Google search engine

“አንድ ቀን ፊሽካና ፍላጉን ይዞ የማያውቅ ሰው ፌዴራል ዳኛ ተብሎ አግኝተናል” ኮሚሽነር ሸረፋ ደሌቾ /የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ/

አንድ ቀን ፊሽካና ፍላጉን ይዞ የማያውቅ ሰው ፌዴራል ዳኛ ተብሎ አግኝተናል

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆኖ 5 አመት የማያገለግል ዳኛን ኤሊት ብለን ለሀገሪቱ ምን ልንሰራ…? “

ኮሚሽነር ሸረፋ ደሌቾ /የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ/

ለበርካታ አመታት የዘለቀው የዳኝነት ህይወቱ  ትልቅ ደስታን እንደፈጠረለት ይናገራል…. ክፉም ሆነ በጎ ገጠመኞችን አልፏል… በዳኞች ኮሚቴ  ተንኮል የተቀጣበትን መጥፎ ጊዜውን  አይረሳም… ኮሚሽነር  ሸረፋ ደሌቾ …. በፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአሁኑ የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ  ሰብሳቢ ሆኖ መስራት ከጀመረ አንድ አመት ያለፈው ኮሚሽነር ሸረፋ ከሰሞኑ በርካታ ዳኞች ስለወደቁበት ኩፐርቴስትና ስለ ኢንተርናሽናል ዳኞች ምርጫ ዙሪያ ስለነሱበት ቅሬታዎች እንዲሁም ሌሎች ኮሚቴያዊ አሰራሮች ዙሪያ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ባልደረባ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ ጋብዘናችኋል…መልካም ንባብ….

ሊግ:- ከ2015 ጠንካራና ደካማ ጎን አንጻር ምን ስራ ሰራችሁ..?

ሸረፋ:- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደተጠናቀቀ ለ2016 ቅድመ ዝግጅትም ስናደርግ ቆይተናል…በተለይ ለዳኞችና ኮሚሽነሮች የጤናው ምርመራ፣ የጽሁፍ ፈተና፣ አዳዲስ ህጎች ላይና ክፍተት ፈጥሯል ባልናቸው ህጎች ላይ በኢንስትራክተር ፓናሎች አማካይነት ለዳኞቹ ገለጻና ስልጠና ሰጥተናል.. የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ፣ አንደኛ ሊግ፣ የክልል ክለቦችን ያካተተ ሁሉን አቀፍ ስልጠና ተሰጥቷል …

ሊግ:– ፕሪሚየር ሊጉ ተጀምሯልና ለውድድሩ ዝግጁ የሆኑት ኮሚሽነሮችና ዳኞች ስንት ናቸው ..?

ሸረፋ:- ለፕሪሚየር ሊጉ ዝግጁ የሆኑ ኮሚሽነሮችን ለይተናል.. 21 ኮሚሽነሮችን ለይተን ለሊግ ኩባንያ የውድድር ክፍል ዝርዝሩን ልከናል… የኮሚሽነሮቹ ምርጫ የጤና ምርመራን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተሰራ ነው በጤና ምርመራ የወደቁት ሁሉ ከምደባ አስቀርተናቸዋል። የጽሁፍ ፈተናን ባንሰጥም ኮሚሽነሮቹ ያሉበትን ደረጃና ያለባቸውን ክፍተት ለማወቅ ፈትነናቸዋል… የዋናና ረዳት ዳኞቹ ዝርዝርን የፊታችን መስከረም 29/2016 በሚኖረን ስብሰባ እንለይና ይፋ እናደርጋለን

ሊግ:- ከሰሞኑ በተካሄደ የአካል ብቃት ፈተና በርካታዎቹ ወድቀዋል ምክንያቱ ምን ይሆን …?

ሸረፋ:- የመጀመሪያው  ኩፐር ቴስቱ ላይ ኮስታራ አቋም ይዘናል.. መናገር የምፈልገው በወንዶችም ሆነ በሴቶች በካፍ ደረጃ የነበረን ኮታ እየቀነሰ መጥቷል። ወጣቶቹን ወደ ኤሊት መቀላቀል እንዳለብን ተግባብተናል.. ሊዲያ ከወጣች በኋላ በሴቶች ምንም የለንም፡፡ በወንዶች በአምላክ ሲያቆም እኛም እንደ ሀገር እንቆማለን.. ስለዚህ ጠንካራ ስራ ሰርተን ለውጥ ማምጣት አለብን፡፡ ለዚህም ኩፐር ቴስቱ መፈተሽ እንዳለብን ከፊትነስ ኢንስትራክተሮች ፓናል ጋር ተግባብተናል.. በዚህ መሠረትም ዘንድሮው ተለባብሶ መስራት የለበትም  በሚል ጠንከር ብለናል፡፡ ተለሳልሰን ማንንም ማሳለፍ የለብንም ብለን በመስራታችን በአግባቡ ያለፈም አለ የወደቀም የቀረም አለ …አምና ኮከብ ያልነውና የሸለምነውን ቢኒያም ወ/አገኘሁን ነው ያጣነው… በእለቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መውደቁ ችግር የለውም ሊያጋጥምም ይችላል በእኛ አግባብ ትክክለኛ ፈተናውን መፈተን ነው፡፡ ከፊትነስ ኢንስትራክተሮች ፓናል ጋር በጥሩ መግባባትና በወሰደነው ቁጥጥር ይህን አድርገናል፡፡ እናም ለጥያቄህ ምላሽ የመጀመሪያው ቁጥጥሩን ጠንከር ማድረጋችን ሁለተኛው ደግሞ ዳኛው  ራሱ በቂ ዝግጅትም አድርጎ አለመቅረቡ ይመስለኛል፡፡ ዝግጅቱ ጊዜ ይፈልጋል ጠንክሮ አለመስራት ለፈተናው በሚመጥን መልኩ አለመዘጋጀታቸው ነው፡፡ ምክንያቱም የፈለግነውን ብንቆጣጠር ከተቀመጠው መመዘኛ በላይ መሄድ ወይም መጨመር  አንችልም፡፡ ፊፋ መመዘኛ ብሎ ያስቀመጠው አምናም ካቻምናም በተመሳሳይ ስራ ላይ የዋለ ነው፡፡ ልዩነቱ ህግ በደንብ አስከብረን መተግበር ላይ  ጠንካራ መሆናችን ይመስለኛል።

ሊግ:- የወደቁት ዳኞች በቀጣይ ያላቸው እድል ምንድነው ..?

ሸረፋ:- እስካሁን ባለው ሂደት ጉዳት ላይም ነበርኩኝ አልተፈተንኩም ብሎ ሪፖርት ያደረገ ዳኛ የለም… ነገር ግን የወደቁት በሙሉ ከስድስት ሳምንት በኋላ መብታቸው ነው ከዚያ ውጪ ግን በፍጹም ምንም ጨዋታ  አያጫውቱም ያ ከሆነም ህገወጥነት ይሆናል። ለሁሉም እኩል የሆነ ኮሚቴ ነው ያለን…

ሊግ:- ከዚህ በፊት በነበሩ ኮሚቴዎች ላይ እንደ ቅሬታ የምንሰማው የወደቁትን ለማሳለፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አልነበረም  ይባላል…እናንተ  ከዚህ ቅሬታ ውጪ ናችሁ…?

ሸረፋ:- ተሻግረነዋል …በርግጠኝነት ተሻግረነዋል …. /ሳቅ/ በጣም ከተሻገርነው ነገር አንዱ ይሄ ነው … በዚህ ተግባር እጃችን ቢኖርበት ቢኒያም ወ/ አገኘሁን ተንከባክበን እናሳልፈው ነበር፡፡ ግን የለንበትም ለሀገርም አይጠቅምም፡፡ ብዙ ጊዜ ዳኞችን ተንከባከብን ፊፋና ካፍም እኛን ተንከባከቡን፡፡ አሁን ግን አይቻልም ቆሟል ህጋዊ አይደለም ..ሁሉንም ነገሮች በአግባቡ  እየሰራን እንቀጥላለን…

ሊግ:- እስቲ ወደ ኢንተርናሽናል አርቢትርነት ምርጫ ጉዳይ እንግባ…. ምርጫችሁን አመናችሁበት..? እርግጠኛ ናችሁ ላለመሳሳታችሁ …?

ሸረፋ:- አሰራራችን በግልጽነት የተሞላ ስለሆነ እንደ ሚዲያ መጥተህ የሰራችሁበትን ማየት እፈልጋለሁ..

እንዴትስ ነው የመደባችሁት..? ለህዝብ መግለጽ እፈልጋለሁ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ ለዚህ ደግሞ በራችን ክፍት ነው፡፡

ሊግ:- አመሰግናለሁ…. እስቲ ልጠይቅ ወንጀል የሰራ ሰው ከመፈረዱ በፊት ቃሉን መስማት የግድ ነው አይደል..?

ሸረፋ:- አዎ ትክክል..።

ሊግ:- ታዲያ በናንተ ምርጫ ላይ ቅሬታ ማቅረብና ይግባኝን አልፈቀዳችሁም… የስም ዝርዝሩን ለፊፋ የምትልኩበት የመጨረሻ ቀነ ገደብ ከምሽቱ 6 ሰአት ላይ ሆኖ የመረጣችኋቸው ዳኞችን ዝርዝር ያሳወቃቸሁት ከለሊቱ 4 ሰአት ላይም ነው። በፊት በነበረው አሰራር ቅሬታ ማቅረቢያ 2 ቀን ይሰጣል እናንተ ግን አላደረጋችሁም ድምጽ ማፈን አይሆንም…አቶ  ሸረፋ..?

ሸረፋ:- ቅሬታ ያላቸውን ዳኞች መስማት ትክክለኛ አሰራር ነው የምቀበለውና ተገቢም የሆነ ነው ነገር ግን ይህንን እድል የከለከሉን ዳኞቹ ራሳቸው ናቸው። በተለያየ ጊዜ የውጪ ጨዋታ የነበረባቸውን ዳኞች ጠብቆ መፈተን ደግሞ ግዴታችን ነበር። ማታ በአውሮፕላን ተጉዘው መተው ጠዋት የተፈተኑም አሉ። ቴዎድሮስ ምትኩ፣ ትግል ግዛውና ሙስጠፋ መኪ መቼ ነው የተፈተኑት…? እነሱን ጠብቀን መፈተን ነበረብን ያ ደግሞ ጊዜውን አሳጥሮብናል በነገራችን ላይ ቅሬታንኮ አሁንም ማቅረብ  ይቻላል..?

ሊግ:- ዋጋ አለው …? ቅሬታው  ለውጥ ያመጣል..?

ሸረፋ:- ስራውን ከሰራን በኋላ ከጽ/ቤትና ከስራ አስፈጻሚ ጋር ተነጋግረን ተስማምተን ግልጽ መሆኑን መግባባት ላይ ደርሰን ነው ይፋ የተደረገው….በኛ በኩል ርግጠኞች ነን። እዚሁ ላይ ሳልናገር የማልቀረው  በሂደቱ በደንብ ተምረንበታል…የአመቱ ውድድር እንደተጠናቀቀ ዳኞቹ እረፍት ያስፈልጋቸዋል የሚለው ፈተና ካልሆነብን በስተቀር ሰኔ ውድድር ተጠናቆ ሀምሌ መዘጋጃ አድርገን ነሀሴ መጀመሪያ ላይ ለምን አይፈተኑም? እያልን ነው።  በቀጣይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር እንጥራለን፡፡

ሊግ:- ልቀጥል… ፌዴራል አርቢትር ዳንኤል ግርማይ  ለቦታው አይመጥንም ….መመዘኛው ለኤፍሬም ደበሌ ያመዘነ አይመስልም …? ማሳያ ልምድ የሚባል ትልቅ መመዘኛ በናንተ በኩል ተዘሏል .. እንዴት ልምድን ከመመዘኛው አወጣችሁት ….?

ሸረፋ:- ልምድ ወሳኝ መሆኑ ጥያቄ  የለውም.. እኛ ሀገር ግን በተለይ ዳኝነቱ ችግር አለው። በተለይ ከልምድ አንጻር ልናጠራው የምንፈልገው ጉዳይ አለ … መነሻ የሚሆነኝ የፌዴራል ሰርተፊኬት የያዙ ዳኞች ጉዳይ ነው.. መምሪያ ሁለተኛ መምሪያ አንደኛ ከዚያ ፌዴራል አርቢትር  እያለ ይቀጥላል… አንድ ቀን ፊሽካና ፍላጉን ይዞ የማያውቅ ሰው ፌዴራል ዳኛ ተብሎ አግኝተናል። ዋናም ሆነ ረዳት ዳኛ ሆኖ የማያውቅ ሰርተፊኬት ይዞ ኮሚሽነርነትን ሊወስድ መጣ ይሄ ያስደነግጣል። አስወጣነው የት ነው የሰራኸው? መቼ ነው የሰራኸው? ለሚለው መልስ የለውም። እንደ ጽ/ቤትም መረጃው የለም። እንደእኛ የልምድን ጥቅም ልንክድ አንችልም። ነገር ግን የምናጠራቸው ነገርች አሉና ለጊዜው ልምድን አውጥተናል.. ሁለተኛው ግን ልምድን በቀጥታምም ባይሆን ታሳቢ አድርገናል… ሜዳ ላይ ያለው አፈጻጸም ከ10 ነጥብ ተይዟል። ይሄ ደግሞ ከልምድ ጋር ቁርኝት አለው.. ይሄ ተመዘዘ እንጂ የኮሚቴ ነጥብ ተብሎ ከ10 ይያዝ ነበር። እሱንም አስቀርተናል… እንደኛ ልምድ የሚለው ለሀገር ካልጠቀመ፣ ልምዱ ለኢንተርናሽናሉ ካላገለገለ ምን ዋጋ አለው…? ብዙ ኢንተርናሽናል አርቢትሮች አሉን። ግን በሚፈለገው ልክ እየሄዱ ነው…? ያለውን ጋፕ  ፈትሸን ለማጥበብ መስራት አለብን

ሊግ:– ሌላስ የለወጣችሁት ነገር አለ ….?

ሸረፋ:– ስለ ፊትነስ ቴስት እናውራ 50 በመቶ ነጥብ ሰጥተነዋል… ይሄ የራሱ የዳኛው ውጤት ነው….. ራስ በራሱ እንዲወስን እድል መስጠት ይሄ ነው። ማንም አይወስንም ለምሳሌ ባህሩ ተካ 50 ነጥብ፣ ተካልኝ ለማ 44.55፣ ኤፍሬም ደበሌ 48.67 ዳንኤል ግርማይ 46.428 አመጡ… ይሄ ራሳቸው መወሰናቸውን ያሳያል … ትልቁን ነጥብ የሰጠነው ለፊትነስ ነው …

ሊግ:- በእስካሀኑ አካሄድ ኤሊት አርቢትሮች የሚባሉት ኢንተርናሽናል አርቢትሮች ሲወድቁ የሚተኩ ናቸው … እናንተ ግን አላደረጋችሁም ምክንያታችሁ ምንድነው …?

ሸረፋ:- የኤሊት ፓናላችን የተበላሸ ነው። በቅርቡ እናስተካክለዋለን ብለን እናስባለን… ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆኖ 5 አመት የማያገለግል ዳኛን ኤሊት ብለን ለሀገሪቱ ምን ልንሰራ…? ኤሊት ፓናሉማ የግድ መጥራቱ አይቀርም። የኛና የሌላ ሀገር ኤሊቶችን ብታይ ታዝናለህ። ልዩነቱ ትልቅ ነው የግድ አንድ ቦታ መቆም አለበት.. ኤሊት ማለት ከትምህርት ቤት ጀምረህ ኮትኩተህ አሳድገህ የምታመጣውን ነው… በካፍና ፊፋ ተቀባይነታችን ለመቀነሱ አንዱ ምክንያት ይሄ ነው… ስለዚህ ኤሊቱ አካባቢ ያለው የግድ መስተካከል አለበት ዘንድሮ እናጠራዋለን አትጠራጠር ….

ሊግ:– ኢንተርቪውንም ከመመዘኛው ውጪ አድርጋችሁታል.. ለምን ወጣ….?

ሸረፋ:- ኢንተርቪው በጣም ወሳኝ ነው። ግን ሳብጀክቲቭ ሊሆን ነው… አትጠራጠር  ለምሳሌ እኔና አንተ ቁጭ ብለን ኢንተርቪውን እናድርግ ..  የምትፈልገውን የምታሳልፍበት ያልፈለከውን የምትጥልበት እንዲሆን ነው የምታደርገው ይሄ መቆም አለበት። ማን ያድርግ እንዴት ይደረግ የሚለው ውይይት ይፈልጋል የኮሚቴን ነጥብ የተውነውኮ ለዚህ ነው.. በርግጠኝነት ግን በቀጣይ አመት የግድ ይኖራል…. ከዩኒቨርስቲ የስፖርት መምህራንን ቁጭ አድርገን እንዲፈትኑ እናደርጋለን።

ሊግ:- የምርጫ ቋሚ መስፈርት እንዲደረግ ዳኞቹ ባሉበት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ መመሪያ ሰጥተው ነበር …መመሪያው አልተከበረም … ምን ተፈጠረ…?

ሸረፋ:– መመዘኛ ያስፈልጋል ጥርጥር የለውም። ግን ቋሚ መመዘኛ ለመቼ ..? የዛሬ አምስት አመትና አሁን ያለው እግር ኳስ ይለያያል። ታዲያ ቋሚ መመዘኛው እንዴት ይሰራል… ? ፊትነስ በጣም ወሳኝ የሆነበት ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። በቫር ታግዘውም ስህተቱ አልጠፋም መመዘኛዎች እንደ ጊዜው ተለዋዋጭ ሊሆኑ ይችላል። ግን አንድ ሁለት አመት ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል። የዘንድሮው መመዘኛ የሚጨመሩ ተጨምረው  በቀጣይ አመትም መጠቀማችን አይቀርም…

ሊግ:- ዳኞቹ ሳናውቅ ሳንዘጋጅ በፊት የነበረውን መመሪያ ቀየሩ የሚል ቅሬታ አላቸው …ለምንስ ተቀየረ…?

ሸረፋ:- /ሳቅ/ ምን ማለት ነው ሳናውቀው የሚሉት …? ስለ ፊትነስ የማያውቅ ምኑን ዳኛ ሆነ..? ዳኞቹ ማወቅ ብቻ ሳይሆን የኖሩበት ነው.. የሜዳ ላይ ትግበራ የኖሩበት ስራቸው በመሆኑ አላውቅም ማለት አይችሉም… በቃኮ በዳኝነት ህይወት ውስጥ የኖሩበትን ወደፊትም የሚኖሩበትን ነው የጠየቅነው …

ሊግ:– የተሻሻለ አላሰራ ያለ ህግ አለ..?

ሸረፋ:- ፌዴሬሽኑ ካሻሻላቸው ህጎች መሃል አንዱ አንድ ዳኛ ፌዴራል ዳኛ መሆን ያሉበት 10 አመት ካገለገለ በኋላ ነው ይላል… አንድ ወጣት የመጀመሪያ ደረጃ ኮርስ በ20 አመቱ ቢወስድ 10 አመት ሲጨመር 30 ይሞላዋል…ኢንተርናሽናል ለመሆን ሌላ 10 አጠቃላይ 40 ገባ… ይሄንን  ጨምሮ ሌሎች የሚስተካከሉ የማያስኬዱ ህጎችን መቀየር አለብን ደግሞም ይቀየራል። ከዚህ ውጪ አንድ የማስበውን ልንገርህ..?  በመመዘኛ ነጥብ ላይ የኮሚቴ ነጥብ የሚለው ቀርቶ ወጣትነት የሚለው ነጥቡ ትንሽም ቢሆን መካተት አለበት ብዬ አስባለው። እንደ ሀሳብ ከኮሚቴ ጓደኞቼ ጋር አውርተንበታል …

ሊግ:- የመጨረሻ ጥያቄ… አንተና  የምትመራው ኮሚቴ አባላት  አርቢትር ኤፍሬም ደበሌን  ለማስመረጥ አርቢትር ዳንኤል ግርማይን አልሰዋችሁትም …?

ሸረፋ:- /ሳቅ/ ከመቶ ፐርሰንት በላይ ርግጠኛ ነኝ የህሊና ወቀሳ ያለው ስራ አልሰራንም… ይህ እንዲከሰት እድልም አልሰጥም.. ወደ ሃላፊነቱ የመጣሁት ያለውን ችግርና ቢሮክራሲ ታግሎ ለመለወጥ ነው ..አበቃ  አለበለዚያ ወደ ቦታው መምጣቴ ምን ትርጉም አለው…? ለምንድነው ዳንኤል የተባለው ለምን ተካልኝ አልተባለም …?

ሊግ:- ፌዴራል አርቢትር ዳንኤል ግርማይ 3ኛና ቀጣይ መሄድ ያለበት እሱ ስለነበር ነው ….ተካልኝማ  ሰባተኛ ደረጃ ላይ ነው አይገናኙም። መብቱ የተነካውም ዳንኤል ስለሆነ ነው ….አሁንስ  ተግባባን ..?

ሸረፋ:- ገባኝ.. የኢትዮጵያ የዳኝነት አፈጻጸም በጣም መሻሻል ካለበት ወጣት ላይ መስራት ግድ ይላል.. ለዚህ ደግሞ ዝግጁ ሆነን ጉዞ ጀምረናል። በነገራችን ላይ ዳንኤልን የምንነካበት ምክንያት የለንም.. ዳንኤልኮ ጨዋታ እየመድበነው እያሰራነው የመጣነው እኛ ነን.. ዳንኤል ደግሞ በስነምግባሩ ጭምር ጥሩ ዳኛ ነው.. እንደኛ ኮሚቴ ከምናምንባቸው ዳኞች አንዱ እሱ ነው..እሱን ለመጉዳት የሚያስችልስ ምንም ምክንያት የለም  ወደፊትም አይኖርም…

ሊግ:-  አመሰግናለሁ ኮሚሽነር ሸረፋ….

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P