የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። የአራት ሳምንት ጨዋታ በቀረው የአመቱ መርሃግብር ለዋንጫና ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ አጓጊ ሆኗል… ከዚህ ጎን ፌዴሬሽኑና ሊግ ኩባንያው በጋራ ከ2017 ጀምረሮ የሚተገበር አዲስ የፋይናንስ ስርዓት አጸድቀው ወደ ትግበራ ሊገቡ ነው በዚህና ሊጉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከማድረግ አንጻር ከባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል ..? በማለት የሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ከአቶ ክፍሌ ሰይፈ ጋር ቃለምልልስ አድርጓልና ተከታተሉት….
ሊግ:- የ2016 የውድድር መርሃግብር በታቀደለት መሰረት ሄዷል ማለት ይቻላል..?
ክፍሌ:-የዘንድሮው የተሻለ አካሄድ ይመስለኛል ውድድሩም የተቆራረጠ አልነበረም የተሻለ ነው ከውሳኔ ጋር ተያይዞ የሚያጨቃጭቅ ነገር ብዙም አልነበረም እስከ 26ኛ ሳምንት ድረሰ ያለው ጥሩ የሚባል ነው። ከተመልካች ጋር ተያይዞ ደግሞ ስናይ ድሬዳዋና አዳማም ጥሩ ነበር ሀዋሳ ላይ ደግሞ በተለይ የደቡብ ክለቦች ጨዋታ ሲኖራቸው ተመልካቹ እየገባ ነው… እንደ አመት አልገመገምነውም ግን የሚረብሽና የሚያስቸግር የውድድር አመት ግን አልነበረም ከነበሩት አመታቶች የዘንድሮው የተሻለ ነው ማለት ይቻላል።
ሊግ:- ከዳኝነት ከፍትህ ጋር ሲታይስ …ለውጡ ምን ይመስላል..?
ክፍሌ:- ዳኝነትን በተመለከተ በቀጥታ እኛ ጋር አይመጣም …ለዳኛ ኮሚቴ ነው የሚላከው … በዚህ አመት ከሌላው ጊዜ አንጻር ሲታይ ወጣት ዳኞች እየመጡ ነው ልምድ እንደሌላቸውም እየታየ ነው በዚያው መጠን ወጣቶችም ሆነው ጥሩ ዳኝነት እየታየም ነው። ከነበሩት አመታቶች አንጻር አዳዲስ ዳኞች ስለመጡ የተወሰነ ክፍተቶች ነበሩ ግን እየተለመደ ሲመጣ ጥሩ የሆኑ ዳኝነት እየታየም ነው የቅሬታው ጉዳይ ኮሚቴው በሪፖርት ሲያሳውቀን የምንረዳው ይሆናል ቅሬታዎች እንዳሉ ግን መረጃዎች አሉን።
ሊግ:- ከቀሪ አራቱ ሳምንታት አንጻርስ የዳኞች ምደባ ለውጥ ነበረው..?
ክፍሌ:- ከኮሚቴው ጋር ተነጋግረናል ስለእያንዳንዱ ጨዋታ አውርተናል። ለእያንዳንዱ ጨዋታ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበናል…የሊጉ ፍጻሜ ያለችግር ያለውዝግብ ጥሩ በሆነ አጨራረሰ እንዲፈጸም እንፈልጋለን። ከዚህ በፊት የነበሩት የሊጉ አጨራረስ የማያምሩና ለእግር ኳሱ መጥፎ አሻራ የጣለ በመሆኑ ደስተኛ አልነበርንም ይሄ እንዳይደገም ከኢንተለጀንሲ ጋር የሚሰራ አንድ ቴክኒካል ግሩፕ አዋቅረናል ለእግርኳሱ መጥፎ አሻራ እንደጣለው ያለፈው የሊጉ አጨራረስ ዘንድሮ እንዲደገም አንሻም ዳኞችን በተመለከተ ከዳኛ ክሚቴ ጋር እየሰራን ነው። ዋንጫ አሸናፊና ወራጁ ባለመታወቁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ተነጋግረናል። ለ27ኛው ሳምንት የተመደቡት ዳኞች ዝርዝር ደርሶናል የተሻሉ ዳኞች መመደባቸውን አይተናል።
ሊግ:- በክፍያ ምክንያት ሆቴሎች ሰው ወይም ሰርቪስ የመያዛቸው ነገር ለሊጉ መጥፎ ምልክት አይሆንም..?
ክፍሌ:- የክለቦች የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ የተዘጋጀውም ይህን መሰል ድርጊት ለማስቆም ነው በእውነት ፈጽም አግባብነት የጎደለው ተግባር ነው መቆም አለበት …ይሄ ሊጉን ያወሬደዋል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ከተቋቋመ ጀምሮ ያልተቀየረ ድርጊት ነው አዲሱ የፋይናንስ መመሪያ በደንብ ከተተገበረ ድርጊቱ እየቀነሰ ይመጣል ብለን እናምናለን ድርጊቱ ግን እጅግ አሳፋሪ ነው። ብዙ ማህበረሰብ የሚደግፈው አንድ ትልቅ ተቋም በአግባቡ ባለው ሂሳብ ፕላን አድርጎ ክፍያዎችን በጊዜው እንዴት መክፈል ያቅተዋል..? ይሄ መወገድ አለበት።
ሊግ:- አዲሱ ህግ ክለቦችን አግባብቷል ማለት ይቻላል…?
ክፍሌ:- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አባላትን አንድ የሚያደርገው የማህበሩ መመስረቻ፣ የውድድር ደንቡና የመተዳደሪና ደንቡ ብቻ ነው አሁን ደግሞ የፋይናንስ አስተዳደር ደንብን ጨምረንበታል ይሄ አንድ ፓኬጅ ነው እግርኳሳዊ የታክቲክና የቴክኒክ ደንቦች ላይ መሠረት ላይ እንዲያተኩሩ ፓኬጅ እያዘጋጀን ነው ይቀጥላል…እየቆየ እያየን ችግሮችን እየፈታን ክለቦችን አንድ የሚያደርጋቸው መመሪያ ላይ እናተኩራለን አሁን በክለብ ላይሰንሲንግ ይህን አሟላ ማለቱ ተመሳሳይ እንዲሆኑ በስታንዳርድ መሰረት እንዲመሩ ታስቦ ነው። እኛም ይህን የፋይናንስ መመሪያ ሶስተኛው ሰነዳችን ነው። እንደ አያያዛችን በጣም ይስተካከላል ለውጥ አለው ብለን እናምናለን።
ሊግ:- ባለድርሻ አካላት ሁሉ ተወያይተውበታል ግንዛቤ ሰጥታችኋል..?
ክፍሌ:- ከአንድ ወገን ውጪ ሌሎቹ የሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ አስጨብጠናል…. አሁን ቀረ የምንለው በጀቱን የሚለቁት ከንቲባዎችና አመራሮች ናቸው በሀገሪቱ ፓርላማ ውስጥ ስፖርትን የሚመለከተው አካል ንም በቀጣይ ግንዛቤ እንሰጣለን ዋናው ግንዛቤው ነው ይህን ደግሞ እያደረግን ነው። በተጨማሪ የ16ቱም ክለቦች የፋይናንስ ዲፓርትመንቶች እየገመገምን እያሰለጥን የምንከታተል ከሆነ የተሻለ ስርዓት ይኖረዋል ብለን እናምናለን የውድድር ደንቡ በየጊዜው እየተሰራበት እየተሻሻለ ጥሩ ሆኗል ይህም የፋይናንስ መመሪያ እንቅስቃሴ ስለሚኖረው እየተሻሻለ እየተስተካከለ እንደሚሄድ ርግጠኛ ነኝ። አንዳንድ የኛ ጉባኤ ሳይ የተቀመጠ የጽሁፍ መመሪያና ደንብ ሳይኖር በራሳችን ስንሰራ እንደነበር ነው ያየሁት … ባለሙያ ተብለው የተቀመጡት ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ከፈጸሙት ይሳካል ….ክለቦቹ ለዚህ ሰነድ በደንብ መዘጋጀት አለባቸው።
ሊግ:- ክለቦቹ ተቀብለውታል ርግጠኛ ናችሁ..?
ክፍሌ:- አንድም የተቃወመ የለም ሰነዱ ተልኮ ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቀርቧል አፈጻጸሙ ላይ ይተግበር እንጂ አንድም ክለብ አልተቃወመም
ሊግ:- ትላንት በነበረው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ሰነዱ ላይ ተፈራረማችሁ…? / ቃለምልልሱን የሰራነው ረቡዕ ዕለት ነው/
ክፍሌ:- አዎ ሁሉም ክለቦች ታርሞ ተስተካክሎ በውይይት በስሎና ዳብሮ የተዘጋጀውን የመጨረሻው ሰነድ ላይ ተስማምተው በፊርማቸው አጽድቀውታል … በቀጣይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ፈርመው ለ16ቱም ክለቦች ይላካል ስራው የኛ የክለቦቹና የፌዴሬሽን የጋራ ስራ ውጤት በመሆኑ ፕሬዝዳንቱ ፈርመው ለሚመለከታቸው ይላካል አሁን የመጨረሻው የተፈረመበት ሰነድ ማተሚያ ቤት ነው ያለው እንዳለቀ ለሁለም ይላካል ያለው እውነት ይሄ ነው።
ሊግ:- በዚህ የበጀት ውሳኔ 57 ሚሊዮን ብር ይሁን ሲባል ተጨዋቾች ድምጻችን አልተሰማም ብለው ቅሬታ ያነሳሉ ….ምላሻችሁ ምንድነው…?
ክፍሌ:- እንደሚታወቀው የማህበሩ አባላት ክለቦች ናቸው …ክለቦቹ መመሪያውን በተመለከተ ከተጨዋቾች ጋር ይወያያሉ ብለን እንጠብቃለን ደግሞም መወያየት አለባቸው። እንደ ማህበራቸው ግን ውይይት አድርገናል.. የተጨዋቾችና የአሰልጣኞች ማህበራት አባላት ሆነዎ አልተካተቱም እንጂ በቀረበው ሰነድ ላይ አወያይተን ስልጠና ሰጥተናል ጥሩ ግብአት ያገኘነውና ያስተካከልነውም አለ እንደ ፕሪሚየር ሊጉ ግን ባለ አክሲዮኖቹ ክለቦቹ ብቻ ናቸው ክለቦቹ ከሚያዋውሏቸው ተጨዋቾች ጋር መነጋገር ሰነዱ ላይ መወያየት አለባቸው ብለን እናምናለን። መታወቅ ያለበት የሊጉ ዓላማ ተጨዋቾቹ በውላቸው መሰረት ደመወዛቸውን በጊዜው እንዲከፈላቸው ማድረግ ነው። በነገራችን ላይ በ2016 ፈርሞ ውሉ በ2017 የሚያልቅ ተጨዋችን ውል አዲሱ መመሪያ አይመለከትም ውል ይከበራል ውሉ ሲታደስ በ2018 ግን በአዲሱ ሰነድ ይቀጥላል።
ሊግ:- ደንቡና መመሪያው ተጨዋችን አይነካም ሰሲባል ሰማው እውነት ነው አይነካም …?
ክፍሌ:- እውነት ነው አሁንም አዲሱ ደንብና መመሪያ የተጨዋቾችን ደመወዝ የሚመለከት አይደለም ዋናው አሰራሩ ይስተካከል ነው ክለቡ ከፈለገ 10 ሚሊዮን 20 ሚሊዮን ይክፈል አይመለከተንም ያለውን በጀት ግን ጠብቆ መሆን አለበት ነው የምንለው ተጨዋቾቹ ማወቅ ያለባቸው ውላቸውን ሲያድሱም ሆነ ሲፈራረሙ ክፍያውን በተመለከተ መደራደር የራሳቸው አቅም የሚወስው ነው የሚሆነው… ተጨዋቾቹ ሁለት ይሁን አራት አመት መዋዋል ይችላሉ የሚከፈላቸውን መጠን ላይ መደራደር ይችላሉ ሰነዱ ይህን አይከለክልም ዋናው ግን ውል አለ ይዋዋላሉ በውሉ መሰረት ለተጨዋቾች ለአሰልጣኙ ለምክትሎቹ ይከፈላል ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ ውል እኛ ጋር ይመጣል። ሲታደስም እንዲሁ….እኛም በመመሪያው መሰረት ይሰራሉ ወይ ለሚለው ክትትልና ድጋፍ እናደርጋለን።
ሊግ:- በጀት ገድቦ የተጨዋችን ደመወዝ ልክ አይነካም ማለት ይቻላል…?
ክፍሌ:– አይነካም … ይሄ ውሸት ነው …. ከዚህ በፊት አሰልጣኞች ለከበደ አበበን አምጣልኝ ብለው ነው የሚያስፈርሙት … በጀቱ ስንት ይሁን አይመለከታቸውም ነበር አሁን ግን አይሆንም። እንደፈለገ የሚሆነው ወጪና ቸገንዘብ ብክነት ይቀራል የግድ ይስተካከላል። የአሰልጣኞቹን አቅም የሚታይበት ነው ወጣት ላይ ትኩረት የሚያደርግ አሰልጣኝ 57 ሚሊዮን ብር ከበቂ በላይ ነው ይሄኮ ደግሞ ጣሪያው ነው ባለፉት አመታት አካሄዶችን በተመለከተ ጥናት ስናደርግ በወጣት ላይ የሚያተኩሩ ከ15- 21 ሚሊዮን ነው የጨረሱት … የአሰራር ክፍተት ያለበት ግን ሊቸገር ይችላል።
ሊግ:- ተገቢ የሆነ ጥናት መደረጉን የሚጠራጠሩ አሉ…እውነት በቂ ጥናት ተደርጓል…?
ክፍሌ:- ዝም ብለንማ አልሰራንም የአራት ሶስት አመታትን ወደ ኋላ ሄደን አጥንተን ነው.. ወጣቶች ላይ ትኩረት እንዲደረግ እንፈልጋለን …ሲኒየሮቹ መኖራቸውም ጥሩ መሆኑ ሳይዘነጋ…. አሰልጣኞቹ ወጣት ላይ እንዲያተኩሩ እንዲሰሩ መመሪያው ያስገድዳል … እገሌን አምጣልኝ እየተባለ ማስፈረም አሁን አይሰራም …አሰልጣኙ ስንት ልምድ ያለው ተጨዋች ልያዝ ስንት ወጣት ቡድኔ ውስጥ ባካትትና እነሱ ላይ ባተኩር ይሻላል የሚል ስራ እንዲሰራ ያደርገዋል አንድ ክለብ ሲመሰረት 25 ዋና 10 ወጣት 8 የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ይኖሩታል ተብሎ ተሰርቶ ነው በጀቱ የተመደበው …ይህን ባለው በጀት መምራትና መስራት ብዙ ማንበብ ብዙ መስራት ይጠይቃል … ኮቾቻችን ወደ ማናጀርነት ለመሄድ ደንቡ ያግዛቸዋል ብዬ አምናለሁ።
ሊግ:- የተጨዋቾች ደመወዝ ለአራት ወር አልተከፈለም ሲባል ሊግ ካምፓኒውን አያገባውም ..? ዝምታችሁ በዛ።
ክፍሌ:- በዚህ ደንብም ሆነ በነበረው የፌዴሬሽን እንጂ የአክሲዮን ማህበሩ ሃላፊነት አይደለም የፌዴሬሽኑ ስልጣን ነው …ወርሃዊ ደመወዝ ከፈለ አልከፈለ ብሎ የመቆጣጠር ስልጣን የፌዴሬሽኑ እንጂ የኛ አይደለም። ዘንድሮ እንደውም በጣም እየተከታተለ ነው ጥሩ ርምጃ ነው እኛ ግን ከ57 ሚሊዮን ብሩ እንዳያልፉ እንቆጣጠራለን በየወሩ ሪፖርት ያመጣሉ… ካልነው ካለፉ ርምጃ ይወሰዳል ካልተስተተካከሉ ደግሞ…
ሊግ:- ካልተስተካከሉ ርምጃ ይወሰዳል የሚለውኮ ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነው…?
ክፍሌ:- አዎ ርምጃው አይቀርም የመጀመሪያው ስህተት ከተገኘ 3 ፣ሚሊዮን ይከፍላሉ ለሁለተኛ ጊዜ ከተደገመ ግን ወደ ታችኛው ሊግ ይወርዳሉ…. ለእኛም ወርሃዊ ሪፖርት ይሰጡናል ያንን እንቆጣጠራለን ክለቡ ለተጨዋቹ በውሉ መሰረት ካልከፈለው ፌዴሬሽኑ በስልጣኑ ርምጃ ይወስዳል.. ዘንድሮ ጥሩ እርምጃ እየወሰደና እያስከፈለ ነው እኛና ፌዴሬሽኑ ከተጋገዝን ትልቅ ስራ ይሰራል ብለን እናምናለን።
ሊግ:- ርግጠኛ ኖት ሃላፊነቱ የናንተ አይደለም..?
ክፍሌ:- አዎ ለፌዴሬሽኑ መረጃ ከማቀበል ውጪ ርምጃ የመውሰዱ ስልጣኑ የለንም ከፌዴሬሽኑ ጋር ስንነጋገር የሚመለከተንና የማይመለከተን ነገር አለ ተጨዋች አሰልጣኝና ዳኛ ጋር ተያይዞ ሙሉ ስልጣኑ የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ብቻ ነው አበቃ ….
ሊግ:- የትግራይ ክልል ሶስቱ ክለቦች ይመለሱ ተብሎ ተወሰነ..?
ክፍሌ:- አዎ ንዲሳተፉ ተወስኗል… ነገር ግን ከአክሲዮኑ ጋር ተያይዞ ከሚመለከተው አካል ጋር እንዲወያይ ለቦርዱ የቤት ስራ ተሰጥቷል… ያው እንደሚታወቀው ክለቦቹ ባለ አክሲዮን አይደሉም … በፎርማቱ ም አይደሉም የገቡትና ካለው የፋይናንስ ስርዓት አንጻር እንዲወያዩ ለቦርዱ ሃላፊነት ተሰጥቷል ከፌዴሬሽኑም ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም ጋር ውይይት መደረጉ የግድ ነው እንደ ውሳኔ ግን ጠቅላላ ጉባኤው እንዲመለሱ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ አጽድቆታል።
ሊግ:- ጨረስኩ …በተለይ ከ27-30ኛ ሳምንት ድረስ ስለሚኖሩት የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ጨዊታዎች ለባለድርሻ አካላት የሚያስተላልፉት ማሳሰቢያ ካለ…?
ክፍሌ:- አመሰግናለሁ…ለቃለ ምልልሱ …..እንደ ማሳሰቢያ ግን የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስካሁኑ ማለትም ከ1-26ኛ ሳምንት የነበረው የተሳካ ነው ማለት ይቻላል ከ27-30ኛ ሳምንት ያለው እንዲሳካና በሰላም እንዲጠናቀቅ በተለይ ተጨዋቾች አሰልጣኞችና ዳኞች ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው… ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ እንዲኖራቸውም እንፈልጋለን። የእግር ኳሱ ዋና ባለቤት ተጨዋች አሰልጣኝ ከዚያ ዳኛ ነው እነኚህ ባለድርሻ አካላት ሙያቸውን አክብረው ክህሎትና አቅማቸውን ብቻ እንዲያሳዩ እንሻለን.. ከዚህ በፊት የተከሰተው አይነት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ዳግም እንዳይከሰት የበኩላቸውን መልካም እሳቤ እንዲተገብሩ መልዕክቴንና አደራዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ … በጀመርነው መንገድ እንዲያልቅ እመኛለሁ..
ኳሱ ጤነኛ ሆኖ ሲያድግ የመጀመሪያ ተጠቃሚ ተጨዋቹ ነውና ከመላቀቅ ጋር ተያይዞ ያለው አላስፈላጊ ድርጊት ዘንድሮ እንዳናይ የሶስቱም አካላት ትብብር ያስፈልጋል ለማለት እፈልጋለሁ…በእኛ በኩል የኢንተለጀንስ ስራ እየሰራን ነው ዋናው ግን ይሄ አይደለመም ሶስቱም የጠራኋቸው አካላት ያላቸው ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ ወሳኝ መሆኑ መታወቅ አለበት የመጨረሻዎቹ 32 ጨዋታዎች በሰላም በእግርኳሳዊ ዲሲፕሊን እንደሚጠናቀቅ ተስፋ አደረጋለሁ…..ዘንድሮ መላቀቅ እንዳይኖር የተጨዋቾች የአሰልጣኞችና የዳኞች ሙያቸውን ማክበር አለባቸው አመሰግናለሁ።