Google search engine

“በህይወቴ እንደ ታሪክ የማውራው የመጀመሪያዬን የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት እንጂ ሁለተኛነትን አልፈልግም” “ለማሸነፍ የሚያስፈልገው መጸለይ ብቻ ከሆነ ሜዳ መግባት አያስፈልግም” ፈቱዲን ጀማል /ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ/

እስቲ ወደ አዶላ ድጋሚ እንውሰዳችሁ …በዚያች የወርቅ ምድር  የቡናማዎቹ አጥቂው አንተነህ ተፈራ ብቅ ያለባት መንደር…ሌላ ኮከብ አፍርታለች ፈቱዲን ጀማልን….

በሊግ ደረጃ የመጀመሪያውን ማሊያ የለበሰው በበርካታ ደጋፊዎቹ ለሚደገፈው ለወላይታ ድቻ ነበር… ቀጠለና   በበርካታ ደጋፊዎቻቸው የተከበቡትን የሲዳማ ቡና፣  የኢትዮጵያ ቡናና የባህርዳር ከተማ ክለቦችን ማሊያ ለብሶ  ተጫውቷል በመሃል ተከላካይነት ጠንካራ ከሚባሉት ተጨዋቾች መሃል አንዱ ነው ..ትልቁ ውጤቴ የሆነውን ሁለተኝነትን ለመርሳት ዘንድሮ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ወይም ሞት ብሏል፡፡ እንግዳችን ፈቱዲን ጀማል…. ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ጠንካራ ግስጋሴ እያደረኩ ነው ለዋንጫው ተስፋ አለኝ ይላል… ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቆይታ ያደረገው ፈቱዲን ለቀረቡለት  ጥያቄዎች የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል….

ሊግ:- ጾሙ እንዴት አለፈ ….ቃለምልልሱን በዚህ እንጀምር…? /ቃለምልልሱ  ማክሰኞ የተደረገ ነው…/

ፈቱዲን:- አሪፍ የጾም ጊዜ ነበር….ጾሙ መግባቱን ሳናውቅ ነው መውጣቱን የሰማነው አንድ ወርኮ በጣም አነሰችብን ረመዳን እንደ ዘንድሮ ፈጥኖ አያውቅም… ሙሉ ሙስሊም ብትጠይቅ ፈጠነብን ትንሽ ሆነ ነው የሚሉህ ያም ሆኖ አሪፍ የጾም ጊዜ ነበር..

ሊግ:- እየተጫወተ መጾም ከባድ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ …ትስማማለህ..?

ፈቱዲን:-  በፍጹም አልስማማም… አንድ ሙስሊም መጾሙ የግድ ነው  ምናልባትም በህመምና አድካሚ ጉዞ በማድረግ ካልሆነ ላለመጾም  ሰበብ መፍጠር  አያስፈልግም ለኳስም ይሁን ለሌላ ስራ ብለህ አለመጾምማ ያስጠይቃል ለዚህ ደግሞ  ምንም ጥርጥር የለውም አለመጾም ልክ አይደለም አንድ ቀን ብታጠፋ ምናልባትም ሁለት ወር መጾም ይኖርብሃል እናም አለመጾም  ከባድ ነው  ኳስ ተጨዋችነት ስራዬ ነው ሙሉ ጾሙን በመጾሜ ግን  የፈጠረብኝ ተጽእኖ የለም ጾሙ አበርትቶኛል እንጂ አላደከመኝም ጠንካራ አድርጎኛል፡፡

ሊግ:- ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ነው የነፈቱዲን ዱአው ጠቅሟል ማለት ይቻላል…?

ፈቱዲን:– /ሳቅ በሳቅ/ ጾማችን አንድ ላይ ስለሆነ የክርስቲያኑም የሙስሊም ዱአችን አንድ ላይ ነው የጋራ ነው /ሳቅ/

ሊግ:- ለእግርኳስ መሸናነፍ እንዴት ይጸለያል የሚሉ አሉ፡፡

ፈቱዲን:-  ሁሉም በየሃይማኖቱ መጸለዩማ የግድ ነው ጸሎት ሙያ አይገድበውም ነገር ግን 90 ደቂቃ ውስጥ የተሻለ የተጫወተ ነው የሚያሸንፈው.. መጸለይ ብቻ እንድታሸንፍ አያደርግም…ከጸለይክ በኋላ ወደ ስራ መግባት ግድ ነው ጸልዮ የተሻለ የተንቀሳቀሰ ያሸንፋል  ለማሸነፍ የሚያስፈልገው መጸለይ ብቻ ከሆነ ጸልዮ ወደ ሜዳ አለመሄድ ነዋ…/ሳቅ/ መስራት መጸለይ የግድ ነው የልፋትን ነው የሚሰጠውም….

ሊግ:- የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለሁሉም ክፍት ነው…?

ፈቱዲን:-  አዘጋጁ አካል በገለጸው መሰረት አሁን ሁለተኛ ዙር ነው፡፡ 10 ጨዋታ ይቀራል የድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታን ለመጨረስ ሁለት ሳምንት ቢቀር ነው፡፡ ፉክክሩ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ነው አምና ከካቻምና ዘንድሮ ከአምና እየተሻሻለ እየተለወጠ መጥቷል አሪፍ ለውጥ ነው ነጥቦቻችንም የሚያሳየው ይሄን ሀቅ ነው  33 እና 32  ነጥብ ያላቸው ክለቦች ቁጥር በዛ ያለ ነው ወደኛ ወደ መሪዎቹ ለመድረስ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ናቸው ያሉት..ሊጉ ላይ ሁሉም ቡድኖች ጠንካራ ሆነው መጥተዋል ከታች ያሉትን ቡድኖች ለማሸነፍ ትልቅ ፈተና ላይ ነው፡፡ የነበርነው ይሄም ጥንካሬው መጨመሩን ያሳያል ከዚያ አንጻር 30 ቤት ውስጥ ያሉ ክለቦች በሙሉ የዋንጫ እድል አላቸው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሊግ:- የኢትዮጵያ  ንግድ ባንክን እንዴት አገኘኧው….?

ፈቱዲን:- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፕሪሚየር ሊጉ መስራች ክለቦች መሃል አንዱ ነው…የተወሰነ አመታት ግን አልነበረም አምና ተመልሶ መጥቶ ዘንድሮ ወደ መሰረተው ፕሪሚየር ሊግ ተመልሶ ይኧው ለዋንጫ እየተፋለመ ነው አምና በሊጉ ላይ ስኬታማ የነበሩትን ምናልባትም ከ1-3 ከወጡ ክለቦች ተጨዋቾችን ማስፈረም መቻሉና ከታች ከመጡት ጋር አቀናጅቶ ወደ ውድድር መግባቱ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል…ጥሩ ነገር አለው…. በነገራችን ላይ አሰልጣኙም ይሆኑ ተጨዋች ብቻቸውን ለውጥ አያመጡም…ነገር ግን  ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ፈርመው  የተሻለ ሆነን እንድንቀርብ የአሰልጣኙ ትልቅ ሚና አለበት በጋራ ጥሩ ቡድን ገንብተናል ብለን እናስባለን ።አሰልጣኝ በጸሎት ከዝግጅት ጊዜ ጀምሮ በሚሰጠን ልምምድ  ላይ ተነስተን እየሰራን ጠንካራ ሆነናል የአሰልጣኙም የተጨዋቾቹም አቅም ጥሩ በመሆኑ  ወደ ውጤት እያመራን ነው

ሊግ:- ደጋፊው ብዙ ባለመሆኑ ከጫና ውጪ  ሆናችሁ ነው  የምትጫወቱትና ተመቸህ…?

ፈቱዲን:- ያን ያህል ቁጥሩ የበዛ ደጋፊ እንደሌለው ይታወቃል ነገር ግን ድሬዳዋ ላይ እያለን የዲስትሪክት ሰራተኞች የተወሰኑ ጨዋታዎችን ጊዜ ሲያገኙ  እየመጡ በሚችሉት መንገድ ደግፈውናል ለዚህም እናመሰግናለን  ስለ ጫና ካወራህ ጫና ባለበት ጨዋታ ላይ መጫወት ነው የምወደው… ደጋፊ ሲኖር ሁሌ ጠንካራ ስራህን ሳትዘነጋ ጠንክረህ እንድትሰራ ያደርግሃልና መኖሩን ነው የምወደው… ነገር ግን ልምድ ላጣና ጫና ለማይችል ተጨዋች አለመኖራቸው  እፎይታ ሊሰጠው ሊጠቅመው  ይሆናል ለኔ ግን ደጋፊው ባለበት መጫወትን እመርጣለሁ ጫና የሚችል ተጨዋች በበርካታ ደጋፊ ፊት ቢጫወት ያበረተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ በርካታ ደጋፊ ባላቸው ክለቦች ወላይታ ድቻ፣ ሲዳማ ቡና፣ ኢትዮጵያ ቡናና ባህርዳር ከተማ መሃል በመጫወቴ አልተቸገርኩም ደጋፊው ጥሩ ነገር እንድትሰራና አላማ እንዲኖርህ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሊግ:–  የ2016 ዋነኛ እቅድህ ምንድነው…?

ፈቱዲን:- ሁለት ክለቦች ላይ በሊጉ ሁለተኛ ሁለተኛ ወጥቻለሁ… ላለመውረድ የተጫወትኩበት ክለብ እንዳለ ሳይረሳ… አሁን ግን ሁለተኝነትን አልፈልግም….ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አሁን ያለንበት ደረጃ ተስፋ የሚሰጠን ነገር ስላለ አመቱን ስጨርስ በዋንጫ እንዲሆን አልሜያለሁ…በግል ህይወቴ እንደ ታሪክ የማውራው የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ እፈልጋለሁ ሁለተኛ ሶስተኛነትን አልፈልግም፡፡

ሊግ:- የድሬ ሜዳ ሰበብ አልባ ነው ማለት ይቻላል…?

ፈቱዲን:- የድሬዳዋ ስታዲየም ምርጥ ቢሆንም በልምምድ ሜዳ ግን ተቸግረናል… ለልምምድ የምንፈልገውን ሰአት ማግኘት አልቻልንም፡፡ የምንፈልገውንም ልምምድ መስራት አልቻልንም ይሄ መስተካከል አለበት… የመጫወቻ ሜዳው ጥራት  የሚታይ ነው አያከራክርም ምቹ ነው እንደ ሀገር ይህን መሰል ሜዳ ያየነው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ጉልበት ይጠይቃል ግጥሚያዎቹ በየአራት ቀኑ አንዴ ሊሆን ስለሚችል ስኳድህ ሰፊ ሲሆን ጉልበት በሚጠይቀው የድሬ ሜዳ ላይ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብዬ አምናለሁ.. በድሬ ሜዳ ምንም አይነት ምክንያት ማቅረብ አይቻልም፡፡ እያነጠረ አስቸገረኝ ብለህ ኳስ ለመጠለዝ ሁሉ አትችልም  ሜዳው ሰበብ የለውም..

ሊግ:- አብሬው ብጫወት የምትለው ተጨዋች አለ..?

ፈቱዲን:- አብሬ ብጫወት ከምላቸው አብዛኞቹ አብሬም ሆነ ተጋጣሚዬ ሆነው የመተያየት የመጫወት እድል አግኝቻለሁ። አሁን ግን ከሀገር ውጪ ረጅም ጊዜ በመቆየቱ ያላገኘሁት ሽመልስ በቀለ ነው። ዘንድሮ ተቃራኒ ሆነን ተጫውተናል በቀጣይ ለአንድ ክለብ አብረን የምንጫወትበት ጊዜ ቢመጣ ደስ ይለኛል እንደሚሳካም ተስፋ አደርጋለሁ…

ሊግ:- በይበልጥ በመሸነፋችሁ የተበሳጨህበት ወይም በማሸነፋችሁ የተደሰታችሁበት ጨዋታ  የትኛው ነው…?

ፈቱዲን:- ምንም ጨዋታ መሸነፍ ያበሳጫል ደስ የሚል ሽንፈት የለም ግን እንደ መሪነታችን ተፎካካሪ ክለቦች ሲያሸንፉን  ያበሳጫል በዚህ እውነት በመቻል መሸነፋችን በጣም አበሳጭቶኛል በሁሉም ባሸነፍነው ጨዋታ ደስ ቢለኝም በይበልጥ ግን  አዳማ ላይ ያደረግነውና ከፍተኛ ፉክክር የነበረበትን ወሳኝ ጨዋታ ከፋሲል ከነማ ጋር አድርገን በማሸነፋችን ተደስቻለሁ፡፡ ተመርተን አቻ ሆነን እንደገና ተመርተን አቻ ሆነን  ያሸነፍነው ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክርና ውጥረት የነበረው ከመሆኑ አንጻር ፋሲል ከነማን ስናሸንፍ በይበልጥ ትልቅ ደስታ ፈጥሮልኛል፡፡

ሊግ:- ቲየሪ ኦነሪ ብለን አርሴን ቬንገር ካልን ፈቱዲን ጀማል ብለንስ..?

ፈቱዲን:- ያለጥርጥር አሰልጣኝ ናትናኤል ጋረዶ … ይህ ሰው ከሰፈር ጀምሮ ፕሮጀክትን አካቶ ወደ እግር ኳሱ ያመጣኝ ወደ ትልቅ ደረጃ ያደረሰኝ አሰልጣኝ ነው እሱን ነው በጣም የማመሰግነው…

ሊግ:– በቦታህ ምርጡ ማነው..?

ፈቱዲን:– ከሀገር ውስጥ ምርጫዬ  አስቻለሁ ታመነ ነው… ከውጪ በወቅቱ ካልን የአርሰናሉ ዊሊያም ሳሊባ ባለፉት አመታት ከህነ ደግሞ ሰርጂዮ ራሞስ ምርጫዬ ነው….

ሊግ:- ከውጪ የማን.ደጋፊ ነህ..?

ፈቱዲን:- የማን.ሲቲ ደጋፊ ነኝ..የማን.ሲቲ ደጋፊ ነኝ ስትል በቅርብ ጊዜ ውስጥ ነውኮ ሲቲ የገነነው አሁን ነዋ ማየት መደገፍ የጀመርከው ይላሉ… እኔ እስከማውቀው ድረስ ማን.ሲቲ  ከእንግሊዝ ክለቦች ከ1-6 ከሚገኙ ክለቦች መሃል የሚገኝ ነው ታሪኩ ትልቅ ነው … እንደ መጀመሪያ የስፔን ላሊጋ ወዳጅና የባርሴሎና ብቻ ደጋፊ ነበርኩ፡፡ ሲቲን የምጠራውና የማደንቀው በሮቤርቶ ማንቺኒ ጊዜ የነበረውን ቡድን ነው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ  ፔፕ ጋርዲዮላ ሲመጣ አድናቂው ስለነበርኩ ድጋፌ ቀጠለ ያለው እውነት ይሄ  ነው…

ሊግ:- የዘንድሮን አርሰናል እንዴት አየኧው..?

ፈቱዲን:-  ከአምና  ጀምሮኮ ጥሩ ቡድን ነው በየአመቱ እየተሻሻለ የመጣ ቡድነ ነው አርሰናል…የዘንድሮ መሻሻሉና ያለው አቅም የተለየ ነው በጣም ነው የገረመኝ…ነገር ግን መጨረሻ ላይ  የማን.ሲቲ የዋንጫ አሸናፊነትን የምናይ ይመስለኛል../ሳቅ/

ሊግ:- የአዶላ ምልክት ነህ ማለት ይቻላል..?

ፈቱዲን:- ከኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ  አንተነህ ተፈራ ጋር ያደረከውን  ኢንተርቪውን አይቼዋለሁ ደስ የሚል ነበር.. አዶላ የወርቅ  አካባቢ ላይ ስለተወለድክ ብቻ በወርቅ ንግዱ ይሳካል ማለት ላይሆን ይችላል ከመሬት ተነስቶ ስኬታማ መሆን አይቻልም  እናም ቢዝነሱ ላይ አልገባንበትም  እንደ አካባቢው ተወላጅነት  ምልክት ሆነን የምናስጠራ መሆናችን ግን ያስደስተናል፡፡

ሊግ:– የመጨረሻ የምታመሰግነው..?

ፈቱዲን:-  በመላው አለም ለሚገኙ የእስልምና እምየት ተከታዮች ለ1445 ኢድ አልፈጥር በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ…በዓሌን አብሬ ባላከብርም ለቤተሰቦቼ እንኳን አደረሳችሁ መልካም በዓል ይሁንላችሁ ማለት እፈልጋለሁ አንተንና ሊግንም ከልብ አመሰግናለሁ…

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P