Google search engine

“ጅማ አባጅፋር ባደገበት አመት የሰራውን ዋንጫ የማንሳት ታሪክ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይደግመዋል” “ኢንተ. አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ ባጫወተኝ ጨዋታ በሙሉ ቀይ ካርድ አይቻለሁ” ፍሬው ጌታሁን (የኢት.ንግድ ባንክ ግ/ጠባቂ)

የእግር ኳስ ጅማሬዬ በሻሸመኔ ከተማ ነው፡፡ በዚህ ክለብ ውስጥ በግብ ጠባቂነት አቤል ማሞን እያየሁ ልምዱን እየቀሰምኩ ነው ያደኩት፡፡ ክለቡን የለቀቅነውም በተመሳሳይ ጊዜ ነው ሲል ይናገራል… ሻሸመኔ የተጀመረው የተጨዋችነት ዘመኑ በአርሲ ነገሌ ቀጥሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የአዲስ አበባን ከተማና የድሬዳዋ ከተማን በር እንዲጠብቅ ያስቻለው እንግዳችን ፍሬው ጌታሁን ዘንድሮ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የግብ በርን አልፎ መረቡን እንዳይነካ የማድረግ ትልቅም ሃላፊነት በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ተሰጥቶታል…. ግብ ጠባቂው በከፍተኛ የራስ መተማመን ስለተገነባው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  እቅድ፣ ስለ ግብ ጠባቂነት ጫና፣ ስለ ፕሪሚየር ሊጉ፣ ስለ አርቢትሮችና እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች  ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል…

 

ሊግ፡  በቆየህባቸው ክለቦች ምርጥ ቆይታ ነበረኝ የምትለው የት ነው ..?

ፍሬው፡ ያለ ምንም ማሰብ ነው የምመልሰው ድሬዳዋ ከተማ ነዋ… ረጅም ጊዜ የመጫወትና አቅሜን የማሳደግ እድል ያገኘሁት እዚያ ነው፡፡ ከአምስት አመታት ቆይታዬ ሳምሶን አሰፋ እያለ ምክትል ሆኜ ሁለት አመት እሱ ከወጣ በኋላ 3 አመት ቋሚ ሆኜ ተጫውቻለሁ። ያንን ቆይታዬ በተለየ መንገድ ነው የማየው…. ከዚያም በቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙም እድል ባላገኝም በክለቡ ማሊያ ሰባት ስምንት ጨዋታ ብቻ ተጫውቻለሁ… ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ቢሆንም ብወደውም የድሬዳዋ ከተማን ያህል ግን ደስታ አልሰጠኝም…

ሊግ፡  ግብ ጠባቂ የሰበብ ማብረጃ ነው ይባላልና ጫናውን ቻልከው..?

ፍሬው፡ ያው ስገባ አምኜበት ነው .. 90 ደቂቃ አሪፍ ሆኜ በጭማሪ ሰአት ቢገባብኝ ዋጋ የለውም እያልኩ ወደ ሜዳ ከገባሁማ አይሆንም.. ያው ሊፈጠር ይችላል፡፡ ግን ተዘጋጅቶ መግባት ከኔ ይጠበቃል፡፡ ምንም አይፈጠርም የሚል ልበ ሙሉነት ኖሮኝ ነው ወደ ሜዳ  የምገባው… እኔ ወደ ሜዳ ስገባ አስቤ የምገባው ቡድኔ በኔ ብቃት ነጥብ ይዞ እንደሚወጣ ነው የሌሎቹ አስተዋጽኦ ሳይረሳ… ብዙ ጊዜ ስለተሳካልኝ የማስበው እንደዚያ ነው፡፡

ሊግ፡ በ20 ነጥብ መሪ ናችሁ.. አንድም ጨዋታ ያልተሸነፋችሁት እናንተ ናችሁ ሂደቱ እንዴት ይገለጻል ..?

ፍሬው፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አዳጊ ቡድን እንደመሆኑ ብዙ ላይጠበቅ ይችላል… በአሰልጣኙና በተጨዋቾቹ ጥምረት በታየው ውጤት ግን ከፍ ያለ ነገር እንድትጠብቅ ያደርጋል፡፡ አብዛኞቹ ሊጉን በደንብ የሚያውቁት ልምድ ያላቸው እንደመሆናቸው ጥሩ ጊዜ እንድናሳልፍ አድርጎናል። ልምምድ አሰጣጡ በነጻነት መስራት መቻላችን ይለይብኛል፡፡ የአሰልጣኝ በጸሎት አቅምና ተጨዋቾችን የሚረዳበት መንገድ ይህን ውጤት እንድናመጣ እንደውም ከዚህ የበለጠ እንድንጠብቅ የሚያደርግ ነው፡፡ ሁላችንም ቀጣዩን ጨዋታ ስለማሸነፍ ሳይሆን ዋንጫ ስለመውሰድ ነው የምናስበው… ፍላጎትና ሃሳባችን የሆነውን ዋንጫ ከፈጣሪ ጋር የምናሳካ ይመስለኛል።

ሊግ፡ ፕሪሚየር ሊግን እንዴት አገኘኸው..?

ፍሬው፡ ፕሪሚየር ሊጉን 8 አመት ሙሉ እንደማወቄ ሂደቱን በደንብ አውቃለሁ፡፡ እያንዳንዱ የሚወርዱትን የሚቀሩትን ማን የተሻለ እንደሆነ ማን ጥሩ አቋም እንደያዘ ውስጡን አውቃለሁ፡፡ እንዲሁም አምና ላለመውረድ ወደ 9 ቡድኖች ነበሩ የሚጫወቱት፡፡ ዘንድሮ በተቃራኒው ወደ 7 ክለቦች የምንጫወት ይመስለኛል። ምክንያቱም ሁሉም ጠንክረው ነው የመጡት፡፡ በተለይ ከአምና የተለየውና ጠንካራ ጎኑ ከወገብ በላይ ያሉት አምስት ስድስት ክለቦች ለማሸነፍ የያዙት መንገድና የመጡበት አካሄድ ጠንካራና ለዋንጫ እንደሚጫወቱ ያሳያል፡፡ አምና ቅዱስ ጊዮርጊስ መድንና ፋሲል ለዋንጫ ተጫውተዋል፡፡ ዘንድሮ እኛም ይህን ፉክክር ተቀላቅለነዋል፡፡ ይሄም ሊጉ እየጠነከረ መምጣቱን ያሳያል።

ሊግ፡ ኢትዮጵያ ቡናን አሸነፋችሁ… ጨዋታው ምን ይመስላል …?

ፍሬው፡ ተጨዋች ስትሆን ፊት ለፊት ያለውን ጠንካራ ቡድን ማሸነፍ ትፈልጋለህ፡፡ ትልልቅ ቡድኖች ሲገጥሙህ በሀሳብም በስነልቦናም ተዘጋጅተህ ነው የምትፋለመው፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሊጉ መሪ ነው፡፡ ከእኛ ሲጫወቱ እኛን አሸንፈው ነጥብና ደረጃቸውን ከፍ ማድረግን ይፈልጋሉ፡፡ እኛም እነሱን አሸንፈን ልዩነታችንን ማስፋት እናስባለን፡፡ ለዚህ ነው የተፋለምነው… አንደኛነታችንን ላለመልቀቅና ዋንጫ ማግኘት ካሰብን እንደ ኢትዮጵያ ቡና ያሉ ጠንካራ ክለቦችን ማሸነፍ የግድ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ቡና ያለ ጠንካራ ቡድን ማሸነፍ የእውነት ዋንጫውን እንድንመኝ አድርጎናል፡፡ ጨዋታውን በማሸነፋችንም ደስ ብሎናል፡፡ በቀጣይ ያሉ ጨዋታዎችንም ተራ በተራ እያሸነፍን የምንጓዝ መሆኑን ያሳያል።

ሊግ፡  ለአንተ ምርጡ በረኛ ማነው..?

ፍሬው፡ ከውጪ ካቆሙት ጂያንሉጂ ቡፎን፡፡ አሁን ካሉት ማኑኤል ኑየር በጣም እወደዋለሁ፡፡  ዴቪድ ደሂያም ደስ ይለኛል… ሀገር ውስጥ አቤል ማሞን እያየሁ ነው ያደኩት.. ከታች ሳድግም እሱ እያለ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ አብሬው ሰርቻለሁ። በጣም እወደዋለሁ አደንቀዋለሁ፡፡ ሌላው ዘሪሁን ታደለን እወደዋለሁ፡፡ እኛ ሀገር ሆኖ እንጂ ዘሪሁን ታደለ የመሰለ ኳሊቲ ያለው ኢትዮጵያዊ በረኛ የለም፡፡ በጥቃቅን ነገሮች ወደታች ዝቅ አደረጉት ያሳዝነኛል…

ሊግ፡ ዘሪሁን ላይ ተጽዕኖ የፈጠረው የቡርኪና ፋሶ ብሄራዊ ቡድን ባስቆጠራቸው ግቦች አይመስልህም ..?

ፍሬው፡ ኳስኮ ነው.. አንድ ምሳሌ ልስጥ ሴካፋ ላይ ሄደን ስንጫዘት ግብ ጠባቂ እሱ ነበር፡፡  ዋሊያዎቹ 5ለ0 ተሸንፈው የጨዋታ ኮከብ ተብሎ የተመረጠውም እሱ ነው፡፡ አሁን ግን አራት የተቆጠሩት በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ስለሆነ ተጋነነበት… እኛ ሀገር ምንም ይቆጠር በረኛ ላይ ብቻ ነው ትኩረቱ.. ግቡ በፔናሊቲም ይግባ በረኛው ላይ ነው የሚተኮረው… ይሄ ያሳዝነኛል እሱ ተሰዋ እንጂ፡፡ የገቡት ግቦችኮ በቃ የሚቆጠሩ ናቸው…  ስለቻለኮ ነው እዚያ የሄደው፡፡ አምና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነበር፡፡ አሁን ከፍተኛ ሊግ ላይ ላለው ከፋ ቡና እየተጫወተ ይመስለኛል።

ሊግ:- ጅማ አባጅፋር ወደ ፕሪሚየር ሊግ ባደገበት አመት ዋንጫ አንስቷል… ኢትዮጵያ ንግድ ባንክስ..?

ፍሬው፡ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ባደገበት አመት ዋንጫ በማንሳት ጅማ አባጅፋር ቀዳሚ ሆኗል… ጅማ አባጅፋርን ባደገበት አመት የሰራውን ዋንጫ የማንሳት ታሪክ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  የሚደግመው ይመስለኛል፡፡ ያለውም ሁኔታ የሚያሳየው ይህንን ነው፡፡ የነገውን የሚያውቀው ፈጣሪ ቢሆንም አጀማመሩ መጨረሻውን የሚያሳይ ነው የሚመስለው።

ሊግ፡ የሊጉን ዳኝነት እንዴት አገኘኸው..?

ፍሬው፡ ዳኝነትን ከሌሎቹ አገራት አንጻር ካየነው ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ሌሎቹ በቫር ታግዘው የሚሰሩትን ስህተት ስታይና እኛ ሀገር ያለምንም እገዛ ሲወስኑ ሲያጫወቱ ሳይ በጣም ነው የማደንቃቸው… ሜዳ ውስጥ ስትገባና ደምህ ሲሞቅ ትበሳጫለህ እንጂ ውጪ ወጥተው ሲያጫውቱ በጣም ትገረምባቸዋለህ … ያለምንም እገዛ ሲያጫውቱ ስታይ አውሮፓ ያለን ነው  የሚመስለው…

ሊግ፡ በዳኛ የተሳሳተ ውሳኔ ነጥብ አላጣችሁም ማለት ነዋ …?

ፍሬው፡ ሁሌ ዳኛውም ሆነ ተጨዋቹ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም… ዳኞች ውሳኔ ሲወስኑ ዋጋ ሊያስከፍሉ ይችላሉ፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን ያለምንም እገዛ በጥረታቸውም እየመሩ ላሉት ዳኞቻችን ድጋፍ ማድረግ እንዳለብን አምናለሁ..።

ሊግ፡ በግልህ በጣም የምታደንቀው አርቢትር ማነው ..?

ፍሬው፡ ኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማን አደንቃለሁ፡፡ በተጨማሪም የኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩም አድናቂ ነኝ።  የሚገርመው ኢንተ. አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ  ባጫወተኝ ጨዋታ በሙሉ ቀይ ካርድ አይቻለሁ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስጫወት ቀይ ካርድ ሳይሰጠኝ በመውጣቱ ገርሞኛል… ደፋርና ያመነበትን ውሳኔ ሰጪ በመሆኑ አከብረዋለሁ።

ሊግ፡  ዋሊያዎቹን የመቀላቀል ህልምህ ምን ይመስላል..?

ፍሬው፡ ማንኛውም ተጨዋች ለሀገሩ መሰለፍ ይፈልጋል፡፡ ዋናው ግን ጥሩ ሆኖ መገኘት ነው፡፡  አሰልጣኙ ከመረጠኝ ዝግጁ ነኝ፡፡ ካልመረጠኝም ውሳኔውን አከብራለሁ፡፡ በእኔ በኩል ለክለቤ ውጤት ጠንክሬ መስራት ብቻ ነው የሚጠበቅብኝ …. ያኔ ጥሩ ከሆንኩ እመረጣለሁ፡፡ ሁል ጊዜም ግን አገሬን ለማገልገል ምንጊዜም ዝግጁ ነኝ፡፡

ሊግ:- በዋናነት በ2016 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያለህ ዕቅድ ምንድነው..?

ፍሬው:- ምንም ጥያቄ የለውም… ኢትዮጵያ .ንግድ ባንክ ዘንድሮ የተነሳው የሊጉን ዋንጫና ዋንጫ ብቻ ብሎ ነው…. ኳስ የምትሰጠውን ውሳኔ እናከብራለን እንጂ ዋና እቅድ ዋንጫ ነው….

ሊግ፡ የምታመሰግነው የመጨረሻ ቃል…?

ፍሬው:– የመጀመሪያ ምስጋናዬ ለእግዚአብሄር ይሁንልኝ… ከዚያ በመቀጠል የማመሰግናቸው ሰዎች አሉ…. በህይወቴ ትልቁን ነገር ያደረገችልኝን እህቴን ታሪኬን አመሰግናለሁ… ነፍሱን ይማረውና ደጀኔ ጫካ ሻሸመኔ ከተማ 5ኛ በረኛ አድርጎ ይዞኝ ለዛሬ ትልቅ ማንነቴ በቅቻለሁና በጣም አመሰግናለሁ…  በሻሸመኔ ከተማ አሁንም ወጣቶችን እያሰለጠነ ያለው አንዷለም መስፍን /ዲሻን/ አመሰግናለሁ… አርሲ ነገሌ ደግሞ እንደ አባት እንደ ታላቅ ወንድም ሆኖ ያሰለጠነኝ አሰልጣኝ ፔፕሴኒ በጣም አመሰግናለሁ…. ከነኚህ ውጪ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች፣ አብረውኝ የተጫወቱ፣ በእኔ ነገር ላይ አስተዋጽኦ ያደረጉ የደገፉኝን በሙሉ አመሰግናለሁ…

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P