ተወልዶ ያደገው ጅማ ከተማ ልዩ ስሙ መርካቶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው…. “እረፍት ሲኖረኝ በቀጥታ የምጓዘው ወደ ጅማ ነው ጅማ ካለችው እናቴ ጋር የማሳልፈው እረፍት ያስደስተኛል እናቴን በጣሞ እወዳታለሁ ረጅም እድሜም እመኝላታለሁ” የሚለው እንግዳችን በታሪኬ ከአንድ ዋንጫ ውጪ ሁሉንም ዋንጫ አንስቻለሁ የቀረኝን የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ከመቻል ጋር ለማንሳት አቅጃለሁ” ሲል ይናገራል…. ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቆይታ ያደረገው የመቻሉ ምንይሉ ወንድሙ ለቀረቡለት ጥያቄዎች የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል….
ሊግ:- አመሰግናለሁ ለመልካም ፍቃደኝነትህ….እስቲ አሳካዋለሁ የምትለው ግብህ ምንድነው ..?
ምንይሉ:- ያለምንም ጥርጥር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማሸነፍ ትልቁ ግቤ ነው …ለብሄራዊ ቡድን ተጫውቻለሁ…የምፈልጋቸውን አግኝቻለሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የተዘጋጁ ዋንጫዎችን አንስቻለሁ….የቀረኝ ዋና የምለው የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫን ነው…ይህንን ለማሳካት ከመቻል ጋር የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ የዘንድሮ ግቤ የሊጉን ዋንጫና ዋንጫ ማንሳት ብቻ ነው…. በነገራችን ላይ ሁለት የውጪ እድል መጥቶልኝ በጉዳት አልተጠቀምኩም እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ወደፊት ይመጣል ብዬ አስባለሁ መለወጥ የተሻለ ነገር ካገኘሁ እጠቀምበታለሁ ዋናው ግቤ ግን የሊጉን ዋንጫ መውሰድ…./ሳቅ/
ሊግ:- ምርጡ ጊዜህ የት እያለህ ያለው ነው…?
ምንይሉ:- መከላከያ….በ2011 የነበረኝ ቆይታ የተጨዋችነት ዘመኔ ምርጡ ጊዜ የምለው ነው…መሃል ላይ የተፈጠረ ችግር ቢኖርም….በነገራችን ላይ አሪፍ ዘመኔ ያልኩት ብዙ ነገር የተማርኩበት በመሆኑ ነው። አቋሜ ምርጥ በሚባልበት ጊዜ ጉዳት አጋጥሞኛል ያ የጉዳት ጊዜ ለኔ ምርጡ የተማርኩበት በመሆኑ አሪፍ ጊዜዬ እንደሆነ ይሰማኛል.በጣም የተማርኩበት በመሆኑ የኔ ምርጥ ጊዜ የተጎዳሁበት ጊዜ ነው”
ሊግ:- ምርጡ አቋምህ አለፈ..ወይስ እንጠብቀው..?
ምንይሉ:- ገና ወደፊትም ይመጣል…ከዚህ የተሻለ አቋሜን ማሳየትም እፈልጋለሁ እችላለሁም ራሴ ላይ መስራት ከቻልኩ አሪፍ ጊዜ ከመቻል ጋር ከፊቴ ያለው ነው …
ሊግ:- መቻል ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ነው…ውስጣችሁ ዋንጫ ዋንጫ አላለም..?
ምንይሉ:- አመቱን ስንጀምርም ሃሳባችን ዋንጫ ማሸነፍ ነው …አሁን ፊት ለፊት የሚገጥመንን ቡድን ማሸነፍና በድሉ ወደ ዋንጫው መቅረብን አልመናል… ቀሪ 11 ተጋጣሚ አለ በየግጥሚያው ማሸነፍ ላይ አልመን ተነስተናል፡፡
ሊግ:- ቅዳሜ ከፊት ለፊታችሁ ያለው ዋነኛ ተቀናቀቃኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው …ምን ውጤት ይጠበቅ..?
ምንይሉ:- አንደኛ ዙር ላይ ሳንሸናነፍ አቻ ወጥተናል አሁን ደግሞ አንደኛና ሁለተኛ ሆነን የምናደርገው ጨዋታ ነው..በእኛ በኩል ማንንም ለማሸነፍ ተዘጋጅተን ነው የምንገባው..ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ላይ ተፎካካሪያችን ነው እሱን ለማሸነፍና ከፍ ለማለት ተዘጋጅተናል… ሁሉም ክለብ ለዋንጫ ነው የሚያልመው…ጊዮርጊስም በተመሳሳይ …እንደ ትልቅ ቡድንነቱ ተዘጋጅተን እንጠብቀዋለን፡፡
ሊግ:- ሁሉም ቡድን ስትል …16ቱም ክለቦች ዋንጫ ያልማሉ እያልከኝ ነው …?
ምንይሉ:- አዎ…ሁላችንም ክለቦች አመቱን ስንጀምር ከዜሮ ስለምንነሳ ሁሉም ዋንጫ አልሞ ይጀምራል ይሄ እውነት ነው፡፡
ሊግ:- ቅዱስ ጊዮርጊስንም ይሁን አምበሪቾ ዱራሜን ስትገጥሙ እኩል ነው ዝግጅታችሁ..?
ምንይሉ:- አዎ ለቅዱስ ጊዮርጊስም ይሁን ለአምበሪቾ እኩል ነው የምንዘጋጀው ….ምክንያቱም ወረቀት ላይ ባለ ስም ሳይሆን ሜዳ ላይ ባለ አቋም በ90 ደቂቃ የሚታይ ነው.. ..ትንሽ ትልቅ እያልን አንዘጋጅም…ሁሉም ጨዋታ እኩል ነው የሊጉ መሪ የነበረውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሸንፈንኮ በሀድያ ሆሳዕና ተሸንፈናል…ይሄ የሚያሳየው ለሁሉም ተጋጣሚ እኩል ተዘጋጅተን መግባት እንዳለብን ነው…
ሊግ:- ከአምናው መቻል የዘንድሮው በምን ይለያል.?
ምንይሉ:- እንደ ቡድን ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ልምድ ያላቸው ቡድናችንን ተቀላቅለዋል ..የአሰልጣኞች ስብስብም ጠንካራ በሆኑ ባለሙያዎች ተጠናክሯል.. የስነ ምግብ ባለሙያ የቪዲዮ አናሊሲስ የሚሰጥ ባለሙያ ሁሉ አለን በትክክል ተጠናክሮ የተዘጋጀ ቡድን ሆነናል የቦርዱ አባላትም በጣሞ ጠንካራ ሰዎች በየስራ ዘርፋቸው በሚጠሩ ተዋቅሯል…የዘንድሮው ስብስባችን ጠንካራ ሆኗል የምንለው በዚህ ምክንያት ነው…
ሊግ:- ከ19ኙ ጨዋታዎች ስታሸንፍ የተደሰትክበት ስትሸነፉ የተበሳጨህበት ግጥሚያ የትኛው ነው …?
ምንይሉ:- ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ በወቅቱ የሊጉ መሪ የነበረውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ስናሸንፍ በጣም ተደስቻለሁ … በዚያ ላይ ግብ ማስቆጠሬ ደስታዬን ጨምሮታል…ሽንፈት ሲገጥመኝ የተበሳጨሁበት በኢትዮጵያ ቡና ስንሸነፍ ነው… እኛን በማይመጥን መልኩ ነው የተሸነፍነው..ጠንካራ ስብስብ ይዘን ያ ሁሉ ግብ ሲቆጠር ያማል አበሳጭቶኛል….
ሊግ:- ሽንፈት ሲገጥማችሁ ሰራዊቱ በውስጥህ ይመጣል ..?
ምንይሉ:- መቻል የሚወከለው እንደ ክለብ ሳይሆን እንደ ሀገር ነው…የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ያሉበት የወታደሮች ቡድን ነው …የኢትዮጲያ የመከላከያ ሰራዊት ደግሞ ሀገር ጠባቂ ነው … ለአንድ ወገን የቆመ ሃይል አይደለም የሁለም መተማመኛ ነው ነውና በኔ በኩል መቻል እንደ አንድ ክለብ አላየውም ከ2006 ጀምሮ ከታችኛው የመቻል ቡድን ያደኩ እንደመሆኔ ለኔ ትልቅ ትርጉም ያለው ክለብ ነው። መቻል ሲሸነፍ የሚሰማኝ ስሜት ከባድ ነው
ሊግ:- ስለ መቻል ደጋፊዎች ምን ትላለህ…?
ምንይሉ:- ለመቻል ደጋፊ ትልቅ ፍቅርና ክብር አለኝ ወታደሩ ደጋፊያችን ነው በሜዳ ላይ መጥቶ ባይደግፉንም ካላቸው ደመወዝ ላይ ቆርጠው የሚከፍሉ ናቸው ሜዳ ላይ አንዳንዴ ተገኝተው ስታያቸው ስሜትህን ይቆጣጠሩታል። ወታደር ማለት ሀገር የሚጠብቅ ነው ሀገር ጠባቂው መጥቶ ሲደግፍህ ደግሞ የሚሰማህ ስሜት አለ በጣም እወዳቸዋለሁ፡፡
ሊግ:- የድሬዳዋ ስታዲየም ተመቻችሁ..?
ምንይሉ:- አዎ …. በጣም ጥሩ ሜዳ ነው ግን ጉልበት ይጠይቃል ጎማም ስለሆነ ከአዲስነቱ ጋር ተያይዞ አቅም ይፈትናል ያም ሆኖ ሰበብ የማታበዛበት ሜዳ ነው። ኳስ የሚችል ተጨዋች የሚጫወትበት ሜዳ ነው ብዬ አስባለሁ…
ሊግ:- የእውነት የሚሰማህን መልስልኝና የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን ቅጣት ትክክል አይደለም ..?
ምንይሉ:- የእውነት ነው የምመልሰው…ተገቢ ቅጣት ነው ብዬ አላምንም..የዚህን ያህል የተጋነነ ነገር አልነበረም አለመባባቶች ሊፈጠር ይችላል ሲጨርሱ ግን ተግባብተው እንደሆነ ነው የማውቀው… ያን ያህል ይቀጣል ብዬ አልጠበኩም ..ያው ቅጣቱ ሁለት ጨዋታ ይቀራል ውሳኔው በጣም ከባድ ነው፡፡
ሊግ:- ፕሪሚየር ሊጉን ጠንካራ ነው ማለት ይቻላል..?
ምንይሉ:- አዎ ጠንከር ብሏል… ብዙ ቡድኖች የዋንጫ ተስፋ ይዘው የሚወዳደሩበት ሊግ ነው በክለቦቹ መሃል ያለው ልዩነቱም የሰፋ ነው ማለት አይቻልም ክለቦች ጠንክረው መጥተዋል ጥሩ ፉክክርም ነበር… የመዋሃድና ያለመዋሃድ ክፍተት እንዳለ ሆኖ ጥሩ ቡድኖችም አሉ..
ሊግ:- መቻል 39 ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እኩል 37 ነጥብ ይዘዋል ከናንተ ውጪ ዋንጫው ለሌሎቹ ክለቦች ክፍት ነው ማለት ይቻላል…?
ምንይሉ:- ገናኮ 11 ጨዋታ አለ….33 ነጥብ ከፊታችን እያለ የዋንጫ ፉክክሩ በሶስታችን ክለቦች ብቻ የሚካሄድ ነው ብዬ አላምንም… እነ ሌስተር ሲቲ የእንግጎሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ሲያነሱ ማን ጠበቀ..? እግርኳስ ነው ምን እንደሚፈጠርበት አይታወቅም የዋንጫ በሩ ለሁሉም ክፍት ነው ትልቅ ትግልና ፉክክር የሚጠበቀው ከአሁን በኋላ ባለው ይመስለኛል..
ሊግ:- ለአንተ በቦታህ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ምርጡ ማነው ….?
ምንይሉ:- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቦታዬ ምርጡ ጌታነህ ከበደ ነው ከውጪ ደግም ክርስቲያኖ ሮናልዶ ምርጫዎቼ ናቸው……
ሊግ:- አብሬ ብጫወተው የምትለው ተጨዋች ማነው..?
ምንይሉ:- በፊት በፊት አብሬው ብጫወት ብዬ ከምመኘው ሽመልስ በቀለ ጋር የመጫወት እድል አግኝቻለሁ…ከርሱ ጋር እየተጫወትኩ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ…ዘንድሮ ጥሩ የመሆኔ ምክንያት እሱ ነው ከሱ ብዙ ኳሶችን አግኝቻለሁ … አሁንም ደግሞ ከሱ ጋር አብሬ ብጫወት ብዬ የምመኘው የሀዋሳ ከተማው ታፈሰ ሰለምን ጋር ነው እንደሚሳካልኝም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሊግ:- የውጪ ኳስ ትከታተላለህ…..ወይስ. ..?
ምንይሉ:- የውጪ ኳስ እከታተላለሁ ኳስን በጣም ነው የምወደው። የማን.ዩናይትድ ደጋፊ ነበርኩ አሁን እንደ ድሮው ተከታትዬ አላይም ሌሎች ኳሶችን ግን በደንብ አያለሁ፡፡
ሊግ:- ቲየሪ ኦነሪ ብለን አርሴን ቬንገር ካልን ምንይሉ ወንድሙ ብለንስ ..?
ምንይሉ:- ገብረመድህን ሃይሌ…
ሊግ:- እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለሀገርህ ምን ትመኛለህ….?
ምንይሉ:- ሰላም .. ወጥቶ ለመጎባት እግርኳስ ለመጫወት ስለ እግርኳስ ለማውራት ሰላም ወሳኝ ድርሻ አለውና ሰላም መቅደም አለበት …አንዱ በአንዱ ላይ ክፉ እንዳያስብና መደጋገፍ እንዲበዛ እመኛለሁ ሀገሪቷ ወደተሻለ ጎዳና እንድትጓዝ ሁሉም በጋራ እንዲነሳ እመኛለሁ…
ሊግ:- የምታመሰግነው ካለ…..?
ምንይሉ:- ፈጣሪዬንና እናቴን በጣም አመሰግናለሁ…