በተለይ ለሊግ ስፖርት
በአለም ሰገድ ሰይፉ
ብዙሃኖች አቶ ዳዊት ውብሸትን ያልተዘመረለት ጀግና እያሉ ያወድሱታል፡፡ አደባባይ ወጥቶ እዩኝ እዩኝ ከማለት ይልቅ አንገቱን ደፍቶ ሀገር ልትጠቀም የምትችልባቸውን ታላላቅ ፕሮጀክቶች በበላይነት እየመራ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ከሚያስተዳድራቸው በርካታ ግዙፍ ኩባንያዎች ባሻገር በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር ጭነቶች /FIATA/ የአየር ጭነት አገልግሎት ፕሬዝዳንት በመሆን ከአፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዝዳንት ሆኖ በመመረጥ ሀገሩ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ የቻለ ወጣት ባለሀብት ነው፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ ከዘር ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ታሪክ የቅ/ጊዮርጊስ ቀንደኛ ደጋፊ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ክለቡን በገንዘብና በእውቀቱ ከመደገፍም ባሻገር ቅ/ጊዮርጊስን በቦርድ አባልነትና በማርኬቲንግ ዲፓርትመንት ኃላፊነት እየመራ ይገኛል፡፡ በወቅታዊ የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ጉዳይ ዙሪያ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አለምሰገድ ሰይፉ ጋር ቆይታ አድርጓል ትከታተሉ ዘንድ የአብሮነት ግብዣዬ ነው፡፡
ሊግ፡- በአሁኑ ሰዓት ቅ/ጊዮርጊስ በከፍተኛ ደረጃ እየተፍረከረከ ነው የሚል ነገር በስፋት ይደመጣል፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
አቶ ዳዊት፡- ምን ማለት ነው መፍረክረክ? ይህ አባባል በፍፁም ታላቁን የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ የሚወክል አይደለም፡፡ አንድ የማንክደው ሀቅ ቢኖር ክለቡ በአሁኑ ሰዓት የገጠመው የፋይናንስ ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር እንዴት እንደመጣ ማወቅ ብቻ ሳይሆን በምን መልኩ መወገድ አለበት? የሚለውንም የመፍትሄ ሀሳብ ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡
የተፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ባለፈው ዓመት ሶስት ስፖንሰሮችን አምጥተናል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ከቢጂአይ ጋር ያለንን የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ትንሽ ዋጋውን ከፍ አድርገን በሂደት ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ሆኖም ያለው ወቅታዊ የገበያ ሁኔታ ትንሽ እያንገዳገደን ነው እንጂ ምንም የተፈጠረ የተለየ ነገር የለም፡፡ እንደው የወሬ ፍጆታውን ከፍ ለማድረግ ታስቦ ካልሆነ በቀር ከአራትና ሶስት ሳምንታት በፊት እኮ የፕሪምየር ሊጉ መሪ ነበርን፡፡
ሊግ፡- አሁን ግን አይደላችሁም?
አቶ ዳዊት፡- እናውቃለን፡፡ ይህ እኮ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እኔ በጣም የሚገርመኝ ነገር ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት የሊጉን ዋንጫ በፈተናና ችግር ውስጥ አልፈን ባለታሪክ ስንሆን እኮ ዜናው ይሄን ያህል በስፋት አልተወራም፡፡ ዘንድሮ በነበሩት አምስት ጨዋታዎች ላይ የተፈጠረውን የውጤት ክፍተት በመጠቀም ወሬውን ይሄን ያክል ለማራገብ የተኬደበት ርቀት በእጅጉ ይገርመኛል፡፡
ሊግ፡- በተደጋጋሚ የምሰማው ነገር አለ፡፡ አሁን ያሉት የክለቡ የቦርድ አመራሮች ቅ/ጊዮርጊስን መምራት ከብዷቸዋል እየተባለ ነው፡፡ የእውነት ኃላፊነቱን ለመሸከም ተቸግራችኋል?
አቶ ዳዊት፡- የተለየ ያደረግነው ነገር የለም፡፡ ከዛ በተረፈ መምራት ከብዷቸዋል እያሉ የሚያስነግሩትና የሚያፅፉት ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ ከክለቡ የራቁ፣ በዲስፕሊን የተሰናበቱና የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊ ነን በማለት ከኋላቸው አፍራሽ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ከዚያ በተረፈ ክለቡና እኛ ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታና አቅም የሚረዱ ሰዎች ግን ያለውን እውነታ በሚገባ ይገነዘቡታል፡፡
ሁላችሁም እንደምታውቁት በአሁኑ ሰዓት ፕሬዝዳንታችን አጠገባችን የሉም፡፡ ከዛ በተረፈ ቦርዱ ውስጥ የነበሩት ገሚሶቹ ከሀገር ወጥተዋል፣ በሞት ያጣናቸውም አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የአባላቱ ቁጥር መቀነስና እንደበፊቱ ዘጠኝ አለመሆናችን ያነስን ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ያለነው የቦርድ አባላት ያለንን የስራ ጊዜ ሰውተን ቅ/ጊዮርጊስን እያስቀጠልን ነው፡፡ እናውቃለን በአሁኑ ሰዓት ውጤታችን ዝቅ እያለ ነው፡፡ እሱን ለማስተካከል ደግሞ ሜዥሮችን እየወሰድን ነው፡፡
ሊግ፡- የዚህ አይነት አመለካከቶች በተደጋጋሚ መስማታቸው በእናንተ ስሜት ላይ የሚፈጥረው ጫና እንዴት ይገለፃል?
አቶ ዳዊት፡- ይሄን ነገር በሁለት አይነት አመለካከቶች እወስደዋለሁ፡፡ በጣም የሚገርመኝ ቅ/ጊዮርጊስን በእጅጉ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ የአሸናፊነት ባህሉንና ውድቆ የመነሳት ታሪኩን በሚገባ እየተረዱት ነገር ግን ከጀርባቸው ድብቅ አጀንዳ በመያዝ ክለቡ እንዲዋረድና እንዲፍረከረክ በመፈለግ በእኛ ላይ ጫና ለማሳደር በሚሞክሩት ግለሰቦች የእውነት ከልብ አዝናለሁ፡፡ እነዚህ ደግሞ ብዙ አይደሉም፡፡ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ እኛም እነርሱን በደንብ ጠንቅቀን እናውቃቸዋለን፤ እነሱም እኛን በሚገባ ያውቁናል፡፡
ልዩነት ካለ በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር ይቻላል፡፡ ኑ ስንላቸው አይመጡም፡፡ እነርሱ የተሰጣቸውን አጀንዳ ማራመድ ስለሚፈልጉ ብቻ ሃሳቡ አይዋጥላቸውም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ለሰባት ዓመታት ያክል ቅ/ጊዮርጊስን ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ሲያንከራትቱ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ መልካቸውን ቀይረው ለቅ/ጊዮርጊስ ክለብ እኛ እናውቅልሀለን የሚሉት ሲሆኑ ገሚሶቹ ደግሞ በእነርሱ የተደለሉና ያለውን እውነታ በሚገባ ሳይረዱ አንድ የጠቅላላ ጉባኤ አለመጠራትን አጀንዳ በመያዝ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ሌላው ነጥብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዋንጫ በመውሰዳችን ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ ከወሰድን የተቀሩት ክለቦች እንደሌሉ ይቆጠራል የምትለዋን ነገር ለማጥፋት እኛ ዋንጫ እንድናነሳ አይፈለግም፡፡ እንዳልኩህ ከውጭ ያሉት ውጤቱን ከመፈለግ አንፃር ሲሆን ለእኛ በጣም አስቸጋሪ የሆነውና ቅ/ጊዮርጊስን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ የሚገኘው የውስጥ ጠላቱ ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬም ሆነ ነገ ሁሉም ቦታ ልናገረው የምችለው እኛ ከማናቸውም ጋር የመርህ ችግር የለብንም፡፡ ከዚህ በተረፈ እኛ ልንቀበል የማንችለው ከጀርባ ይዘው የመጡትን አጀንዳ ለማስፈፀም ቢሞክሩ መቼም ቢሆን የዚህን አፍራሽ ተልዕኮ አናስተናግድም፡፡ ሆኖም ቅ/ጊዮርጊስን ከፍ የሚያደርግና የሚያሻግር ሃሳብ ይዘው እስከመጡ ድረስ የፈለጉበት ቦታ ድረስ ሄደን ልናናግራቸው ፈቃደኞች ነን፡፡ ግን እነርሱ እኛን በሙሉ አይናቸው ለማየት አይፈልጉም፡፡
በጣም የሚገርመው ደግሞ አሁን እኛ የክለቡ ተቆርቋሪ ነን በማለት በየቦታው የሀሰት መዝሙራቸውን የሚለቁት ላለፉት 5 ዓመታት የክለቡን የአባልነት ክፍያ ያልፈፀሙ፣ ክለቡን በክስ ሲያሯርጡ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በቁጥርም ይሁን በስም ጠንቅቀን እናውቃቸዋለን፡፡ እነርሱ እንደፈለጉ ሲፈነጩ እኛ ዝም ስንላቸው ፍራቻ መሰላቸው፡፡
ሊግ፡- መሠረታዊ ጥያቄው ጠቅላላ ጉባኤ ከሆነ እናንተ ጉባኤውን ለመጥራት ምን አስፈራችሁ?
አቶ ዳዊት፡- ምን የሚያስፈራን ነገር አለ? እየደጋገሙ ጠቅላላ ጉባኤ አልተጠራም እያሉ አይደል? ይኸው በቅርቡ ጉባኤው ይጠራል፡፡ ነገር ግን ይህ የታላቁ ክለብ ጉባኤ ሲጠራ የእነርሱ አይነት ሰዎች እንዲመጡ አይደለም፡፡
ሊግ፡- ለምንድነው የማይመጡት? በአንድ የክለቡ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመገኘት መስፈርቱ ምንድነው?
አቶ ዳዊት፡- በዚህ ጉባኤ ላይ መሳተፍ የሚያስችለው ቅድመ ሁኔታ ምን እንደሆነ ሁሉም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ እናም በዛን ወቅት ጉባኤ ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት የዚህን ታላቅ ክለብ ራዕይ ማስቀጠል የሚችሉ አመራሮች በደጋፊው ይሁንታ ይመረጣል፡፡ ባለፈውም ጊዜ ተናግሬዋለሁ፡፡ ደጋፊው ምርጫ ሲያደርግ እጅግ ከልቡ የሚወደውን ክለብ ወደፊት ማሻገርና ከፍ ማድረግ የሚችል ምርጫ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል፡፡ ቅ/ጊዮርጊስን መምራት ያለውን ከፍተኛ ጫና መሸከም ከባድ ከመሆኑ አንፃር ደጋፊው ከወዲሁ ማን መምጣት አለበት የሚለውን የቤት ስራ አሁን መጀመር አለበት፡፡ ከዚያ በተረፈ ለክለባችን ተራ አሉባልታ ምንም አይጠቅመውም፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ በዘመናት ርካሽ የተባለውን ማሊያ ለብሶ ተጫውቷል፡፡ በአንፃሩ ውድ የተባለውን ማሊያ አጥልቆም ወደሜዳ ገብቷል፡፡ በታሪክ ሂደት ውስጥ በፖለቲካ ችግር ውስጥም ገብቶ ተንደፋድፎ ወጥቷል፡፡ አሁን ደግሞ በታሪክ ታላቅ የሚባል የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ገብቶ ተንደፋድፎ እየወጣ ነው፡፡ እናም ክለባችን መቼም አይወድቅም፡፡ አሁን የእኛ ተርም አልቋል፡፡ በአዲስ መልክ የሚመጡት ደግሞ የክለቡን ሕልውና ያስቀጥሉ፡፡ ይሄን ለማድረግ ምክር አሊያም ፋይናንሺያል ድጋፍ ካስፈለገ አሁንም ቢሆን በእኔ በኩል ቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ እታች ሆኜ ለማገልገል ምንጊዜም ዝግጁ ነን፡፡
ሊግ፡- ይሄ ማለት በድጋሚ ብትመረጥ ቅ/ጊዮርጊስን ለማገልገል ፈቃደኛ አይደለህም ማለት ነው? ከሆነስ? እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስከው ጫናውን ፍራቻ ነው?
አቶ ዳዊት፡- በፍፁም፤ ጫና ፍራቻ ቢሆን ኖሮ የዛሬ ሁለት ዓመት ነበር የምለቀው፡፡ አንተም እነደምታውቀው ባለፉት ሁለት ዓመታት ክለቡ ሻምፒዮን ሲሆን በቁጥር ከሶስት የማንበልጥ የቦርድ አመራሮች ነበርን፡፡ አሁንም እየሰራን ያለነው እኛ ነን፡፡ እናም ይህ ጉዳይ ከጫና ፍራቻ ጋር ፈፅሞ አይገናኝም፡፡
አሁን ያለሁበትን ሁኔታ አንተም ታውቀዋለህ ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁለትና ከዚያ በላይ ኢንተርናሽናል ስራዎች አሉብኝ፡፡ አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ለሶስት መልቲ ሞዳል ላይሰንስ ከተሰጣቸው ኩባንያዎች ውስጥ አንደኛው እኔ ነኝ፡፡ እንደሀገርም እንደስራም ከፍተኛ ጫና ያለበት ዘርፍ ነው፡፡ እነዚህ ሰራዎች በጠቅላላ ደግሞ እኔ ከሌለሁበት መስራት ስለማይችል እነዚህን ትላልቅና ግዙፍ የስራ እንቅስቃሴዎችን ፈር ማስያዝ አለብኝ፡፡ በጣም በሚገርም ሁኔታ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውጭ ሀገር ያሉኝን ሁለት ቢሮዎች ዘግቼ ነው ቅ/ጊዮርጊስን ሳገለግል የነበረው፡፡ አሁን ግን ያለው የስራ ጫና እንደበፊቱ መስዋዕትነት የሚከፈልበት አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ባለችኝ ሰዓትና በማንኛውም ጉዳይ የምወደው ክለቤን ለማገልገል ዝግጁ ነው፡፡
ሊግ፡- ሌላው የሚነሳው ነጥብ በሚዲያ ቀርበው በቃን ይላሉ ነገር ግን አይለቁም የሚል ነገር አለ፡፡ እናም በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ሁሉ ነገር መፍትሄ ያገኛል ማለት ነው?
አቶ ዳዊት፡- ያገኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ ወደዚህ ቦርድ ከገባሁ 6 ዓመት ሆኖኛል፡፡ እናም አንዴ ከተመረጥክ በኋላ አራት ዓመት ማገልገል መብትህ ነው፤ ከዛ በተረፈ ቦርዱ ጉባኤ ሳይጠራ ኤክስትራ ተጠቅሟል ከተባለ ሁለት ዓመት ነው የሚሆነኝ፡፡
ዋናው ነጥብ ዕድሜ መቁጠር ሳይሆን በዚህ ስድስት ዓመታት ውስጥ ምን ተሰርቷል? የሚለው እውነት የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ መቶ ሚሊዮን ብር የፈጀ አካዳሚ ሰርተናል፡፡ 80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በስርዓትና በደመቀ ሁኔታ አክብረናል፡፡
በወቅቱ የነበረውን የኮቪድ ችግር በመቋቋም ክለቡ ተንገዳግዶ እንዳይወድቅ ሰርተናል፡፡ የክለቡ አንጋፋና ወሳኝ የሚባሉ ተጨዋች በዲስፒሊን ግድፈት በማሰናበት በጣም በውስን በጀት ተጨዋቾችን በማስመጣት ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ክለቡን ሻምፒዮን እንዲሆን ለማስቻል ሰርተናል፡፡ ከዚያ በተረፈ በቅርቡ በተወሰኑ ጨዋታዎች በተፈጠረው የውጤት መቀነስ ሁሉ ነገር እንደተገለባበጠ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡
እውነት ነው ቅ/ጊዮርጊስን ማገልገል ለእኛ ክብር ነው፡፡ ነገር ግን ለመውጣት አይፈልጉም የሚለውን ነገር ስሰማ በጣም እገረማለሁ፡፡ እስቲ አንተን ልጠይቅህ የክለቡ የቦርድ አባል በመሆንህ ቅ/ጊዮርጊስ ምንድነው ለእኛ የሚሰጠን? ይሄን የምናደርገው ክለቡን በፍቅር ስለምንወደው ነው እንጂ የራስህን ውድ ጊዜ ሰውተህና ገንዘብህን አውጥተህ የምትመራው ተቋም እንጂ እንደሌላው ቦርዶች ጥቅም የምታገኝበት አይደለም፡፡ እኔ በትንሹ አምስትና አራት ቦርዶችን እየመራሁ እገኛለሁ፡፡ እናም እኔ ያን ያክል የቦርድ ጥማት የለብኝም፡፡ ከዛ በተረፈ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቦርድ መሆን ያን ያክል የሚያጓጓ አይደለም፡፡ መጥቶ ያላየው ካልሆነ በቀር እዛ አካባቢ ያለውን እውነታ የሚያውቅ ግለሰብ እግር ኳሱ አካባቢ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ እውነት ነው በታሪክ ውስጥ የቅ/ጊዮርጊስ የቦርድ አባል መሆን መታደል ነው፡፡ እኔም እኮራበታለሁ፡፡ ግን ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ በሚገባም ቅ/ጊዮርጊስን እንዳገለገልኩ ይሰማኛል፡፡ እናም እንደገና ከመጣ ያለችኝን ጊዜ አጣብቤ ለመምራት እሞክራለሁ፡፡ እውነቱን ግን ስነግርህ ባይመጣ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም እንደኔ ቅ/ጊዮርጊስን የሚወዱ ደጋፊዎች ስላሉ እነርሱም በተራቸው ቢሞክሩት ደስ ይለኛል፡፡ ያን ያክል ጊዜህን ሰውተህ፣ ስራ በድለህ፣ የፋሚሊ ጊዜ ተሻምተህና ከኪስህ ገንዘብ አጥተህ እየሰራህም በዚህ ልክ መሰደብህ በጣም ያማል፡፡
እኔ ውጭ ያለኝን ክብር ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ ነገር ግን እዚህ መጥቼ በማይሆንና ለእኔ ክብር በማይመጥኑ ግለሰቦች ጠዋትና ማታ መሰደብ በራሱ ትልቅ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ጓደኞቼን ብታይ ምን ስለሆንክ ነው ሁሌም እየተሰደብክ የምትሰራው? ትክክለኛ ማንነትህን እኛ እናውቃለን፡፡ ለምንድነው በዚህ ደረጃ ዋጋ የምትከፍለው? ይሉኛል፡፡ ይሄን ሁሉ የማደርገው የክለቡ እውነተኛ ፍቅር እንጂ ያለው እውነታ እዛ ቦታ አንድ ቀን የሚያቆይ አይደለም፡፡
እኔ የክለቡን አደራ ተቀብያለሁ፡፡ ነብሱን ይማረውና ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ እኔ ቢሮ እየመጣ ስናወራ “ይሄን ክለብ አደራችሁን ሁሉም የእናንተ ነው ጠብቁት፣ አንድ ቦታ አድርሱት” ይለኝ ነበር፡፡ የአባቴም አደራ ስላለብኝ እንጂ ከዛ በተረፈ ሌላ አጀንዳ ይዞ ማራገብ ለክለባችን ምንም አይነት ፋይዳ የለውም፡፡
ሊግ፡- አሁን አንተ ከምትለው አንፃር የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊ ሆነው የክለቡን መዳከም የሚፈልጉ አሉ ማለት ነው?
አቶ ዳዊት፡- ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ማሳያው እኮ ሁሌም እኛ ስንሸነፍ ነው ለመሳደብና ለወሬ ከያሉበት ቦታ ብቅ ብቅ የሚሉት፡፡ ከባለፉት አራትና አምስት ሳምንታት በፊት እኮ ምንም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ውጤት ካለ ምንም ብለው ሊናገሩ አይችሉም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታትም ሞክረው ነበር እኮ? ያልተሳካላቸው ክለቡ ውጤታማ ስለነበር ብቻ ነው፡፡ አሁን ትንሽ ውጤቱ ዝቅ ሲል እነርሱም ብቅ አሉ፡፡
አንተ ለ5 ዓመታት ያክል ሀገር ውስጥ ሳትኖር ምን አውቀህ ነው ክለቡን ከእኔ በላይ የሚያውቀው የለም ብለህ የምታወራው? አይደለም አምስት ዓመት አንድ ሳምንት ውጭ ሀገር ተመልሼ ስመጣ ነገሮችን ሁሉ በጠቅላላ ከአዲስ የምጀምር ነው የሚመስለኝ፡፡ ምክንያቱም ነገሮችን በቅርበት በተጠጋህ ቁጥር ነው የምታስተካክለው፡፡ በዛ ላይ ሕጋዊ የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ወረቀቱ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ እናም ለዓመታት፣ ለወራትና ከዛ ለበለጠ ጊዜ ግዴታቸውን ያልተወጡና ለክለቡ ድጋፍ ከኪሳቸው አስር ብር እንኳን ያላዋጡ በአንፃሩ ግን ከውጭ ሆነው የሚሳደቡት ቦርዱ ከሰራው ስራ ሁለት ፐርሰንት እንኳን መስራት ያልቻሉ ናቸው፡፡ ያው የፈረደበት ሶሻል ሚዲያውን ተጠቅመው እንደፈለጉ ይሳደባሉ፡፡ እኛም ችለነዋል፡፡ ግን ይህ ጠቅላላ ጉባኤ ይመጣና የዛኔ የቅ/ጊዮርጊስን መፃኢ ጊዜ የምናይበት ይሆናል፡፡
ሊግ፡- አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የታገደበት ትክክለኛ ምክንያት ምንድነው?
አቶ ዳዊት፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ በታሪኬ እስከማውቀው ለ6 ተከታታይ ሳምንታት ውጤት ሉዝ ያደረግንበትን ጊዜ ለማስታወስ እቸገራለሁ፡፡ በዚህ ጨዋታ 18 ነጥብ ማግኘት ነበረብን፡፡ ያሳካነው ግን ሁለት ነጥብ ነው፡፡ ለዛም ነው ከፊት ያሉት ክለቦች ከእኛ በነጥብ ርቀውን የሄዱት፡፡ ይሄንኑም ለማስተካከል ነው የተሞከረው፡፡ በፊትም እንደምናደርገው የክለቡን አስተዳደራዊና ቴክኒካል ጉዳዮችን ፈትሸናል፡፡ ክለባችን የጨዋታ አናሊስቶች አሉት፡፡ ከዛ በተረፈም እኛም ሁሌ ወደ ሜዳ እንገባለን፡፡ በእነዚህ ወቅቶች የተለያዩ ውይይቶችን እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን የተደረጉት ጥረቶች በሙሉ ውጤቱን መቀየር አልቻሉም፡፡
ምክንያቱን ስንፈትሽና ስንጠይቅ ደግሞ ፕሬዥርን ያለመቋቋም ችግር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ እናም በዚህ ስነ ልቦና ሁሉም የቡድኑ አባላት ጫና ውስጥ ሆኖ መቀጠሉ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ አያስችለንም፡፡ ስለዚህ በጥንቃቄ ዲቴል ገብተን ባየነው መሠረት ለጊዜው ዘሪሁንና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙን ለማገድ ተገደናል፡፡
አንድ መታወቅ ያለበበት ነገር እነርሱ ለጊዜው ታገዱ ማለት ተባረሩ ማለት አይደለም፡፡ ለሚቀጥሉት ቀሪ ጨዋታዎች አግደን በሌላ መንገድ ለመሄድ በማሰብ ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ አይነተኛ ለውጥ እንዲመጣ ለማስቻል ሳይሆን ያንኑ ፎረማት ይዘንና ልጆቹን ከጭንቀት በማላቀቅ ያለንንና የተወሰነ ነገር ጨምረን ወደ ውጤት መሸጋገር እንዲያስችለን ቦርዱ ቁጭ ብሎ ብዙ ሰዓት ከተነጋገረ በኋላ ነው ውሳኔው የተላለፈው፡፡
ሊግ፡- አንተ በዚህ መልኩ ብትገልፀውም ከሌላ ቦታ የሰማሁት ቦርዱ በዚህ ሰዓት አሰልጣኝ ዘሪሁን ላይ ይሄን ውሳኔ ያስተላለፈው በአሁኑ ጊዜ በእነርሱ ላይ የተቀሰቀሰውን ቁጣ ለማብረድ ዘሪሁንን መስዋዕት አድርገውታል ነው የሚባለው፡፡ በዚህ ዙሪያስ ምን ትላለህ?
አቶ ዳዊት፡- ዘሪሁን ምን ሆኖ ነው መስዋዕት የሚሆነው? ተጠያቂ መሆን ካለብን እኛ ነን የምንጠይቀው፡፡ ዘሪሁን ማሰልጠን እንጂ እዚህ እኛ ጋር የአስተዳደር ስራ አይሰራ፡፡ ከአሁን በፊትም ዘሪሁን እዚህ የአመራር ስራ ሲሰራ አላውቅም፡፡ እኛ እንደውም ታች እየወረድን እሱን እናግዘዋለን፡፡ እኔ መጠየቅ ካለብኝ ዳዊት ውብሸት ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ እንደቦርድ ከሆነም ሁሉም የቦርድ አባል ይጠይቃል እንጂ ሌላ የተለየ ታሪክ አይፈጠርም፡፡
ዘሪሁን የነበረበት ችግር በነበሩት አምስት ጨዋታዎች የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለማረም ስንል የወሰድናቸው ውሳኔዎች እንጂ ከዛ ሌላ ምንም የተለየ ነገር የለም፡፡ እኔ እንደው መተዳደሪያና የጠቅላላ ጉባኤያችን ሕግ ስላለው ነው እንጂ ዛሬ መጥቶ ይሄን ኃላፊነት እወስዳለሁ ለሚል አካል አሁኑኑ ቦታውን መልቀቅ እችላለው፡፡
ከዚህ በተረፈ አሉባልታ ለክለባችን ምንም አይጠቅመውም፡፡ ዛሬ አንድ መናገር የምፈልገው እውነት ሚድሮክን በተመለከተ ከእነርሱ እኛ እንቀርባለን፡፡ አብረን ሰርተናል፣ አብረን በልተናል ጠጥተናልም፡፡ እነርሱ የእኛን ያክል ሚድሮክን አያውቁትም፡፡ አሁን የተፈጠረው ክፍተት በሂደት ይፈታል ብለን ነው እስካሁን በትዕግስት የተጓዝነው፡፡ እስቲ ንገረኝ ክለቡ ቢሰጣቸው ምን ሊያደርጉት ነው? የትኛውን ስፖንሰር ፕላን አድርገው ነው አሊያስ ምን ያክል ስትራቴጂክ የሚቀይስ እውቀት ያለው ሰው ይዘው ነው? ጠንቅቀን እናውቃቸዋለን እኮ፤ ፈፅሞ ይሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ በተረፈ ሚድሮክ በድጋሚ ከመጣ እሰየው፡፡ ይህ ኩባንያ እኮ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከታች አንስቶ ለብዙ ዓመታት ሲደግፍና ሲያኖር የነበረ ታላቅ የክለቡ ባለውለተኛ ነው፡፡ እናም ደግሞ ተመልሶ ቢመጣ በእኔ በኩል ትልቅ ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡ የእኔ አለመኖር ከሆነ ችግሩ እኔ አልኑር፡፡ እውነታው ግን እነርሱ ከጀርባው ሌላ አጀንዳ ይዘው ነው የመጡት፡፡ እነዚህን ልጆች በሚገባ እናውቃቸዋለን እኮ፡፡ እኛ ጋር እንዲሰሩ ዕድል ሰጥተናቸው ምን ሰርተው እንደሄዱ ይታወቃል፡፡ ይሄን እውነታ ሚዲያ ላይ ማውጣት አያቅተንም ስለማንፈልግ ነው፡፡ ለምን ቢባል ቅ/ጊዮርጊስን ስለምናከብረው ነው እንጂ እያንዳንዱ የሰራትን ነገር ጠንቅቆ ይውቃል፡፡ ካስፈለገና አርፈው ካልተቀመጡ ሙሉ መረጃው አለን፡፡ ክለቡን እንደዛ ሲያንከራትቱ የነበሩ ግለሰቦች አሁን ክለቡን እንዲመሩ ደጋፊው ከፈቀደ የእነርሱ ውሳኔ ነው፡፡ በእኔ በኩል ግን ይሄን ታላቅ ክለብ ለማይመጥኑ ሰዎች አሳልፈን አንሰጥም፡፡
ሊግ፡- በንፅፅር ደረጃ ሲታይ ከእናንተ በላይ በርካታ ስም ያላቸው ተጨዋቾችን ያሰባሰቡ ክለቦች በውጤት ደረጃ ከእናንተ በታች ሆነው አሰልጣኝ ሳያሰናብቱ የእናንተ ውሳኔ ዘሪሁን ላይ ተግባራዊ መደረጉ ፍትሃዊ ውሳኔ ነው ብለህ ታስባለህ?
አቶ ዳዊት፡- እዚህ ጋ አንድ ነገር ግልፅ መሆን አለበት፡፡ እኛ አሰልጣኝ አላሰናበትንም፡፡ ማገድና ማሰናበት ይለያያል፡፡ ይህ ቴክኒካል ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የእኛ የቤት ስራ ነው ሲጀመር ሌላ ሰው መግባት አልነበረበትም፡፡ ቀደም ብዬ በገለፅኳቸው መሠረታዊ ጉዳዩች ጊዜያዊ እገዳ አድርገናል፡፡ ዘርዬ እኮ ይቀጥላል፡፡ በቀጣዩ እቅዳችን ምን መምሰል እንዳለበት ከዘሪሁን ጋር በየጊዜው እናወራለን እኮ፤ እንደው ሁኔታውን ለሚዲያ ዘመቻ ሊጠቀሙበት ካልሆነ በቀር አንድ ተጨዋች ቀይ ካርድ አይቶ አራት ጨዋታ ይቀጣ የለም እንዴ? እናም በዛው መሠረት ለቀጣዮቹ ሰባት ጨዋታዎች እንዲያርፍ አድርገናል፡፡ ከዚህ በተረፈ እኛ ዘሪሁንን አላባረርነውም፡፡ አብረን የሰራው ቡድን ነው፡፡ ወደፊትም እስከተግባባን ድረስ አብረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡ ከዚያ ውጪ መጋጋል ያለበት ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ በተረፈ ሌላው ክለብ ለምን ይሄን አላደረገም? የሚል ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡
ሊግ፡- በአሁኑ ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስን እያመሰ የሚገኘው በሁለት ጎራ የተከፈሉት ወገኖች ናቸው የሚባለው ነገር ምን ያክል ትክክል ነው?
አቶ ዳዊት፡- ትክክል ነው፡፡ ራሱን የቻለ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ የእኛ ተጨዋቾች ከጌም በኋላ ፌስ ቡክ፣ ቲክ ቶክና ሌላ ሌላ ነገሮችን የሚከታተሉ ስለሆነ የሚባለውን ነገር ስለሚሰሙ ተፅዕኖ ሊፈጥርባቸው ይችላል፡፡ እኔ ደስ የሚለው ነገር የዚህ አይነቱን ሚዲያዎች የምከታተልበት ጊዜም ሆነ ሀፒታይቱ የለኝም፡፡ ስለዚህ የሚባለውን ነገር አልሰማም፡፡ ዝም ብሎ አሉባልታ ከማውራት እውነት ከያዙ ለምን አይመጡም? ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልህ በመርህ ደረጃ ምንም የሚያጣላን ነገር የለም፡፡ ትልቁ ችግር ከበስተጀርባ አንግበው የሚንቀሳቀሱት አፍራሽ አጀንዳ ነው፡፡ እኛ ክለብ ሲሆን ነገሮች በዚህ ደረጃ ለምን እንደሚራገቡ አላውቅም፡፡ በርካታ ክለቦች የአራትና የሶስት ወር ተጨዋቾች ደሞዝ ያልከፈሉ አሉ፡፡ እስቲ በዚህ ደረጃ እኛ ክለብ ውስጥ ደሞዝ አልተከፈለኝም የሚል ተጨዋች ካለ ለምን ሚዲያ ላይ ወጥቶ አይናገርም? እኛ ክለባችንን በአነስተኛ በጀት በስርዓትና በአግባቡ እየመራን ነው፡፡ በተረፈ እነ ወሬ ቀለቡም ዘመቻቸውን ይቀጥሉ፡፡ አንድ ቀን እውነታውን ደጋፊው ጠንቅቆ ይረዳዋል፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ከልቡ የሚወደው ዳዊት ውብሸት ወደፊት ምን ያስባል?
አቶ ዳዊት፡- በጣም ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ቅ/ጊዮርጊስን እንዲደርስ የምፈልግበት ቦታ አሁንም ውስጤ አለ፡፡ በሰነድ የተደገፈውን ትልቅ የቤት ስራ ለማጠናቀቅ ፋይናንስ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ለማሳካት ደግሞ ትልቅ ጃሌንጅ ነው፡፡ አንደኛ ነገር የምትሰራውን የሚያደናቅፍ ሳይሆን አብሮ በአግባቡ የሚሰራ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛውና ዋናው ነጥብ ደግሞ ክለቡን በፋይናንሺያል ደረጃ ጠንካራ የሚያደርግ አጋር ያስፈልጋል፡፡ ይህ እንዲሳካ ደግሞ እዛ ብኖርም ባልኖርም ለቅ/ጊዮርጊስ የምችለውን ነገር አደርጋለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ልጆቼም እየደረሱ ነው፡፡ እነርሱም ወደፊት የታላቁ ክለብ ትልቅ ተስፋ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በአጠቃላይ ፈጣሪ ይጨመርበትና ይሄን ታሪካዊ ክለብ የበለጠ ወደ ከፍታ ለማድረስ ተባብረን እንስራ እላለሁ፡፡