Google search engine

“ወደ ቱኒዚያ የሄዱት 18ቱ ተጨዋቾች እኔ መርጫቸው ነው ስለሌሎቹ ተጓዦች ግን የክለቡን ኃላፊዎች መጠየቅ ይቻላል” “አገራችን ኢትዮጵያ ሰላም ሆና ደጋፊዎቹ በነጻነት የሚደግፉበት አመት እንዲሆን እመኛለሁ” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው /ባህርዳር ከተማ/

ባህርዳር ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ሆኖ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን ለመወከሉ የመልበሻ ቤቱ አለቃ  የሆኑት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ትልቁን ሚና ይወስዳሉ… ባህርዳር ከተማ  በመጀመሪያ የአፍሪካ ተሞክሮው ጥሩ ተፎካክሮ ልምድ ወስዶ እንደተመለሰም አሰልጣኙ ይናገራሉ… በፕሪሚየር ሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን መሸነፋቸውን ከድካምና ተነሳሽነት ከመቀነሱ ጋር ያያያዙት አሰልጣኝ ደግአረገ ከመቻል ጨዋታ ጀምሮ ጠንካራውን ባህርዳር ከተማ ለመመለስ እንደሚጥሩ አስረድተዋል። በቱኒዚያ በክለብ አፍሪካ ተሸንፈው ከኮንፌዴሬሽን ካፕ የምድብ ድልድል ውጪ የሆኑት ባህርዳር ከተማዎች በቀጣይ የፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብሮች በተሻለ አቋም ጥሩ ተፎካካሪ እንሚሆኑ አሰልጣኝ ደግአረገ ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ አስረድተዋል።

ሊግ:-  ከኢንተርናሽናል ጨዋታ መልስ ሽንፈት ገጥሟችኋል… እንዴት አገኛችሁት….?

ደግአረገ:- እንደ ውድድር ዘንድሮ ሊጉ ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት ክለቦች ጠንክረው እንደሚመጡ ይገባናል፡፡ በመጀመሪያውም ጨዋታ 3ለ2 ተሸንፈናል… ተጨዋቾቼ ከክለብ አፍሪካ ጨዋታ በኋላ ከቱኒዚያ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ እንግልት የበዛበት እረፍት ያላገኙበት ኤርፖርት ሄደንም ጉዞው ተሰርዞ የተንገላታንበት በመሆኑ ድካም ነበረው፡፡ እንደዚያ በድካም ውስጥ ሆነን ያደረግነው ጨዋታ ነው፡፡

ሊግ:– ለአወዳዳሪው አካል የቀን ለውጥ እንዲደረግ አልጠየቃችሁም..?

ደግአረገ:– ከቱኒዚያ መልስ የነበረን አንድ የልምምድ ቀን በመሆኑ ቀኑ እንዲራዘምልን ለአወዳዳሪው አካል በደብዳቤ ጠይቀን ነበር፡፡ ያው እንደማይቻል ጥያቄውን እንደማይቀበል ተነግሮን በግድ ተጫውተናል፡፡ በዚህ ድካምና ጫና ውስጥ ሆነን ያደረግነው ጨዋታን ስናይ ተጨዋቾቼ የተቻላቸውን ውጤት ለመያዝ ጥረዋል፡፡ የተገኘውን አጋጣሚ አልተጠቀምንም፡፡ በተጨማሪም ድክመታችን ታክሎበት ተሸንፈናል.. ከጠንካራ ውድድር ወደዚህ ውድድር ስንመጣ የነበረው ድካም ጎድቶናል፡፡ ግን  በምንፈልገው ልክ ተዘጋጅተናል ብለንም አናምንም፡፡

ሊግ:- እንዴት …?

ደግአረገ:- ወደ  ኮንፌዴሬሽን ካፕ ስንገባ  በጣት የሚቆጠር ዝግጅት አድርገን ነው፡፡  ውድድር ውስጥ ሆኖ መዘጋጀትና ተገቢ የሆነውን የቅድመ ውድድር ዝግጅት ማድረግ መሃል ልዩነቱ ሰፊ ነው… የተፈጠረው የጊዜ መጣበብ ተጽዕኖ ፈጥሯል.. አሁንም ውድድር ውስጥ ሆነን ክፍተታችንን እያረምን ጎን ለጎን ለአመቱ ውድድር ዝግጅት እያደረግን ጠንካራ ተፎካካሪ እንሆናለን ብዬ አስባለሁ።

ሊግ:- በክለብ አፍሪካ የደረሰባችሁን ጫና ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ በተመሳሳይ አናደርግም.. ልክ ነው ይሄ …?

ደግአረገ:- በአንድ በኩል ኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ነው፡፡ ያደግንበት ማህበረሰብ ከመስመር የወጡ ነገሮችን እንድናደርግ አይጋብዝም አይፈቅድም። በእኛ ሀገር እንግዳ ክቡር ነው፡፡ እናም እኛ ሀገር ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይከብዳል፡፡

ሊግ:– እስቲ  በቱኒዝ ምን ገጠማችሁ…?

ደግአረገ:-  እነሱኮ እዚህ ነው የጀመሩት.. በአበበ ቢቂላ ስታዲየም፡፡ የተጠባባቂ ተጨዋቾች መቀመጫና መልበሻ ቤት የነበረውን መስተዋት ሰብረው ነው የወጡት፡፡ ለማሰራት የተሞከረውኮ በእኛ ነው… እዚያ ከሄድን በኋላም የልምምድ ሜዳዎችን መከልከል፣ የጨዋታው ቀን ጫና መፍጠር ተጨዋቾቻችንን የሚያስጨንቁ ተቀጣጣይ ነገሮች ነበሩ፡፡ ከልክ ያለፈ የአደጋገፍ ስርአት ነበር፡፡ ውጤቱን ለመቀልበስ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ከዳኝነቱ ጋርም ተያይዞ ፈታኝ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ቀን ልምምድ ጨዋታ በምናደርግበት ስታዲየም ማድረግ ይገባን ነበር። በትግል ለአንድ ሰአት ፈቀዱና ከሆቴል ስንወጣ ፖሊሶች ሊያጅቡን አልፈቀዱም፡፡ ትራፊክ በተጨናነቀ መንገድ ስንሄድ አልደረስንም ብቻ የእኛን  አዕምሮ ለመጉዳት ሞክረዋል… ለኮሚሽነሩ ሜዳ መከልከላችን ነገርነው በቀጣዩ ቀንም እንቢ አሉን፡፡ ብዙ ፈተና ነበረው፡፡ እንደመጀመሪያ ተሳትፏችን ግን ትልቅ ልምድ አግኝተንበታል፡፡ ከላይ እስከ ታች በተቀናጀ ሁኔታ ነው ውጤቱን ለመቀልበስ የሰሩት.. ኮሚሽነሩ ከአልጄሪያ ነበሩ ዳኝነቱ የሚነገር አይደለም፡፡  ጎሎች ተቆጥሮብን ወደ መልበሻ ክፍል ስንገባ እንኳን ተጨዋቾቼን የመገፍተር የማበሳጨት ድርጊት ነበር፡፡ ያ ደግሞ ስሜታዊ አድርጎን እረፍቷን እንዳንጠቀም አድርገውናል፡፡ የወታደሮቹ እኛን ከብበው ነው እንድንሰጋ ያደረጉን፤ የሚገርም ጫና ነበር…. ከመስመር በወጣ ሂደት ሀሳባቸውን አሳክተዋል… ጨዋታው አልቆ አንድ ሰአት ሙሉ መልበሻ ክፍልና መኪና ውስጥ ነው እንድንቆይ የተደረገው፡፡ ውሃ ያለው ኮዳ ወርውረው መተውናል…

ፖሊሶቹም ለማስቆም አልሞከሩም፡፡ እዚህ ላይ ግን ደጋፊያቸው 90 ደቂቃ ሙሉ ሲደግፍ ስታይ ያስቀናሉ … የክለቡ አደረጃጀት አጠቃላይ ፋሲሊቲው የሚገርም ነው፡፡ በሌላ በኩል ከስፖርታዊ ተግባር ውጪ በጫና ለማሸነፍ የሄዱበት ርቀት ደግሞ ያበሳጫል፡፡ አዝኛለሁ በተቻለ መጠን በጨዋታው የተሻለ ሆነው ቢያሸንፉን እንማርበት ነበር.. ያ ግን አልነበረም… እኛ ጋርኮ ሲመጡ በነጻነት ተጫውተው ፎክረው ነው የሚሄዱት፡፡ ይሄ የህዝባችንን ጨዋነት ያሳያል።

ሊግ:- ካፍ ላይ የሚሟገትልን ሰው አለመኖሩ እንደጎዳን አያሳይም..?

ደግአረገ:- ይሄ ነው ማሳያው …ኮሚሽነሩ ጽፌያለሁ ብሏል፡፡ ለፊፋም አቤት ብለናል፡፡ የተወሰደ ምንም ርምጃ ግን የለም.. በጫና ነው ውጤቱን የለወጡት ..የተወሰነ መረጃ ቢኖረንም እንዲህ አይነት ጫና ግን አልጠበቅንም.. ካሰብነው በላይ የሆነ ፈተና ነው የገጠመን፡፡ እንደ አሰልጣኝ ወደ ምድብ ድልድሉ የምንገባበትን እድል ማጣታቾን ቅር ያሰኛል፡፡  በተቃራኒ ግን እኛም ይህን መሰል ጫና ተቋቁመን እንዴት ስኬታማ እንደምንሆን ያገኘነውን የግብ እድል እንዴት መጠቀም እንዳለብን ተምረንበታል፡ ተጨዋቾቼ በቁጭት ነው ሜዳውን ለቀው የወጡት በርትተን ከሰራን ስኬታማ እንደምንሆን እኛም ለሌሎች የሀገራችን ክለቦች ትምህርት የሰጠንበት መሆኑ ግን በጎ ጎኑ ነው።

ሊግ:-  ትልቁ ትምህርት ምን ሊሆን ይችላል ..?

ደግአረገ:- በሁለቱ የውድድር መድረክ የሚካፈሉ ክለቦቻችን ረጅም ርቀት ለመጓዝ ይህን መሰል ጫና መቋቋም እንዳለባቸው  እንዲዘጋጁ ያደርጋል ብለን እናምናለን፡፡ በተለይ ከአረብ ሀገራት ክለቦች ጋር ስንጫወት ይህን መሠል ጫና እንደሚጠብቀን ተረድተን መዘጋጀት እንዳለብን ትምህርት የወሰድንበት ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ከአዛምና ከክለብ አፍሪካ ጋር ያደረግነው ጨዋታ የተማርንበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ለውድድሮቹ  ምን ያህል መዘጋጀት እንዳለብን ደረጃችንን እንድንመረምር ያደረገ መሆኑን በጥሩ ጎንና በእድለኝነት ነው የማየው…

ያም ሆኖ ለምን ይሄ ሆነ ብሎ እንደ ሀገር የሚሞግት ተሰሚነት ያለው ሰውም በካፍና በፊፋ ሊኖረን እንደሚገባ ያየንበት አጋጣሚ ነው። እዚህ ላይ ውድድሩን ስለሚመሩት የኛ ሀገር ዳኞች መናገር እፈልጋለሁ።  በሻምፒየንስ ሊግም ይሁን በኮንፌዴሬሽን ካፑ የሚዳኙ ኢትዮጵያዊያን አርቢትሮችን አደንቃለሁ፡፡ ምን አይነት ጫና ውስጥ ሆነው ውድድሮቹን በብቃት መርተው ፈተናዎችን እንዴት አልፈው እንደሚመሩ ያየሁበት በመሆኑ ያለኝን ክብር እገልጻለሁ፡፡  የሀገራችን ዳኞች በትልቅ ጫና ውስጥ ሆነው ውድድሩን በስኬት መርተው በመመለሳቸው ያለኝ አድናቆት ጨምሯል፡፡ ከበፊቱም ለዳኞቻችን ክብር አለኝ አሁንም አክብሮቴ እንዲጨምር አድርገውታል።

ሊግ:- ወደ ቱኒዚያ ስትጓዙ እዚህ የቀሩ ተጨዋቾች ነበሩና የሄዱትም የቀሩትም በእርስዎ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል..?

ደግአረገ:-  ሀገራችን ላይ ባደረግናቸው ሁለት ጨዋታዎች ተመልካች ስላልገባ ገቢ አልነበረንም፡፡ ያንን ተንተርሶ ቦርዱ ከፋይናንስ እጥረት አኳያ ወደ ቱኒዚያ ስትሄዱ የተጨዋቾቹ ቁጥር 18 ቢሆን ብሎ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ችግሩን ስለተረዳን የምናየውም በመሆኑ ተስማምተን 18 ተጨዋቾችን ወስደናል።  የሆነው ይሄ ነው…

ሊግ:-  ካሏችሁ 26 ተጨዋቾች 8 ቀንሳችሁ 18ቱን ብትወስዱም የሄደው የልኡካን ቡድን ብዙ ከሆነ ምን ለውጥ አለው … ይሄ  አይጋጭም ..?

ደግአረገ:– ክለቡ ቦርድና ስራ አስኪያጅ አለው ጉዞው ምን እንደሚመስል፣ እነማን እንደሄዱ፣ ለምን እንደሄዱ መጠየቅ ይቻላል፡፡ የክለቡን ስም እያጠለሹ ያሉት አሉባልታዎች ዝም ብለው ነው …

ሊግ:-  በቀረበው ጥያቄ 18 ተጨዋቾችን ብቻ ይዛችሁ ስትሄዱ በመቅረቱ የጎዳችሁ ተጨዋች የለም..?

ደግአረገ:- ይህን ስናደርግ በየቦታው አንድ አንድ ተጠባባቂ አድርገን ወስደናል… ከቦርድ በመጣልን ጥያቄ መሠረት 18 ተጨዋቾችን ብቻ ነው ይዘን የምንሄደው ብለን ለተጨዋቾቻችን ነግረናል… ለግብ ጠባቂ አንድ፣  ለመስመር አጥቂዎች አንድ፣ ለፊት አጥቂው አንድ፣ ለአማካዮች አንድ፣ ለተከላካይ አንድ ይዘን ነው የሄድነው። ሙሉ ሃላፊነቱ የኔ ነው  በመቅረቱ ግን ጎዳን የምንለውም ተጨዋች የለም፡፡

ሊግ:-  አብዲ አባስ በመቅረቱ አልተጎዳችሁም …? ብዙዎች ለምን ቀረ እያሉ እያነሱት ነው ..?

ደግአረገ:- ቆይ ቆይ ተደጋጋሚ ነው የተነሳው ይሄ ጥያቄ… የቀረው ግን አንድ አብዲ ብቻ ነው..?  የቀሩ ሌሎች ተጨዋቾች የሉም..?  ጤናማ የሆነ ጥያቄ አልመሰለኝም.. ለሌሎቹ የሚጮህ የለም..?  የሚገርመው ለዚህ ያበቃሁት  እኔኮ ነኝ ከኤልፓ ወደንግድ ባንክ የወሰድኩት… ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ባህርዳር ከተማ  እንዲሄድ ፈቀድኩ፡፡ ከጊዜ  በኋላ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ወደ ባህር ዳር ከተማ ስገባ እዚያም አገኘሁት። ስንመለስ አግኝቼ አውርቼዋለሁ የሚልኩትና የሚሳደቡትን ስክሪን ሹት አድርጌ ይዣለሁ ነው ያለኝ…. ኮች ለማንም ምንም አላልኩም ነው ያለኝ …ያው የሰዎቹን አስተሳሰብ ማቆም አይቻልም፡፡ ያሉትን ተጨዋቾች ብጠቀምና ክለባችን ውጤታማ ቢሆንኮ የምጠቀመውና እውቅናን የማገኘው እኔ ነኝ፡፡

ሊግ:-  ፊታችሁን ወደ ሊጉ አዙራችኋል… የኮንፌዴሬሽን ካፑ ውድድር ጠቀሜታው የጎላ ነው ማለት ይቻላል..?

ደግአረገ:– በፈልገነው መንገድ ዝግጅት ባናደርግም በአፍሪካ ውድድር ውስጥ ሆነን ለፕሪሚየር ሊጉ መዘጋጀታችን አልቀረም.. ተጨዋቾቼ ጫናን እንዴት መቋቋም እንዳለባቸውና የማች ፊትነሳቸውን እንዲያገኙ ማድረጉ ደግሞ ጠቅሞናል… በቂ የዝግጅት ጊዜ ባናገኝም አሁን ላለንበት ውድድር ራሱን የቻለ ጥቅም ይኖረዋል።  ፕሪሚየር ሊጉ ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በውድድር ውስጥ ሆነን ጠንካራና ደካማ አቋማችንን የምናይበትና የበለጠ የምንዘጋጅበት ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ

ሊግ:-  በኢትዮጵያ መድን የደረሰባችሁ ሽንፈት ምክንያት ድካም… ..ወይስ…?

ደግአረገ:- በዋናነት የተነሳሽነት ልዩነት አይቻለሁ… ኢትዮጵያ መድኖች የማሸነፍ ተነሳሽነታቸው የተለየ ሆኖብኛል፡፡ በፍጹም ቁርጠኝነት ነው ሲጫወቱ የነበረው፡፡ እኛ ጋር ደግሞ ተነሳሽነቱ ተቀዛቅዞ ነበር ያየሁት፡፡ ትልቁ ልዩነት ይሄ ነው፡፡ ምናልባት ከትልቅ ውድድር ከመምጣታችን የተነሳ ጨዋታውን ከግምት ሳይከቱት ንቀው ገብተው ይሆን የሚል ጥያቄ ፈጥሮብኛል የግድ በውይይት ማስተካከል ይኖርብናል።  ውድድሩ ጠንካራ መሆኑን ማንም እኛን ሊገጥም ሲመጣ በተነሳሽነት ጠንክሮ እንደሚመጣ ከነበርንበት ውድድር አንጻር አክብደው እንደሚመጡ ከጨዋታው በፊት ተነጋግረን ነበር የገባነው፡፡ ሜዳ ላይ ያየነውም ይሄ ነው እነሱ ጠንክረው ተነሳሽነታቸውን ጨምረው ሲመጡ እኛ በተቃራኒ የምንታወቅበት ጨዋታን አሸንፎ የመውጣት ቁርጠኝነትና ተጋድሎ ተቀዛቅዞ በመግባታችን 3ለ2 ለመሸነፍ ተገደናል… በጨዋታ እንቅስቃሴ ግን ጥሩ ተንቀሳቅሰን የግብ እድል ፈጥረን ያልተጠቀምንበት ምናልባት እድሉን ብንጠቀም ውጤቱ የሚለወጥበት ነበር፡፡ ግብ የተቆጠረውን ስናይ እኛ አባክነነው ኳሱ እኛ ላይ መጥቶ ተቆጥሯል፡፡ ይሄ እግር ኳስ በመሆኑ እንማርበታለን፡፡ በቀጣይ ወደነበርንበት ደረጃ ለመመለስ ከተጨዋቾቼ ጋር ጠንክረን እንሰራለን፡፡ ትልቅ ትምህርት የወሰድንበት የማንቂያ ደወል ሆኖልናል…

ሊግ:- በክለብም ይሁን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የተገኘውን እድል ወደ ግብነት ያለመቀየሩ ክፍተት በምን ሊታረም ይችላል…?

ደግአረገ:- በቃ ብቸኛ መፍትሄ መስራት ደጋግሞ መስራት ነው .. በእርግጥ የኛ ቡድን ወደ ግብ የመድረስ ችግር የለበትም ግብ በማስቆጠርም ጥሩ ነን፡፡ በ2015 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ ሁለተኛ ግብ አስቆጣሪ እኛ ነን፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች  54 እኛ ደግሞ 51 ግብ ነው ያስቆጠርነው ይሄ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለን ያሳያል ግን ያገኘነውና የፈጠርነውን  የግብ እድል ሙሉ በሙሉ የመጠቀም ክፍተታችን ተቀርፏል ማለት አይቻልም፡፡ ብዙ ስራ ይጠብቀናል እንዳልከው  በክለብና በብሄራዊ ቡድን ብዙ እድል ተፈጥሮ የሚባክነው ይበዛል፡፡ በቀጣይ እንደ ተጨዋቹ የግልና የቡድን ጥረት ጠንክሮ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ለወደፊቱ በርትተን ትኩረት ሰጥተን እንሰራበታለን።

ሊግ:-  በ2016 የጥሎ ማለፍ ውድድር ተካሂዶ የኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳታፊ እንደሚታወቅ ፌዴሬሽኑ አሳውቋል… በሊጉ ያለው ፉክክር ለዋንጫ እና ላለመውረድ የሚደረገው ብቻ መሆኑ ፉክክሩን ቀዝቀዝ አያደርገውም ..?

ደግአረገ:–  እዚህ ላይ የተለየ አቋም ነው… እውነት ነው በሊጉ ላይ የራሱ ተጽዕኖ ይኖረዋል… በተቃራኒው የጥሎ ማለፍ ውድድር መጀመሩ ጠቀሜታው ትልቅ ነው። በተለይ ለተጨዋቾች ብዙ የመጫወት ዕድልን የሚፈጥር በደንብ ታሽተው ተፈትነው አቋማቸው ጠንክሮ በአካልም በአቋምም የጠነከሩ ተጨዋቾችን ለብሄራዊ ቡድኑ ግልጋሎት የመጥራት እድል ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ… ከፎርማቱ ጋር ተያይዞ ከአለምአቀፉ ፕሮግራም ጋር ቢስተካከል ደስ ይለኛል፡፡ በኮንፌዴሬሽን ካፕ እኛን የጎዳን የሊጉ ፎርማት ነው፡፡ ሌሎች ክለቦች አርፈው ተዘጋጅተው ሲመጡ እኛ ግን ውድድሩ ዘግይቶ ከመጠናቀቁ የተነሳ ያለእረፍትና ያለ ጥሩ ዝግጅት እንድንገባ አድርጎናል፡፡ ያ ትልቅ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ አሁንም ጥሎ ማለፉ ከተጀመረ ከሊጉ ጋር ሳይጣረስ በአለም አቀፍ ካላንደር ቢመራ የተሻለ ይሆናል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ የወዳጅነት ጨዋታ ቢፈልግ የሊጉ የጥሎ ማለፉ ካላንደር ሳይንዛዛ ቢካሄድ የተሻለ ይሆናል። በኔ አመለካከት የጥሎ ማለፍ ፉክክሩ መጀመሩ ጥሩ ነው፡፡ የውድድሩ መርሃግብር ግን ሊታሰብበት ይገባል ብዬ አስባለሁ…  የእስካሁኑ አካሄድ ከቀጠለ ግን ስጋት ይፈጥራል ያም ሆኖ ውድድሩ ግን ለክለቦች ጥቅሙ ሰፊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሊግ:- እሁድ ከመቻል ጋር ሁለተኛ ጨዋታችሁን ታደርጋላችሁ… እነሱ አሸንፈው እናንተ ተሸንፋችሁ የምትገናኙ እንደመሆኑ ምን ውጤት ይጠበቃል …? ውጤት መገመት ይቻላል..?

ደግአረገ:- መቻል ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች አካቶ ነው ለውድድሩ የቀረበው….. ጠንካራ ፉክክር ይጠበቃል፡፡ እኛም ድጋሚ ላለመሸነፍ ጨዋታው ላይ ትኩረት ሰጥተን ነው የምንገባው፡፡ ተጨዋቾቼ በቁጭት የሚገቡበት ግጥሚያ ይሆናል፡፡ በግጥሚያው ጥሩ ፉክክር እጠብቃለሁ.. በውጤት ደረጃ በ90 ደቂቃው የሚታይ ይሆናል… ቡድኔ ግን ወደ ቀድሞ ጥንካሬው የሚመለስበት ጨዋታ ይሆናል ብዬ አስባለሁ….

ሊግ:- ጨረስኩ… የመጨረሻ ቃል ….?

ደግአረገ:– በቅድሚያ ሊግን አመሰግናለሁ.. እናንተን ጨምሮ የአገራችን ሚዲያዎች የስፖርቱን እድገት ከፍ ለማድረግ የስፖርት ጋዜጠኞች የሞትሰሩትን ስራ ሳላደንቅ አላልፍም… ስራችን ወደ ህዝብ ተደራሽ እንዲሆንና እግር ኳሱ እንዲያድግ ሳትታተክቱ ተገቢ ነው የምትሉትን አስተያየት ስለምትሰጡ ለናንተ አክብሮት አለኝ … አገራችን ኢትዮጵያም  ሰላም ሆና ደጋፊዎቹ በነጻነት ወደየትኛውም ስፍራ ተንቀሳቅሰው የሚደግፉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ማየት እመኛለሁ፡፡ በኢንተርናሽናል ውድድሩ ደጋፊው ከምንም በላይ  ምን እንደሚመስል አይቻለሁና ስታዲየሞቻችን  በደጋፊ ተሞልተው ውድድሮች አምረውና ደምቀው የሚታዩበት አመት እንዲሆን እመኛለሁ… ለሁሉም ነገር ግን ፈጣሪን አመሰግናለሁ።

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P