ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለው ትስስር የሚፈታ አይመስልም ….ደጋፊዎቹ በአካል ቢለየንም ልቡ ጊዮርጊሳዊ ነው ከሚሏቸው ጥቂት ባለሙያዎች መሃል አንዱ ነው። መቻል ባህርዳር ከተማና አዳማ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት የመምራት ዕድሉን አግኝቶ የዋና አዘጋጅ ሞገስ ካገኘ ጊዜያቶች ተቆጥረዋል ….ተጫውቶ ማሊያውን ለብሶ ክፉ ደጉን ያሳለፈበትን የሚወደውን ክለብ የማሰልጠን ዕድል አግኝቷል..አሁንም ያስተሳሰራቸው ገመድ ተሳሳበና ዳግም የሚወደውን ክለብ ሃላፊነት በመረከብ የፈረሰኞቹ የመልበሻ ክፍል አለቃ ሆኖ ዳግም ተመልሷል … እንግዳችን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ….ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ለቀረቡለት ጥያቄዎች የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።
ሊግ:- ዕረፍቱ እንዴት አለፈ..?
ፋሲል:– ዕረፍቱን ባልፈልገውም ጥሩ ጊዜ ነበረኝ ለቤተሰቦቼ ጥሩ ጊዜ አግኝቻለሁ ራሴን ለመመልከትና ለማሻሻል ደግሞ አንዳንድ ጠቃሚ ነገሮችን ለማድረግ ሞክሬያለሁና ተጠቅሜበታለሁ ማለት እፈልጋለሁ ረጅም ጊዜ ስራ ላይ ስለነበርኩም ማረፉን በጥሩ ጎን ወስጄዋለሁ።
ሊግ:- በዕረፍቱ ምን ተማርክበት ..?
ፋሲል:– ብዙ ነገር ተምሬበታለሁ… አምንባቸው የነበሩ ለኢትዮጵያ እግርኳስም ይጠቅማል ብዬ ያመንኩባቸውና ያሰብኩባቸው ነገሮች ወደኔ ተመልሰው ሊጎዱኝ ሲሆኑ አይቻለሁ እነኚህን ነገሮች በጥሞና ቁጭ ብዬ በማሰቤ ተረድቼበታለሁ የጥሞና ጊዜ እንዲኖረኝ በቂ ጊዜ ነበረኝ ብዬ አስባለሁ።
ሊግ:- የፓሪስ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ተሳትፎ እንዴት አገኘኧው..?
ፋሲል:- ከኦሎምፒክ ብዙ የምንጠብቀው ነገርማ ነበር ..ዘንድሮ ግን አልሆነም በተለይ ገና ከዚህ ሲሄዱ ጀምሮ ከውድድሩ መነሻ እስከ ፍጻሜው ድረስ በውዝግብ የተሞላ ነበረና የምንፈልገው ውጤት ላይመጣ እንደሚችል ገምቼ ነበር… ዞሮ ዞሮ ኦሎምፒክ የምንደሰትበት ክብር የምናገኝበት የምንጨፍርበት ውድድር ስለሆነ በምንፈልገው ደረጃ ባለማየታችን እንደ ሀገሩን እንደሚወድ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ቅር ብሎኛል፡፡
ሊግ:– ኮከቡ አትሌት ገዛኧኝ አበራም ገና ከመሄዳቸው ውጤት የሚገኝ አይመስለኝም ብሎ ገምቷል …. ተመሳሳይ ግምት ሆነብኝሳ..?
ፋሲል:– /ሳቅ/ ገጠመኙ ይገርማል እሱ ግን የበለጠ ስለ ኦሎምፒከ የበለጠ የሚያውቅ ሮጦ ድል አግኝቶ ያስደሰተን አሁን ደግሞ አመራር ሆኖ ያለ ባለሙያ ነው .ጀግናችንም ነው ለስፖርቱ እንደ መቅረቡ የታዘበው ነገር ይኖራል… እንደ አጠቃላይ ግን ስፖርት ውስጥ እንዳለ ሰው በውዝግብ የተጀመረ ነገር የቡድን መንፈስ ከማጥፋቱ ጋር ተያይዞ የምንፈልገውን ውጤት ላናገኝ እንችላለን ብዬ እንድገምት አድርጎኛል፡፡
ሊግ:– ወደ ፈረሰኞቹ እንመለስ…ወደቤቱ ተመለሰ የሚለው የሰበር ዜናው ባለቤት በመሆኔ ክብር ይሰማኛል..
ፋሲል:-/ ሳቅ /ያኔማ ገርሞኛል../ሳቅ/
ሊግ:– የመመለስህ እንቅስቃሴ እንዴትና መቼ ተጀመረ..?
ፋሲል:- ገና ሊጉ ሳያልቅ ወደ መጨረሻ ጨዋታዎች አካባቢ እንደዚያ አይነት ፍላጎቶች እንዳሉ በተለያየ መንገድ ጭምጭምታዎችን እሰማ ነበር …. የመጨረሻ ሳምንት ደርሶ ንግግር ውስጥ እስክንገባ ድረስ መረጃዎች ጭምጭምታዎች ነበሩ… የሚቀርቡኝ የነበሩ ሰዎችም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብመለስ ደስተኛ እንደሆኑ ይነግሩኝ ነበር፡፡ በመጨረሻም ተሳክቶ ወደቤቴ ልመለስ ችያቸሁ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሊግ:- የመመለስህን ፍጥነት ጠብቀኧው ነበር …?
ፋሲል:- ከዚህ በፊትም ከአንተ ጋር ቃለምልልስ ስናደርግ አንድ ቀን ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እመለሳለሁ የሚል እምነት እንደነበረኝ ተናግሬያለሁ የማላውቀው መቼ እንደነበር ብቻ ነው..ያው ጊዜው ደርሶ ተመልሻለሁ፡፡ ከጊዮርጊስ በፊት ከሌሎች ክለቦች ጋር የተጀመሩ ንግግሮች የማድረግ እንቅስቃሴዎች ነበሩ በኋላ ላይ በማላውቀው መንገድ ዕድሉ ተዘጋ አልተሳካም ለካ ለዚህ እድል ነበር የዘገየው …ለዚህ ሊያበቃኝ ነው እግዚአብሄር ያስጠበቀኝ አልኩና አመሰገንኩ፡፡
ሊግ:– ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዴት አገኘኧው …?
ፋሲል:- ከቅርብ ጊዜ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች እንደተፈጠሩ ሁሉም ሰው ያውቃል እኔም ውጪ ሆኜ እሰማለሁ አሁን በደንብ ወደ ስራ ውስጥ ስገባ ሁሉንም ነገር እረዳለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ሰዓት ጊዮርጊስን መረከቤ ፈተናውን የበለጠ ሊያበዛ ቢችልም ለፈተናው ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ወደ ምትወደው ቤት ስትመጣ እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመቋቋምና ለመወጣት የምትችለውን ታደርጋለህና ያለውን ችግር ተጋፍጦ ጊዮርጊስን ውጤታማ ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ፡፡
ሊግ:- ረዳቶች የራስህን አመጣህ …ወይስ ያሉትን ይዘህ ትቀጥላለህ..?
ፋሲል:- አሁን ባሉት ነው የምቀጥለው …ጊዮርጊስን ያውቃሉ…የጊዮርጊስ ናቸው ….በጊዮርጊስ ማሊያ አድገዋል….አዲስ ሰው የለም ….ከኔ ጋርም ያደጉ እንደመሆናቸው ከእነሱ ጋር ኘው የምቀጥለው…
ሊግ:– አሰልጣኝነት ውጤታማ የሚሆነው እንጀራ ሲሆን ወይም የምትኖርለት በፓሽን የተሞላ ሲሆን ነው ..?
ፋሲል:- አሰልጣኝነት ምንም ጥርጥር የለውም ሙያ ነው በየትኛውም ሙያ ውስጥ ሁን ግን ያለፓሽን ውጤታማ መሆን አትችልም እግርኳስ የኖርኩበት ነው፡፡ በጣምም እወደዋለሁ የእኛ ሀገር እግርኳስ ከፍ ብሎ ቢገኝ አንተን ጨምሮ የሁላችንም ደስታ ነው ፓሽኑ ሲኖር የበለጠ እግርኳስን ትወዳለህ በዚያ የምትወደውን እየሰራህ ገንዘብ ተከፍሎህ ሲሆን ደስታውን ርካታውን ይጨምራል፡፡
ሊግ:– አንተ ከአመራሮቹ ጋር ስትስማማ ጊዮርጊስ ላይ የተጣለው እገዳ ሲነሳ እኩል ሆነ … ዕድለኛነትህን አያሳይም ..?
ፋሲል:- /ሳቅ በሳቅ/ አይ አስቀድሞ ፕሮሰስ ላይ የነበረ ጉዳይ ነው ..ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢንሹራንስን በተመለከተ አዲስ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን እንዳገኘሁት መረጃ ጊዮርጊስ በአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን የለመደው የኢንሹራንስ አይነት አለ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ በተለየ መንገድ በማቅረቡ እነዚያ ነገሮች ፕሮሰስ ሲደረጉ ነው የዘገየው.. በፈረምኩበት ቀን ከሁሉ ነገር ነጻ ሆኖ ወደ ዝውውር በመግባቱ እድለኛ ነኝ ማለት ነው /ሳቅ/፡፡
ሊግ:- የአሰልጣኝ በጸሎት ልኡልሰገድ ቡድን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንዴት አገኘኧው..?
ፋሲል:- ምንም ጥያቄ የለውም አመቱን ሙሉ ጠንካራ የነበረ ቡድን ነው አሰልጣኝ በጸሎት ከታች ይዞት የመጣውን ቡድን አሳድጎ ደረጃውን ከፍ አድርጎ የዋንጫ አሸናፊ አድርጎታል ይሄም የልፋቱ ውጤት ነው ይገባዋል። አመቱን ሙሉ በነበረው ጥንካሬ ዋንጫውን ማሸነፉ ይገባዋል በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ በጸሎትን እንኳን ደስ አለህ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ:- ከወጣት አሰልጣኞች ጋር መግባባቱ ይቀላል የሚሉ አሉ እውነት ነው…?
ፋሲል:- ተመሳሳይ የእድሜ ክልል ላይ ስትገኝ የበለጠ መግባባት ይፈጠራልና ወጣቶች ወደ አሰልጣኝነቱ መምጣታቸው ወደፊት የአገሪቱ እግርኳስ ተቀባይ መሆናቸውን ያሳያልና በጥሩ ጎኑ አየዋለሁ እንደ ወጣት አሰልጣኝ ለቡድኔ ምንም አይነት ሰው ነኝ ብዬ አስባለሁ በግሌ እውቀት ከተላይም ከታችም ይገኛል ብዬ አስባለሁና ወጣቶች ሲመጡ ደስ ይላል።
ሊግ:- የዋንጫ ፉክክሩ እክከ መጨረሻ ሳምንት ሄዷል አንተ እንዴት አገኘኧው ..?
ፋሲል:- ምንም ጥያቄ የለውም በጣም ጥሩ ፉክክር ኖሮ የመጨረሻው ሳምንት ድረስ ሲጓዝ ለሊጉ ውበት ይሰጠዋል በዘንድሮም ይሄ ነው የታየው… ፉክክሩ የመጨረሻ ሳምንት ድረስ ቀጠለ ማለት አንደኛ ለሊጉ ጥንካሬ ይሆናል ሁለተኛ ደግሞ ለደጋፊና ለተመልካች ሶስተኛ ለገለልተኛ ተመልካችም ደስታ ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ በየአመቱ ተመሳሳይ ፉክክር ቢኖር የተሻለ እድገት ያመጣል። 2003 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ዋንጫ ሲያሸንፍ ፉክክሩ አስከ መጨረሻ ሳምንት ዘልቆ ነበር በእያንዳንዱ ጨዋታ ስታዲየሞች በተመልካች ሙሉ ነበሩ፡፡ ፉክክሮቹ መኖራቸው ለሊጉ ወሳኝ ነው፡፡ ዘንድሮምኮ አስከ ተወሰነ ሳምንት ድረስ ቅዱስ ጊዮርጊስም ባህርዳር ከተማም ፉክክሩ ውስጥ ነበሩ ወደ መጨረሻም ሳምንታቶች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መቻል ተገንጥለው ፉክክሩን የግላቸው አድርገውታል መቻልም ጠንካራ ጉዞ በማድረጉ ፉክክሩን እስከ መጨረሻ እንድናይ አድርገውታል።
ሊግ:– በዘንድሮ የውድድር አመት የተመቸህ ቡድን ማነው ..?
ፋሲል:- በአንደኛ ዙርና በሁለተኛ ዙር የነበረው የኢትዮጵያ መድን በፍጹም የተለያዩ ናቸው በሁለተኛው ዙር የነበረው ኢትዮጵያ መድን ተመችቶኛል ሌላው ደግሞ አዳማ ከተማ በወጣቶች ከመገንባቱ አንጻር ጥሩ ቡድን ሆኖ አግኝቼዋለሁ
ሊግ:– ሊጉ “ሃያል ክለብ” አለው ማለት ይቻላል ..?
ፋሲል:- ሃያል ክለብ ለማለት ምን ሊያሟላ ይገባል ሃያልነት እንዴት ይገለጻል የሚለው ምላሽ ያስፈልገዋል… በሊጉ የወቅቱ የዋንጫ አሸናፊ አለው ነው ማለት የሚቻለው …የሊጉ ሃያል እገሌ የተባለው ክለብ ነው ለማለት ተደጋጋሚ ጊዜ ማሸነፍን ይጠይቃል ሁለት ወይም ሶስት አመታት በተከታታይ ማሸነፍ አለብህ አንድ አመት ግን ልታሸንፍ ትችላለህ ሃያል ለመሰኘት ግን መድገም አለብህ ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት አመታት በተከታታይ ዋንጫ አሸንፎ ሃያልነቱን አሳይቷል ከዚያ የተወሰኑ አመታት ከዋንጫ ራቀና ባለፉት ሁለት አመታት ዋንጫ ወሰደ ..ደጋግመህ ስታሸንፍና ጠንካራ ቡድን መሆንህን ስታሳይ ነው የሊጉ ሃያል የምትባለው … እንደኔ አሁን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ክለብ ነው ከአሸናፊነት በዘለለ ሃያል ለመባል ሊጉን ደጋግሞ ማሸነፍ አለበት አንድ ቡድን ሃያል ለመባል ጠንካራነቱን ደጋግሞ በማሸነፍ ማስመስከር ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ
ሊግ:– የፋይናንስ ገደቡ ላይ የምትለው ነገር አለ..?
ፋሲል:- እኔ ተቀጣሪ ነኝ ሊጉ ይህን ማድረግ አለበት ክለቦቹ ይህን መክፈል አለባቸው ብዬ ክርክር ውስጥ አልገጥምም አንድ ክለብ ስሄድ ይሄን ያህል ክፈሉኝ እላለሁ። ክፍያው ደግሞ በክለቡ በቀጣሪዎቹ የሚወሰን ነው የሚሆነው … ክለቦቹ ተሰብስበው በዚህ የፋይናንስ ህግ የምንመራው ብለው ከወሰኑና ከፈረሙ ያን ማክበር አለባቸው ብዬ አምናለሁ ካነሰም አነሰ ከበዛም በዛ ማለት የሚችሉት ስብሰባው ላይ ነው ተሰብስቀው ተስማምተው ከፈረሙ ግን ያንን ማክበር አለባቸው። ተስማምተው ወጥተው በተቃራኒው ካደረጉ ለእግርኳሱ አይበጅም ብዬ አስባለሀ።
ሊግ:- የደጋፊውን አቀባበል እንዴት አገኘኧው ..?
ፋሲል:- ከምጠብቀው በላይ ያገኘኋቸው…. በተጨዋችነትም ሆነ በአሰልጣኝነት ለክለቡ በታማኝነት የምችለውን ሁሉ አድሬጌያለሁ ስወጣም ምክንያቴም ራሴን በዋና አሰልጣኝነት ለመሞከርና አቅሜን ለማየት በሚል ነው የወጣሁት በክብር ነው የወጣሁት ..
በመጀመሪያ የክለብ ዋና አሰልጣኝ ሆኜ ስመጣ ደጋፊው አክብሮ ነው የተቀበለኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ እኔና ደጋፊውን በፍቅር አስተሳስሮናልና ስመለስም ደጋፊው በፍቅር ተቀብሎኛል በዚህም ተደስቻለሁ የምችለውን ለማድረግና ደጋፊው የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣት እጥራለሁ
ሊግ:- በቀጣይ ከፈረሰኞቹ ጋር ምን አቀድክ..?
ፋሲል:- ከሌላው ጊዜ በተለየ የአሁኑ ቡድን በወጣት የተሞላ ነው እነኚህ ላይ ነባርና ልምድ የተሙሉ ተጨዋቾችን ለመጨመር እንጥራለን ውጤት መቀየር የሚችሉ የውጪ ተጨዋቾችንም ለማካተት እንሞክራለን። ወጣቶቹን በስነልቡናም ይሁን በአካላዊ ብቃት እንዲያድጉ የመርዳት ለቅዱስ ጊዮርጊስ የወደፊቱ ተስፋዎች መሆናቸውን ማሳየት ነው።
ሊግ:- ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ሁለተኝነት ቦታ የለውም …ለዋንጫ ደግሞ የሚፎካከሩ ክለቦች በዝተዋልና የሊጉም ቁጥር 19 ይሆናል ..ሃላፊነቱን አሁን ተረክበህ ዋንጫ ለማግኘት አሰብክ ..? ወይስ ..?
ፋሲል:- አሁን የተለየ ቡድን ነው ያለን …ጊዜ የሚያስፈልገውም ይሆናል … ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ተዘጋጅተናል ጊዮርጊስ ጋር የበዛው ወጣት ነው በወጣቶች የተገነባ በመሆኑ የተወሰኑ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች እንጨምራለን የነዚህን ወጣቶች ችሎታ ከፍ አድርጎ የወደፊቱን ጊዮርጊስ ለመገንባት ጠንካራ ተፎካካሪ ለማድረግ ያለኝን ሁሉ ነገሬን ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ
ሊግ:- ጨረስኩ .. የመጨረሻ ቃል..?
ፋሲል:– ስራ ላይ ባልነበርኩበት አመት ውስጥ ዕረፍት ላይ መሆኔ ያስጨነቃቸው ቶሎ ወደ ስራ እንድመለስ የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ ..በአካልም ሲያገኙኝ በስልክም ያወሩኝ ነበር…..ሁሉንም በጣም አመሰግናለሁ። በከፍታም በዝቅታም አብረውኝ ያሉ ቤተሰቦቼን በጣም በጣም አመሰግናለሁ ቅዱሰ ጊዮርጊስ አምኖኝ ለቡድኑ የሆነ ነገር ያመጣል ብሎ ጠርቶ ሃላፊነቱን የሰጠኝን የክለቡን የስራ አመራር ቦርድ ከልብ አመሰግናለሁ.. እንደ ሁልጊዜውሞ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ክብር ለሚሰጡኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በሙሉ ያለኝን ፍቅርና ክብር መግለጽ እፈልጋለሁ አመሰግናለሁ።