በክለብ ደረጃ የመጀመሪያ ማሊያ ያደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 አመት በታች ቡድንን በመቀላቀል ነው .. ለአንድ አመት ከተጫወተ በኋላ ለኢትዮጵያ ቡና ከ20 አመት በታች ቡድን ፈርሞ አንድ አመት ተጫውቶ ወደ ዋናው ቡድን እንዲያድግ አሰልጣኙ ፈረንሳዊው ዲዲየር ጎሜዝ ይወስኑና ለዋናው ቡድን ይመረጣል ጥሩ ጊዜ ነበረኝ የሚለው እንግዳችን ለ6 ወር ከፋ ቡና 2 አመት አዲስ አበባ ከተማ ከተጫወተ በኋላ ለባህርዳር ከተማ ፈርሞ ዘንድሮ ሁለተኛ አመቱን ይዟል…በያዝነው የውድድር አመት ኮንትራቱ የሚጠናቀቀው ፍጹም ጥላሁን ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በታሪካቸው የመጀመሪያ የሆነውን ቃለምልልስ አድርጓል….
ማስታወሻ:– ይሄን ቃለምልልስ ያደረግነው ባለፈው ሳምንት ባህርዳር ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ከመጫወቱ 3 ቀናት በፊት ነው…ማተሚያ ቤት በተፈጠረ የቴክኒክ ችግር ምክንያት ሊግ ባለፈው ሳምንት ባለመውጣቷ ቃለምልልሱ ወደ ዛሬ የዞረ መሆኑን ታሳቢ እንዲደረግ ክቡራን አንባቢዎቻችንን ለማስታወስ እንወዳለን…
ሊግ:– በተጫወትክባቸው ክለቦች የተሻለ የማይረሳ ምርጥ ጊዜ ነበረኝ የምትለው ለየትኛው ክለብ ስትጫወት ነው..?
ፍጹም:– በእግርኳስ ቆይታዬ ደስተኛ ነኝ… በቢ ቡድንና በተስፋ ቡድን ዋንጫ አግኝቻለሁ…በዋናው ቡድን ደረጃ ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ዋንጫ አንስቻለሁ….
ከባህርዳር ከተማ ጋር ደግሞ ትልቁን ዋንጫ ትልቁን ተሳትፎ አሳክቻለሁ በአጠቃላይ እንደ ግል ያሳካሁት ባይሆንም እንደ ቡድን ግን ከሁሉም ጋር በሚባል ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ…
ሊግ:- እግርኳስ ተጨዋች እንድትሆን ያደረገህ ተምሳሌት አለህ….?
ፍጹም:- ከልጅነት ጀምሮ ለፕሮጀክት ስንጫወትም ተምሳሌት እሱን ብሆን የምትለው ሰው ይኖራል…ልጅ ሆኜ ፕሮጀክት ስጫወት ተምሳሌቴ የነበረው አስራት መገርሳ ነው በወቅቱ የሰፈሬ ልጅ ስለነበረ ሙሉ የቄራ ሰው ስለሱ ሲያወራ እየሰማሁ አድጌያለሁ ኢትዮጵያን ወክሎ በትልልቅ የአፍሪካ መድረክ ላይ ሲካፈል ሳይ እሱን መሆን እፈልግ እመኝ ነበር
ሊግ:- ምን ያህሉን አሳካሁ ብለህ ታምናለህ..?
ፍጹም:- እግርኳስ ተጨዋች የመሆን ህልሜን አሳክቻለሁ…በዚህ ደስተኛ ነኝ ኢትዮጵያ ከበርካታ አመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍና ሀገር የመወከሉ ህልሜ ገና ነው በተሻለ መንገድ ማሳካት እፈልጋለሁ ይሄኛው ህልሜ ይቀራል ነገ ላይ ተስፋ አለኝ በርትቼ ለማሳካት እጥራለሁ
ሊግ:- በርካታ አሰልጣኞች አሰልጥነውሃል ብዬ እገምታለሁ ..ምርጡ.ላንተ እዚህ መድረስ ባለውለታ አድርገህ የምትጠራው አሰልጣኝ ማነው..?
ፍጹም:- በእግርኳስ በሙሉ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች አመሰግናለሁ ብዙ ነገር ጨምረውብኛል የፕሮጀክት አሰልጣኞቼ መሰረት እንዲኖረኝ አድርገውኛል አካዳሚ የነበሩ አሰልጣኞች ደግሞ መሰረት የያዝኩበትን መስመር እንዳሳድገውና በአዕምሮ መጫወትን አሳይተውኛል ከዚያ በኋላ ያሉ አሰልጣኞች ደግሞ ሙያዬን አክብሬ ወደ ተሻለ ደረጃ እንድደርስ አድርገውኛል ለዚህም ሁሉንም ከማመስገን ውጪ እገሌ ብዬ በተለየ መንገድ የምጠራው ሰው የለም።
ሊግ:- ለኔ ብቸኛ የምጠራው ባለሙያ የለም እያልከኝ ነው..?
ፍጹም:- በምሳሌ ልንገርህ …! ለቢ ስጫወት አሰልጣኝ ደረጄ አንገቴ ብዙ ነገር አሳይቶኛል በኔ ውስጥ የነበረ ግን ያልተረዳሁትን ያየሁት በሱ ነው. እግርኳስን በነጻነትና በራስ መተማመን እንድጫወት አድርጎኛል…ከዚያ በመቀጠል እነ ዮሴፍ ተስፋዬ ፣እነ እስማኤል አቡበከር፣ አሁን ያለው ደግአረገ ይግዛው ፈረንሳዊው ዲዲየር ጎሜዝ ያለኝን አቅም ተረድተው ምን መስራት እንደሚጠብቅብኝ በሚያደርግ አቅሜን ጨምረውብኛል ሁሉም የየራሳቸውን ድርሻ አበርክተውልኛል ስለዚህ ሁሉንም ከማመስገን ውጪ የምለው የለም ያልኩህ ለዚህ ነው…
ሊግ:– ምርጡ አቋምህ አሁን ያለው ነው ወይስ ገና ከፊታችን ባሉት አመታት ይጠበቅ..?
ፍጹም:- አሁን ያለው አቅሜ ከ100 አስር ፐርሰንቱ ነው ብዬ አላምንም ቻሌንጆች ሲገጥሙህ በምትፈልገው መንገድ ላትጓዝ ትችላለህ ውስጤ የሚለኝ ፍጹምና ሌላ ሰው የሚለኝ ፍጹም በጣም ይለያያሉ አቅሜ ይሄ አይደለም የተሻሻለው አቅሙን የጨመረ ፍጹምን ወደፊት የሚመጣው ነው በዚህ ደጎሞ ርግጠኛ ነኝ
ሊግ:- በዋናነት ማሳካት የምትፈልገው ህልምህ ምንድነው ..?
ፍጹም:– እነ ሊዮኔል ሜሲ በል ክርስቲያኖ ሮናልዶን አለም ላይ ያለ ማንኛውም እግርኳስ ተጨዋች ትልቁ ግብ አገሩን ማገልገል ነው …. ከሁሉም በላይ ትልቁ ክብራቸው ለሀገራቸው መጫወታቸው ነው… እናት ከሌላው ጋር እንደማትወዳደር ሁሉ ሀገርህም ከምንም ነገር ጋር አትነጻጸርም በህዮይወቴ ትልቁ ግቤ ሀገሬን ማገልገል ነው ደግሞ ርግጠኛ ነኝ አሳካዋለው ብሄራዊ ቡድንን ለማገልገል የጊዜ ገደብ አላስቀምጥም አቅም ኖሮህም አሰልጣኙ ሌላ ሊመርጥ ይችላል ነገር ግን የምችለውን ሁሉ አድርጌ ለመመረጥ ሀገሬን ለማገልገልም እጥራለሁ
ሊግ:- ፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ነው ማለት ይቻላል…?
ፍጹም:– አዎ… በተለይ ደግሞ ዲ ኤስ ቲቪ ከመጣ ጀምሮ ፉክክሩ ጠንከር ብሏል….አቅም ያላቸውን ወጣት ተጨዋቾች እያየን ነው…. ጠንካራ ተፎካካሪዎች ያሉበት ሊግ ሆኗል….
ሊግ:- ዋንጫ ይወስዳል አቅም አለው የምትለው ቡድን አለ..?
ፍጹም:- ገናኮ 17 ጨዋታ አለ ብዙ ነገር ሊፈጠር ይችላል በአሁኑ ሰአት ዋንጫ ይወስዳል የምለው ቡድን የለም እኛ ከላይ እያለን ከ1-3 ያለውን ደረጃ ባሉ ክለቦች መሃል የነበረው ልዩነት ሁለት ወይም ሶስት ነጥብ ብቻ ነበር አራትና አምስት ጨዋታ ከተካሄደ በኋላ ግን ልዩነቱ ሰፊ ሆኗል….ገና 17 ጨዋታ እንደመቅረቱ ብዙ ነገር ሊፈጠር ይችላልና አሁን ላይ የዋንጫ ቡድን የምለው ቡድን ሊኖር አይችልም…
ሊግ:- የክለባችሁን ደጋፊዎች እንዴት ትገልጻቸዋለህ..?
ፍጹም:- የባህርዳር ከተማ ደጋፊኮ ምንም ጥርጥር የሌለው ቡድኑን የሚወድና ጨዋነቱ የተመሰከረለት ነው ሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ደጋፊዎች መሃል ምርጥ የሚባል ደጋፊ ነው ያለን… ለክለባቸው ያላቸው ታማኝነት የተረጋገጠላቸው እኛ በምንገኝበት ቦታ ሁሉ የሚገኙ ምርጥ ደጋፊ ናቸው
ሊግ:- በጨዋታው ሂደት ሜዳ ላይ ይነጫነጫል የሚሉ አሉ…እውነት ነው ..?
ፍጹም:- አልሸነፍም ባይነቴ አለ እውነት ነው… አልሸነፍ ባይነቱ ያላቸው የሚረዱትና ሌላው የሚረዳው ይለያያል… ላለመሸነፍ ካለኝ ባህሪ አንጻር ስሜታዊ ልሆን እችላለሁ ክለቤ እንዳይሸነፍ ስለማልፈልግ እናገራለሁ ያን አይተው ይሆናል…አንድ ተጨዋች ማሸነፍም መሸነፍም ግድ የማይሰጠው ከሆነ ጸጥ ይላል… ዝምታ ጨዋነት ብቻ አይይለም … አንዳንዴ ቡድንህ ተሸነፈም አሸነፍም ዝም ካልክ ዝምታው ራስወዳድነት ይሆናል… ስሜቴ ከማሸነፍ አንጻር የሚነሳ እንጂ የባህሪ ችግር አይደለም
ሊግ:- የመጨረሻ ጥያቄ…እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለሀገርህ ምን ትመኛለህ..?
ፍጹም:- ሁለት ነገር በዋናነት እመኛለሁ የመጀመሪያውና ዋናው ሰላም ነው…ያለ ሰላም ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም ወጥቶ መግባቱ ያለው ሰላም ሲኖር ነው ሁለተኛው ደግሞ ሀገሬ ከፍ ብላ ልክ እንዳደጉ አገራት የምትከበር፣ የምትመሰገንና የምትፈራ የምትታፈርና የምትከበር ሆና ማየትን እመኛለሁ።