Google search engine

“ለሙያተኞች መብት በመታገሌ ኢንተርናሽናል አርቢትር የመሆን እድሌን ተነፍጌያለሁ” “በዚህ ማህበር የመጣው ለውጥ ሁሉ ከ90 በመቶ በላይ የኔ ትግል ውጤት ነው” ፌዴራል አርቢትር ሚካኤል አርአያ /የኢት. ዳኞችና ታዛቢዎች የሙያ ማህበር ም/ል ፕሬዝዳንት/

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ ካለፉት ሁለት አስርት አመታት በላይ በሊጉ ላይ አለ.. ከረዳት ዳኝነት እስከ ዋና ዳኝነት ሰርቷል፡፡ በረዳትነት ለ7 አመታት በዋና ዳኝነት 17 አመታት  አጫውቷል…ካርድ በመምዘዝ መታወቁ ደግሞ ተጨዋቾች በሆነ ባልሆነ እንዳይቃወሙት አድርጓል… ለዳኞች መብት ጥግ ድረስ ተሟግቷል…. ዳኝነቱን ለማቆም ሲወስን ውለታው የገባቸው የሙያ አጋሮቹ ተሰብስበው ሸልመውታል… ፌዴራል አርቢትር ሚካኤል አርአያ… ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቆይታ ያደረገው አርቢትሩ  ከዳኞች ኮሚቴና ከማህበሩ አመራሮች ጋር በገጠመው ትግል፣ ስለዳኞች መበደል.. ስለኮሚሽነሮች ችግር ከፌዴሬሽኑ ጋር ስለተመሰረተው ጥሩ ግንኙነት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ምላሹን ሰጥቷል….

ሊግ:- ከዳኞችና ኮሚሽነሮች ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች አሉ..?

ሚካኤል:- ባለኝ መረጃ በኮሚሽነሮች ፈተናና ሌሎች ዳኞች ጋር ቅሬታ መጥቷል፡፡ በኤሊትና በኢንተርናሽናል ዳኝነት ምርጫ ያልተፈቱ ቅሬታዎች አሉ ሃላፊነቱ የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ነው፡፡ ማህበራችንን አይመለከትም ግን ተበደልን ሲሉ ሄደን እንጠይቃለን በቃ… አርቢትር ኮሚቴው ትክክል ሰርቻለሁ ቢልም ቅሬታዎች አሉ… የተደሰቱም ቅር የተሰኙም ባለሙያዎች አሉ…

ሊግ:- ብሄራዊ ዳኞች ኮማቴ መመዘኛውን ሳያሳውቅ እንዴት ይፈትናል የሚሉ ወገኖች አሉ… ማህበሩስ ምን ይላል..?

ሚካኤል:- ቅሬታ እያቀረቡ ያሉ አባላቶቻችን አሉ… እዚህ ላይ መናገር የምፈልገው ባህርዳር ላይ የነበረው የፊፋ የኤሊት ኮርስ ላይ መስፈርቱ ባለመውጣቱ ቅሬታ ፈጥሮ ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ነበርና በወቅቱ ለሰራው ስራ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ፕሬዝዳንት ነኝ ብሎ ሳይኩራራ በሄደበት ዳኞች ኮሚሽነሮችን አናግሮ ይመጣል ይሄ ትልቅ ደስታ ፈጥሮልኛል። ችግሮች ካሉ ፈትቶ ይመጣል… አንዳንዴ እንቅልፍ ሁሉ ያጣል… ዳኞቹ ስልክ ሲደውሉ ቀን ማታ ሳይሰለቸው አንስቶ ችግራቸውን የሚያዳምጥ ነውና አመሰግነዋለሁ…. እንደ ጽ/ቤትም ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ባህሩ ጥላሁን ጥሩ ስራ እየሰራ ነው… ችግሮች ብዙ ጊዜ መነሻቸው ከአርቢትር ኮሚቴው ነው ይሄ መስተካከል አለበት..

ሊግ:- በመስፈርት አወጣጡ ላይ ክፍተት አለ ማለት ይቻላል…?

ሚካኤል:- ባለፈው በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል አቶ ባህሩ በነበረበት ፌዴሬሽኑ ጥሩ ነገር አድርጎ ነበር፡፡   ባለሙያዎች እንዲተቹት አድርጎት መመሪያው እንዲጸድቅ መድረክ ያሉት ብዙም ምላሽ እንዳይሰጡ እንደ ግብአትነት ብቻ እንዲጠቀሙ አድርጎ ነበር፡፡ ከማህበራችን እኔና ፕሬዝዳንቱ አቶ ትግል ግዛው፣  ኢንስፔክተር ጌታቸው፣ አቶ ይግዛው፣ አቶ መኮንን አስረስ ኢንስትራክተር ሽፈራው የክልል ማህበራት ተወካዮች ተገኝተው በመመሪያው ላይ ሀሳቦች ትችቶች ተሰጥተውበታል፡፡ ከትችት ሰጪዎቹ  አንዱ ደግሞ እኔ ነበርኩ፡፡ መጀመሪያ መመሪያ ይወጣል ከዚያ መስፈርቱ ..መስፈርቱ በየደቂቃው በየሰአቱ አይወጣም፡፡ ፊፋ ህጎችን ሲያወጣ  የአመቱ መጀመሪያ ላይ ነው ባለሙያው አውቆት ዝግጅት አድርጎበት ነው የሚተገበረው፡፡ እዚህ ግን ሲታይ ብንን ሲሉ ነው መስፈርት የሚያወጡት… በመመሪያው ላይ አርቢትር ኮሚቴው ተጨማሪ መስፈርት ያወጣል ይላል፡፡ እኔ ደግሞ ተቃውሜያለሁ መስፈርት ሲወጣ መጀመሪያ ወጥቶ ከጸደቀ በኋላ ለአመት ይሰራል፡፡ ሊቀይሩት ከፈለጉ እንኳን ከአመት በኋላ ነው፡፡ ፊፋም ህግ ሲቀይር በየአመቱ ነው እኛ ጋር ግን መስፈርቱ በአመት ስድስት ሰባት ጊዜ ሊያወጡ ይችላሉ… መስፈርት ማውጣት መብታቸው ቢሆንም የበላይ አካሉም የሚመለከተውም ማወቅ አለበት ባይ ነኝ፡፡

ሊግ:- ይሄ መሆኑ ..መስፈርት  እንዲያወጡ እድል ማግኘታቸው የፈለጉትን ለማሳለፍ ያልፈለጉትን ለመጣል እድል ይፈጥራል የሚሉ አሉ …አንተስ ..?

ሚካኤል:- የሚፈልጉት ይኑር አይኑር የነሱ ህሊና ነው የሚያውቀው.. የነሱን ልብ ማወቅ አልችልም፡፡ ግን ጥርጣሬ ይፈጥራል፡፡ የአካል ብቃትህን ለማሳደግ ቢያንስ 6 ወር ይፈልጋል፡፡ መስፈርቱ ሲቀየር አስቀድሞ መታወቅ አለበት ባይ ነኝ፡፡ አንድ ምሳሌ ልስጥ ሁለት ዳኞች እኩል ጨዋታ ላይሰጣቸው ይችላል.. መስፈርቱ ላይ በርካታ ጨዋታ ያጫወተ ብለህ መመዘኛ ካወጣህ አስቀድሞ መታወቅ አለበት…  ጨዋታ ለዳኞች ስትሰጥ ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ ብቃት የሌለው ዳኛ ከሆነ ብቃት የለውም ብለህ መመለስ አለብህ…. የድሮ መስፈርት ላይ ለኢንተርናሽናል የሚወዳደር ከ8 ጨዋታ በላይ ያጫወተ ይላል… ነጥቡ ከ8 በላይ የሆነ ይላል አበቃ፡፡ ከ8 በታች ከሆነ ውድድሩ ውስጥ አይገባም… ከዚያ በላይ ያጫወቱ አንዱ 12 አንዱ 13 ቢሆን ባላቸው ነጥብ ይካፈላል… መሆን ያለበት ይሄ ነው… ከዚያ በታች ያገኘ ብቃት የለውም አይመደብም ካልተመደበ ደግሞ ውድድር ውስጥ አይገባም …ለዚህ ደግሞ ሃላፊነቱ የኮሚሽነሮች ነው…

ሊግ:- የአመቱ ኮከብ ለመባል የግድ ኢንተርናሾናል መሆን የለበትም ብለህ ስትታገል ኖረሃል… ዘንድሮ  ደግሞ ሀሳብህ ተሳክቶ ኮከቡ ፌዴራል አርቢትር  ቢኒያም ወ/አገኘሁ ሆኗል ….ምን ተሰማህ ..?

ሚካኤል:- ሽልማቱን ያገኘው ፌዴራል አርቢትሩ ቢኒያም ወ/አገኘሁ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ… ግን ከመነሻው ኮከብ መባል ያለበት ኢንተርናሽናል ዳኛ የሆነ የሚሉት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ነው…. የፊፋም ህግ አይደለም፡፡ ይሄ ለምን ሆነ ብለን አቶ ባህሩና በወቅቱ ቴክኒካል ዳይሬክተር የነበረው ቴዎድሮስ ፍራንኮን ስንጠይቅ ከፊፋ ያገኙት መልስ የሀገሪቱን ትልቅ ውድድር የሚያጫውት ነው ኮከብ የሚባለው ሲባል ፌዴራልም ስለሚያጫውት መብት ነበረን ማለት ነው… እኔ ውድድሩ ፕሪሚየር ከተባለበት ቀን ጀምሮ አለሁ… ችግሮችም ገጥመውኛል …. በሴፍ ብላተር ዘመን ሶስቴ በኢንፋንቲኖ ዘመን ሁለቴ በአጠቃላይ አምስት ጊዜ የፊፋን ኮርስ ወስጃለሁ…

የአውሮፓንም በነ አቶ ጸሃዬ ገ/እግዚአብሄር ጊዜ ወስጃለሁ፡፡ እንደነሱ ኢንተርናሽናል ዳኛ ተብሎ ፊፋ ጋር እንደተገኘ ኮርሱን የወሰዱ ፌዴራል ዳኞችም አሉ… የፊፋ ሊስቱ ውስጥ አለን ብለው ብቻቸውን መጠቀም የለባቸውም። ያንን እድልንም ያላገኙ ጀግኖች ፌዴራል ዳኞችም አሉ፡፡ ይሄ መታወቅና እኩል መብታቸው መከበር አለበት… የኢትዮጵያ ብሄራዊ አርቢትር ኮሚቴ አባላት ሁሉም ኢንተርናሽናል ዳኞች ናቸው፡፡ በፊፋ የተቀመጠ ህግ  ግን አይደለም…የፌዴራል አርቢትር ቢኒያም ኮከብ መባል ለኛ መብት ጥየቃ በር ከፍቷል… በዚህም ደስተኛ ነኝ።

ሊግ:– የኤሊት ኮርስ ምርጫ ላይ ቅሬታ ያነሳው ፌዴራል አርቢትር ዮናስ ከምደቡ ተነሰቶ ወደመጣበት እንዲመለስ ተደርጓል ….ልክ ነው የማህበሩስ አቋም ምንድነው …?

ሚካኤል:– ቅሬታ ያነሱ አላደግንም ያሉ ዳኞች አሉ፡፡ ለኛ ግልባጭ ሲደርሰን እንጠይቃለን… ስንጠይቅ ዕድገት የሚሰጠው ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ነው፡፡ ለምን አሳደጉት በምን መመዘኛ የሚለውን የሚያውቁት ራሳቸው ናቸው ጣልቃ መግባት አንችልም… በእኛ በኩል ጥያቄ ያነሱ ዳኞችን ስናይ ጥሩ አቅም ያላቸው ስለሆነ  ትክክለኛ ጥያቄ እንዳቀረቡ እናምናለን.. አንዳንድ ዳኞች ማመልከቻ ባያመለክቱም ወሬ ስንሰማ ደውለን አጣርተን የሚመለከተውን አካል እንጠይቃለን፡፡ ለማጣራትም ለዮናስም ደውዬለት እንደነገረኝ ምርጫውን ካደረጉት የኮሚቴው ዳኞች ሶስቱ አዳማ ነበሩና ዮናስም ለጨዋታ ተመድቦ እዚያ ስላገኛቸው አለመመረጡ ልክ አለመሆኑን ገልጾ ቅሬታውን ያቀርባል። ምን እንደተናገረ ምን እንደመለሱለት በቦታው ስላልነበርኩ አላውቅም፡፡ መብቱን ሲጠይቅ እንዲህ ቅሬታ እያለህ ተከፍተህ ማጫወት ስለማትችል ወደ አዲስ አበባ ሄደህ የፌዴሬሽን  ጽ/ቤት አመልክት እዚህ ግን ከተመደብክበት ቀይረንሃል እንዳሉት አስረድቶኛል …የኔ ጥያቄ ሁሌ አቶ ባህሩ  ጋር ሂድ ለምን ይላሉ….? አቶ ባህሩ ዳኛ መዳቢኮ አይደለም ..አስተዳደራዊ ችግሮች ካሉ ሁሌ ያስተናግዳል፡፡ አዎ ጥሩ ነው እንደኔ ከዳኞች ጋር ተያይዞ አቶ ባህሩ ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳያስና ሌሎቹ ስራ አስፈጻሚዎች የተጨነቁ እነሱ ይመስሉኛል… ይሄ ደግሞ ያሰጋኛል..

ሊግ:- ለኮሚሽነሮች ጥያቄ መልስ ተሰጠው…? አነጋጋሪ እንደሆነ መረጃው አለኝ..

ሚካኤል:- አዎ ለኮሚሽነሮች መልስ ተሰጥቷል፡፡ ያም ቢሆን ለኔ እንደ ባለሙያ ትንሽ ባለችኝ እውቀት ልናገር እነሱ ይበልጡኛል ያው ኢንተርናሽናል ነን ስለሚሉ.. ከነሱ የምማረውም ይኖራል… ማመልከቻ ያቀረቡ ኮሚሽነሮች በዓይን ፈተና ወድቀዋል ነው የተባለው… ከታችኛው ሊጎችም ወደ 60 የሚጠጉ ወድቀዋል … በዓይን ችግር ወድቀዋል ከተባሉ ለምን ፈተና ላይ አስቀመጧቸው ..? ከፈተኗቸው ለምን ይጥሏቸዋል..? በዓይን ችግር የወደቀን ኮሚሽነር ለምን ይፈትናሉ …? ህክምና ኮሚቴ ወድቀዋል ብሎ ስም ካላስተላለፈ ማን ፈትኑ አላቸው ..? ይሄ በጣም ያሳዝናል የኔን ምሳሌ ልናገር …ከ17 አመት በፊት ረዳት ዳኛ እያለሁ አይንህ አያይም ተብዬ ፈተና ላይ ሳልቀመጥ ቀረሁና ኢንተርናሽናል ፈተና አመለጠኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ተከራክሬ ነው በቦርድ የተመለስኩት… ቦርዱ ማጫወት ይችላል ብሎኝ ወደ ምወደው ዳኝነት ተመልሼ 17 አመት ሙሉ በዋና ዳኝነት ሰራሁ… ካሉት ዳኞች ብዙ በማገልገል ቦጋለ…..ብቻ ነው የሚበልጠኝ… ሁለት አመት ይበልጠኛል… 17 አመታት ሳጫውት አንድም ቀን ተቀጥቼ አላውቅም… የምንሰራው በህግ ከሆነ በአይናቸው  ከሆነ ፈተናው ላይ መቀመጥ አልነበረባቸውም…. የኮሚሽነሮቹ ጥያቄ ለኔ ትክክል ነው… የሚገርመው አስቀድሞ እንዲያስተካክሉ ደብዳቤ ልከናል አልተቀበሉትም…  አሳይሃለሁ ብለህ ከመጣህ ልክ አይደለም፡፡ ልክ አይሆንም..  የኮሚቴው ሰብሳቢ ኮሚሽነር ሸረፋ ደሌቾ ኮሚሽነር እያለሁ ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ተቀጥቼ ነበር ብለው አንተ ጋር ቃለምልልስ ሰጥተው አይቻለሁ… ነገሮችን እንደራስ ማየት ነዋ….

ሊግ:- የኤሊት ምርጫ ሁሌ ያጋጫል ለምን ይሆን …?

ሚካኤል: እንደ እድገት ስለሚታይ ነው… እንደ አጠቃላይ ለምን ኤሊት አልገባንም ብለው እየጠየቁ ያሉ ዳኞች አሉኮ… ለኔ ስለ ኤሊት ብትጠይቀኝ ሁለት አይነት ነው ያለው…. አንደኛው ኢንተርናሽናል የሚሆነውና ፕሪሚየር ሊጉን የሚያጫውቱ ዳኝች የተካተቱበት ….ሁለተኛው ደግሞ ደግሞ የታችኛው ሊግ ያሉት ናቸው…  ሁለተኛው ውስጥ የተካተቱት ተስፋ ያላቸውና ወደ ላይ የሚያድጉ ማለት ነው፡፡ ተስፋ ማለት ወደ ላይ የሚያድጉ ከሆነ ከፕሪሚየር ሊጉ አምጥተው ወደ ታች ማን አስገቡ አላቸው..? ይሄ ነው ችግር …. ይሄ ክፍተት መታረም አለበት።

ሊግ:- ባለፈው ሰኞ በተካሄደውም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አልተወከላችሁም ..

ለምን ይሆን …?

ሚካኤል:- ጉዳዩ በህግ የተያዘ በመሆኑ ባላብራራው ደስ ይለኛል …

ሊግ:- አንድ መረጃ ልስጥህ። ጉዳዩም የማህበራችሁ ማዕተም ላይ ጥያቄ በመነሳቱ ነው…አንተ በሌለህበት ወቅት አመራሮቹ ሌላ ማዕተም አሰሩ አንተ ስትመጣ ደግሞ ነባሩ ማዕተም አለ…. እነሱ የአንተን ቀድሞ የነበረ ማዕተም ህገወጥ ነው አሉ፡፡ አንተ ደግሞ የነሱ ነው ህገወጥ የኔ አይደለም አልክና በፍ/ቤት አሳገድክ ፌዴሬሽኑ በነሱ ማዕተም የተሰጠ ውክልና አልቀበልም ታግዷል አለና ተወካዮቹ እንዳይገቡ ተደረገ …ይሄ አይደል እውነቱ …?

ሚካኤል:- የተናገርከው እውነት ነው …በህግ ጥላ ስር በነበርኩበት ወቅት  የተፈጠረ ነው …. የማህበራችን ዋና ጸሃፊ የነበረው አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ ሲሆን ማዕተሙን ተረከብኩ.. አበላችንን ሆነ መብታችንን ስናስጠብቅ የነበረው በዚህ ማዕተም ነው፡፡ ያኔ በህግ ጥላ ስር ሳለሁ ማዕተሙን መጠየቅ የሚችሉበት ዕድል ነበር፡፡ በአጃቢ ሄጄ ልስጥ ህጉ በሚለው ሌላ መንገድ መረከብ እየቻሉ ስራችንን ተጎዳ ጊዜያዊው ማዕተም ይፈቀድልን ብለው ጠየቁ፡፡ ፌዴሬሽኑ ፈቅዶላቸው የትብብር ደብዳቤ ተጻፈላቸው… ጊዜያዊ ማዕተም አወጡ፡፡ ይህን አላውቅም ነበር፡፡ ከማህበራት ማደራጃውን የወጣ ህጋዊ ማእተም መስሎኝ ነበር ..

ሊግ:- ህጋዊ አልነበረም ማዕተሙ..?

ሚካኤል:– ህጋዊማ አይደለም …ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ተወስኖ የወጣ ነው የመሰለኝ፡፡ ግን አይደለም እንዳወኩ ለአቶ ባህሩ  ሄጄ ጉዳዩን አብራራሁ፡፡

ሊግ:– ታዲያ በምን ታወቀ…?

ሚካኤል:- በአንድ መብት ማስከበር ባለብን ጉዳይ ላይ ከተነጋገርን በኋላ ደብዳቤ ይጻፍና እኔ ጋር ባለው ማዕተም ለፌዴሬሽኑ ይገባል፡፡ የማህበራችን አመራሮች ግን ደብዳቤው የገባው በታገደ ማዕተም ስለሆነ ተቀባይነት እንዳይኖረው ብለው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ፌዴሬሽኑም ይቀበልና የገባውን ደብዳቤ ውድቅ ያደርጋል፡፡ ይሄ ማለት ከነ ጥያቄያችን ተቀባይነት አጣ… ማዕተሙ ሲታገድ የአበል ጭማሪ ጥያቄም ታገደ፡፡ ይሄ ያሳዝናል… በዚህ ጊዜ የነበረውን አስረድቼ መብቴን ጠየኩ፡፡ አቶ ባህሩም ጊዜያዊ ማዕተሙ ገቢ እንዲደረግ አዘዘ። እስካሁንም ማዕተሙ ገቢ አልተደረገም… ተጠያቂ እንዳልሆን በመስጋቴ ህግ ቦታ ሄጄ አመለከትኩ..  ፍ/ቤቱ የትኛው ትክክለኛ የሚለውን ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ሁለተኛው ማዕተም ታገደ … እኔ ሳላውቅ የማህበሩ አመራሮች ለካ ለፕሬዝዳንቱ ትግል ግዛውና ለሃይለ ራጉኤል ወልዳይ ውክልና ሰጥተው ጠቅላላ ጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ በዚሁ የታገደ ማዕተም አስመትተው አስገብተዋል። ፌዴሬሽኑም አትችሉም የናንተ ማዕተም ታግዷል ብሎ እንዳይገቡ ከለከለ፡፡ ውክልና ሲሰጥ ፕሬዝዳንቱ እንዳለ ሆኖ ሌላኛው ተወካይ የሚመረጠው በማህበሩ የስራ አስፈጻሚ  ኮሚቴ አባላት ነው ይህም አልተደረገም፡፡

ሊግ:- ታዲያ ደብዳቤው መታገዱ ጥቅማችሁን አልገጎዳም ..?

ሚካኤል:- ጎድቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን መብቴን የግድ ማስከበር ነበረብኝ፡፡ እኔ ጋር ያለው ማዕተም ታገደ ማለትኮ ውንጀላ ነው። ማህበር ይታገድ አልተባለም የታገደውኮ ማዕተሙ ነው፡፡

ሊግ :- ማህበሩ ያለ ማዕተሙ ምን ይሰራል… ?

ሚካኤል:- በወቅቱምኮ ቀኑ ቅዳሜና እሁድ ስለነበር እንጂ ተነጋግረን ተስማምተን እኔ ጋር ባለው ማዕተም መስራትና ውክልናውንም ማስገባት ይቻል ነበር… ህጋዊ ማዕተምኮ አለን.. ስራ አስፈጻሚው ተነጋግሮ ማስተካከያ ለማድረግ ሲያስብ ፌዴሬሽኑ ግን ጉባኤው ለሚካሄድበት የአፍሪካ ህብረት አሳውቄያለሁ አይቻልም አለን፡፡ በሱ ምክንያት ሳንወከል ቀረ..ያለው እውነታም ይሄ ነው፡፡

ሊግ:- የማስተካከል የመተራረም ዕድሉ አለ…?

ሚካኤል:- አዎ እድሉማ አለ…. ግን ሁላችንም ወደ ህጋዊነት መግባትና ጠቅላላ ጉባኤው መካሄድ አለበት፡፡ ስከራከር የቆየሁትም ለዚህ ነው.. ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት አለበት… ለምን ጠቅላላ ጉባኤ ሲባል እንደሚፈራ አልገባኝም፡፡ ጉባኤ ጠርተን አባላቱ የሚሉንን ሰምተን መሄዳችን ግዴታ ነው፡፡  የክሱ ጉዳይ ማንም ያሸንፍ ማንም ሲወሰን ነው የምናየው፡፡ ሌላ መናገር ያለብኝ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ችግሩን ለመፍታት ከጉባኤው መካሄድ በፊት ለባለፈው አርብ ጠርተውን ነበር …ነገር ግን አመራር ለአመራር ተነጋግረው ቀኑ ተራዘመ፡፡ በቀጣይ ግን ፌዴሬሽኑ ችግሩን ለማስተካከል ጉባኤ እንደሚጠሩ ተነግሮናል…

ሊግ:– ጨረስኩ የመጨረሻ ቃል …?

ሚካኤል:- ሰው በግልጽ ሲናገር በበጎ ጎኑ መቀበል ብንችል ደስ ይለኛል… በማህበራችን በኩል ባለሙያዎች እንዲመረጡ ጥረናል…. ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴን በሰብሳቢነት የሚመሩት  ኮሚሽነር ሸረፋ ደሌቾ ይሄ ማህበር ደግፎት ነው የገባው… ሙያተኛ ሲባል የግድ ዳኞች ብቻ አይደሉም … እነ  ዶክተር ዳኛቸው፣ ዶ/ር ወገኔ  ሙያተኞች ናቸው እነዚህን ሁሉ ደግፈናል… የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴው አባላት ተናግሮኛል፡፡ እንዲህ አደርገዋለሁ ከማለት ተቀራርቦ ተጠራርቶ መነጋገርን መልመድ አለባቸው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች የሙያ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ከተባልኩ ክብሬ መጠበቅ አለበት፡፡ የኔ ክብር የሚካኤል ብቻ አይደለም የሙያተኞች ክብር ነው ይሄ መታወቅ አለበት። ከኮሚቴው ጋር አብረን ተደጋግፈን ልንሄድ ይገባል፡፡ የሀሳብ ልዩነት ቢኖርም አጣጥመን መሄድ እንጂ ባላንጣ መሆን አይገባም … በግሌ  ለዚህ ሙያተኛ የከፈልኩት  መስዋትነትኮ ይታወቃል፡፡ በመታገሌ እንኳን ያጣሁት ዋጋ አለ… ከኢንተርናሽናል አርቢትርነት ተሰርዤበታለሁ፡፡ ለባለሙያተኞች በመታገሌ በአምላክ ተሰማ 5ኛ ወጥቶ እኔ 4ኛ ወጥቼኮ ኢንተርናሽናል አርቢትር የመሆን እድሌን አጥቻለሁ ተሰርዤበታለሁ… በዚህ ማህበር የመጣው ለውጥ ሁሉ ከ90 በመቶ በላይ የኔ ትግል ውጤት ነው፡፡ በአጠቃላይ ችግር ካለ ተነጋግሮ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን እውነት ሆኖ ለምን ተናገርክ ማለት አይገባም። በዚያ ላይ ኮሚቴ ገብቶ ስለመበቀል መታሰብ የለበትም፡፡ መድረክ ላይ ስናገር እንቀጣዋለን የሚሉ አሉ ዝም ብሎ አይቻልም፡፡ በማህበሬኮ እኔም ሃላፊ ነኝ፡፡ ፉከራ አይጠቅምም በየቦታው የሚወራውኮ ሰው ያናክሳል እንጂ አይጠቅምም፡፡ ለውጥ የለውም ወደ መስመር መግባት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ማህበር አጠቃላይ ውስጡ ስላለው አሰራር መነጋገር ይቻላል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ፌዴሬሽኑን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ እንደ ዳኛ መብታችንን ስንጠይቅ ጥሩ ምላሽ ይሰጠናል፡፡ ለዚህም እናመሰግናለን፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የኛን ችግር ለመቅረፍ ከሚያደርገው ጥረት አንጻር እንደ ፕሬዝዳንት ሳይሆን እንደ ጓደኛ ነው የምናወራው። የጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁንም የውድድር ክፍል ሃላፊው አቶ ከበደም ሄደን ስናናግራቸው አክብረው ያዳምጡናል.. እናመሰግናለን፡፡ የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ግን ትንሽ መስተካከል ያለበት ይመስለኛል..

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P