በእስካሁኑም በደንብ እየመራው እንዳለ ነው የሚገባኝ…

ሊግ:-  ወጣት አሰልጣኝ መሆንህ አልተቸገርክበትም ወይ እያልኩህ ነው..?

በጸሎት:- /ሳቅ/ አልተቸገርኩበትም ያለኝ ነገር ነው የሚያስገምተኝ የአቅም የማኔጅመንት ጉዳይ ሊሆን ይችላል እንጂ  ችግር የለውም በሚፈልጉት ደረጃ ተገቢ አቅም ይዘህ ካልተገኘህ ነው ችግሩ የሚፈጠረው እንጂ ለኔ ያን ያህል አልከበደኝም.. በዚያ ላይ ስንገናኝ የተገናኘው እንዴት  ነው…? ፕሮፌሽናሊዝም ተከብሮበት ነው ወይስ በጓሮ በጓዳ የሚለው መታየት አለበት፡፡ በተለይ በኛ ሀገር ይሄ ልዩነት ይፈጥራል… ግንኙነቱ የአሰልጣኝና የተጨዋች እስከሆነ ድረስ ችግር አይፈጥርም በቀጣይም እንደማይፈጠር ርግጠኛ ነኝ።

ሊግ:-   በፀሎት የብቃት ጥያቄ  የለበትም ጎበዝ ነው ነገር ግን የ ሊጉን ፖለቲካ አያውቀውም የሚሉ ወገኖች አሉ…ምላሽህ ምንድነው..?

በጸሎት:–  ሰው በሚፈልገው በሚያቀው ልክ ነው የሚመዝነው… ይህን ያለው ሰው ባለሙያ  አይደለም እኔ ግን ባለሙያ ነኝ፡፡ ምን እንደሚያስፈልግ አውቃለሁ መመዘንም ካለብኝም በባለሙያ ብቻ ነው  በተረፈ የማላውቀው ምንም  የተለየ ነገር አለው ብዬ አላምንም።

ሊግ:-   በርካታ ጨዋታ የተጫወቱ ተጨዋቾችን  ውል ሳታድስ ትንሽ የተጫወቱትን አስቀረሃቸው የሚል ስሞታ ይቀርብብሃል…ምላሽህ ምንድነው..?

በጸሎት:- በመጀመሪያ መረጃው  ፈጽሞ የተሳሳተ ነው 

ሊግ:- ምን እያልክ ነው… የጌቱና ዳግማዊን ውል ሳታድስ  አሰናበትካቸው፡፡  ሁለቱ ግን ኢትዮ ኤሌክትሪክና ድሬዳዋ ከተማ ገቡ..,እውነት አይደል..? መመዘኛህስ ምን ነበር..?

በጸሎት:-  ጌቱ የተቀነሰው ስታንዳርዱ በከፍተኛ ሊግ ስለነበር ነው፡፡ በጫና ውስጥ የመጫወት ልምዱ ከፍተኛ ሊግ ውስጥ ነው፡፡ ቦታው ወሳኝና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው፤ በጫና ውስጥ ሆኖ የመጫወት አቅሙ አናሳ በመሆኑ በዚያ ቦታ ላይ ልምድ ያለውና ጫና መቋቋም የሚችል ተጫዋች አስፈርመናል። ይዘን ከመጣንበት አላማና ሪስኩን ከመቀነስ አንጻር  ውሳኔውን ወስነናል። ርግጥ ነው ከፍተኛ ሊጉ ላይ በጥሩ ሁኔታ ተጫውቷል፡፡ ነገር ግን ስለሱ ለማወቅና ለመናገር ከባለቤቱ በላይ ያወቀ ቡዳ ነው እንዲሉ እንዳይሆን  ያሰጋል።

ሊግ:– ተረቷን እናቆያትና  ለቦታው የሚመጥን  ተጨዋች ማስፈረም ወይም  ያለውን ተጨዋች ብቃቱን እንዲያወጣ እንደ አሰልጣኝ አግዞ ተጨዋቹን ጥሩ ማድረግ  ከሁለቱ አንዱ ይጠበቃል…ከባለቤቱ ያወቀ እንዳልከው ካወከው  አግዘኸው እንዲቆይ ማድረግስ አይቻልም ነበር….?

በጸሎት:-  ቶሎ ብለህ አሰርተኸው የምትጨምረውን ጨምረህ የምታመጣው ተጨዋች ሊኖር ይችላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጊዜ የሚፈልግ ይኖራል፤ ጌቱ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በዚያ ላይ  አዲስ ቡድን ነው እየገነባን ያለነው.. ምን አድርጌ ቡድኑን ላስተካክል እንጂ ይህን ማሰብ አትችልም። ከግለሰብ ክለብ ይቀድማል፡፡ ክለብ በማስቀደማችን ነው የወሰነው…ሌላ ምንም ምክንያት የለውም  ተጨዋቹን ደውለህ ብትጠይቀው ምንም ቅሬታ የለውም፡፡  ተማምነን ነው የተለያየነው…አሁንም እየተደዋወልን ነው….

ሊግ:- ድሬዳዋ ከተማ የገባው የዳግማዊ ዓባይስ ጉዳይ..?

በጸሎት:-  በዳግማዊ  ዓባይ ቦታ የመጣው ሱሌይማን ሃሚድ ነው፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስና በብሄራዊ ቡድን ያገኘው ልምድ በጣም አስፈላጊያችን ስለሆነ ፈርሟል። ዳግማዊ ብዙ ልምድ ያለው በከፍተኛ ሊግ ላይ ነው፡፡  የቡድናችንን የተከላካይ መስመር ደረጃ ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል ለዚህ ነው ርምጃ  የወሰድነው። ሊጉ ላይ ያለውን ፉክክር ለማሸነፍ ልምድ ወሳኝ ነውና መቀላቀል ነበረብን፡፡ 

ሊግ:-  ከሁለቱ ተጨዋቾች በቁጥር ያነሰ ጨዋታ የተጫወቱትን ውል ማደስህ ከላይ ካልከው ሀሳብ ጋር አይጋጭም..?

በጸሎት:-  አንዳንዴ ይከሰታል። ዝቅተኛ ጨዋታ የተጫወቱት ተጨዋቾች በተለያየ ምክንያት ሊሆን ይችላል…በጉዳት፣ በታክቲክ ልዩነት  ወይም ቦታው ሊሆን ይችላል ለምሳሌ  20 ጨዋታ ያደረገ ተከላካይና 10 ጨዋታ የተጫወተ አጥቂ ብታወዳድር ለኔ  የተሻለው አጥቂው ነው፡፡ አጥቂ ብዙ ጊዜ የመቀየር እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ብዙ ይሮጣል ብዙ ቦታ ያካልላል፡፡ ብዙ ጊዜ ለውጥ የሚደረገው ከወገብ በላይ ነው አብዛኛው ጊዜ ተከላካይ ክፍልህን አትነካም፡፡ ሁለቱ ከላይ የጠራሃቸው  ተጨዋቾች ደግሞ ተከላካይ ናቸው ለዚያ ነው በብዛት የተጫወቱት…

የኛ ኮከብ ግብ አግቢ የሆነው ተጨዋች አንዳንዴ እየተቀየረ እየገባ  ሌላ ጊዜ ቋሚ እየሆነ ነው አጥቂው መስመር ላይ ሮቴሽን ስጠቀም ተከላካዩን ግን አልነካሁም፡፡ ከተግባቡና ጥሩ አቋም ካሳዩ ለምን ይነካሉ..? ቤንች ላይ ጥሩ ተከላካዮች ነበሩ ነገር ግን ሁለቱ ተዋህደው ስለነበረና ብዙውን ጊዜ ስለተጠቀምንባቸው ነው ቁጥሩ የበዛው….

ሊግ:-  ከነዚህ ልጆች አልወጣሁም…መድን ውሉን አላድስም ሲል እንዴት የለፋበትን ፍሬ ሲያፈራ አሰናበቱት ብለን ጮህን ..ይሄ ህመም ያለበት አሰልጣኝስ ተጨዋቾቹ ላይ ይሄን እንዴት  ወሰነ… በሚል ቅሬታ የሚያነሱ  ወገኖች አሉ …ውላቸው እንዳይታደስ ስትወስን ምን ተሰማህ..?

በጸሎት:- በጣም ቅር የምትሰኝበት ስሜት ይኖራል፡፡ ሁሉም የወጡት ቢቀጥሉ ደስ ይለኛል… ግን ይሄ የሊግ ደረጃ ያመጣው ልዩነት ነው፡፡  እዳለ  ይዤው ብቀጥል አደጋውስ እንዴት ይቻላል? የለገጣፎ ገጠመኝ አይረሳም፡፡ ያ እንዳይሆን ውሳኔዎችን መወሰን ነበረብን.. ከ30ኛው የተወሰነውን ይዘን ልምድ ያላቸው ሊጉን የሚያውቁትን ቀላቅለን ደረጃውን ከፍ የማድረግ ስራ ነው የተሰራው፡፡ ይሄ ግዴታ ነው ተጨዋቾቹን ልጥቀም ብዬ ቡድኑን ላፍርስ..? ይሄን ለመከላከል ስንል ውሳኔውን ልንወስን ችለናል …

ሊግ:- አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይዞ ሁለት ተከታታይ አመታት  የሊግ ዋንጫ  ወሰደ.. አንተ ደግሞ በሁለት ተከታታይ አመታት  ሁለት ክለቦችን ወደ ሚመኙት ፕሪሚየር አሳደግክ …በሁለታችሁ መሃል ያለው ደስታ ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል..?

በጸሎት:- የኔ  ከሱ የሚለየው ከሁለት የተለያዩ ክለቦች ጋር መሆኑ ነው .. ሁለቱም አዳዲስ ቡድኖች ተገንብተው የመጣ ውጤት ነው…የተዋኸደ ሊጉ ላይ የቆየ ክለብን ድል አድራጊ ማድረግ ጋር ሲተያይ ስሜቱና ባህሪያቱ ይለያያል..ደስታው ግን  ተመሳሳይ  ነው…. 

ሊግ:– ለዋንጫ ማሸነፍ፤ ላለመውረድም ማሸነፍ ብቻ የሚጠበቅባቸው ሁለት ቡድኖች መሃል የሚፈጠረው ስሜትስ..?

በጸሎት:- ይሄ  ከባድ  ፍልሚያ ነው፡፡ ትርጉሙም ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ዞሮ ዞሮ  የሻምፒዮንነት ስሜቱ ግለቱ  ይበልጥብኛል። ምክንያቱም አመቱን ሙሉ የተለፋበት  የታገልክበት መሆኑ  ሲታይ የተለየ ያደርገዋል፡፡ የአሸናፊነት ስነልቦናው ራሱ ልዩነት ይፈጥራል… ያኛው ደግሞ ብዙ ከመሸነፍ የመጣ ብዙ ውድቀቶች የታዩበት ከዚያ ውስጥ የመትረፍ  ምኞት  ይዞ ላለመውረድ የሚደረግ ትግል መሆኑ  ይለያቸዋል ባይ ነኝ። የሁለቱ አላማ ግለት ቢመሳሰልም ላለመውረድ የተጫወተውና የተሳካለት ክለብ ደስታ አጭር ይመስለኛል ምክንያቱም በብዙ ሽንፈቶች ውስጥ የመጣ ድል ስለሆነ….

ሊግ:- ዘንድሮ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር  የምታመጣው ውጤት በፕሪሚየር ሊጉም  ውጤታማ  የመሆን አቅም እንዳለህ  የማሳየት  ጫና ውስጥ ሆነህ  የምታደርገው ውድድር  ነው ማለት ይቻላል…?

በጸሎት:-   እውነት ለመናገር ጫና  ውስጥ እንደሆንኩ አይሰማኝም… ስራውን መስራቴን የሚገባኝን ማድረጌን ማረጋገጥና  አቅሜ የፈቀደውን ስለማድረጌ እንጂ ሌላ ጫና አይኖርብኝም…. ቶፕ የሆነ ቡድን ሰርቼ  ውጤታማ ብሆን ሀይለኛ አሰልጣኝ ነኝ የምልበትም ሆነ ውጤት ባይሳካ ደግሞ  በቃ ለሊጉ አልሆንም አልችልም የምልበት ስሜት የለኝም …ሙያው መውጣትና መውረዶች አሉበት፡፡ ሂደቶች ያስፈልጉታል ይህን ስለማውቅ  ጫና ውስጥም አይደለሁም…

ሊግ:-  የከፍተኛ ሊግ አሰልጣኝ እንጂ የፕሪሚየር ሊጉ  አሰልጣኝ አይደለም ለሚሉ ወገኖች ምላሽህ ምንድነው..?

በጸሎት:-  ሰው የፈለገውን ሊል ይችላል፡፡ እኔ ግን በተቃራኒው ነው የማስበው… ክለቡን ወደ ፕሪሚየር ሊግ አሳድጎ በሊጉ ምን ማድረግ አለብኝ ብሎ እንደሚያስብ አንድ አሰልጣኝ ነው ራሴን የማየው… ብዙ ጊዜ የኛ ሀገር ስታንዳርዶች የተዘበራረቁ ናቸው፡፡ የሚወጡ መስፈርቶች ስሜታዊነትና ግለኝነት የሚታይባቸው ናቸው። ለሚፈልጉት ሰው በሚመች መልኩ የሚዘጋጁበት ነው ይሄ ትክክል አይደለም…  ምንም ውጤት የሌለው ሰው ከመሬት ተነስቶ ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ሲያሰለጥን ይታያል፡  ስልጠና የሌለው ደረጃውን የማይመጥን ሆኖ በባለስልጣን ወይ በሆነ ሰው በኩል ይሆናል የመጣው ሲያሰለጥን ታየዋለህ… በዚህ ደረጃ ተገምግሞ  ትክክለኛ ሙያዊ ግምገማ ሳይደረግ የሚካሄድ ደረጃና ግምገማ  በትክክለኛ መስመር የተደረገ ግምገማም ነው ብዬ አላምንም ። አስተሳሰቡም ሆነ አካሄዱም ሙያዊ ነው የሚል እምነቱ የለኝም…

ሊግ:-የምትፈልጋቸውን ተጨዋቾች አግኝተሃል…? ከሆነ ውጤት የማስመዝገብ ጫና ውስጥ ነህ…?

በጸሎት:- በመጀመሪያ ደረጃ ምንም  ጫና የለብኝም፡፡ መስራት ያለብኝን ነው የምሰራው ወደ ዝውውሩ ስንገባ  መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ዝውውር ሲጋነን ነበር ከፍተኛ ዋጋ ቀርቦ እንዳስፈረምን የተሰጠው መረጃ  ትክክል አይደለም… አንተ በተለይ ዳታ የማግኘት አቅምህ ከፍተኛ በመሆኑ እስቲ አጣራና ከሁሉ ዝቅተኛ ወጪ ያወጣው ክለብን ፈልግ… እኛ ነን ….. የተወሰኑ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች ናቸው እንጂ አብዛኞቹ በመቶ ቤት ውስጥ ነው የፈረሙት… መጀመሪያ አከካባቢ የማይሆን ወሬ ተወርቶ ዝውውሩን አቁመን እንደገና ነው የጀመርነው… በዚህ ምክንያት ያመለጡን ተጨዋቾች   አሉ ……

ሊግ:- ፌዴሬሽን ከገቡ ሊስቶች የተወሰኑትን ነው የማምነው …አብዛኛው ውሸት ይመስለኛል..እጅ በእጅ የሚሰጥ ስላለ ትክክለኛውን ሂሳብ ፌዴሬሽን አገኛለሁ ብዬ አላምንም…. ይሄ ውዥንብር ውስጥ ቡድንህ የለበትም…?

በጸሎት:- በፍጹም አይኖርም …ትክክለኛውን  ሂሳብ ያለማሳወቅ ችግር  የክልል ወይም የከነማ ክለቦችን እንጂ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አይመለከትም… ትክክለኛውና የተለመደው አሰራርን  ነው የምንከተለው…ተጨዋቾችን ሲያስፈርሙ የነበሩት  በከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ ቦርድ አባላት ናቸው፡፡ ተጨዋቾቹ ይገባሉ ከቦርድ አመራሮቹ ጋር ነው የሚደራደሩት … በወቅቱ  እኔ ሳደርግ የነበረው የተጨዋቾቹን ፕሮፋይል ማቅረብ ብቻ ነው … 

ሊግ:- ተጨዋቾቹ ሙሉ በሙሉ በአንተ ፍቃድ ከፈረሙ ለውጤቱ ሙሉ በሙሉ  ሃላፊነቱን ትወስዳለህ….?

በጸሎት:-  እኔ ስገባ ቀድሜ የተደራደርኩት በስራ ነጻነቴ ዙሪያ ነው… ይሄ ነጻነት የተጨዋቾችን ምልመላንም ይጨምራል…. ዝውውሩ ሙሉ በሙሉ በኔ ፍላጎት  የተከናወነ ነው… በ2014  አሰልጣኝ ደግአረገ እዚህ እያለ ባህርዳር ከተማ ሳይሄድ ተጨዋቾችን መልምሎ  ነበር… በሙከራ መልክ የሚያያቸው ተጨዋቾችም ነበሩ.. አሁን እኔ ስመጣ ሊስቱ ተሰጠኝ ስለማውቃቸው ምንም አይነት ሙከራ ስሳላደርግ የምፈልጋቸውን አስቀረሁና እንዲፈርሙልኝ አደረኩ፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ተጨዋቾችንም አመጣሁ፡፡ ዘንድሮም የተደረገው  ይሄ ነው…. ያለኔ ፍቃድ የተደረገ ዝውውር የለም….  ለዚህም ሙሉ  በሙሉ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ፡፡ በርግጥ ፈልጌያቸው የነበሩትን ተጨዋቾች ሙሉ በሙሉ ባላገኝም በያዝኳቸው ተጨዋቾች  ፊርማ ሙሉ ሃላፊነቱ  የ ኔ ነው፡፡ አንዳንዴ ግን ዝብርቅርቅ ያለ ነገር ነበር በተለይ ተጨዋቾቹ እኛ ጋር እየተደራደሩ በጎን ሌላ ጋር በስልክ እየደወሉ ወደ ሌላ ቦታ እየሄዱ መቸገራችን አልቀረም… በምንፈልገው መጠን ባናገኝም ለቡድኑ ግን ደግሜ መናገር እፈልጋለሁ  ሃላፊነቱ የኔ ነው…  ዝውውሮቹ የተከናወነው ንጹህና ፕሮፌሽናሊዝምን  በተከተለ  መንገድ ነው.. ለዚህ በአስር ጣቴ እፈርማለሁ….

ሊግ:- ዝውውሩ ላይ የኤጀንቶች  ተሳትፎና ድርሻ ምን ነበር…?

በጸሎት:- ስርዓትና ህግን በተከተለ መልኩ ነው ዝውውር የፈጸምነው….እንደሚወራው ለአመራርና ለኮሚቴ ተሰጥቶ ነው የሚለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አይመለከትም…. የሚገርመው  አንድም ኢትዮጰያዊ ተጨዋች በደላላ አላስፈረምንም… አንድም… ምርመራ በማድረግ ጎበዝ አይደለህ….? በፈለከው መንገድ አጣራ  በደላላ  አላስፈረምንም ….ለንግድ ባንክ የፈረመ  አንድም ተጨዋች ስለኮሚቴና ደላላ  ሊያወራልህ አይችልም… ምናልባት ዜጎቹ  ጋር ስንደውል ራሳችን ኤጀንት አለን ብለውን ያለ ኤጀንት  ስለማይንቀሳቀሱ  እነሱን ብቻ  አናግረን  አስፈርመናል…

ሊግ:– በ2016 እንደ ግብ የያዛችሁት ምንድነው..?

በጸሎት:- ጠንካራና የተረጋጋ ቡድን መገንባት… ጠንካራ ቡድን በአንድ ጀንበር ስለማይገነባ በሂደት ቡድኑን  አደራጅቶ ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን የመገንባት ዕቅድ ይዘናል…  ግንባታ ሂደት ይፈልጋል ኮከቦችን ሰብስበሃልና  ሻምፒዮን እሆናለሁ ወይም ሁለት ሶስት ደረጃ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው… ጥሩ ተፎካካሪ ስለመሆን እናቅዳለን…

ሊግ:- የመጨረሻ  ጥያቄ ..? ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ስታልፉ  ቃል ተገብቶ የተሸለማችሁት ሽልማት  ተመቸህ…?

በጸሎት:- አዎ በደንብ ተመችቶኛል…../ሳቅ በሳቅ/

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: