ባለግራ እግር ሀዋሳ ያፈራችው ኮከብ ነው …. ለሀዋሳ ከተማ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስና ለወልቂጤ ከተማ ተሰልፎ ተጫውቷል። ከረጅም ጊዜ በኋላ ድምጹ የተሰማው ና ከሊግ ጋር ቆይታ ያደረገው እንግዳችን በራስ መተማመኑ አሁንም ከፍ እንዳለ ነው ልምምድ ወሳኝ ነው ያለ ልምምድ ምንም ማሳካት አይቻልም ሲል ይናገራል…
.ከወልቂጤ ከተማ ጋር የነበረው የአንድ አመት ውል በመጠናቀቁ ከውል ነጻ ሆኖ ዝውውር ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው ከርሱ ጋር ግንኙነት የጀመሩ ክለቦችም እንዳሉ ይናገራል..እንግዳችን ጋዲሳ መብራቴ..ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ለቀረበለት ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ሊግ:– ከረጅም ጊዜ በኋላ ተገናኘን…. እንዴት ሰንብተሃል ..? ግን ጠፋህኮ..?
ጋዲሳ:– ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው የተገናኘነው ይገርማል ጊዜው ..ለነገሩ አለሁ አልጠፋሁም … ያው ስራው ይቅደም ብዬኮ ነው…ይህን አመት ወልቂጤ ከተማ ነበርኩ መጥፎ ጊዜሜ አልነበረም ያሳለፍኩት ..
ላለመውረድ ብንጫወትም በግሌ ጥሩ ነበርኩ…እንዳንተ ገፍቶ የመጣ ሚዲያም ባለመኖሩም ይመስለኛል፡፡ የጠፋሁት እንጂ አለሁ ..የኛ ዋና ሚዲያ ሜዳው ነው እሱ ላይ አለሁ አልጠፋሁም /ሳቅ/
ሊግ:-ዕረፍቱንስ እንዴት እያሳለፍከው ነው ..?
ጋዲሳ:- ጥሩ የእረፍት ጊዜ እያሳለፍኩ ነው በዚያ ላይ የሰመር ካፕ አለ ከጨዋታ ሳልርቅ ህዝቡን እያዝናናን እኔም ዘና እያልኩ ነው ..በተጨማሪ በባለቤቴና ልጆቼ ከእህቶቼ ና ጓደኞቼ ጋር ሆኜ እረፍቴን እያሳለፍኩ ዘና እያልኩ ነው በቆዬታዬ ደስተኛ ነኝ፡፡
ሊግ:– አመቱን ከወልቂጤ ከተማ ጋር እንዴት አሳለፍክ..?
ጋዲሳ:– አመቱ እንደ ቡድን ለኛ ከባድ ነበር በግሌ ግን ስኬታማ ነበርኩ ..ምክንያቱም ከነበረብን ችግርና ከተከሰተው የፋይናንስ እጥረት አንጻር ያሳለፍኩት ጊዜ መጥፎ የሚባል አይደለም በጣም በቂ ነው ባይባልም ጥሩ አቋም ነበረኝ ብዬ አስባለሁ…
ሊግ:- ከመውረድ መትረፉም ስኬት ነው..?
ጋዲሳ:- በጣም ጥሩው ነገር እሱ ነው .. ለስሜም ለሲቪዬም ወልቂጤ ከተማ እያለሁ ክለቡ ባለመውረዱ ደስ ብሎኛል ቡድን ማውረድ ከባድ ጥቁር ነጥብና መጥፎ ታሪክ ነው ለሁላችንም አለመውረዱ አስደስቶናል …
ሊግ:- ከደመወዝ መክፈል አለመቻልም ይሁን ተደጋጋሚ ሽንፈት መግጠሙ ጋር እንደ 2016 ተፈትነህ ታውቃሐህ..?
ጋዲሳ:- በፍጹም …እንደ ዘንድሮ የተፈተንኩበት አመቱ ፈተና የሆነብኝ አመት የለም በዚህ በኩል ደመወዙ በተገቢው መንገድና ጊዜ አለመከፈሉ ሌላው የውጤት ማጣት ጫና ውስጥ ሆነን ነው ያሳለፍነው .. የክለቡ አሰራር ደካማ ነው.. ልምምድ እንጀምራለን እናቋርጣለን ጨዋታው አንድ ቀን ሲቀረው ነው የምንመጣው…ያን ሁሉ ተቋቁመን ቡድኑን በፕሪሚየር ሊጉ ማቆየታችን ትልቅ ነገር ነው በአጠቃላይ ስናየው አመቱ የፈተና ነበር ማለት እችላለሁ..
ሊግ:- ከወልቂጤ ከተማ ጋር ውል አለህ..? ወይስ .?
ጋዲሳ:- ጨርሻለሁ…ነጻ ነኝ የፈረምኩት ለ2016 ስለነበር ተጠናቋል…የተወሰኑ ክለቦች ጋር ግንኙነት ጀመሬያለሁ እየተነጋገርን ነው ከእግዚአብሄር ጋር ተሳክቶ በቀጣይ 2017 ከሌላ ክለብ ጋር ታየኛለህ ብዬ አስባለሁ…
ሊግ:- በኳስ ተጨዋችነትህ ደስተኛ ነህ..?
ጋዲሳ:- በጣም እንጂ …ከልጅነቴ ጀምር እግርኳስ መጫወት እወዳለሁ ከልጅነቴም ጀምሮ ሜዳ ውስጥ ከገባሁ ጀምሮ ደስተኛ ሆኜ ነው የምጫወተው.. ወልቂጤ ከተማን ሲያሰለጥን የነበረው ሙሉጌታ ምህረት በጣም ስለሚያቀኝ ብዙ የመጫወት እድሉን ሰጥቶኛልና አመሰግናለሁ፡፡ እኔም ዕድሉን እንደ ተጠቀምኩ ይሰማኛል… ከአሰልጣኞቼና ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ቡድኑን ከመውረድ እንዲተርፍ አስችለናል ይሄም ትልቅ ታሪክ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ሊግ:- ላለመውረዳችሁ ርግጠኛ የሆያችሁት ከማን ጋር ስትጫወቱ ነው ..?
ጋዲሳ:- ወሳኝ የሆኑ ጨዋታዎችን አድርገናል ከሁሉም ግን ለመትረፋችን ዋናው ብዬ የማምነው ከሀዋሳ ከተማ ጋር 2ለ2 ተለያይተን አንድ ነጥብ ስናገኝ ነው በዚያ ላይ ሁለቱንም ግቦች ያስቆጠርኩት እኔ ነኝ በጣም አሪፍ ጨዋታ ነበር።
ሊግ:- ያደክበት ክለብ ላይ ግብ ማስቆጠር ስሜታዊ ያደርጋል.?
ጋዲሳ:- አዎ ስሜታዊ ያደርጋል … ያደኩበት ቡድን የሀገሬ ቡድን ነው ስለሆነ የሚፈጥረው ስሜት አለ…ያው ግን ስራዬ እግርኳስ መጫወት እንደመሆኑ ላለሁበት ቡድን ታማኝ ነኝ ለወልቂጤ ከተማ ማሊያ ታማኝ ነበርኩ.. ግብ በማስቆጠሬ ደስተኛ ነኝ ለለበስኩትም ማሊያ መቼም ቢሆን ታማኝ ነኝ ሀዋሳ ላይ ሳስቆጥር ግን የሚሰማ ስሜት ይኖራል።
ሊግ:- አልፋለሁ አታልፍም ትግል የሚገጥምህ ከባዱ ተከላካይ ማነው ..?”
ጋዲሳ:- ጠንካራ ተከላካዮች ነባርም ይሁን አዲሶቹ በጣም ይፈትናሉ ለጥያቄህ መልስ ግን ካልከኝ አስቻለሁ ታመነ ነው እሱ ጠንካራ ተከላካይ ነው ለየትኛውም አጥቂ ፈታኝ የሆነ ተጨዋች ነው አንድ ለአንድ ለማለፍም ከበድ ይላል..
ሊግ:- ረጅም ጊዜ እየተጫወትክ ለመገኘትህ ምክንያቱ ምንድነው ..?
ጋዲሳ:- ጠንካራ ያደረገኝ ትልቁ ምክንያት ልምምዱን ጠንክሬ መስራቴ ነው … የፈለገ ጎበዝ ሁን አቅም ይኑርህ ወይም ዲሲፕሊን አክባሪ ሁን ልምምድ ማድረግ በተገቢው መንገድም ማረፍ ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ… ጠንካራ ልምምድ ያደረገ ተጨዋች ያለውን በሙሉ ሜዳ ላይ እንዲሰጥ ያደርገዋል… ስለኔ ላልከው ጠንካራ የሆንኩት በልምምዱ ነው፡፡ ልምምድ እወዳለሁ አሞኝ ቢሆን እንኳ ሰአት አሳልፌ አልሄድም እናም ልምምድ ራስን መመልከቻ ከቡድን ጓደኞችህ ያለህን ልዩነት የምታይበት ነውና ልምምድ ላይ ቀልድ የለም ..
ሊግ:– በሽንፈታችሁ በይበልጠ የተናደድከው የትኛው ሽንፈት ላይ ነው..?
ጋዲሳ:- ማሸነፍ እየቻልን ብዙ ነጥብ የጣልንባቸው ጨዋታዎች አሉ ለምሳሌ አዳማ ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስንጫወት ብዙ የግብ ዕድል ፈጥረንና ብዙ ኳስ ስተን 1ለ0 የተሸነፍንበት ጨዋታ ከፋሲል ከነማ ጋር ባለቀ ሰዓት ገብቶብን የተሸነፍነው ጨዋታ ያበሳጫል አይረሳም ጥሩ ሆነን ፈትነናቸው የተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች ያበሳጫሉ አልረአሳቸውም፡፡
ሊግ:- ከፈረሰኞቹ ጋር የነበረህ ቆይታ ትውስታው ግን አለ..?
ጋዲሳ:- አዎ አይረሳም ፈጽሞ ልረሳው አልችልም ከቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ብዙ ትዝታዎች አሉኝ፡፡ በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሰላፊነቴ ዘመን ጨዋታው ሊካሄድ አካባቢ የየበረው የስታዲየሙ ድባብ በተለይ ዲ ኤስ ቲቪ ከመምጣቱ በፊት የነበረው የደጋፊዎቹ ድጋፍና ድባቡ የሚገርም ነበር፡፡ የሚገርምህ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎቹ ተጨዋቾች አዲስ አበባ ስታዲየም ናፍቆናል የሚገርም ትውስታ ነው ያለኝ..
ሊግ:- ቀጣይ ፕላንህ ምንድነው..? ኳስስ ስታቆም በእግርኳሱ አካቢ መቆየት ታስባለህ..?
ጋዲሳ:- አሁን መጫወት ብቻ ነው የምፈልገው የማልመው 10 አመት 8 አመት ወይም 3 አመት የሚወስነው እድሜዬና ጤናዬ ነው ጥሩ ልምምድ ሰርቼ መጫወት እስከቻልኩ ድረስ የምጫወትበት ጊዜዬን አልገድበውም ..ረጅም አመት እንደመጫወቴ ሱስ ሆኖብኛል የማቆም ከሆነ ኦንኳን መራቅ አልፈልግም የጤና ቡድን ይኖራል የአካባቢ ቡድን አለ እዚያም ገብቶ መጫወቴ አይቀርም… እግርኳስን ማቆም ከባድ ውሳኔ ይሆናል…
ሊግ:- ቢሆን ደስ የሚልህ ምንድነው ..?
ጋዲሳ:- ቡድኖች ከክፍያ ጋር ያለውን ችግር አስወግደው ትክክለኛ መስመር ውስጥ መግባት አለባቸው…
ለሀገር ውለታ የሰሩ ተጨዋቾች ክብር መሰጠት አለበት ..ያልተለመደ ነገር ነው እንዲያውም በዚህ አመት የተሻለ ነገር ታይቷል.. እነ ሽመልስ በክብር የተሸኙበት መንገድ ደስ የሚል ነው፡፡ ይሄ መለመድ አለበት.. አገርን ላገለገሉ ተጨዋቾች የሚሰጠው ክብር መጠናከር አለበት፡፡
ሊግ:- የክለቦች የበጀት ገደብንስ እንዴት አገኘኧው..? ተቀበልከው..?
ጋዲሳ:- በፍጹም ምንም ሊገባኝ አልቻለም ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለሁም ይሄ ሃሳብ መጥቷል.. ነጻ ገበያ መሆኑን ነው የማውቀው …የትኛውም ክለብ የፈለገውን መግዛት ያልፈለገውን መሸጥ አለም ላይ እየተሰራበት ያለ ነገር ነው፡፡ እኛ ሀገር ግን እንዴት እንዳሰቡት አላውቅም፡፡
ሊግ:- የተጨዋች ደመወዝን አልገደብንም በጀቱን ነው የገደብነው አብቃቅቶ እንደብቃታቸው የፈለገውን መክፈል ይችላል ነው ያልነው ይላሉ… ይሄስ…?
ጋዲሳ:- ጥናት ተደርጎ ጊዜ ወስደው መክረውበት ማንንም የማይጎዳ ነው ብለው ሊያወጡት ይችላሉ ግን በጀትም ቢሆን ያለውን አይቶ መመደብ ያለበት ቡድኑ ነው በህግ ሊከለከል አይገባም ብዬ አስባለሁ። ክለቡን አመራሩ እንጂ ሌላው አካል መግባቱ አልተመቸኝም ከፈለገ 100 ሚሊዮን ወይም 200 ሚሊዮን ማለት ይችላል ይሄን በገደብ ማገድ ልክ ነው ብዬ አላምንም ነጻ ገበያ ነው በፊት ቅዲስ ጊዮርጊስ እያለሁ የክለቡ የቦርድ ፕሬዝዳንት ጋሽ አብነቶ ገ/መስቀልም ተቃውመው ምላሽ ሰጥተውበት እንደነበር አልረሳውም፡፡
ሊግ:– ያኔኮ ደመወዙ ከ50 ሺህ ብር መብለጥ የለበትም ስለሚል ነው የአሁኑኮ በጀት ነው የገደበው ..?
ጋዲሳ:– ምንሞ ቢሆንም የደመወዝን ቁጥር ይሁን የበጀት መጠኑን ሌላ አካል መወሰኑን አልቀበለውም።
ሊግ:- ሁሉም ተጨዋች ቋሚ 11 ይሁን ተቀያሪ ወይም ብዙ ጊዜም የማይገባ እኩል 400 300 ወይም 200 ሺህ ብር ደመወዝ መጠየቁ በናንተ በኩል ያለና እንደ ክፍተት የሚታይ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ ..ምን ምላሽ አለህ…?
ጋዲሳ:– ይሄን እቀበላለሁ.. ግን የተጨማለቀ ነገር ስላለ ይመስለኛል እንደተባለው ልዩነቱን የሚቆጣጠር ወይም የሚገመግሞ ለየክለቡ የተጨዋችን ደረጃ በትክክል የሚያወጣ መኖር አለበት ..ያ ግን የተጨዋችን ክፍያ ለመከልከል መዋል የለበትም፡፡ ቋሚ ሆኜ ጨርሼ በአመት ሁለት ጨዋታ ያልተጫወተ ከኔም በላይ ሲወስድ ማየት ያበሳጫል ያ ልክ አይደለም ክለቦቹ የሚፈልጓቸውን ተጨዋች ደረጃ አውጥተው መነጋገር አለባቸው ትክክለኛ አሰራር ይሄ ይመስለኛል። ማንኛውም ተጨዋች ተገቢ ክፍያ ማግኘት አለበት መጠቀምም አለበት ምቀኝነት አይደለም የተሻለ ተጨዋች ገበያው ላይ የተሻለ ሊከፈለው ይገባል የሚለው አያከራክርም እንደየደረጃው መስተካከያ ቢደረግ አሪፍ ነው ባይ ነኝ፡፡
ሊግ:- ወደ ዋሊያዎቹ የመመለስ ፍላጎትና አቅም አለህ..?
ጋዲሳ:- ዋናው ጥንካሬ ጥሩ አቋምና ፍላጎት ወሳኝ ናቸው ጠንክሬ እየሰራሁ ስለሆነ የመመለስ ዕድል አለኝ ተስፋ አልቆርጥም ከ2 አመት ወዲህ ነው በዋሊያዎቹ ማሊያ ያልታየሁት ጠንክሬ ሰርቼ እመለሳለሁ ሀገሬን የማገልገል ፍላጎቱ አሁንም አለኝ፡፡
ሊግ:- ጠንካራ ነኝ ብለህ ታምናለህ…?
ጋዲሳ:– ሁሌም ጠንካራ ነኝ ብዬ ነው የማምነው ..በራሴ ስለማምን የሆነ ሰአት ዋሊያዎቹ ስብስብ ውስጥ እከሰታለሁ፡፡
ሊግ:– ቲየሪ ኦነሪ ብለን አርሴን ቬንገር ካልን ጋዲሳ መብራቴንስ ብለን ማንን እንጥራ..?
ጋዲሳ:– /ሳቅ/ ሲጀመር ጤናዬን ጠብቆ በሰላም ያደረሰኝን ፈጣሪን አመሰግናለሁ …በእስካሁኑ ቆይታዬ ከጅማሮ እስከአሁን ላለሁበት ደረጃ ያበቁኝን ባለሙያዎች በሙሉ ከልቤ አመሰግናለሁ። ጥያቄውን ለመመለስ ግን ኦነሪ ብለን ቬንገር ካልን ጋዲሳ ብለን ውበቱ አባተን እንጠራለን… አሰልጣኝ ውበቱ በእግርኳስም በእውቀቱም የተወሰነ ግንዛቤ እንዲኖረኝ አድርጓል በዚህ አጋጣሚ ደግሜ አመሰግነዋለሁ…
ሊግ:– ለኦሎምፒኩ ፍልሚያ ፓሪስ ስለሚገኙት የኦሎምፒክ ቡድናችን ምን ትመኛለህ ..?
ጋዲሳ:– የአውሮፓ ዋንጫን ቁጭ ብዬ አይቻለሀ.. ይሄ ደግሞ እኔም ሀገሬም የምንወከልበት በመሆኑ አንድም ሩጫ አያመልጠኝም ቁጭ ብዬ የምደግፋቸው.. እነሱም አሳፍረውን አያውቁም አትሌቶቻችን ሁሌ እንዳኮሩን ነው አሁንም ያኮሩናል መልካም እድል እመኛለሁ፡፡
ሊግ:- የአውሮፓ ዋንጫ በደንብ አይተሃል የማን ደጋፊ ነበርክ..?
ጋዲሳ:– የክርስቲያኖ ሮናልዶና የፖርቱጋል ደጋፊ ነበርኩ አሁንም ነኝ አንድ ጥሩ ቦታ ደርሰው ውጤታማ ሆነው ማየት እፈልጋለሁ የሮናልዶ ወዳጅ ነኝ/ሳቅ/
ሊግ:-, አመሰግናለሁ በኔ በኩል ጨረስኩ ቀረ የምትለው ካለ የመጨረሻ ዕድል ልስጥህ..?
ጋዲሳ:- የመጀመሪያ ምስጋናዬ ለፈጣሪዬ ይሁን ሲቀጥል አስታውሰኧኝ የት ነው ብለህ ፈልገህ ቃለምልልስ በማድረጋችን አንተንና ሊግን ከልብ አመሰግናለሁ… ባለቤቴንና ቤተሰቦቼን ፣ ከልጅነት እስካሁን የረዱኝን ከጎኔ የነበሩትን አሁን ላለሁበት ስላበቁኝ ሁሉንም ከልቤ አመሰግናለሁ …መላውን የስፖርት ቤተሰብ አመሰግናለሁ …ለወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ ቢጨነቁም ቡድኑ ከመውረድ ተርፏልና እንኳን ደስ አላችሁ በቀጣይ አመት ጥሩ የተባለ የተሻለ ቡድን ሰርተው እንደሚመጡ ተስፋ አደርጋለሁ .. ሌላው ደግሞ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለኝ ውል በመጠናቀቁ ከውል ውጪ ነኝ የሚፈልጉኝ ክለቦች ካሉ በሬ ክፍት ነው ደውለው ማናገር ይችላሉ ..የማንን ማሊያ እንደማደርግ አላውቅም ለፈለጉኝ ለውይይት በሬ ክፍት መሆኑን ደግሜ መናገር እወዳለሁ……አመሰግናለሁ፡፡