ዕድገቱ መተሃራ ነው … እግርኳስንም በመተሃራ ስኳር ጀመረ… “ወላይታ ድቻ ከአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋር ለሁለት አመት ሰራሁና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ወደ አዳማ ወሰደኝ ሁለት አመት ተጫወትኩ ከዚያ ወልዲያ ሄድኩ በወቅቱ የተላለፈብኝ ቅጣት ሞራሌን አቀዝቅዞት ነበር ነገር ግን አዳማ ባለውለታችን ነው ብለው ከቅጣት ስመለስ እንደገና ፈረምኩ በወቅቱ አማራጭ ቢኖረኝም አዳማን መረጥኩ ለአዳማ አንድ አመት ከ6 ወር ተጫውቼ ለአንድ አመት ለሀድያ ሆሳዕና ፈረምኩ ከሀድየያ ሆሳዕና ወደ ድሬዳዋ ተጉዤ ሁለት አመት ተጫውቼ አሁን በሀምበሪቾ እገኛለ” ያለው እንግዳችን ብሩክ ቃልቦሬ ነው ላለፉት አምስት ወራቶች ደመወዝ ያልተከፈላቸው ተጨዋቾች መሃል ዘጠኝ የሚጠጉትን ሳይይዙ ወደ ድሬዳዋ ያቀኑት የሀምበሪቾ አመራሮች ጋር በተፈጠረ አለመግባባትና ሌሎች ጉዳዮ ዙሪያ የሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ላነሳለት ጥያቄ ብሩክ ቃልቦሬ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።
ሊግ :- ብሩክ ቃልቦሬ የሚታወቅ ስም ነው.. ለምን ይመስልሃል..?
ብሩክ:- የአባቴ ስም ለየት ስላለ በደንብ ይታወቃል ..የምጠራውም በቃልቦሬ ነው ሁለተኛ ደግሞ ከተጨዋቾች ጋር ያለኝ ግንኙነትና መብቴን በመጠየቅ እታወቃለሁ አሁን አሁን ግን መብቱን የሚጠየቅ ተጨዋች በክለቦች አይወደድም በዚህ ምክንያት በራቸውን የዘጉብኝ ክለቦች አሉ.. ጨርሼ ገባሁ ስል ሳይሳካ ይቀራል ወደምወደው እግርኳስ እንዳልመለስ እያደረገኝ ነው
ሊግ :- መታገስ ነበረባቸው ይላሉ ምንድነው ምላሽህ..?
ብሩክ:- ክለቦችኮ አንዳንዴ ደመወዝ የመክፈል ችግር ሊከሰትባቸው ይችላል ይህን እረዳለሁ ግን አምስት ወር ሙሉ ደመወዝ አለመከፈሉ ግን ልክ አይመስለኝም የተወሰነ የምትችለው ነገር አለ አምስት ወር ላይ ሙሉ ደመወዝ ማጣት የምመራው ቤተሰብ አለ የማስተምራቸው ልጆች የማስተዳድራቸው አሉ ያንንም ችግር ተሸክሜ ኳስ መጫወት ይከብዳል። አንደኛው ዙር ላይ ሳይከፈለን ሁለተኛው ዘር ላይ ሄዶ መጫወትም አልፈልግም እናትና አባቴን የምጦረው እኔ ነን። እናትና አባቴን የለመዱትን አስቀርቼ እንዴት ብዬ ሄጄ ልጫወት..? አንድነ ምሳሌ ልስጥህ ድሬዳዋ ከተማ ሁለት አመት ተጫውቻለሁ ምንም አይነት ችግር ሳይፈጠር በመልካም ተለያይቼ የምደዋወላቸው እንዲቀናቸው የምመኝላቸው ናቸው ጥሩ ግንኙነት የፈጠርንባቸው ክለቦች አሉ አሁን ግን እዚህ ያለውን እንዴት ይታለፍ ከቤተሰብ የሚበልጥ የለም ስራዬኮ ከቤተሰብ ቀጥሎ የሚመጣ ነው። አሞህ ታክመህ ደረሰኝ ስታመጣ አይከፍሉም ከባድ ወጪ ሳይሆን ብር የለም ይላሉ እግዚአብሄር አያምጣው እንጂ ሜዳ ውስጥ ብትጎዳ ለማን አቤት ትላለህ..? በዚህ አይነት ሞራል አትምጡ ሲሉን ገረመኝ ደግሞ የሰማሁት ውል ላይ ደምወዝ ካልተከፈለው ይልቀቅ አይልም የሚል ነገር አለ ይሄ ቀልድ ነው የሚጠበቅብኝን ካላደረኩ እንደምቀጣ ሁሉ እነሱም ደመወዜን በግድ መክፈል አለባቸው ይሄ ነው እውነቱ …
ሊግ :-የሀምበሪቾ ዱራሜ ውጤት ማጣት ከደመወዝ ክፍያ በወቅቱ አለማግኘት ጋር ሊያያዝ ይችላል..?
ብሩክ:- በሚገባ እንጂ… መጀመሪያ ተሰባስበን ስናወራ ሀምበሪቾ በፕሪሚየር ሊጉ እንዲቆይ ታሪኩ እንዲቀጥል በፕሪሚየር ሊጉ ትልቅ ተፎካካሪ እንዲሆን ከነበረው አሰልጣኝ ጋር ተመካክረን ነው ወደ ውድድር የገባነው በኋላ ግን ክለቡና ተጨዋቹ መሃል ክፍተት ተፈጠረ ተጨዋቹም ሞራሉ ወረደ ሜዳ ውስጥ ብጎዳ የምሆነው ምንድነው የሚጠይቀኝ አካልኮ የለም መባል ተጀመረ በዚያ መልክ የነበረው ህብረትና አንድነት እየጠፋ ሄደ በኋላ ከኳሱ ውጪ ሌላ መልክ ይዞ መጣ በቃ የነበረው ችግር ውጤቱ ላይ አስተዋጽኦ አለው የምለው በዚህ ነው
ሊግ;- ደመወዛችሁ እንዲከፈል በይፋ ጠይቃችኋል..?
በብሩክ:- በተደጌጋሚ ጠይቀናል ለምነናል ግን አልሆነም የለፋንበትን ደመወዛችንን ስጡን ብለን ከመለመን ውጪ ምን ይመጣል..? መብት ስትጠይቅ አሳማጭ ምናምን ትባላለህ ሲሰለቸን ወደ 22 ሆነን ፌዴሬሽን ቢሮ ሄድንንና አነጋገርን ዋና ስራ
አስፈጻሚው አቶ ባህሩ ጥላሁን የተፈጠረውን አልሰሙም ነበር ያለውን ነገር አብራራንላቸው አዘኑ በቃ ችግር የለውሞ መብታችሁን መጠየቅ ትችላላችሁ እኛ በህጋዊ መንገድ እንፈታዋለን ብለውን ተለያየን እስካሁን መልስ የለም ከፌዴሬሽኑ መብታችንን የሚያስከብርልንን ምላሽ ግን እየጠበቅን ነበር እንደገና ሄደን አመለከትን እስካሁን አልተከፈልንም ስንላቸው ከአሁን በኋላ የሚለምኑት እናንተን ነው አሉን መብታችሁ ይከበራል ብለውን ምላሽም እየጠበቅን ነው።
ሊግ:- እስቲ ስለተሰጣችሁ ቼክ እናውራ..?
ብሩክ:- ቼኩን ተቀብለን ለጥቅምት 20 ቀጠሩን ብሩ የለም በተደጋጋሚ ለመንን ጠየቅን ግን ምላሽ አሁንም የለም ከዚህ በኋላ አንጠይቅም አልን ቼኩ 6 ወር ካለፈው ኤክስፓይርድ ይሆናል ተብለን ቀድመን አስመታነው ብር መክፈል አቅቷቸው ይሁን ባናውቅም ጠበቃ ቀጥረን እየተከራከርን ነው ስራ አስኪያጂም የክሱን ደብዳቤ ፈርሞ ተቀበለ አሁን ያለው ነገርም ይህን ይመስላል
ሊግ :-ወደ 9 ተጨዋቾችን ትተዋችሁ ወደ ድሬዳዋ ሄዱ መባሉ እውነት ነው..?
ብሩክ:-‘ የአምስት ወር ደመወዝ አለመክፈላቸው ሳያሳስባቸው እኛ ከኳስ ብንቀር የምንጎዳ መስሏቸው ወደ 9 ለምንጠጋ ተጨዋቾች በስምምነታችን እንለያይ ብለው አስቀሩን… እያገለገልን በሙያችን እየሰራን ነው ያስቀሩን… ለኔ ቡድን መሪው ደወለና በስምምነት እንለያይ ብለዋል ሲለኝ ችግር የለም የስንብት ወረቀት ስጡኝ ስል አልመለሱልኝም ትተውን ወደ ድሬዳዋ ሄደዋል ይሄ በጣም ገርሞኛል
ሊግ :- ሌሎች ክለቦች ከፈለጉህ በርህ ክፍት ነው..?
ብሩክ:-በሚገባ … መጫወት ስለምፈልግ ለሚፈልገኝ ክለብ በሬ ክፍት ነው በግሌ እየተዘጋጀሁ ከቤተሰብ ጋር ነኝ ለፈለገኝ ክለብ ያለኝን ልሰጥ ዝግጁ ነኝ
ሊግ :- ፕሪሚየር ሊጉን እንዴት አገኘኧው።..?
ብሩክ:- ከበፊቱ የተወሰነ ወረድ ያለ ይመስለኛል አብዛኞቹ ቡድኖች ነጥብ እየጣሉ ነው አምና የነበሩ ወራጅ ክለቦች ነጥባቸው አሁን ወራጅ ላይ ካሉት ክለቦች ነጥብ ይበልጥ ነበር ጠንካራ ፉክክር ተቀራራቢ ነጥብ ነበር ከአምና… የዘንድሮ ቀነስ ብሎብኛል
ሊግ :- በፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ቡድን አለ..?
ብሩክ:- ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥሩ ጥሩ ልጆች ፈረሙ ሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን ቢሮ ውስጥ ያለ ሁሉ ሃላፊነቱን ተወጣ ተጨዋቾቹን በደንብ ተንከባክበው ያዙ አሁን እንደሆነው ለዋንጫ እየተፎካከሩ ነው
ሊግ :- ሶስታችሁ ወደ ፕሪሚየር ሊግ አብራችሁ አድጋችሁ ሻሸመኔና ሀምበሪቾ ላለመውረድ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግን የዋንጫ ፉክክር ላይ መሆኑ አያስቀናም..?
ብሩክ:- እውነት ነው ይሰማሃል …ልዩነቱ በጀቱ አሪፍ ነው ጥራት ያላቸውን ተጨዋቾች ይዟል ተጨዋቾቹን የያዘበት መንገድና ቢሮ ውስጥ ያለው የአስተዳደር ስራ ቅንጅት ነው ውጤት የሚያመጣው የለፉበትን ፍሬ እየበሉ ነው ልዩነቱ ይሄ ይመስለኛል። ይሄ ትምህርት ነው ተገቢ ክፍያ ከተከፈለኝ ያንን ላለማጣት ጠንክሬ ነው የምፋለመው ቀንና ለሊት እንዳስብ የው የሚያደርገኝ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረገው እሱን ነው።
ሊግ :- በቦታህ ለአንተ ምርጡ ማነው …?
ብሩክ:- ሀገር ውስጥ ላልከኝ ለመከላከያ አሁን ለመቻል ይጫወት የነበረው ብሩክ /ቡራ/ በጣም እወደው ነበር ነፍሱ ይማርና በመኪና አደጋ ህይወቱ አልፏል አጨዋወቱን እወደው ነበር …አሁን ደግሞ እነ አለልኝ
እነ ፉሃድ እነ ባሴሩ አሉ ጥሩ ጊዜ አሳልፈዋል…ከውጪ ደግሞ የቀድሞ የቸልሲ ተጨዋች ንጎሎ ካንቴን እወደዋለሁ።
ሊግ :- የተከላካይ አማካይ ቦታ ተሰላፈዎች የማይታዩ ግድግዳዎች ናቸው ግን ትትልቅ ጥቅም ያላቸው አይደል….?
ብሩክ:- አዎ የማንታይ ግድግዳዎች ነን በቡድን ስራ ላይ የሚሰሩ ግን የማይታዩ ግድግዳ ሲባል ስያሜው ደስ ይላል…ቦታው ትልቅ ደስታ ይፈጥራል በብሄራዊ ቡድንም ይሁን በክለብም ደረጃ ከተከላካይ አማካይ ውጪ ስኪመር፣ የግራ ተመላላሽ፣ የመሃል ተከላካይ፣ የመስመር አጥቂ ሆኜ ተጫውቻለሁ አሰልጣኜ በሚፈልገው ቦታ ቢያሰልፈኝ ቅሬታ የለብኝም በዚያ ቦታ ላይ ማገልገልን እመርጣሁ ከግል ይልቅ ለቡድን ድል የሚተጋ ተጨዋች እመርጣለሁ እኔም እንዲሁ ነኝ
ማንንም ብትጠይቅ በክለብም ይሁን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከእኔ ጋር የተጫወቱ ሁሉ ያውቁኛል ጥሩ ሳልሆን ቡድኔ ካሸነፈ የምጨፍር አይነት ሰው ነኝ ጥሩ ሆኜ ካላሸነፈም እበሳጫለሁ በቡድኑ ድል ውስጥ ነው የኔ ስኬት ያለው ብዬ አስባለሁ የሚፈልጉኝም ይህን ብሩክ ያገኙታል….
ሊግ:- አመሰግናለሁ ለቃለ ምልልሱ…
ብሩክ: እኔም አመሰግናለሁ… ለሰጣችሁኝ እድል ያለውን ትልቅ ችግር እንድገልጽ ስላደረጋችሁ ሊግን ከልብ አመሰግናለሁ።