Google search engine

“የዳኛውን ውሳኔ የቀየረው የባህርዳር ከተማ ተጨዋቾች ጫና እንጂ ረዳቱ አይደለም” “በአገሪቱ ትልቅ ሊግ ላይ ተጨዋች ሲያመናጭቅህ  ውጤት የምትቀይር ከሆነ አስቸጋሪ ነው” ሚሊዮን ሰለሞን /ሀዋሳ ከተማ/

አዲስ አበባ ከተማ፣ ለሲዳማ ቡና፣ ለአዳማ ከተማ ተጫውቷል። አሁን ደግሞ በአንድ አመት ኮንትራት በአሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ስር ለሀዋሳ ከተማ እየተጫወተ ይገኛል… በመሃል ተከላካይነት ሚና በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስር ለዋሊያዎቹ ተመርጦ ተጫውቷል…

በተጨዋችነት ዘመኑ መነሻ በቦታህ ማነው ተምሳሌት ሲባል “ልጅ እያለሁ የሀዋሳ ት/ቤቶች ውድድር ላይ ስንሄድ ደጉ ደበበን አይቼ እንደሱ መሆን እፈልግ ነበር። ኳስን እየተጫወትኩ ደግሞ ሲዳማ እያለሁ እንደ ፈቱዲን ጀማል መጫወት ተመኝቻለሁ። እነአስቻለሁ ታመነም ጥሩ ናቸው” ሲል የሚመልሰው የሀዋሳ ከተማው የተከላካይ መስመር ተጨዋች ሚሊዮን ሰለሞን ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በታሪኩ የመጀመሪያ የሆነውን ቃለምልልስ አድርጓል…….።

ሊግ:– ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ቃለምልልስ ስናደርግና ለፈቃደኝነትህ ከልብ አመሰግናለሁ… ሀዋሳ ከተማ ተመቸህ..?

ሚሊዮን:– አንተም ዕድሉን ስለሰጠኧኝ አመሰግናለሁ። አዎ ሀዋሳ አሪፍ ነው። ነገር ግን ከብዙዎቹ ተጨዋቾች ጋር አብሬ አልሰራሁምና አዲስ ቤት እንደመሆኑ የክለቡን ባህል ሁኔታ ለመልመድ ትግል ነበረብኝ። አሁን ግን አሪፍ ነው …። በብሄራዊ ቡድንና በአዳማ ከተማ የነበረው አጨዋወት ይለያልና ሀዋሳ ይዞት ወደመጣው አጨዋወት ለመግባት እየጣርኩ ነው ያ ነው ቻሌንጅ የገጠመኝ …

በቆይታዬም ደስተኛ ነኝ። ልጅ ሆኜ ለሀዋሳ የመጫወት ህልም ነበረኝና ያን በማሳካቴ ደስ ብሎኛል።

ሊግ:-ሀዋሳ ከተማ ለምን ምርጫህ ሆነ …?አጨዋወት ..? ክፍያው ወይስ ምን..?

ሚሊዮን:– ከአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጋር በሲዳማ ቡናና በአዳማ ከተማ አብረን ሰርተናል .. ለአዳማ የፈረምኩት በሱ ምክንያት ነው። ጥሩ ግንኙነት አለን …በወቅቱ ለአዳማ ከተማ ስፈርም ጉዳት ላይ ሆኜ ነበር። አምኖብኝ ነው የወሰደኝ ይሄ ደግሞ ከርሱ ጋር እንድቀጥል አድርጎኛል በዚህም ደስተኛ ነኝ።

ሊግ:- በአዳማ ከተማ የነበረውና የሀዋሳ ከተማ አጨዋወት የሰፋ ልዩነት ነበረው ..?

ሚሊዮን:- አዎ እንደ አጨዋወት ይለያያል…. አዳማ ከተማን ስናይ ኳስ ከበረኛ ጀምሮ መስርተን ነው የምንጫወተው… ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ኳስን በፍጥነት ወደፊት በመላክ ተጋጣሚ የግብ ክልል ላይ ቶሎ መግባትን ይጠይቃል … ለኔ ትንሽ የከበደኝ ዋሊያዎቹም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጊዜ ተመሳሳይ አጨዋወት ስለነበር በአዳማ ከተማ ቶሎ ለምጃለሁ። የሀዋሳ ደግሞ በፍጥነት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል መግባትን ስለሚፈልግ ትንሽ ከብዶኝ ነበር አሁን ግን ለምጄዋለሁ።

ሊግ:– ሊገባ የነበረ ኳስ ከማዳን ወይም ግብ ከማስቆጠር የቱ ይመችሃል ..?

ሚሊዮን:– እንደ መረጥኩት ቦታዬ ሊገባ የነበረ ኳስ ማዳን ምርጫዬ ነው። ግን ግብ ማስቆጠርም ያስደስታል…. ከመከላከል አንጻር ካለብኝ ሀላፊነት ገባ የተባለ ግብ ማዳን ደስ ይለኛል …

ሊግ:-  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጥሩ የምትለው ቡድን ገጥሞሃል ..?

ሚሊዮን:– ጥሩ ቡድንን የምገልጸው ከትኩረት ጋር ነውና ለኔ ፋሲል ከነማ አሪፍ ቡድን ነው። ከስብስቡ ጥራት ጋር ጠንካራ እንደሆነ ይሰማኛል። በተወሰነ መንገድ ሜዳው አልተመቻቸውሞ ይሆናል እንጂ ጥሩ ናቸው። ከአጨዋወት አንጻር ምርጫዬም ናቸው።

ሊግ:- ቅዱስ ጊዮርጊስ የዋንጫ ተፎካካሪ ነው ብለህ ታምናለህ..?

ሚሊዮን:- ቅዱስ ጊዮርጊስም ጥሩ ቡድን ነው። ዋንጫ ሊወስድም ይችላል። አንድ ጨዋታ ቢሆን ዕድል ይባል ነበር ግን አመቱን ሙሉ ተጫውቶ ውጤታማ ከሆነ ችሎ ስለሆነ ጠንካራ አይደለም ማለት አይቻልም። ጊዮርጊሶች ዋንጫ ደግመው ካነሱ አስራ አምስታችንም ለቀጣይ አመት በርትተን እንድንመጣ ያደርጋል እንጂ ቅሬታ አይፈጥርም። በነገራችን ላይ በርግጥ ከቤስት 11 አብዛኛው ለቋል ግን በነሱም ደረጃ የፈረመ የለምም ይባል ይሆናል። ሌሎቹም የነበሩት ቤስት አይደሉም እንጂ ወደ ሌሎች ክለቦች ቢሄዱ ቋሚ የሚሆኑ ናቸው። እነሱ አሁንም ቦታ አግኝተው እነተጫወቱ ናቸው። ይሄ መረሳት የለበትም። ግን አምና እያፈራረቀም ይጫወት ነበር። እነ ምኞትና ጋቶችን እያረፉ ሌሎቹ ይገቡ ስለነበር አሁን ስለወጡ ክለቡ አይጎዳም። ጥሩ ተፎካካሪ እንደሚሆን ርግጠኛ ነኝ። ያሉትም ተጨዋቾች ክፍተቶችን መሸፈን የሚችሉ ይመስሉኛል።

ሊግ:- የእግር ኳስ ስኬት ዋንጫ ነው የሚሉ አሉ… አይ ስኬት በተጨዋችነት ዘመን ጥሩ ግልጋሎት በመስጠትና በታማኝነት ነው የሚሉ አሉ …ለሚሊዮንስ ስኬት ምንድነው….?

ሚሊዮን:- እንደኔ እምነት ደግሞ የዋንጫ ስኬት ለክለቡ ነው። የተጨዋች ስኬት ከታች ወረዳ ዞን ከተማ ክልል ብሄራዊ ሊግ ከፍተኛ ሊግ  ፕሪሚየር ሊግ ወጥቶ ፕሮፌሽናል ደረጃ መድረስ ዋሊያዎቹን ማገልገል እያለ የሄደ ዕድገት ለኔ ስኬት ነው። ራሱን ወደ ከፍታ መምሬት ነው ስኬት ለኔ…

ሊግ:- የውጪ ዕድል  አልነበረም ..?

ሚሊዮን:- አምና ለቻን ውድድር  በሄድኩበት ጊዜ እድል አግኝቼ  ነበር። የፈለገኝ ክለብ ቪዲዮ ፈልጎ ሳልዘጋጅ በመሄዴ ሳይሳካ ቀርቷል … የዝውውር መስኮቱ ሊዘጋ 3 ቀን ብቻ በመቅረቱ በዚህ ቀን ውስጥ ማዘጋጀት ባለመቻሉ እድሉ አምልጦኛል። በርግጥ ትምህርት ሆኖ አልፎኛል ተዘጋጅቶ መጓዝ የግድ ነው። ቀጣይ እድሉች እንደሚመጡም ተስፋ አደርጋለሁ…

ሊግ:- ውጪ ወጥቶ መጫወት የማይፈልጉ ተጨዋቾች ገጥመውኛልኮ

ሚሊዮን:– እነሱ ካላቸው አቅምና የፍላጎት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። እኔ ግን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በመጫወቴና ወጥቼም በመጫወቴ ፕሮፌሽናል ከሚባሉት ተጨዋቾች ጋር የመተያየት እድል አግኝቻለሀና ተጫውቼ ስላየሁ ጥሩ ልሆን እንደምችል ተረድቻለሁ። ተመሳሳይ አጋጣሚም ካገኘሁ ለመጠቀም ዝግጁ ነኝ።

ሊግ:- እስካሁን በተካሄዱ የሰባት ሳምንት ጨዋታዎች ያበሳጨህ ውጤት አለ..?

ሚሊዮን:– ተሸንፈን ነጥብ የጣልነው በሁለት ጨዋታዎች ነው። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በባህርዳር ከተማ ነው የተሸነፍነው … የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት ያገኘነውን የፍጹም ቅጣት ምት ዳኛው ከልክሎን ነው። የባህርዳር ከተማም ሽንፈት አይገጥመንም ነበር። አቻ የምንወጣበት የገባ ግብ ዳኛው ሽሮብን ነው የተሸነፍነው ..ዳኛው ግብ ነው ብሎ የባህርዳር ከተማ ተጨዋቾች ጫና ሲያደርጉበት ግቧን በመሻሩ ተሸንፈናል። ሁለቱም አበሳጭተውኛል. ዳኝነቱ መታሰብ አለበት በዳኞቹ ስህተት ነጥብ ማጣት መቆሞ አለበት…።

ሊግ:-  ከጨዋታው በኋላ ቪዲዮውን ስታየው ግቡ ገብቷል ….? ርግጠኛ ነህ..?

ሚሊዮን:- አዎ በደንብ ገብቷል። በረኛው ይዞት መረቡን ሲነካ ነው ኳሷን የለቀቀው .. እሱ ከለቀቀው በኋላ ነው መስመር ላይ ኳሱ የነጠረው እንጂ መስመር አልፏል። ኳሷ ውስጥ መሆኗ መታወቅ አለበት …ረዳት ዳኛው አይቶ በምልክት ነግሮት አጽድቆት ደስታችንን ከገለጽን በኋላ ነው የሻረው። በዚህ ቅር ብሎኛል።

ሊግ:– የመሃል ዳኛው ግብ ነው አለ …ባህርዳሮች ደግሞ ረዳቱ ይጠየቅ አሉ። ተጠየቀ አልገባም በማለቱ የመሃል ዳኛው ግቡን ሻረ ..ያለው እውነት ይሄ አይደል ..?

ሚሊዮን:- የሚገርም ነገር ልንገርህ …ዳኛውና ረዳቱ ሲያወሩ አጠገባቸው ነበርኩ… የመሃል ዳኛው ገብቷል ወይ ሲለው ረዳቱ አዎ ገብቷል አለ… ርግጠኛ ነህ አይደል ሲለው ተጠራጠረና የገባ አልመሰለኝም አለው። ያኔ ነው የሻረው. እንጂ መጀመርያ ረዳቱ ግብ ነው ብሎ አሳይቶታል … በባህርዳር ከተማ  ተጨዋቾች ጫና የተሻረ ግብ ነው። ከጨዋታው በኋላኮ አንተ ነህ ያሳሳትከኝ ሲባባሉ እንደነበር ሰምቻለሁ።  በርግጥ አጠገባቸው አልነበርኩም።

ሊግ:- በዲ.ኤስ. ቲቪ አለም እያየው የሁለታችሁም ቡድኖች ተጨዋቾች መሃል  የታየው ስነምግባር የለሽ ድርጊት ግን አያስተችም ..?

ሚሊዮን:- እውነት ነው ተገቢ አይደለም… ነገሩን የቀየረውን ግን ማወቅ አለብን። ጎል ብሎ ደስታችንን እየገለጽን እያለ ዳኛውን ቀድመው አመናጨቁት.. በአገሪቱ ትልቅ ሊግ ላይ ተጨዋች ሲያመናጭቅህ ውጤት የምትቀይር ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ያኔ ነው ስለጮሁብህ እንዴት ውጤት ትቀይራለህ በሚል የተጨዋቾቻችን ቅሬታ ወደ ቁጣ የተቀየረው.. ዳኝነትን በተመለከተ ዋናና ረዳቱ ተስማምተው ያጸደቁትን ነገር መቀየር ተገቢ አይደለም። ያን ማስተካከል አለባቸው ድርጊቱ  ልክ ባይሆንም ከእኛ ይልቅ የነሱ ድርጊት ልክ አይደለም። ጨዋታውን  አቁመን ነው ፍትህ የጠየቅነው…

ሊግ:- በባህርዳር ከተማ ተጨዋቾች ተቃውሞም ነው የቀየረው እንጂ በረዳቱ አይደለም እያልክ ነው..?

ሚሊዮን: አዎ….  የዳኛው ውሳኔውን የቀየረው በባህርዳር ከተማ ተጨዋቾች ጫና እንጂ  ረዳቱ አይደለም … በዚህ ርግጠኛ ነኝ…  ምናልባት ሃይላይቱን አይተው ግብ መሆኑን ሲያውቁ ሊደብራቸው ይችላል። ለኛ ግን ለውጥ አላመጣም።

ሊግ:- ቫር ያለበት ሀገርም ዳኞች እየተሳሳቱ ነው ..ለኛ ሀገር ዳኞች አይከብድም ታዲያ…?

ሚሊዮን:- እግር ኳስ ከነስህተቱ ነው የሚያምረው በሚለው አምናለው። አለበለዚያ ጣዕም የለውም። እዚህ ግን ይለያል …ዳኛው ተሳስቶ ግብ ያልሆነውን ለኛ አጸደቀ ይባል ድጋሚ ተሳሳትኩ ብሎ ግን ግቡን መሻሩስ ምን ይባላል..? /ሳቅ/ አንድ ነጥብ ለኛ ትልቅ ነው። በዳኛ መነጠቅ ያበሳጫል…

ሊግ:– በቀይ ካርድ ወጥተህ ያልተቀበልከው የዳኛ ውሳኔ ገጥሞሃል …ቦታህ ለቀይ ካርድ ያጋልጣልና …?

ሚሊዮን:- በመሃል ተከላካይነት ስጫወት በተለይ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ሁለቴ በቀይ ካርድ ወጥቻለሁ። የወጣሁት በትክክለኛ ጥፋት ስለሆነ አልተቃወምኩም። አምኜ ነው የወጣሁት ቅሬታ የለኝም።

ሊግ:– በእስካሁኑ ጨዋታዎች ፕሪሚየር ሊጉን እንዴት አገኘኸው..?

ሚሊዮን:– ጠንካራ ፉክክር ይኖራል። በእስካሁኑ ግን ወራጁ ሁለት በመሆኑ በተወሰነ መልኩ ቀዝቀዝ አድርጎታል … ብዙዎቹ ቡድኖች ለዋንጫ የሚጫወቱ ናቸው። ልዩነቱ 3,4, ሰፋ ካለ 5 ነጥብ ብቻ በመሆኑ ጥሩ ፉክክር እጠብቃለሁ። የዋንጫ ፉክክሩ እስከ መጨረሻ ሳምንት ድረስ የሚሄድ ይመስለኛል። አምናና ካቻምና የነበረው የሁለት ክለቦች የዋንጫ ፉክክር ዘንድሮ ቁጥሩ የሚጨምር ይመስለኛል። አብዛኛው ክለብ ራሱን አጠናክሮ ነው የመጣው… እና ሊጉ ጥሩ ፍልሚያ የሚኖርበት ይመስለኛል።

ሊግ:– በቦታህ ከሀገር ውስጥም ከውጪም ምርጫህ ማነው..?

ሚሊዮን:- በመሃል ተከላካይ ቦታ በሀገር ውስጥ. የፈቱዲን ጀማል አድናቂ ነኝ…  አብሬው ብጫወት የምለውም ፈቱዲንን ነው። በመሃል ተከላካይነት አብረን አልተጫወትንም። ልምምድ ነው የሰራነው … በመሃል ተከላካይነት ከሱ ጋር ተጣምሬ ብጫወት ደስ ይለኛል። ከውጪ ግን የስፔናዊው ሰርጂዮ ራሞስ አድናቂ ነኝ። አሁንም ወደፊትም የሱ አድናቂ ነኝ..

ሊግ:-  ስለ ዋሊያዎቹ እናውራ.. የነበረህን ቆይታ እንዴት ታየዋለህ…?

ሚሊዮን:- ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። እኔን ጨምሮ ሀገርን መወከል የሁሉም ተጨዋች ህልም ነው ብዬ አስባለሁ። ህልሜን እንዳገኘው የረዳኝን ፈጣሪን አመሰግናለሁ… በቡድኑ ውስጥ ውጤት ሲመጣም ሆነ ሲጠፋ በመመረጤ ብቻ ደስተኛ ሆኜ ነው። በዚያ ላይ ሀገርህን የመወከል አቅም አለህ ብሎ አሰልጣኙ ሲያምንብህና ሲጠራህ የበለጠ ደስ ይላል …. በአጠቃላይ ቆይታዬ ደስተኛ ነኝ። በቀጣይም ከአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ጋርም እንደምሰራ ተስፋ አደርጋለሁ…

ሊግ:- ለቲየሪ ኦነሪ አርሴን ቬንገር ካልን ለሚሊዮን ሰለሞንስ..? እነማንስ አሰልጥነውሃል…?

ሚሊዮን:– /ሳቅ/ የተወለድኩበት አካባቢ እያለሁ ኳስ ያስጀመረኝ አሰልጣኝ ነበር ኢያሱ ቡናሬ /ካምፓላ/ ይባላል… እግር ኳስ መጫወት ብፈልግም ጎበዝ ተጨዋች ሆኜ አሁን የደረስኩበት ደረጃ እደርሳለሁ ብዬ አላስብም ነበር። ያኔ ግን አቅም አለህ መጫወት አለብህ። ትልቅ ደረጃ ትደርሳለህ ብሎ ራሴን ሳላምን እኔን ያመነና እየያዘኝ እየሄደ ኳስ ያስቀጠለኝ አሰልጣኝ ነው። በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ….ከዚያ ውጪ ጥሩ የተባሉ አሰልጣኞች ገጥመውኛል… በክለብ ደረጃ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ፣ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ፣ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ፣ አሰልጣኝ  አሰራት አባተ በዋሊያዎቹ  ሃላፊነት አሰልጣኝ ውበቱ አባተን በአጠቃላይ ማመስገገን እፈልጋለሁ….

ሊግ:-  አመሰግናለሁ….

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P