በተጨዋችነት ዘመኑ ለሀዋሳ ከተማ፣ ለኤልፓ፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ለሲዳማ ቡና ተጫውቶ አሳልፏል… አግሬሲቭ መሆኑን ከሰርጂዮ ራሞስ ተምሬያለሁ ይላል… አሁን ደግሞ ለሀድያ ሆሳዕና እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን ጥሩ የውድድር አመት ባናሳልፍም እንሻሻላለን፡፡ ወደ ድል አድራጊነት እንመለሳለን ሲልም በድፍረት ይናገራል… የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቹ ግርማ በቀለ…. ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቆይታ ያደረገው ተጨዋቹ ስለ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ፣ ስለትዳሩና ሶስተኛ ልጁ፣ ስለ ሊጉ ፉክክር፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢት.ቡና ጠይቀውት እንቢ ስለማለቱ፣ ከሲዳማ ቡና ጋር ስላላቸው ቀጣይ ጨዋታና ሌሎች ጉዳዮች ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል…
ሊግ:- ካንተ ጋር ቃለምልልስ ሳደርግ የመጀመሪያዬ ነው… ለሰጠኧኝ ፍቃድ አመሰግናለሁ…. በጨዋታ ዘመንህ ሃትሪክ ሰርተህ ታውቃለህ..?
ግርማ:- አይ አላውቅም….
ሊግ:- ቤትህ ውስጥ ግን ሰርተሃል..?
ግርማ:- /ሳቅ በሳቅ/ ሳልፈልግ አሳከኝ /ሳቅ በሳቅ/
ሊግ:- እንኳን ደስ አለህ…
ግርማ:- /ሳቅ በሳቅ/ አመሰግናለሁ… በርግጥ የቤቱማ ሀትሪክ የግድ ነው፡፡ ከሰሞኑ ሶስተኛ ልጄ ይቺን አለም ተቀላቅሏል… /ሀትሪክ…!/ የመጀመሪያ ልጄ ኢሚሊያ ሁለተኛው ልጄ “አለን” ፈጣሪ አለን ተናገረን ማለት ነው፡፡ ሶስተኛው ልዑል ይባላል …ሀትሪክ የሰራሁበት…/ሳቅ/
ሊግ:- 3ለ2 እየመራህ ነው…. አቻ የመሆን ዕቅድ የለም ..?
ግርማ:- /ሳቅ/ አንተ እንዳልከው 3ለ2 እየመራሁ ነው …. ውዷ ባለቤቴ ትፈልጋለች፡፡ ግን ያሉንን በሚገባው እናሳድግ ብዬ እየተወያየን ነው፡፡ የኖርኩትን ኑሮን እንዲደግሙት አልፈልግም… ያው ባል መሪ የቤት ራስ አይደል ..? እየመራሁ እገኛለሁ… ልጅ አንድም ይሁን ሶስት በራሱ ደስታ ይፈጥራል ህይወት ይቀይራል መኖር የጀመርኩት ያኔ ነው፡፡ ባንተ መኖር ውስጥ ሌሎችን ማኖር ስትችል ነው መኖር ጀመርኩ የምትለው የምትጠነቀቀው…
ሊግ:- ባለቤትህን አስተዋውቀን..?
ግርማ:- ከባለቤቴ ጋር የተገናኘነው 12ኛ ክፍል እያለን ነው … እኔ ኳስ ውስጥ ስለነበርኩ እሷን አስተምሬ ዶክትሬቷን ሰርታ አሁን ባለቤቴ ዶክተር ሆናለች፡፡ እኔ ጋር ሆና ነው የጨረሰችው …ውዷ ባለቤቴ ዶ/ር ሰላማዊት ዳዳ ትባላለች….
ሊግ:- ልጅ ስወልድ ተለወጥኩ እያልክ ነው ..?
ግርማ:- በፊት በፊት አስቸጋሪ ነበርኩ፡፡ ልጅ ስወልድ እንዴት እንደተቀየርኩ አላውቅም፡፡ ህይወቴ አኗኗሬ ቅይር አለ.. ሳንቲም ላይ ሰውና አንበሳ አለ አይደል..? በቃ ልጅ ስወልድ እንደዚያ ተቀየርኩ፡፡ በባህሪይ ልውጥ አልኩ ይገርመኛል…
ሊግ:- ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንመለስና ምርጥ የምትለው ቡድን ገጥሞሃል …?
ግርማ:- በዚህ ሰአት መገመት ይከብዳል…. ለመገመት እንኳን የተወሰነ ጊዜ ሊጉ ቢቀጥል ጥሩ ነበር ሁሉም ባለው ጉልበት ስለመጣ ማወቅ አይቻልም፡፡ ይሄ ጥሩ ነው ጥሩ አይደለም ለማለት ጊዜው ገና ይመስለኛል… አሁን ላይ ጥሩ ነው አይደለም ማለት ይከብዳል፡፡
ሊግ:- በቀይ ካርድ ወጥተህ የዳኛው ውሳኔ ልክ አይደለም ብለህ ያልተቀበልከው ውሳኔ አለ..?
ግርማ:– የለም …በታሪኬ በቀይ ካርድ የወጣሁት ሁለቴ ነው፡፡ አምና በሀድያ ተሰላፊነቴና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አዳማ ከተማን ይዞ የሀዋሳ ከተማ ተጨዋች እያለሁ ስንጫወት ያየሁት ቀይ ካርድ ብቻ ነው…. በዚህም አሰልጣኝ አሸናፊ ክሮስ የተደረገ ኳስን የመጠቀም አቅሜ ጥሩ ስለነበር ያዙት ያዙት ሲል ተጨዋቹን ስራህ ነው ማርክ ማድረግ ትችላለህ፡፡ ግን አትጎትተኝ ሳንነካካ ስራችንን እንስራ ስለው አልሰማኝም፡፡ በተፈጠረ ንክኪና ግፊያ ነው፡፡ በቀይ ካርድ የወጣሁት ሁለቱም ቀይ ካርድ ያሰጠኛል፡፡
ሊግ:– የአምስት ክለቦችን ማሊያ አድርገሃል ….ምርጡ ጊዜህ የትኛው ነው..?
ግርማ:– ሲዳማ ቡና ነዋ… በ2011 ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሆነን ያጠናቀቅንበት ጊዜ ምርጡ ጊዜ ነበር፡፡
ሊግ:- ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠይቀውህ እንቢ ማለትህን መረጃ አግኝቻለሁ …እውነት ነው ..?
ግርማ:- አዎ …. ኢትዮጵያ ቡና ብዙ ጊዜ ጠይቆኛል… በ2009 ቡናን እንቢ ብዬ ነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገባሁት… ኤልፓም ስገባ ቡናን እነንቢ ብዬ ነው… ኤልፓም ሆኜ ዕድሉ ነበረኝ አልፈለኩም እንጂ፡፡ ፋይናንሺያል ደካማ ስትሆን የተሻለ ክለብ ጥሩ የሚከፍል ብለህ ችግርህን ለማስወገድ ትሞክራለህ ግን ቡና መግባት ፈራሁ፡፡ ካለኝ ባህሪይ አንጻር አንዱ ቢናገረኝ አጸፋ መልስ ብሰጥ ነገሮች ሊበላሹ ይችላሉ ብዬ እንቢ አልኩ፡፡ በርግጥ እዚያ ብገባ ታዋቂ ሊያደርገኝ ይችላል፡፡ በተቃራኒው ቢገጥመኝ ሊያጠፋኝ ይችላል ብዬ አልተቀበልኩትም። ቅዱስ ጊዮርጊስም እንዲሁ ሁለት ጊዜ ጠይቆኝ ከሀዋሳ ምን የተሻለ ነገር አላችሁ ብዬ መልሼያለሁ… ደደቢትና ሌሎች ክለቦችም ጠይቀውኛል፡፡ የትኞቹም ጋር ባለመግባቴ አልጸጸትም። ሀዋሳን ግን ያደኩበት ቤት ስለነበር ስለምወደው ቤተሰቦቼም ስላሉ ጥሩ ስሜት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ከሀዋሳ የወጣሁበት መንገድ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ስለነበር ውስጤ ጥላቻን ፈጠረ…. ሆድ ይፍጀው…
ሊግ:- ግልጽና የፊት ለፊት ሰው ነበርክኮ….?
ግርማ:- አዎ …ግልጽ ሰው ስለነበርኩ የሚመስለኝን የማየውን ፊት ለፊት በግልጽነት ነበር የምናገረው፡፡ ትክክል ነኝም ብዬ አምን ነበር፡፡ ለካ ግን ህይወት እንዲህ አይደለም… ከዚያ በኋላ ከማውራት ዝምታን እመርጣለሁ ምንም ጉዳይ ላይ አስተያየት አልሰጥም፡፡ ሜዳ ላይ ስሜታዊ ልሆን እችል ይሆናል እንጂ ዝምታን መርጫለሁ፡፡ የምናገረው እየተተረጎመ አይቻለሁ ህይወት አስተምራኛለች… የኔ ዝም ማለት ለቤተሰቤ ከጠቀመ ለምን ዝም አልልም ..? ዝምታን የመሰለ ነገር የለም..
ሊግ:- በተጨዋችነት ዘመንህ እስካሁን አላሳካሁትም የምትለው ነገር አለ…?
ግርማ:- አዎ አለ… እስካሁን የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን አልሆንኩም መሆን እፈልጋለሁ… እንደውም በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው ብዙዎች ሀዋሳ እያለሁ የሊጉ ሻምፒዮን እንደሆንኩ ነው የሚያስቡት፡፡ ግን ሻምፒዮን ሆኜ አላውቅም… ሲዳማ ቡና እያለን ከጫፍ የደረስንበት ጊዜና ስብስብ የተለየ ነበር …ያኔ የነበርነው ተጨዋቾች አሁን ድረስ እንደ ቤተሰብ ነው እንደታላቅና ታናሽ ተፈላልገን እንገናኛለን….. ፍቅራችን ልዩ ነው
ሊግ:– የእግር ኳስ ስኬት ዋንጫ ማግኘት ነው የሚሉ አሉ ..አንተስ..?
ግርማ:– በፍጹም … እንደዚያም አላስብም በተጨዋችነት የኖርኩበት ጊዜ ራሱ ስኬት ነው፡፡ እወደዋለሁ በነገራችን የኛ ሀገር ዋንጫ እንዴት ነው…? ሚዛናዊ ነው ?
ትክክለኛ ነው ብለህ ታስባለህ..? የዋንጫ ድሎቹ በብዛት ሚዛናዊ አይደለም.. በሜዳህና ከሜዳህ ውጪ ስትጫወት የትኛው ሜዳ ላይ ነጥብ ጥለህ እንደምትመጣ የትኛው ሜዳ ላይ እንደምታሸንፍ ታውቀዋለህ….ያ አያጓጓኝም /ሳቅ/
ሊግ:- ሀድያ ሆሳዕና 2 ሽንፈት 3 አቻ … በ3 ነጥብ 13ኛ ግርማ ያለበትን ቡድን ይመጥናል..?
ግርማ:- ኧረ በፍጹም አይመጥንም …ልክ አልነበርንም፡፡ ግን ይመለሳል ይስተካከላል… እኛ ሀገር ላይ ስነ ልቡና ያለው የተሻለ የተንቀሳቀሰ በወቅታዊ አቋም ነጥብ ይይዛል እንዲህ ያለመሆን ክፍተት ነው የገጠመን፡፡ በርግጠኝነት ያለንበት ደረጃ አይመጥነንም መመለሳችን ግን አይቀርም፡፡
ሊግ:- ቀጣይ ጨዋታ ከሲዳማ ቡና ጋር ነው …ምን ውጤት ይጠበቅ…?
ግርማ:- እናሸንፋለን ያለጥርጥር 100 ፐርሰንት ድሉ የኛ ነው… አምና የመጀመሪያ 3 ነጥብ ያገኘነው በሲዳማ ቡና ነው፡፡ ዘንድሮም 3 ነጥቡን ማግኘት በሲዳማ ቡና ይጀመራል፡፡
ሊግ:- አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ለቋል …ጥሩ ጊዜ ነበራችሁ..?
ግርማ:- አዎ ምርጥ ጊዜ ነበረን… አሰልጣኙ በራሱ ምክንያት ከክለቡ ጋር ተወያይቶ ለቀቀ እንጂ አሰልጣኝ ዮሀንስ ከተጨዋቾች ጋር ጥሩ ጊዜ ነበረው…
ሊግ:- በቦታህ ምርጡ ማነው …?
ግርማ:- በተከላካይ ቦታ በሀገር ውስጥ ዳግም ንጉሴን እመርጣለሁ፡፡ ሌላም ካየን ምናልባት አሉላ ግርማ… ከውጪ ሰርጂዮ ራሞስ ምርጫዬ ነው፡፡ ቀይካርዱን አልኮረጅኩም እንጂ ብዙ አጨዋወቴ ከርሱ ጋር ይሄዳል እሱ መሪ ነው ብዙ ነገር ከእሱ ወስጃለሁ….
ሊግ:- የመጨረሻ የምታመሰግነው ካለ….?
ግርማ:- የመጀመሪያ ምስጋናዬ ለፈጣሪዬ ይሁን …..የምወዳት ውዷ እናቴንም በጣም አመሰግናለሁ.. ውዷ ባለቤቴንና ልጆቼን ከልብ አመሰግናለሁ… በተጨዋችነት ዘመኔ አንድ ነገር የጨመሩልኝ አሰልጣኞቼን በተለይ ለዚህ ደረጃ መድረሴ ትልቁን ሚና የተወጣው አሁን የሀዋሳ ከተማ ም/ል አሰልጣኝ የሆነውን ብርሃኑ ወርቁ /ፈየራ/ን በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ… ጓደኞቼን፣ የስፖርት ቤተሰቡን፣ ደጋፊዎችን እናንተንም በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ…