Google search engine

“በጣም የምጠላው ቋንቋና የማልጠራበት ስም ቢኖር ሰርሳሪ የሚለውን ነው” “አሁን ያለንበት 7ኛ ደረጃ እኛን አይመጥነንም ወደላይ ከፍ ለማለት ለእኛ አልረፈደም” አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ /ማሜ/ (ኢትዮጵያ ቡና)

ተወልዶ ያደገው ነገሌ ቦረና ውስጥ ነው …. የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑን በፕሮጀክት ጀምሮ ወደ ክለብ አቅንቶ የተጫወተው የመጀመሪያው ክለቡ አየርሃይል ነው፡፡ በአየር ሃይል የሶስት አመት ቆይታ  ክለቡን የብሄራዊ ሊግ ባለድል አድርገው ወደ ፕሪሚየር እንዲያድግ ካደረጉ ተጨዋች መሃል ይጠቀሳል… በ1998 ከአየርሃይል ጋር የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመት ያሳለፈው እንግዳችን ወደ ሀዋሳ ከተማ አቅንቶ በወቅቱ ውዝግብ ቢኖርበትም የሊጉን ዋንጫ አንስቷል… ሻሸመኔ ከተማ፣ ደቡብ ፖሊስ፣ ሲዳማ ቡናና ሰበታ ከተማ እስከ 2007 ተጫውቶ የእግር ኳስ ህይወቱን አጠናቋል… ሰበታ ከተማን በገጠመው ጉዳት ለቅቆ ወደ ነገሌ ቦረና አቅንቶ ከአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ጋር እንደ ተጨዋችም እንደ ረዳት አሰልጣኝ ጋር ሆኖ የአሰልጣኝነት ህይወቱን ጀመረ፡፡ እንግዳችን የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ /ማሜ/ … ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ ደርቢው ድልና ስለደስታ አገላለጹ፣ ስለተጨዋችነትና አሰልጣኝነት ህይወቱ፣ ስለክለቡ ደጋፊዎች፣ ስለ ፕሪሚየር ሊጉ ፉክክርና ሌሎች ጉዳዮች ለቀረቡለት ጥያቄዎች የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።

ሊግ:- በተጨዋችነት ዘመንህ ለአንተ በቦታህ ምርጡ ማን ነበር..?

ነጻነት/ማሜ/:- ምናልባት የሀገርህ ልጅ ስለሆነ እንዳልባል እንጂ በኔ ቦታ በሃይሉ ደመቀ ምርጫዬ ነበር፡፡ እያየሁት ነው ያደኩት .. ለስፖርት ቤተሰቡም አዲስ ስምም አይደለም ሀዋሳ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስም ተጫውቷል…

ሊግ:-  በነገሌ ቦረና የተጀመረው የአሰልጣኝነት ህይወትህን እስቲ አስታውሰን..?

ነጻነት/ማሜ/:- ነገሌ ቦረና እያለሁ ግማሽ አመት ላይ ተጨዋችነቱን አቁሜ በሙሉ ምክትል አሰልጣኝነት መስራት ጀመርኩ። ብሄራዊ ሊግ የሚለው አጠራር ወደ ሱፐር ሊግ ሲቀየር ነገሌ ቦረናም አደገ፡፡ ያኔም አሰልጣኝ አብዲ ወደ ቡራዩ ከነማ ሲሄድ እኔ ሙሉ ሃላፊነቱ ተሰጥቶኝ ከ2008- 2011 ድረስ ክለቡን አሰለጠንኩ… ከዚያ 2012  መጨረሻ አካባቢ የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ሆኜ ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር ታንዛኒያ ባስተናገደችው የሴካፋ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ነበርኩ.. ከዚያ መልስ ሲዳማ ቡናን ግማሽ አመት አሰልጥኜ ወደ ወልቂጤ ከተማ አቀናሁና ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና  ጋር ግማሽ  አመት ሰርቼ አሰልጣኝ ተመስገን ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሲያቀና አብሬው ተጓዝኩ… እናም ያለፉትን ሁለት አመታት በኢትዮጵያ ቡና እገኛለሁ…

ሊግ:- ምርጥና ታማኝ ረዳት አሰልጣኝ በመሆንህ ለምክትልነት ሲወስዱህ አልፈሩም…?

ነጻነት/ማሜ/:-  በጣም የምጠላው ቋንቋና የማልጠራበት ስም ቢኖር ሰርሳሪ የሚለው ነው…. ወደፊትም በዚህ ባህሪ አልታወቅም፡፡ ከማንም ጋር ልስራ ስራው የሚፈልገውን እገዛ ከማድረግ ውጪ ምንም አላደርግም፡፡ የእውነትም ረዳት መሆን ነው የምፈልገው… ከአሰልጣኝ ተመስገን በኋላኮ አሰልጣኝ ዮሴፍ መጥቶ አብሬው ሰርቻለሁ፡፡ በቅርቡ መጥቶ የሄደውም ሰርቪያዊው አሰልጣኝ ሲመጣ በደንብ ለማገዝ ስሞክር ቆይቻለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ሌላ አላስፈላጊ ባህሪ አይኖረኝም፡፡ እግር ኳሱም ይሄን አይፈልግም… ነገም ተመሳሳይ እድል ሳገኝ የሚገጥመኝ ረዳት የዘራሁትን ነው የማጭደውና በዚህ በኩል አልገኝም… በስራ ድርሻዬ ልክ እሰራለሁ አግዛለሁ ዋና አሰልጣኙ አለቃዬን ታማኝ ሆኜ ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡ ምናልባት የሀሳብ ልዩነት ቢኖርም በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር ልዩነት በመፍታት አምናለሁ፡፡

የሊግ:- ማሜ በብዛት የምትጠራበት ስም ነው የመታወቂያው ደግሞ ነጻነት ….. ምንድነው ልዩነቱ…?

ነጻነት/ማሜ/:- /ሳቅ/ የመታወቂያ ስሜ ነጻነት… ይባላል፡፡ ማሜ የሚለው ደግሞ በሰፈሬ ባደኩበት አካባቢ ጀምሮ የምታወቅበት የቅጽል ስሜ ነው፡፡ በተለይ ይሄ ትውልድ ተወልጄ ባደኩበት ነገሌ ቦረናን ጨምሮ የምታወቀው በማሜ ነው፡፡ ከተወለድኩበት ስወጣ መጠሪያ ስሜ ራሱ ማሜ ቦረና ነው… ከልጅነት ጀምሮ ማሙሽ ነበር ከዚያ አብዛኛው ሰው ማሜ እያለኝ ይጠራኛል፡፡ እዚያ አካባቢ በተለይ  ነጻነት የሚለውን ማንም አያውቀውም፡፡ እንደ መታወቂያ ሁለቱም ስሞች ቢመቹኝም በይበልጥ ማሜ የሚለው ለምጄዋለሁ ይበልጥም ይመቸኛል፡፡

ሊግ:- የደርቢውን ጨዋታ ማሸነፍ  ከቻሉ አሰልጣኞች መሃል አንዱ አንተ ነህ… አርቢትሩ የጨዋታው መጠናቀቅን የሚያበስረው ፊሽካ ሲነፋ ግብ እንዳስቆጠረ ተጨዋች ወደ ላይ ዘለልክ …. የድሉ ስሜት ወይስ የነበረብህን ጫና እያራገፍክ…?

ነጻነት/ማሜ/:-… /ሳቅ በሳቅ/ ዕድሉ በብዙ መንገድ መመልከት ይቻላል… አንደኛ ውጤት ርቆን ደጋፊዎቻችንን አስከፍተናቸዋል… ባለፉት ሁለት ሳምንታት ደስተኛ አለመሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ጫናም ስለነበረ ከጫናው መውጣት እንዳለብን እንረዳለን፡፡ ሳምንቱን ሙሉ በስነልቦና ደረጃ ከ16ቱ ክለቦች አንዱ ነው፡፡ መሸነፍ የሚችልም ቡድን ነው በሚል እየተነጋገርን ስለነበር ያ መሳካቱ ትልቅ ደስታ ፈጥሯል። ዋናው ግን ደርቢ ነው፡፡ በደርቢ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሸነፍን 3 አመት ሞልቶናል፡፡ ይሄን ደካማ ታሪካችንን ለመሻር  በመቻላችን ደጋፊዎቻችን ላይም ደስታ ስናይ ድሉን የተለየ ያደርገዋል… በአጠቃላይ ከእግዚአብሄር ጋር ውጤታማ በመሆናችን ተደስቻለሁ …. በነገራችን ላይ ከጨዋታው በኋላ ፊልሙን ስመለከት በአጨፋፈሬ ስቄያለሁ፡፡ ለካ ደስታ ሲሰማህ የተለየ ስሜት ከውስጥህ ይመነጫል፡፡ የጠበቅነውን ስላገኘን ደስታችን ልዩ ነበር፡፡ ተጨዋቾቼ ካላቸው 100 ፐርሰንት በላይ አውጥተው በመጫወታቸው በዚሁ አጋጣሚ አመሰግናቸዋለሁ ።

ሊግ:- ከሀዋሳ ከተማ ጋር ጨዋታ አላችሁ… ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፋችሁ ስለመጣችሁ ሀዋሳዎች በከባድ ዝግጅት ውስጥ ሆነው ይገጥሙናል የሚል ስጋት የለባችሁም…? /ቃምልልሱን የሰራነው ረቡዕ ዕለት ነው/

ነጻነት/ማሜ/:- ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈናል አበቃ፡፡ የዚያን ቀን ደስታችኝ ያኔውኑ ጨርሰን በነጋታው ከሀዋሳ ከተማ ጋር ስላለብን ጨዋታ ነው መዘጋጀት የጀመርነው…. መታወቅ ያለበት ይሄ ቡድን አቅም አለው… አሁን ያለንበት 7ኛ ደረጃ እኛን አይመጥነንም፡፡ ወደላይ ከፍ ለማለት ለኛ አልረፈደም… እያንዳንዱን ጨዋታ ትኩረት ሰጥተን  ልክ እንደ ዋንጫ ጨዋታ መጫወት አለብን፡፡ ፍላጎት ጥረት ከእኛ ያስፈልጋል አሁን ያለው ስሜት የአንድ ጨዋታ ውጤትና ስሜት ብቻ እንዲሆን አልፈልግም፡፡ ከረዳቶቼና ተጨዋቾቼ ጋር በመሆን በክፍተቶቻችን ላይ ሰርተን ቡድናችንን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ እንጥራለን፡፡ በግሌ አንድም ጨዋታም ልምራ ሁለትም ልምራ ለታሪክ የሚሆን ስራ ለመስራት እጥራለሁ…

ሊግ:- ፕሪሚየር ሊጉን እንዴት  ገመገምከው ….? ባንተ ዕይታ ጠንካራ ነው ቀላል…?

ነጻነት/ማሜ/:- ፕሪሚየር ሊጉ እየጠነከረ የመጣ ነው … በተለይ ዲ ኤስ ቲቪ ከመጣበት አመት በኋላ የሁለት ክለቦች ፍልሚያ ነው የሚለው ነገር የቀረ ይመስለኛል፡፡ በፊት የተወሰኑ ክለቦች ነበሩ የፋይናንስ ጥንካሬ የሚታይባቸው የሚፎካከሩት፡፡ አሁን ግን ተለውጧል፡፡ ብዙዎች ራሳቸውን አጠንክረው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነዋል። በሊጉ ሁለቴ ስታሸንፍ ደረጃህ ከፍ ይላል ስትሸነፍ ደግሞ ደረጃህ እታች ይሆናል… ይሄ የሚያሳየው በክለቦቹ መሃል ያለው ፉክክር ተቀራራቢ መሆኑን ነው… አንድ ጨዋታ ስታሸንፍ አምስት ስድስት ደረጃ ነው የምታሻሽለው፡፡ ስትሸነፍም ወደታች የምትወርደውም በዚያው ልክ ነውና ውድድሩ ጠንካራ መሆኑን ነው የማምነው…

ሊግ:-  ከውጪ አሰልጣኞች የወደድከውና የምትከተለው አሰልጣኝ ማነው..?

ነጻነት/ማሜ/:-  በሀገር ውስጥ ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር በመስራቴ  ደስተኛ ነኝ… ለእኔ የእግር ኳስ አባቴ ልለው እችላለሁ… ከእግዚአብሄር ቀጥሎ በሀገር ደረጃ የመወከል እድል ያገኘሁት በርሱ ስልጠና ሂደትም ብዙ ነገር ተምሬያለሁና በዚህ አጋጣሚም ተመስገንን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ከውጪ ደግሞ የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የየርገን ክሎፕ አድናቂ ነኝ… የርሱ ስልጠናና አካሄዱ ይመቸኛል… በጨዋታ ወቅት ባለው ሽግግርና በፈጣን መልሶ ማጥቃቱ ጊዜ ስለሚከተለው መንገድ ነው የምከታተለው… በጣም ይመቸኛል፡፡

ሊግ:- ራስህን የት ደረጃ ደርሰህ ለማየት ትመኛለህ..?

ነጻነት/ማሜ/:- ትልቁ ስኬት የምለው ጊዜዬ እንደሚመጣ አምናለሁ… ዋናው ያ ደረጃ ላይ ስገኝ ለቦታው የሚሆን ዕውቀት ይዤ ተገኝቻለሁ የሚለውም ነውና በይበልጥ ያን አቅም  መፍጠር ላይ አተኩራለሁ፡፡ በተጨማሪ መፍትሄ ላይ አተኩራለሁ፡፡ ለዚያ የሚሆን እውቀት መሰብሰብ ይመቸኛል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እድለኛ ነኝ፡፡ በመጣሁባቸው መንገዶች ላይ ብዙ እየተማርኩ መጥቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ አሰልጣኞች ስር የራሴን እውቀት ወስጃለሁ፡፡ አጭር ጊዜ ቢሆንም ከውጪ ሀገር አሰልጣኝ ጋር ሰርቻለሁ፡፡ በአጭሩም ጊዜ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ፡፡ ብዙ እውቀት አግኝቻለሁና እነሱንም በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ…

ሊግ:- ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነህ… እስቲ የመሰረትከውን ቤተሰብ አስተዋውቀን…?

ነጻነት/ማሜ/:- ባለቤቴ ወይንሸት ጌታቸው ትባላለች… የመጀመሪያ ልጄ ሄቤሎም ይባላል፡፡ ሄቤሎም ማለት ፍቅር ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው አቤኔዘር ይባላል፡፡ በሁሉም ውጣ ውረድ ውስጥ ከጎኔ ያሉ አበርታቾቼ እነሱ ናቸው፡፡ እንደምወዳቸው መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡

ሊግ:- ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ የምታስተላልፈው መልዕክት አለ….?

ነጻነት/ማሜ/:-  ምንም ጥያቄ የለውም… ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ቡድን ነው … እኔም እግዚአብሄር ፈቅዶ ይህን ትልቅ ቡድን ለአንድ ጨዋታም ቢሆን መምራቴ ዕድል ነው…. እንደኔ ላለ ወጣት፣ እየተማረ ያለ፣ ነገን በትልቅ ደረጃ ለመገኘት እንደሚያልም አሰልጣኝ ቡናን ማሰልጠን መቻሌ ፈተናዎችንም ከዚሁ ጀምሮ የማየት ዕድል ፈጥሮልኛል፡፡ ይህም አድለኛ ያደርገኛል… ደጋፊዎቻችን ደግሞ  ይታወቃሉ..  የኛ ደጋፊዎች ውጤት ኖረም አልኖረም ከሜዳ የማይርቁ ሀይል የሆኑን ናቸው… እንደሚታወቀውም ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ሲኖረው ነው ስታዲየሞቻችን ሞላ የሚሉትና እነሱን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ እነሱ ውጤት ይፈልጋሉ፡፡ ምክንያቱም ያለ የሌላቸውን ሰውተው የሚደግፉን በመሆናቸው ይለዩብኛል፡፡ ሰው ታሞ ታማሚውን ሆስፒታል ትተው የሚመጡ ወሳኝ ጉዳይ እያላቸው ትተው የሚመጡ መሆናቸውንና ሌሎች መሰል ልብ የሚነኩ ታሪኮች እንሰማለን።  የአሰልጣኞቹ ቡድንና ተጨዋቾቼ ከዚህ በኋላ በትልቅ ሞራል እየተጫወትን ደጋፊውቻችንን ለመካስ እንጥራለን በሚል እየተነጋገርን ነው፡፡ ከምንም በላይ ለደጋፊዎቻችን የምጠይቀው እንዳስለመዳችሁን በመጥፎ  ሰአትም ቢሆን  ከጎናችን እንድትሆኑ ነው፡፡

ሊግ:- የምታመሰግነው ካለ የመጨረሻ ጥያቄዬ ይሁን …?

ነጻነት /ማሜ/:- ከምንም በላይ እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ…. ባለቤቴና ልጆቼ ቤተሰቦቼ እናት አባቴን  አመሰግናለሁ… አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ማመስገን እፈልጋለሁ.. አሰልጣኝ ተመስገን ኢትዮጵያ ቡናን ሲለቅ ሁሉንም ነገር መዝነው እንድቆይ ያደረጉንን የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ አመራሮችን አመሰግናለሁ፡፡ የክለቡ ሙሉ አባላትንም እንዲሁ አመሰግነናለሁ… ደጋፊዎቹን በተመለከተ ለእስካሁኑ ድጋፋቸው ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ በቀጣይ ደግሞ ከእነሱ ብዙ እንጠብቃለን፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ጥሩ ነገር ሰርተን እናንተን ለማስደሰት እንጥራለን። የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ተጨዋቾቼን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ በአንድነት በመስማማት እየሰራን ነው፡፡ ከልብ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ የልብ ጓደኛዬ ለሆነው በማንኛውም ክፉ ደግም ጊዜ አብሮኝ ላለው የቀድሞ ተጨዋች መስቀሌ መንግስቱ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ እንደዚሁም ላሰለጠኑኝ አሰልጣኞች በኔ ነገር ላይ አንድም ነገር ይሁን የጨመሩትን አመሰግናለሁ፡፡ ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ያስተዋወቀኝ የሊግ ጋዜጣ ዝግጅትም ክፍልንም ማመስገን እፈልጋለሁ..

ሊግ:- ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ መልካም የስራ ጊዜ እመኛለሁ…

ነጻነት/ማሜ/:-  እኔም አመሰግናለሁ እግዜር ይስጥልኝ…

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: