በአለምሰገድ ሰይፉ
ፕሪቶሪያ በአንድ ሳምንት ልዩነት ናፈቀቸኝ፣ የወንድምነት ጥግ ምን እንደሆነ ልብ ያልኩትበት ጎጆ፣ እንደ ልቤ እንዳሳደገችኝ እናቴ ቤት እንደፈለግኩ ማዕድ ከፍቼ ገበታ የምቋደስበትና ደግነቷ ወደር የሌለው የነሄሉ ቤት ውለታ ዘመን ላይሽራቸው በእኔ ውስጥ የዘላለም ማህተም ተክለዋል፡፡
ሳቂታዋ፣ ፍልቅልቋና ሁሌም ከኔ ጎን የማትነጠለው የአራት ዓመቷ ታዳጊ ሕፃን ሀሴት ፍቅር መስጠት ትችልበታለች፡፡ እውነትም አስተዳደጓ የቤተሰቦቿን የእንግዳ አቀባበል ምንነት በእርሷ ውስጥ ሰርፆ ገብቷል፡፡ ሀሴትዬ አሁን ሀገር አቋርጬ ወደ ኢትዮጵያ ብሻገርም ሁሌም ለእኔ የምትመግቢኝ ፍልቅልቁ ቀረቤታሽ መቼም እንዳልረሳሽ አድርጎኛል፡፡ አቢና ናሆሚም ቤታችሁን ብቻ ሳይሆን ቤተሰብነትን ስላጋራችሁኝ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው፡፡ ካቻ ፈጣሪ ቤትህንና ቤተሰብህን በቸርነቱ ይሙላው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካ በነበረኝ ቆይታ ሁሉ ፍቅር ለሰጣችሁኝ በአጠቃላይ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው እያልኩ ለዛሬ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያውያን ባህልና ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ከሆነው ከአቶ ይልማ ተስፋዬ ጋር የተደረገውን ቆይታ ላጋራችሁ፡-
ሊግ፡– የአንተ ስም ሲነሳ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር ያሳለፍከው ስኬታማ ጉዞ ነው የሚታወሰው እስቲ በዚህ ዙሪያ የተወሰነ ነገር በለኝ?
ይልማ ተስፋዬ፡– ከሐዋሳ ዱቄት ወደአዲስ አበባ ስመጣ ካናገሩኝ ክለቦች መካከል አንደኛው ኢትዮጵያ ቡና ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ነበር፡፡ እኔም ከበፊት ጀምሮ ለቅ/ጊዮርጊስ የመጫወት ፍላጎቴ ከፍተኛ ስለነበር ከአንድ ዓመት የአየር መንገድ ክለብ ቆይታዬ በኋላ ለተመሳሳይ ዓመት ቆይታ ለመድን ተጫውቼ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ መግባት ችያለሁ፡፡
ይህ ክለብ በሀገራችን አንጋፋና ታላቅ ክለብ ከመሆኑ አንፃር ለዚህ ቡድን መጫወት ትልቅ ክብር ነው፡፡ እዛ ከገባህ በኋላ ደግሞ የቡድኑ መንፈስ ማሸነፍና ማሸነፍ ብቻ ነው፡፡ እኔም በጨዋታ ሕይወቴ ማሸነፍን ነው የማስበው ሜዳ ስገባ፡፡ እናም ትልቅ ቲም ተቀላቀልኩ ብዬ ስላሰብኩ ለቅ/ጊዮርጊስ የምችለውን ነገር ሁሉ አድርጌ ከቡድኑ ጋር በርካታ ስኬታማ ድሎችን ማጣጣም በመቻሌ ሁሌም ኩራት ይሰማኛል፡፡ ምንም እንኳን የጨዋታ ዘመኔን በአግባቡ ሳልጠግብ ከኳሱ አለም በጊዜ ብሰናበትም በክለቡ የነበረኝን ጣፋጭ ጊዜ ግን መርሳት አልችልም፡፡
ሊግ፡– አሁን ካለፈ በኋላ በኳስ ሕይወትህ ጊዜ የሚቆጭህና የሚፀፅትህ ነገር አለ?
ይልማ ተስፋዬ፡– እኔ ሁሌም በአንድ ነገር አምናለሁ፡፡ ሁሉም ነገር የሚሆነው በፈጣሪ ፈቃድ ነው የሚል የጠነከረ እምነት አለኝ፡፡ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁንና ይኸው በሕይወት አለን፡፡ እውነቱን ለመናገር በኳስ ትልቅ ቦታ ላይ የመድረስ አላማ ነበረኝ፡፡ ነገር ግን እኔ እራሴን በአግባቡ አለመጠበቅና ለውጤት ከመጓጓት የተነሳ እየተጎዳሁም ጨዋታ በማድረጌ ኳስን ሳልጠግባት በጊዜ እናዳቆም አድርጎኛል፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን አልቆጭም፡፡ ምክንያቱም የምችለውንና የምፈልገውን ነገር አድርጌ ነው የማልፈው፡፡ ሁሌም ደግሞ የእውነት ሰርተህ ስታልፍ የልብህን መሻት አይቶ ፈጣሪ ያግዝሃል፡፡ ጥሎም አይጥልህም፡፡ እናም በኳስ ሕይወቴ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም፡፡ እኔ በዚህ አጋጣሚ አሁን የሚወጡ ታዳጊዎች ከእኔ ሕይወት መማር አለባቸው የምለው ነገር ቢኖር ኳስ እየጫወቱ መማር መቻል አለባቸው፡፡ ምክንያቱም አንድም ልክ እንደእኔ በጉዳት ያቆማሉ አሊያም ዕድሜ ገፍቶ አቅም ሲያንስ ታቆማለህ፡፡ እናም ተጨዋቾች ከዚህ መነሻነት በሁለት መልኩ መዘጋጀት አለባቸው እላለሁ፡፡ መማሩ እንዳለ ሆኖ እግረመንገዱን ቢዝነስን አብሮ መጀመር ያዋጣል፡፡ እኔም በኳስ ሕይወቴ የምችለውን ነገር አርጌ በማለፌ ፈጣሪ ጥሎ አልጣለኝም፡፡ እዚህ ከመጣሁ በኋላ ስደት አስቸጋሪ ቢሆንም ያንን የሕይወት ፈተና አልፌ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለሁት፡፡ ሕይወትን ማሸነፍ ከቻልኩ በኋላ ደግሞ ሁሌም ስፖርት ከውስጤ ስለማይወጣ እዚህ ሀገር የአሰልጣኘነት ኮርስ በመውሰድ አሁን አንተም መጥተህ ያየኸውን ፌዴሬሽን ከሙያ አጋሮቼ ጋር በመሆን ተቋሙን ትልቅ ደረጃ ላይ አድርሰነዋል፡፡ እናም ሕይወቴ ሙሉ ከስፖርት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ አሁን ብቻ አይደለም ወደፊትም ከምወደው ስፖርት የሚነጥለኝ ነገር አይኖርም፡፡
ሊግ፡– ይልማ ተስፋዬና የስደት ሕይወቱ እንዴት ይገለፃል?
ይልማ ተስፋዬ፡– ደቡብ አፍሪካን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት ጉዳት ደርሶብኝ ለሕክምና ከመጣሁ በኋላ ነው፡፡ አንዳንዴ ፈጣሪ የራሱ የሆነ መንገድ አለው፡፡ በጨዋታ ዘመኔ ጉዳት ደረሰብኝ፡፡ ያ ጉዳት ደግሞ ወደዚህ ሀገር እንድመጣ ምክንያት ሆነኝ፡፡ ኢትዮጵያ እያለን ከእኔ ጋር አብረው ዱቄት ይጫወቱ የነበሩ ጓደኞቼ እየመጡ ይጎበኙኝ ነበር፡፡ እነርሱ ቀደም ብለው ወደዚህ በመምጣታቸው ስደትን በአግባቡ ተላምደውት ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የማስበው ታክሜ ወደሀገሬ በመመለስ በድጋሚ ኳስ እንደምጫወት ነበር፡፡ ሕክምናው በአጥጋቢ ሁኔታ ቢጠናቀቅም ተመልሼ ኳስ መጫወት እንደማልችል ከዶክተሩ ስሰማ በጣም ግር አለኝ፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን እንደመጣሁ በዛው ለመቅረት አልፈለግኩም፡፡ ተመልሼ በመምጣት ከክለቡ ኃላፊዎች ጋር ስናወራ የአሰልጣኝነት ኮርስ እንሰጥሀለን የሚል ተስፋ ከሰጡኝ በኋላ በመሀል ለምን ሃሳባቸውን እንደቀየሩ አልገባኝም፡፡ እናም ከዚህ በኋላ አንድ ነገር መወሰን እንዳለብኝ ስለተረዳሁ ለሕክምና መጥቼ ያየኋት ሀገር ሳበችኝ፡፡ በዛ ላይ ቀደም ብዬ የማውቃቸው ጓደኞቼን ሳማክራቸው ምንም ችግር የለውም ሲሉኝ ለቼክአፕ መጥቼ እዛው ስደትን ተቀላቀልኩት፡፡
ከዚያም የአሁኗ ባለቤቴ ሄሉ ያን ጊዜም ጓደኛዬ ነበረች፡፡ ተነጋገርንና እሷም መጣች፡፡ አዲሱን ሕይወት ደቡብ አፍሪካ ላይ ጀመርነው፡፡ እርግጥ ስደት ከባድ ነው፡፡ ይሄን ሕይወት ለማሸነፍ ደግሞ መጠንከር የግድ ይላል፡፡ እዚህ ሀገር ደግሞ በብዛት የሚሰራው ንግድ በመሆኑ ከአሁን በፊት ሩዋንዳ ላይ ተጫውተን አሸንፈን ስንመለስ የተሰጠን የመሬት ሽልማት ስለነበር ያንን መሬት ሸጠን ከጓደኛዬ ጋር ወደዚህ መጣን፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ አንተ ራስህ ስላየኸው ምንም አልልም፡፡ ሶስት ልጆች አሉን፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ጥሩ ሕይወት እየኖርን ነው፡፡
ሊግ፡– በመጀመሪያ ደረጃ እኔን ለዚህ ታላቅ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን እንድመራ ስለመረጣችሁኝ በድጋሚ እያመሰገንኩ በሶስቱ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ስለተቋቋሙት ፕሮጀክቶች በጥቂቱ ንገረኝ?
ይልማ ተስፋዬ፡– ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ያደረግንበት ምክንያት ልጆቹ የሚኖሩት ውጭ ሀገር ነው፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች ደግሞ ዕድሜአቸው 15 እና 16 አካባቢ እየደረሰ ነው፡፡ ሀገሩ ደግሞ ትንሽ ከባድና አስቸጋሪ ነው፡፡ ክራይም የበዛበትና የሴፍቲ ችግር ያለበት ሀገር ነው፡፡ እናም የሁላችንም ልጆች ከትምህርት ቤት ከተመለሱ በኋላ ቤት ነው የሚቀመጡት፡፡ እናም ይሄን ተመሳሳይ የሆነ የላይፍ ዘዴ ለመቀየር አሰብንበትና ልጆች ላይ ለምን አንሰራም? የሚል ሃሳብ አንስተን ፐሪቶሪያ ላይ ጀመርነው፡፡ ጥሩ ውጤትም አየንበት፡፡ ፕሪቶሪያ ላይ በደንብ ከሰራን በኋላ ወደ ጆበርግ ሄድን፡፡ እዛም ልክ እንደፕሪቶሪያው የተሳካ ሆነ፡፡ ከዛ ደግሞ ወደ ረስተንበርግ አቅንተን ፍላጎታችን ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ መሆን ችሏል፡፡ ሁሉን ነገር ስናደርግ ወላጆቻቸውን እያማከርን በመሆኑ ያለውን ፕሮግረስ በማየትም ወላጆቹ ከጎናችን ቆሙ፡፡
ዋነኛው አላማችን ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎችን ማሰባሰብ ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ እቤት ውስጥ ቁጭ ብለው ስትረስ ከሚይዛቸው ሜዳ ወጥተው ጤናቸውን እንዲጠብቁ ለማስቻልና የኳስ ቤዝ ብናስይዛቸው ከሚል እሳቤ ነው፡፡ ከዛ በተረፈ ደግሞ ወደፊት ከእነርሱ መካከል ውጤታማ ተጨዋች ማፍራት ይቻል ይሆናል፡፡ ምንም እንኳን ጅማሬው አጥጋቢ ቢሆንም ወደፊት ግን የተሻለ ስራ እንደሚያስፈልግ እናውቃለን፡፡
ሊግ፡– በቅርቡ ፌዴሬሽናችሁ ዓመታዊ በዓሉን መጀመሩ እንዳለ ሆኖ ባለፈው ጊዜ በድምቀት ስለተጠናቀቀው የአስራ ኃይሌ ካፕ ትንሽ እናውራ?
ይልማ ተስፋዬ፡– አጋጣሚ ሆኖ እኔ ለጉብኝትና ለሌላ የስራ ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ ሄጄ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከጓደኛዬ ጌቱ ውቤ ቁጭ ብለን ስናወራ ለምን አስራትን ሰላም አንለውም ተባባልን፡፡ ተያይዘን ወደ ቤቱ አቀናን፡፡ እዛው አስራት ቤት ቁጭ ብለን እያወራን እንደዚህ አይነት ነገር እንደደረሰበትና የሃኪም ውጤቱን ሲያሳየኝ በጣም ደነገጥኩ፡፡ ከዛም ፈጣሪ ለአንተ ምህረቱን ያምጣልህ ብዬ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመለስኩ፡፡ አንተም እንደምታውቀው ይሄን ፌዴሬሽን የመሰረትነው ከአሁን በፊት ለብሄራዊ ቡድን አብረን የተጫወትነው ፍቃዱ በላይና ማሞ አለም ሻንቆ (አስፕሬላ) ጉዳዩን አማከርኳቸው እናም ጊዜው ሳይሄድ አንድ ነገር መስራት አለብን ወደሚል ድምዳሜ ደረስን፡፡
ከዚያም አንድ መግለጫ ሰጥተን ለምን ቲሞችን አናሰባስብም? የሚል ሀሳብ መጣ፡፡ የቡድኑ አስተባባሪዎችም ለዚህ አላማ ስኬታማነት ወደውድድሩ እንደሚገቡ ቃል ገቡልን፡፡ እናም በፌዴሬሽኑ ስር ለሚደረገው ቶርናመንት ሰባት ቡድኖችን አገኘን፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ታላቅ ሙያተኛ ለኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ ውለታን ሰርቷል፡፡ እኛም የእርሱ ውጤቶች ነን፡፡ ስለዚህ ከእርሱ ጎን መቆም ግዴታችን ስለነበር ከእርሱ ጎን መቆም ጀመርን፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ከሩዋንዳ ዋንጫ ያመጣንበት ውድድር ላይ ሶስታችንም አብረን ነበርን፡፡ አሰልጣኙ ደግሞ አስራት ኃይሌ ነበር፡፡ እናም ስራው በተፋጠነ ሁኔታ እንዲካሄድ ተደረገ፡፡ እዚህ ያለው ማህበረሰብም አላማውን ለመደገፍና ለማገዝ ከፍተኛ የሆነ ቅንነት ስለነበረው ስኬታማ መሆን ችሏል፡፡ እግር ኳስ ደግሞ በባህሪው ንፁህ የሆነና ዘር፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ የሌለበት መድረክ በመሆኑ ለመሰብሰብ በጣም አመቺና ቀላል ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካ ሕይወት ከባድ ቢሆንም ሁሉንም ነገር በመቋቋም በጣም ስኬታማ የሆኑ በርካታ ኢትዮጵያዊያኖች አሉ፡፡ እናም ለእነዚህ ወንድምና እህቶቻችን ከስራቸው ውጪ ፕሮግራም አስተካከልንና ወደ ውድድሩ ገባን፡፡ ሰባቱ ተወዳዳሪ ክለቦች እያንዳንዳቸው ለመመዝገቢያ 10 ሺህ ራንድ ሲከፍሉ ይህንን ገንዘብ ወዲያውኑ ወደ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ አካውንት ገቢ እንዲሆን አደረግን፡፡ የገንዘቡ መጠንም 382 ሺህ ብር አካባቢ ነው፡፡ ከዛ የግዴታ ውድድሩን መቀጠል ነበረብንና መክፈቻውን ጆሀንስበርግ ላይ አድርገን ጀመርነው፡፡
ከዚያም ይህ የዙር ውድድር አራት ወር ፈጅቶ ባለፈው አንተም በተገኘህበት የፍፃሜው ውድድር ተካሂዷል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ ትኬቶች አዘጋጅተናል፡፡ አሁንም አስራት ሕክምናውን ገና አልጨረሰም፡፡ ፈጣሪ ምህረቱን ያውርድለት እኛ ግን የተቻለንን ለማድረግ እየጣርን ነው፡፡ ይህ ቶርናመንት የእርሱ ውድድር ስለሆነ ትኬቶች ተሸጠዋል፡፡ ገና ሂሳብ አልሰራንም፡፡ እዚህ የውድድር ስነስርዓት ኮሚቴዎችም አብረውን ስላሉ አንድ ላይ ተሰብስበን ሂሳቡ ይሰራና በእርሱ ስም የተሰበሰበው ገንዘብ በአጠቃላይ በአስራት ኃይሌ አካውንት ገቢ እንዲሆን ይደረጋል፡፡
ሊግ፡– ለዚህ ውድድር ስኬታማነት እገዛ ያደረጉና ያጋጠማችሁ እንቅፋት ካለ ቢገለፅልኝ?
ይልማ ተስፋዬ፡– በዋናነት ለዚህ ፕሮግራም ስኬታማነት ከፍተኛ እገዛ ያደረጉት በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሰባቱ ቡድኖች ናቸው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ቲሞቹን ኦርጋናይዝድ ያደረጉ ከየቡድኑ ሶስት ሶስት ግለሰቦች አሉ፡፡ እናም ለእነዚህ ሰዎች እጅግ የከበረ ምስጋናዬን በፌዴሬሽኑ ስም ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ እኛም በኳስ ስላሳለፍን ለእኛ ሪስፔክት ሰጥተውን አብረን መስራታችን ትልቅ ኩራት ፈጥሮብናል፡፡ አንዳንዴ በስራ ሂደት ከእኛ ዕድሜ በላይ የሆኑትን ነው የምናዘው፡፡ እንደዛም ሆኖ ትልቅ ከበሬታ ሰጥተውህ ነው ኃላፊነቱን የሚቀበሉት እናም ይሄን ይሄን ስታይ በጣም ደስ ይልሃል፡፡ ለረጅም ጊዜ በኳሱ ማሳለፍ ትርፉ ይሄ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለፕሮግራሙ ስኬታማ መሆን የሁሉም ድርሻ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የሁሉንም ስም መጥራት አስቸጋሪ በመሆኑ በአጠቃላይ በፌዴሬሽኑ ስም ላቅ ያለ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡
አንዳንዴ ደግሞ መሀል ላይ ያልሆኑ ነገሮችን ታያለህ፡፡ ነገር ግን አላማ ስላለህ ነገሮቹን እንዳላየ ታልፋለህ፡፡ እየሰማህ እንዳልሰማ ትሆናለህ፡፡ ሌላው ቢቀር ፐርሰናል የሆነ ስድብ የመጣብኝም ጊዜ ነበር፡፡ ምንም ከአንተ ጋር አንድ ቀን ቡናና ሻይ ጠጥቶ የሚያውቅ ሰው ስለአንተ ፐርሰናል ሕይወት አሊያም ስለፋሚሊህ ሁሉ የሚያወሩ ሰዎችም አሉ፡፡ እኔ በዚህ ሁኔታ ከመበሳጨት ይልቅ እኔ ያንን ነገር ስሰማ ለካ አንድ ስራ ሰርቻለሁ ማለት ብዬ ነው ያሰብኩት፡፡ እናም የዚህ አይነቱን ተራ ነገር ኢግኖር በማድረግ የፍፃሜው ውድድር እጅግ ባማረ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሆኗል፡፡ ለእነዚህ ተራ ነገሮች ቦታ ሰጥቼ ቢሆን ኖሮ ሂደቱ ይሰናከል ነበር፡፡ ግዴታ ስራ ስትሰራ የሚመጡ ነገሮች ስላሉ እንደ የአመጣጣቸው አስተናግጄአቸዋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡
ሊግ፡– በሚቀጥለው ዓመት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ፌዴሬሽን ዓመታዊ ውድድሩን እንደሚጀምር በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ይሄን ፍላጎት ለማሳካት ያላችሁ ቁርጠኝነት እንዴት ይገለፃል?
ይልማ ተስፋዬ፡– የተነሳንበት አላማ አንድና አንድ እሱ ነው፡፡ ሞዴላችን ደግሞ በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ፌዴሬሽን (FSFNA) ነው፡፡ ከመነሻው የእነርሱን ሕግና ደንብ አስመጥተን አንድ ሁሌም ስሙን ሳልጠቅስ የማላልፈው ወዳጄ ወልዳይ ይባላል፡፡ እዚህ ሀገር ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚማር ነበር፡፡ ልጆቼንም ያስጠናልኝ ነበር፡፡ እሱን አማክሬው በዚህ ሀገር ሕግ መሠረት ሕጉን ተርጉሞ የገለበጠልን እሱ ነው፡፡ እናም በዚህ አጋጣሚ በጣም ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡ በነገራችን ላይ አሁን እሱ ዶክትሬቱን ጨርሶ ወደሀገር ቤት ተመልሷል፡፡ እናም ባለበት ቦታ ሁሉ ለእርሱና ቤተሰቡ ሰላሙን ሁሉ እመኛለሁ፡፡
ይሄን ተመክሮ አድርገን በመነሳት ባለፈው ጳጉሜ 6 የመጀመሪያውን አንድ ቀን ሙሉ የፈጀ ውድድርን አካሂደን ሕዝቡ በጣም ነው የተደሰተው፡፡ በነገራችን ላይ እኔም ይሄን ሳይ የድካሜን ፍሬ የለቀምኩበትና ልፋቴን የረሳሁበት ወቅተ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ይሄን ሳደርግ አቅምና ጊዜዬን ብቻ ሳይሆን ገንዘቤንም የማወጣበት ነው፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ በመስራትህ የምታገኘው ምንም አይነት ገቢ የለም፡፡ በነገራችን ላይ ይህን ፌዴሬሽን እዚህ ደረጃ ለማድረስ ከሙያ ጓደኞቼ ጋር ሆነን ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለናል፡፡ ውጤቱን ግን የዛን ዕለት ነው ያየነው፡፡ ለሙከራ ቀኑን የያዝንበት ያ ቀን ሲሆን ምላሹም አጥጋቢ ስለነበር ከልብ ረክተናል፡፡ በመሆኑም ይሄን ዓመታዊ በዓሉን በድጋሚ እንደምናደርገው ምንም አይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ እግዚአብሔር ዕድሜና ጤናውን ይስጠን፡፡ ሀገራችንንም ሰላም ያደርግልን፡፡
ሊግ፡– ይልማ ተስፋዬ (ካቻማሊ) አሁን በደቡብ አፍሪካ ሕልሙን እየኖረ ነው ማለት ይቻላል?
ይልማ ተስፋዬ፡– ያው አንተም እንደምታውቀው የእኔ ሕይወት ስፖርትና ስፖርት ብቻ ነው፡፡ ያውም እግር ኳስ፤ እስካሁንም ከምወደው ስፖርት አልተለየሁም፡፡ ከጎኔ ሆና ሁሌም የምታበረታኝ ባለቤቴ አለች፡፡ ብዙ የቢዝነስ ሰው አይደለሁም፡፡ ጀመርኩት ግን በኋላ ባለቤቴ የበለጠ ራን እንድታደርገው አደረግኩኝ፡፡ እሷ በዚህ ዘርፍ ከእኔ የተሻለ ትሰራለችና ከእርሷ ጎን ሆኜ የሚያስፈልገውን ነገሮችን እያቀረብኩኝ ስራ ተከፋፍለን እንሰራለን፡፡ እሷም እኔ ምን ያክል ከፍተኛ የሆነ የኳስ ፍቅር እንዳለኝ ስለምታውቅና ሕይወትን ካሸነፍን በኋላ ለስፖርቱ ብዙ ጊዜ እየወሰድኩ ነው፡፡ ምን አደከመህ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከስፖርቱ አልጠፋም፡፡ በተለይ ፕሮጀክቱን ከጀመርን በኋላ ቢያንስ ለ6 ወራት ያክል የእኔን እገዛ ስለፈለገ ለስፖርቱ በጣም ታይም ሰጥቻለሁ፡፡ ባለቤቴም ያለውን እውነታ በጣም ስለምትረዳኝ በዚህ አጋጣሚ በጣም ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡ በአጠቃላይ አንተ ከላይ እንዳልከው አሁን ባለው ሁኔታ በደቡብ አፍሪካ ሕልሜን እየኖርኩ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወደፊት ደግሞ የሚቻለውን ነገር የበለጠ ለማድረግ ትምህርትም እየተማርኩ በመሆኑ የተሻለ ነገር እሰራለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሊግ፡– በምትወደው ስፖርት ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ለመስራት ታስባለህ?
ይልማ ተስፋዬ፡– ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሌም የሚቆጨኝ ነገር አለ፡፡ በጉዳት ከኳሱ ከወጣሁ በኋላ በጊዜው የአሰልጣኝነት ኮርስ አግኝቼ ቢሆን ኖሮ ለስፖርቱ የተቻለኝን ነገር ሁሉ አደርግ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኳስ አፍቃሪ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው እውነት ደግሞ የደጋፊው ስሜትና የኳሱ ሁኔታ ፈፅሞ አብሮ አልሄደም፡፡ እናም ይሄ ብልጭ ድርግም የሚል ነገር መቀየር አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ የግዴታ ታች ወርዶ መስራትን ይፈልጋል፡፡ እስከአሁን የሕይወት ጉዳይ ነው የያዘን፤ ከዚህ በኋላ ግን አንድ ትልቅ ሃሳብ አለኝ፡፡ አካዳሚዎች ላይ ስራ መስራት እፈልጋለሁ፡፡ አካዳሚ ስልህ ደግሞ ዝም ብሎ ሳይሆን ሁሉን ነገር ያሟላ አካዳሚ ኢትዮጵያ ውስጥ መገንባት አለበት ብዬ ስለማስብ እግዚአብሔር ከፈቀደ በዚህ ስራ ላይ እሰማራለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡