እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎ….የተጫወቱበትን ክለብ የማሰልጠን ዕድል ስንቱ ያገኝ ይሆን ብለው ያስባሉ.? እንግዳችን ግን ዕድለኛ ከሆኑት መሃል ይጠቀሳል… ብዙዎች የሚመኙትን ያገኘ አሰልጣኝ ነው በተጨዋችነት ዘመኑ አዳማ ከተማ፣ ወንጂ ስኳር፣ መተሀራና ሀረር ቢራ ተጫውቶ አሳልፎ በአሁኑ ወቅት የተጫወተበትን ክለብ አዳማ ከተማን እያሰለጠነ ይገኛል..በወጣቶች ያምናል “በወጣቶች ማመኔ ጠቅሞኛል” የሚለው ወጣቱ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ… ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በታሪኩ የመጀመሪያ የሆነውን ቃለምልልስ ያደረገውና ዛሬ ምሽት ከባህርዳር ከተማ ጋር ጠንካራ ጨዋታ ያለበት አሰልጣኝ ይታገሱ ለቀረበለት ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል…
ሊግ:- በተጨዋችነት ዘመንህ ለአንተ በቦታህ ምርጡ ማን ነው..?
ይታገሱ:- በተጨዋችነት ዘመኔ ለኔ ምርጥ የነበሩት ጌቱ ተሾመና አንተነህ አላምረው ናቸው፡፡ በቦታዬ ምርጥ የሚባሉ ነበሩ፡፡
ሊግ:- ለአንተ ከውጪ ምርጡ አሰልጣኝ ማነው …..?
ይታገሱ:- ጣሊያናዊውን ካርሎ አንቾሎቲ በጣም የምወደው አሰልጣኝ ነው … ብቃቱ ለየት ይልብኛል አሁን ደግሞ የተቆጣጠረኝና ትኩረቴን የሳበው የብራይተኑ ዲዘርቢ ነው። ሀሳብ ላይ የሚያተኩር አሰልጣኝ ነው፡፡ በስብስቡ ላይ የተመሰረተ የሆነ ተጨዋች ሲጎል የሚጎዳ በተጨዋቾች ላይ የተንጠለጠለ ቡድን ሳይሆን ሀሳብ ያለው ቡድን ገንብቷል፡፡ ዌልቤክን እየው ከማን.ዩናይትድ ከወጣ ከ9 አመት በላይ ሆኖታል እንደ አዲስ እየተነሳ ነው የዲዘርቢ አጨዋወት እሱንም የማይታወቁትንም ከፍ አድርጓቸዋል፡፡ በትናንሽ ብር ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው ውስጡ ያለውን ሃሳብ ነው የሚያሳያቸው ብዙ ምርጥ ተጨዋቾች ሄደውበት ብዙ ያልተጎዳው ለዚህ ነው በአጨዋወት ዘይቤው ሁሌ ባየው ደስ ይለኛል …ፔፕ ጋርዲዮላን እወደዋለሁ ባሉት አቅም ባላቸው ተጨዋቾች የሚታይ ኳስ እያሳየን ነው ለሱ አድናቆት አለኝ… እንደ አጠቃላይ ግን የሁለቱ የአንቾሎቲና ዲዘርቢ አድናቂ ነኝ።
ሊግ:- አቅም አለኝ ብቃቴ ላይ እገኛለሁ ማለት ትችላለህ..?
ይታገሱ:- አይይ… ወጣቱ ገና እየሰራ ያለ በነገው ላይ ህልም የሚያልም አሰልጣኝ ነኝ ብዬ ነው የማስበው .. ምርጥ ነኝ ልዩ ነኝ ብዬ አላምንም ወጣት ስራውን የሚወድ ለማደግ ገና የሚማር ጀማሪ አሰልጣኝ መሆኔን ነው የማውቀው….
ሊግ:- የት የመድረስ እቅድ አለህ…?.
ይታገሱ:- ማንኛውም አሰልጣኝ የራሱ ግብ አለው መነሻ መድረሻም አለው የትኛውም አሰልጣኝ የሀገሩ ብሄራዊ ቡድንን ማሰልጠን ይፈልጋል ፡፡ እኔም ተመሳሳይ አላማ አለኝ፡፡ ከሀገር ወጥቼም እንደነ ውበቱ አባተ እንደ አብርሃም እንደ ስዩም ወጥቼ ማሰልጠን እፈልጋለሁ እንደዚያ ስላልኩኝ ብቻ አይሳካም መማር መታገል ይጠይቃል ትልቅ ግብ አለኝ አሁን ያንን ግብ ለማሳካት ጉዞውን የጀመረ አሰልጣኝ ነኝ…
ሊግ:- በቅርብ ጊዜ ውስጥ ብሄራዊ ቡድን ቢሰጠኝ ብለህ ትመኛለህ..?
ይታገሱ:- የብሄራዊ ቡድን ሃላፊነት ቢሰጠኝ በፍጹም አልቀበልም ቦታው አቅም ትልቅ ሃላፊነት የሚጠይቅ ነው…በኔ በኩል በፕሪሚየር ሊጉ ገና ሁለቴ አመቴ ላይም ነኝ፡፡ ለዚያ ሀላፊነት ዝግጁ አይደለሁም ገና መማር አለብኝ፡፡ ና ያዝ ተባልኩ ብለህ የምትገባበት አይደለም፡፡ አቅሜን ሰው ሊነግረኝ አይገባም ልኬን ራሴን ማወቅ አለብኝ ሁሉም በጊዜው ይሆናል ብዬ አስባለሁ በእድሜና በአስተሳሰብ በመማር በማወቅ ራሴን እያበረታሁ ከፍ እያደረኩ ስሄድ ሃሳቤ ይሳካል… በእውቀት የዳበሩ አሰልጣኞች እያሉ አሁንኳ ያገኘሁትን እድል ልደሰትበት ይገባል…ለማንኛውም ለቦታው አቅም ልምድ እንደዚሁም በአዕምሮ ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል ታማኝ መሆን ይጠይቃል….
ሊግ:- የእውነት ምክትል ወይም ረዳት ነበርክ ..? ከነሱስ
ብዙ ተጠቀምክባቸው….?
ይታገሱ:- ምክትል አሰልጣኝ ሆኜ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ፣ አሰልጣኝ ኤፍሬም እሸቱ፣ አሰልጣኝ ምትኩ ፍቃዱና አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር በምክትልነት ሰርቻለሁ…አብሬ ለሰራኋቸው አሰልጣኞች እውነተኛ ረዳት ሆኜ በታማኝነት አግዣቸዋለሁ እውነተኛ ረዳት ነበርኩ… ከእነሱም የተለያየ ትምህርት አግኝቻለሁ እነሱም በደንብ ያላቸውን ሳይሰስቱ ሰጥተውኛል ደስተኛ ነኝ ከእያንዳንዱም የተሻለ እውቀት ገብይቻለሁ ጨዋነትን ከነዚህ ሰዎች አግኝቻለሁ ለዚህም rአመሰግናለሁ….
ሊግ:-. የአዳማ ከተማ ደጋፊን እንዴት አገኘኧው..?
ይታገሱ:- .አሁን ላይ የአዳማ ደጋፊ ጋር የበፊቱ ስሜት አለ ብዬ አላምንም በከተማችን ብንጫወትም ደጋፊው ባዶውን ሆኖ ይታያል፡፡ አንዱ ምክንያት ዲ ኤስ ቲቪ መኖሩ ሊሆን ይችላል ሌላው የክለቡ የደጋፊ ማህበር አመራሮች ገና አንድ አመታቸው ነው የሚችሉትን እየሰሩ ነው በቀጣይ ለውጥ እጠብቃለሁ.. ያረፉ የክለቡ ደጋፊዎችን ነፍስ ይማርና እንደነሱ አይነት ዘመን ለመመለስና ያን ስሜት ማምጣት ቢቻል ደስ ይለኛል፡፡ ማህበሩም የሚችለውን ለማድረግ እየታገለ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ከዚህም በላይ መጣር አለባቸው.. ያኛው ዘመን ይናፍቀኛል በተወሰነ ደጋፊዎች ያለው ድጋፍ ጥሩ ነው ጨዋታው በሜዳችን እንደመካሄዱ የሜዳ አድቫንቴጅ ባይገኝ እንኳን የደጋፊ መገኘት ነበረበት 12ኛ ተጨዋች ሆነው ከሀገር ሀገር ሄደው የሚደግፉት ደጋፊዎች ሊበዙ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ሊግ:- የፕሪሚየርር ሊጉን ዋንጫ ማን ይወስዳል ብለህ ትገምታለህ..?
ይታገሱ:-. የዋንጫ አሸናፊን ገና በ12ኛ ሳምንት ላይ መገመት አይቻልም .. 18 ጨዋታ እየቀረ አሁን ስለዋንጫ አይገመትም ልዩነቶቹም የሰፉ አይደሉም ብዙ ጨዋታ ይቀራል በደረጃ ታች ያለው 6 ነጥብ ያለው አምበሪች ምርጥ ቡድንኮ ነው ደረጃው ነው የከፋው…. ሶስትና አራት ጨዋታ ቢያሸንፍኮ በደንብ ነው ከፍ የሚለው ነገ ምን እንደሚፈጠር መገመት አይቻልም የምለው ለዚያ ነው፡፡ ያ ማለት ግን ጭላንጭል የሚታይባቸው ቡድኖች የሉም ማለት አይደለም እኔም ተወዳዳሪ እንደመሆኔ ራሴን እዚያ ፉክክር ውስጥ ለማግኘት መጣር ይጠበቅብኛል፡፡ ለጊዜው ግን ዋንጫ ይወስዳል የምለው ክለብ የለም፡፡
ሊግ:- ለስፖርት ቤተሰቡ ምን ትመኛለህ..?
ይታገሱ:- የተሻለ እግርኳስ የተሻለ ውጤት ለሀገሬ ይገባል… የሚያስፈልጉት ነገሮች ተሟልተው ኳስ ወዳዱ የስፖርት ቤተሰብ ጥሩ ኳስ እንዲያይ እመኛለሁ…. እመኛለሁ ስል ግን የሚሰራ የሚሟላ ነገር የግድ ነው፡፡ ከጥራት ከቡድኖች መዋቅር ከፋይናንስ ጋር ተያይዞ ያሉት ችግሮች ተቀርፈው የተሻለ ጨዋታ እንዲያዩ እመኛለሁ ከሜዳ ጋር ተያይዞ ያሉትም ችግሮች መፈታታቸው ግን የግድ ነው፡፡
ሊግ:- ፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ነው ማለት ይቻላል…?
ይታገሱ:- ሊጉ ጠኔካራ የማይሆንባቸውን ምክንያትኮ ይታወቃል እንደ ሀገር ከባድ የሆኑትን ችግሮችን ተቋቁሞ ውድድር መኖሩ ትልቅ ነው በቲቪ የሚታየውን አይቶ ጠንካራ ነው አይደለም ማለት ሳይሆን ጥናት ይጠይቃል
ሊግ:- በኛ ሀገር ከኳሱ እንዲርቅ እንዳይኖር የምትፈልገው ምንድነው…?
ይታገሱ:- ትልቁ ችግር የሜዳ እጥረት ነው በየቦታው 100 እና 200 አባወራ በሰፈረበት ኮንዶሚኒየም ላይ አንድም ሜዳ በሌለበት ለውጥ መጠበቅ ከባድ ነው…. ከሜዳ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ የተጀመሩ ነገሮች አሉ… በክልልም መጀመር አለበት፡፡ በረኛ የለም ይባላል፡፡ ከአ/አ በረኛ ማውጣትና አልተቻለም እየተባለ ነው፡፡ ሜዳ በሌለበት በረኛ ከየት ይምጣ ..? ከየትኛው ሜዳ ላይ ይገኝ ..? አሁን ደግም ችግሩ እየሰፋ ነው፡፡ ሊጋችን አደገ አላደገ የምንለው በመረጃ ነው… አንድ ሜዳ ላይ ለአራት ክለቦች እየሰራን ነው እሱም ተገምቶልህ 30 ደቂቃ ወይም አንድ ሰአት ነው ተብሎ ተገምቶልህ በአሰልጣኙ የልምምድ እቅድ ሳይሆን የሊግ ኩባንያው ፕሮግራም ውስጥ እየሰራህ እንዴት ለውጥ ይጠበቃል..? ይሄ መታረም አለበት ሜዳ ላይ ይዤ የምቀርበውን ቡድንና አጨዋወት የሚወስነውኮ ሜዳው ነው፡፡ ሁለት ወይም ሶስት ቡድኖች ብቻ ናቸው ተሟልቶላቸው የሚሰሩት .. ከእነሱ እኩል ጥሩ ነገር አድርጉ ማለት ይከብዳል፡፡ በእኔ እምነት የሜዳዎች ችግር ይብቃ ኖ ሞር እላለሁ፡፡
ሊግ:- ለሜዳ ችግሩ መፍትሄ ክለቦችስ ድርሻ የላቸውም?
ይታገሱ:- አላቸው እንጂ ሁሌ መንግስት የምንለው መቆም አለበት፡፡ ለ25 ተጨዋቾች ከፍተኛ ክፍያ ከፍለው ከሚያመጡ ሜዳው ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው የሚረባ ሜዳ በሌለበት ሀገር ላይ የኳሱን እድገት መጠበቅ ከባድ ነው፡፡ አንዳንዴ ወደራሳችን ፊታችንን እናዙር …በዋናናነት ግን የልምምድ ሜዳ ወሳኝ ነው
ሊግ:- ትዳርህን እስቲ እስቲ አስተዋውቀኝ …?
ይታገሱ:- እንደ ልቤ ሆኜ ብዙ ሃሳብ ሳይኖርብኝ ስራዬን ለመስራት አጠገቤ ያለችው ባለቤቴ ዮርዳኖስ ጎሳዬ ትልቁን ድርሻ ትወስዳለች፡፡ የሷ መኖር ሰላሜን ነጻነቴን ሰጥቶኛል አራት ወንድ ልጆች አሉኝ በእምነት፣ በፍቅር የአብስራና በአማን ይባላሉ…
ሊግ:- 5ለ1 እየመራህ ነዋ..?
ይታገሱ:- /ሳቅ በሳቅ/ አዎ የኋላ አራቱ የተከላካይ መስመሬ ሙሉ ነው በዚህም ደስተኛ ነኝ/ሳቅ/ በየሀገሩ እሄዳለሁ አዳማም ሆኜ ሳምንቱንም ቤት ላልሄድ እችላለሁ፡፡ አብረውኝ ያሉት አሰልጣኞችና ተጨዋቾቼ ቤተሰብ አላቸው፡፡ እኔ አዳማ ስላለሁ ብመላለስ አይሆንም በግሌ ስራውን ማክበር አለብኝ … ቤት እየሄድኩ እነሱ ቢጠይቁኝ እንቢ ማለት አልችልምና መሪ መሆኔን ማሳየት አለብኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ እናም ብቻዋን ተቆጣጥራ ስራዬን በነጻነት እንድሰራ ያደረገችኝን ባለቤቴን አመሰግናለሁ በስራዬ ላለሁበት የአንበሳውን ድርሻ የያዘው፡፡ የሷ ታታሪነት፣ ፍቃድና ፍቅር ነውና በሷም ደስተኛ ነኝ…
ሊግ:- የመጨረሻ የምታመሰግነው ካለ….
ይታገሱ:- በህይወት አጋጣሚ በጉዞህ ውስጥ ገፋ ደገፍ የሚያደርጉህ ሰዎች ያስፈልጉሃል.. እኔ አዳማ ከተማን እንድይዝ ያመኑኝ ሃላፊነት የወሰዱልኝ በተከታታይ አራት ጨዋታ ስሸነፍ ታግሰው ያበረቱኝ ባለውለታዎቼ ናቸው የወጣቶችና ስፖርት ይሰራ የነበረው አቶ አለማየሁ ቱሉ፣ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ መገርሳና የስፖርት ጽ/ቤት ሃላፊው ለአቶ ሙአታ አብደላ ትልቅ ምስጋናና ክብር አለኝ ሶስት አራት ጨዋታ ስትሸነፍ በምትባረርበት ሊግ ላይ ለሰጡኝ እምነት ክብር አለኝ ማባረር አየቻሉ ጠብቀው ታግሰውኝ ሁለተኛ አመቴን ይዣለሁ ከባዱን ሀላፊነት ወስደው ከምክትልነት እንድመጣ አድርገውኛል እምነት ጥለው ዋና አሰልጣኝ ሆኛለሁ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
እግዚአብሄር ብድራችሁን ይክፈል ማለት እፈልጋለሁ የወቅቱ ኮሚቴዎች የስፖርት ጽ/ቤቱና የክለቡ ሰራተኞችንም አመሰግናለሁ፡፡ የክለቡም የቦርድ አባላትና ቴክኒክ ኮሚቴውንም አመሰግናለሁ፡፡ በተጨማሪ በሙያዬ እያገዙኝ እያበረቱኝ ያሉትን ውበቱ አባተና ተድላ በላቸውን አመሰግናለሁ፡፡ ውበቱ አብሬው ሰርቻለሁ አሰልጥኖኛል ያለውን ሰጥቶኛል ሃላፊነት ወስዶ ነው ምክትሉ ያደረገኝ አመሰግናለሁ፡፡ ተድላን በእጅ የያዝነው ሆኖ እንጂ ላይብረሪ በለው እንደ ሀገር መጥቀም የሚችል ወንድማችን ነው፡፡ ብዙ ነገር ነው የሚረዳኝ፡፡ ታማኝነትን ጨዋነትን ፈሪሃ እግዚአብሄር እንዲኖረኝ አድርጎኛል፡፡ እንዳልዋዥቅ አበርትቶኛል፡፡ ከአዲስ አበባ አዳማ እየተመላለሰ ጨዋታዎችን ያያል፡፡ ትልቅ ደጋፊዬ ነው፡፡ ከልብ አመሰግናቸዋለሁ…