Google search engine

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ማንም ይምጣ ሁልጊዜ ዋንጫ ያልማል” “ለሻምፒዮንነት እስከተጫወትን ድረስ በየትኛውም ክለብ መቆም የለብንም” ቢኒያም በላይ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

በበሰለ አስተሳሰቡ አንደበተ ርትዑ በሆነው አነጋገሩ ይለያል …የ2015 የአመቱ ኮከብ ተጨዋች ቢኒያም በላይ….. በጉዳት አራት ሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ ወደ ዘጠኝ ጨዋታዎች አምልጦታል… በዚህ መከፋቱን የሚገልጸው ቢኒያም 2016 የዋንጫ አመት እንደሚሆን በድፍረት ይናገራል… ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር  ቆይታ ያደረገው ቢኒያም በበርካታ ጉዳዮች ላይ የሰጠው ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል….

ሊግ:– በዘንድሮው ውድድር በጉዳት ምክንያት ፈረሰኞቹን ማገዝ አልቻልክምና የጉዳቱ ጊዜን እንዴት አለፍከው…..?

ቢኒያም:– ጉዳቱ የሚደብር ነው፡፡ ምንጊዜም ጉዳት ጥሩ ስሜት አይፈጥርም፡፡ በዚያ ላይ ከሻምፒየንስ ሊግ ውጪ ነው ያደረገኝ… ከአልአህሊ ጋር መጫወት ሳልችል ቀርቻለሁ፡፡ ጨዋታውን ስጠብቀው ስለነበር ባለመሳካቱ ደግሞ ቅር ብሎኛል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ውስን ጨዋታዎችም አምልጠውኛል… አሁን ግን አገግሜ አርብ ቡድኑን እቀላቀላለሁ/ ቃለምልልሱን ያደረግነው ማክሰኞ ዕለት ነው/ ከዚህ በኋላ ከባባድ ጨዋታዎች ስላሉ በነሱ ላይ የምሳተፍ መሆኑ ያጽናናኛል… ግን ምንም ይሁን በራሱ አለመጫወት ያበሳጫል… እዚህ ላይ ስለ ደጋፊዎቻችን መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ደጋፊዎቹ ሜዳ ላይ ምነው በኖርኩ እስክል ድረስ ነው ያስጨነቁኝ፡፡ በእያንዳንዱ ቀን መቼ ነው የምትመለስልን .. ናፍቀኧናል ነው የሚሉት፡፡ ሲያገኙኝ ቴክስትም የሚልኩትና  በኖርኩና ባረካኋቸው ብዬ ተመኘሁ….ቶሎ ቶሎ ተሽሎኝ አቅም ኖሮኝ እንድመጣ ያደረጉኝ እነሱ ናቸውና በዚህ አጋጣሚ አመሰግናቸዋለሁ፡፡

ሊግ:- ብዙዎቹ ተጨዋቾቼ ስለሚያገኙት ብር እንጂ ሻምፒየንስ ሊግ አያጓጓቸውም …የአንተ ጉጉት ግን ተለየብኝ…

ቢኒያም:- እንዴ… የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒየንስ ሊግን ካልተጫወትክ ምን ያደርጋል…? ቡድናችን ውስጥ የተሻለ ተጫውተንና ውጤታማ ሆነን ከተለመደው ዙር በላይ እንሄዳለን የሚል ስሜት ነበር፡፡ በቃ ስብስቡ ታሪክ የመስራት ህልምም ነበረው..

ሊግ:- ተጎድተህ ይሁን ተቀጥተህ… ቡድንህን አለመርዳት ምን ትርጉም አለው ..? ስሜትህ ምን ነበር ..?

ቢኒያም:- በጣም የሚገርምህ ለመመለሴና ቡድናችንን በምችለው መልኩ ለማገዝ ጓጉቻለሁ፡፡ ሜዳውም ናፍቆኛል በተጎዳሁበት ጊዜ በድኔን አለማገዜ እንዴት እንዳስከፋኝ ብታይ ….? መጽናኛዬ የሆነው የቡድን ጓደኞቼ በአምስቱ ጨዋታዎች ያስመዘገቡት ውጤትና ያሳዩት ምርጥ አቋም ምነው ቡድኔን ገብቼ ባገዝኩ እንዳልል አድርገውኛል፡፡ በነሱ ተደስቻለሁ፡፡

ሊግ:– ከአዳማ ከተማ ጋርስ..?

ቢኒያም:– ከአዳማ ከተማ ጋር የነበረው ጨዋታ ከባድ ነበር፡፡ ጨዋታውን የጀመርንበት መንገድ ይመስለኛል፡፡ ከባድ ያደረገው …. መጀመሪያ ላይ በቀላሉ ነው ግብ የተቆጠረብን… ከባድ ጨዋታ ነበር፡፡ ግን ደግሞ ወደ ጨዋታው ተመልሰን ሁለት ግብ አስቆጥረን አቻ የወጣንበት መንንገድ ደግሞ የሚገርም ነበረና አቻውን አልተቆጨሁበትም…

ሊግ:– ይሄ ስብስብ ዋንጫ ይደግማል…?

ቢኒያም:– እውነት ነው። ምን ጥያቄ አለው..?

ሊግ:- ባለፉት ሁለት አመታት ሻምፒዮን ስትሆኑ ወሳኝ ሚና የነበራቸው፡፡ ከሰባት በላይ የሚሆኑ ተጨዋቾች ወጥተው ዛሬም ስለዋንጫ ማለም አልተጋነነም..?

ቢኒያም:- በፍጹም አልተጋነነም… እውነት ለመናገር አብረው ተጫውተው ክለባችንን ለለቀቁት ወንድሞቼና ጓደኞቼ ክብር አለኝ፡፡ ያለ እነሱ ያን አመት ላይ ሻምፒዮን የመሆናችን ነገር አደጋ ይፈጠርበት ነበር፡፡ ያለነሱ ከባድ ነበር .. አብረን የሚገርም አመት ነው ያሳለፍነው የነሱን ክሬዲት ማሳጣትም አልፈልግሞ… እንደ ታሪክ ይቀመጥላቸዋል… እግር ኳስ ደግሞ የአሁን ጊዜ ነው፡፡ ትላንትናም ለታሪክ አስቀምጦ ይጓዛል እነሱም ታሪክ ውስጥ አሉ…….። አሁን  ያለውን ስናይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚፈለግበትን እያደረገ ነው፡፡ እስካሁን አልተሸነፈም ማግኘት ካለበት 15 ነጥብ 13 አሳክቶ ሊጉን እየመራ ነው…. ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት አመቱ ሲጀመር ለዋንጫ ነው የምትጓዘው… የነሱ አለመኖር ፈተናውን ያከብድብናል ግን ቤቱ የፈረሰኞቹ ነውና ለዋንጫ መጫወታችን የተረጋገጠ ነው…

ሊግ:- ልምድ ያላቸውን ኮከቦቹን ለቅቆ በወጣት ስብስብ ዋንጫ  ቢያነሳ …የሊጉን ድክመት አያሳይም..?

ቢኒያም:- በፍጹም አያሳይም… እንደዚያ ብዬም አላስብም… እግር ኳስ ያልተጠበቁ ክስተቶች የሚከሰትበት ቢሆንም  ለቅዱስ ጊዮርጊስ አይሰራም… ሁሉንም አመት ብታይ የሚጫወተው ለዋንጫ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ማንም ይምጣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ዋንጫ ያልማል ክለቡ ሻምፒዮና ብቻ ለመሆን የሚጫወት ክለብ ነውና በ2016 ዋንጫ ቢያነሳ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አዲሱ አይደለም፡፡

ሊግ:- ሻምፒዮን ከሆነባቸው ያለፉት ሁለት አመታት አንጻር  ይሄኛው ስብስብ አልሳሳም ..?

ቢኒያም:– እውነት ለመናገር የስብስባችንን አቅም ማሳነስ አልፈልግም… ተጨዋቾቹ ምርጥ አቋም አላቸው ጥያቄ የለውም እዚህ ለመሰለፍኮ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ ቦታ ላይ ሁለት ሶስት ጥሩ አቅም ያላቸውን በአማራጭ የያዘ ቡድን ነው… አሰልጣኝ የሚያሰልፈው አንድ ስለሆነ እንጂ አሁን ያሉት ወጣቶች አቅም ስላጡ አይደለም.. የመጫወት ዕድል አጥተው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ አግኝተዋል ያንን እያሳዩ ነው… አበቃ ተጨዋቾቹ የመሰለፍ እድሉን አግኝተው ጥሩ አመት አሳለፉ ማለት ሌሎቹ 15 ክለቦች ደካማ ናቸው ማለት ግን አይደለም… የሚሰማኝ እንዲህ ነው..

ሊግ:-  በወጣቶቹ ዋንጫ ማለም ….?

ቢኒያም:- አዎ በወጣቶቹ አምናለሁ.. አሁን ጥሩ አቋም አላቸው የሚባሉት ፋሲል ከነማ ባህርዳር ከተማና  ኢትዮጵያ ቡና ትልልቅ ቡድኖች ናቸው ምንጊዜም ለሻምፒዮንነት ነው የሚጫወቱት ብዬ አስባለሁ… ሻምፒዮን የሚሆነው ክለብ ግን አንድ ነው ጊዮርጊስ ደግሞ በሊጉ የዋንጫ ባለቤት የመሆን ጠንካራ ልምድ አለው፡፡ አሁን ያሉት ወጣት ተጨዋቾች ላይ ደግሞ  ይሄ  ታሪክ ተጋብቷል ብዬ አስባለሁ  በዚያ ላይ አሰልጣኝ ዘሪሁን ቡድናችንን ከያዘ ጀምሮ አብረውን  ያሉ ናቸው፡፡ የተወሰኑትም ቢሆን የመሰለፍ እድል እያገኙ ነበር፡፡ አሁን ላይ ፉክክሩ አዲስ ይሆንባቸዋል ብዬ አላስብም የተሰራ ቡድን ላይ ስለነበሩ ሁሉን እያዩ ነው የቆዩት… ለዚህ ነው ስጋት የሌለኝ …

ሊግ:- ከ15ቱ ቡድኖች ለዋንጫ ይበናቀነኛል የምትለው ቡድን  አለ…?

ቢኒያም:- ለ15ቱም ክለቦች ክብር አለኝ… ለይቼ ከፍ ዝቅ ማድረግም አልፈልግም፡፡ እንደ ቡድን ግን ያቆመናል፡፡ አያቆመንም ብዬ የምናገረው ቡድን የለም… ለሻምፒዮንነት እስከተጫወትን ድረስ የትኛውም ክለብ መቆም የለብንም… አልሸነፍ ባይ መሆን ይጠበቃል፡፡ በቡድኖቹ ካልወደቅን ነው ዋንጫ የምናነሳው … አንድ ቡድን ሻምፒዮን ስለሚሆን በአንዱ ከቆምን ዋንጫውን እናስረክባለን ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አይደረግም ለሶስተኛ ተከታታይ አመት ሻምፒዮን መሆን ከፈለግን  ለ15ቱም ክለቦች ተመሳሳይ አመለካከት ሊኖረን ይገባል ..ሁሉን አክብረን  ግን እኛ ነን ሻምፒዮን የምንሆነው ብለን መፋለም አለብን…

ሊግ:- ራስን ከመጠበቅ ተገቢ በሆነ መንገድ ከማረፍ አንጻር የእኛ ተጨዋቾች ጋር  ክፍተት የሀም..?

ቢኒያም:- ፕሮፌሽናሊዝም ራሱ የሚለው ነገር አለ….እያንዳንዱ ተጨዋች ያለው ሰውነቱ ይለያያል ይላል..ሜሲን ብታይ ጨዋታው ድረስ እየተዝናና ነው የሚቆየው… ሜዳ ሲገባ ማን ያቆመዋል…? ሌላውም እንደዛ በራሱ መንገድ ….ሁሉም አንድ አይነት ስሜት ይሰማዋል ብዬ አላስብም… ተጨዋቹ ሰውነቱን ስሜቱን ማዳመጥ አለበት ብዬ አምናለሁ…..ማረፍ ያለበት ሰአት ማረፍ የግድ ነው … እዚህኮ የቀን እንቅልፍ መተኛት የማይችሉ አሉ…  አሁን ብተኛ  ለሊት እንቢ ይለኛል የሚሉ አሉ …/ሳቅ/ ዋናውኮ ግን ውስጡን ማዳመጥ አለበት ባይ ነኝ …..

ሊግ:- በእግር ኳሱ ተጠቅሜያለሁ ብለህ ታስባለህ…?

ቢኒያም:- /ሳቅ በሳቅ/ እግዚአብሄር ይመስገን… መጠቀምን በብዙ መንገድ ነው የማየው… መልካም ሰው አግኝቼበታለሁ… የተለያዩ ሰዎችን ሳውቅ የተለያዩ ዕውቀት ገብይቻለሁ… እነኚህም ጥቅሞች ናቸው። ዋናው ግን በሚወደድ ሙያ ላይ የምንገኘውን እየተከፈለን ነው፡፡ ይሄም ጥቅም ነው፡፡ ኑሮው ከባድ ቢሆንም እየተጎዳሁ ነው የምንጫወተው ማለት ግን ውሸት ነው የሚሆነውና እኔንም ጨምሮ ሁሉም ተጨዋች እየተጠቀመ ነው የምንጫወተው /ሳቅ/

ሊግ:- የውጪ ዕድል ሙከራ ላይ  እንዴት ነህ..?

ቢኒያም: ዕድሎቹማ ይኖራሉ…. አሁን ላይ ግን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች በመሆኔ ሙሉ ትኩረቴ ክለቤ ላይ ነው። የአመቱ ውድድር ተጀምሯል፡፡ ምንድነው የምናሳካው በሚለው ላይ በሌላ ላይ ማተኮር አልፈልግም… ብዙ ጥያቄዎች መጥተው ነበር፡፡ ከክለቡ ጋር በመነጋገር እንደ ቤተሰብ ከክለቡ ጋር የወሰናቸው አሉ …

ሊግ:- የአመቱ ኮከብ ለመሆን እያለምክ  ነው..? ወይንስ በ2015 ኮከብነትህ ላይ ነህ..?

ቢኒያም:- /ሳቅ/ እውነት ለመናገር ኮከብ መሆን ያስደስታል… ብዙ ታላላቅ ተጨዋቾች ያሳኩት ነው… ይሄ አዋርድ  መሸለም ያስደስታል፡፡ የ2015 ኮከብነቴ ግን ታሪክ ሆኖ በማለፉ ለሌላ ኮከብነት ነው የማልመው… ይሄን ለማሳካት ከክለቤ ጋር ጠንካራ ውጤት በማምጣት የተሻለውን ቢኒያም ለማሳየት ነው የምጥረው.. ለዚህ ደግሞ ከአርብ ጀምሮ ቡድኑን ተቀላቅዬ የምታገል ይሆናል… ቡድኑ ስኬታማ ከሆነ ኮከብነቱ ይመጣል፡፡ አሁን ግን ለክለቤ ውጤት ነው የምጥረው…

ሊግ:- ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ  ላይ ጉጉትህስ ..?

ቢኒያም:- የትኛውም ተጨዋች የመጨረሻ ህልሙ ለሀገሩ ብሄራዊ ቡድን መሰለፍ ነው… ለየትኛውም ክለብም ልትጫወት ትችላለህ መጨረሻው ግን ሀገርህን ማገልገል ነው፡፡ እኔም በጉዳት ከቡድኑ ውጪ ተደርጌያለሁ… ለክለቤ የተሻለ ነገር ካደረኩ የሀገሬን ማሊያ የማድረግ እድል እንደማገኝ ተስፋ አለኝ… የመጀመሪያው ቢኒያም ለጊዮርጊስ ከጠቀመ ሀገሩን እንዲጠቅም መጠራቱ አይቀርም።

ሊግ:- በቦታህ ምርጡ ተጨዋች ማነው ..?

ቢኒያም: እንደ አጠቃላይ ለኔ ምርጡ  ሊዮኔል ሜሲ ነው… በቦታዬ ላልከው ደጋግሜ የማያቸው አንድሬስ ኢኒየሽታና  ሉካ ሞድሪች ናቸው… ስለ ኤውነት እነሱን እሆናለሁ ብዬ አላምንም አልችልምም ያሳኩትን ስታይ እነሱን ለመሆን ማሰብ ከባድ ነው ግን እወዳቸዋለሁ፡፡

ሊግ:- ኢትዮጵያዊው ኢኒየሽታ የመሆን ዕድል ግን አለህኮ..?

ቢኒያም:- እውነት ለመናገር ኢትዮጵያዊው ኢኒየሽታ ለመባል የሚችሉ ብዙ ምርጦች አሉን ከእነሱ ውስጥ እንደ አንዱ ስሜ ቢኖር ደስ ይለኛል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሊግ:- የሀያት ሪጀንሲ የኮከቦች ሽልማት መድረክ ላይ ባለቤትህ ተናጋሪ መሆኗን አሳይታለች… ታዳሚውንም  አስጨብጭባለች… አነጋገር አስተማርካት እንዴ..?

ቢኒያም:- እውነት ነው እንደዚያ ትናገራለች ብዬ አላሰብኩም አስገርማኛለች… በወቅቱ የሻምፒየንስ ሊጉ የመልስ ጨዋታ ስለነበር ከሀገር ውጪ በመሆናችን የሽልማት ስነስርዓት ላይ ላንገኝ እንችላለን ብለን አስበናል። ምናልባት ኮከብ ከሆንክ ብለው ቪዲዮ ቀርጸውኝ ስለነበር ኮከብ ሆኜ ከተመረጥኩ ወክለሽኝ ንግግር የምታደርጊው አንቺ ነሽና ተዘጋጂ ብያት ነበር … በወቅቱ የሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ደረስን መድረክ ላይ ሲጠሯት የሆነ ነገር ማለቷ አይቀርም ብዬ ነበር እሷም በአሪፍ ሁኔታ ንግግር አደረገች… ታዳሚውን ብቻ ሳይሆን እኔንም አስገርማኛለች… /ሳቅ በሳቅ/

ሊግ:- ጨረስኩ የምታመሰግነው ሰው ካለ..?

ቢኒያም:- የቅድሚያ ምስጋናው ለፈጣሪዬ ይሁንልኝ…. ከዚያ ውዷ ባለቤቴ፣ ቤተሰቦቼ፣ በእያንዳንዱ የእድሜ ደረጃ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞቼን /ኢዮብ ተዋበ፣ አሰልጣኝ ጣሰው፣ አሰልጣኝ ሲሳይ፣ አሰልጣኝ ጸጋዬ፣ በተለይ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ታች ላይ እያለሁ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን የጠራኝ እሱ ነው፣ የውጪ ዕድሉን ያመቻቸልኝ ጀርመናዊው  ዮሀኪም ፊከርት፣ አሁን ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት አሰልጣኝ ዘሪሁን፣ አዲሴ፣ ውበሸት፣ ደረጄ፣ አዴ፣ የክለቡ አመራሮችና ደጋፊዎች የቡድኑ አጠቃላይ አባላትን ጓደኞቼን በሙሉ አመሰግናለሁ…

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P