በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት የትግራዩን ክለብ መቀሌ 70 እንደርታን የተቀላቀለው የመከላከያው የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ሳሙኤል ሳሊሶ ቡድናቸው ከወዲሁ እያደረጋቸው ባሉት ጨዋታዎች ውጤታማ እየሆነ ያለው ‘‘አጥቅቶ የሚጫወት” ቡድን ስላላቸው መሆኑን አስተያየቱን ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥቷል፡፡ በፕሪምየር ሊጉ የቅርብ ዓመታት የውድድር ተሳትፎው
ለክለቡ መከላከያ የተጫወተው ይኸው ተጨዋች ባለው ፍጥነቱ እና በተደጋጋሚም ጊዜ ወደ ተቃራኒ ቡድን የሜዳ ክልል በመድረሱ ብዙዎቹ የሚያደንቁት ሲሆን ተጨዋቹ የአጨራረስ ችግሩን ማረም ከቻለ ወደፊት ትልቅ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ብዙዎቹም ግምትን እየሰጡት ይገኛል፡፡ የመቀሌ 70 እንደርታ ክለብ ያስፈረመው ሳሙኤል ሳሊሶ በሊጉ የሁለት ሳምንታት ጨዋታዎች ለክለቡ ሁለት የድል ጎሎችን ከወዲሁ ያስቆጠረ ሲሆን በሊጉ ጅማሬም የኮከብ ግብ አግቢነት መሪነቱን ሊይዝም ችሏል፤ የመቀሌ 70 እንደርታውን ተጨዋች ስለ አዲሱ ክለቡ፣ በመከላከያ ስለነበረው ቆይታ እና በራሱ አቋም ዙሪያ ጥያቄዎችን አቅርበንለት ምላሹን ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት፡፡ ሊግ፡- ያለፉት ሁለት የሊጉ ጨዋታዎቻችሁ ጅማሬ በውጤታማነት የታጀበ ነው፤ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ሳሙኤል፡- በአሁን ሰዓት ላይ ክለባችን ውጤታማ ሆኖ በስኬታማነት እያንፀባረቀ የሚገኘው አጥቅቶ የሚጫወት ጥሩ ቡድን ስላለን ነው፤ ከዛ ውጪ የቡድናችን ተጨዋቾች ልምድ ባላቸው እና በወጣት ተጨዋቾች ስለተገነባ እንደዚሁም ደግሞ በሊጉ ሻምፒዮና የሆነ አሰልጣኝ ስላለን እና አመራሮቻችን እና 90 ደቂቃ ሙሉም የሚደግፉን ምርጥ ደጋፊዎቻችንም ከአጠገባችን ስለሚገኙ የእነዚህ ድምር ውጤት ለውጤት ሊያበቃን ችሏል፡፡ ሊግ፡- የመቐሌ 70 እንደርታ ውጤታማነት በዚሁ ይቀጥላል? ሳሙኤል፡- አዎን፤ ቡድናችን በጥሩ መልኩ የተሰራ ነው፤ ስለዚህም በአሸናፊነታችን እንቀጥላለን፤ የሚያቆመንም የለም፡፡ ሊግ፡- መቐሌ 70 እንደርታ በአንተ እይታ ምን አይነት ቡድን ነው? ሳሙኤል፡- ክለባችን ሁሉንም ያሟላ ነው፤ በአብዛኛው በጣም ያጠቃል፤ ተከላክሎም መጫወት ይችላል፤ ሲጀመር ግን የአሰልጣኙ የኳስ ፍልስፍና ከዚህ ቀደም ባሰለጠናቸው ብዙ ቡድኖች እንደታየው በፈጣን ማጥቃት ላይ የተመሠረተ ቡድንን ስለሚሰራ እና ይሄ የታክቲክ አጨዋወትም በእኛ ቡድን ውስጥ አሁን እየታየ በመሆኑም ቡድናችንን የምገልፀው የሚያጠቃ አይነት መሆኑን ነው፤ እንዲህ ያለ ቡድን የግድ ያስፈልግካል፤ ውጤታማም ያደርግካል፡፡ ሊግ፡- በሊጉ የውድድር ተሳትፎህ በፈጣን አጥቂነትህ ትታወቃለህ፤ አጥቅታችሁ ከመጫወታችሁ አንፃር የመቀሌ 70 እንደርታ አጨዋወት ተመችቶሃል ማለት ነው? ሳሙኤል፡- በጣም፤ ለእዛም ነው በሊጉ ጅማሬዬ ለክለቤ ጎሎችን እያስቆጠርኩ ያለሁትና የግብ ሙከራም ያደረግኩት፤ ሲጀመር ደግሞ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌም እኔን ከመከላከያ እንደተለያየሁ ወደ ቡድኑ ያመጣኝ ያለኝን ብቃት ስለሚያውቅም ነውና በፈጣን ሽግግር ላይ የሚገኘው የመቀሌ 70 እንደርታ አጨዋወት ለእኔ የተመቸኝ ነው፤ በዚሁ አጨዋወትም ዘንድሮ ጥሩ ብቃቴን አሳያለው፡፡ ሊግ፡- ደደቢትን እና ወልዋሎ አዲግራትን አሸንፋችሁ መሪነቱ ላይ ተቀምጣችኋል፤ አንተም የድል ግቦችን አስቆጥረሃል፤ በጨዋታው ዙሪያ፣ ግብ በማስቆጠርክና ስለ ድሉ ምን ትላለህ? ሳሙኤል፡- የሊጉ የጅማሬ ጨዋታዎቻችን ላይ ደደቢትንም ወልዋሎንም ማሸነፋችን የሚገባን ውጤት ነው፤ ደደቢትን የረታነው አጥቅተን ስለተጫወትንና ከራሳቸው ሜዳ እንዳይወጡ ስላደረግን ነው፤ የትግራይ ደርቢ በነበረው የወልዋሎ ጨዋታም በሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች መካከል አንዱ በአንዱ መሸነፍን ስለማይፈልግ እኛ ከእነሱ በተሻለ ጥሩ ስለነበርን ጨዋታውን ልናሸንፍ
ችለናል፤ ወልዋሎን በረታንበት ጨዋታ የደጋፊዎቻችን የድጋፍ አሰጣጥ ድባብ ልዩ ነበር፤ ለደጋፊዎቻችንም ምርጥ የድል ስጦታን ሰጥተናቸው ቀኑን ልናደምቀው ችለናል፤ በሁለቱ የሊጉ ጨዋታዎቻችንም የፈጣሪ ስራ ሆኖ ውጤታማ ከመሆናችን ባሻገር እኔም ሁለት የድል ጎሎችን ስላስቆጠርኩ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ሊግ፡- በመከላከያ ክለብ የነበረህ ቆይታህ ምን ይመስላል? ከክለቡስ ጋር በምን ተለያየህ? ሳሙኤል፡-የመከላከያ ክለበ የአራት አመት ቆይታዬ ጥሩ እና ደስ የሚል ነበር፤ በቡድኑ እንደቤተሰብ ሆኜም ነው ኳስን የተጫወትኩት፤ ያም ሆኖ ግን የቡድኑ አሰልጣኝ ሁለተኛው ዙር ላይ ከመጣ በኋላና ለአዲሱ ዓመትም ከእኛ ጋር እንደሚቀጥል ሲታወቅ እኔ የእሱ እቅድ አካል ስላልሆንኩና የውል ማራዘሚያምንም አሰልጣኙ ስላላቀረበልኝ ነው ከክለቡ ጋር ተለያይቼ እኔን ወደሚፈልገኝ መቀሌ 70 እንደርታ ምንም ሳላመነታ እና ግራና ቀኝ ሳልል ቡድኑን የተቀላቀልኩት፡፡ ሊግ፡- መቀሌ 70 እንደርታ ዘንድሮ ምን ውጤት ያመጣል? በሊጉ ይቆያል መሀል ሰፋሪ ይሆናል ወይንስ ሻምፒዮና ይሆናል? ሳሙኤል፡- የቡድናችን አሰልጣኝ በሙያው ቆይታ ዛሬ አይደለም ከበፊት ጀምሮ በሚያሰለጥነው ቡድን መሀል ሰፋሪም ሆነ በሊጉ የሚቆይ ቡድን ሰርቶ አያውቅም፤ ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ነውና የሚሰራው ለሻምፒዮናነት ነው የምንጫወተው ይሄንን እልም እንድናሳካም ጥሩ ቡድን አለን፤ ከዛ ውጪም ደግሞ 90 ደቂቃ ሙሉ የሚያበረታቱን ምርጥ ደጋፊዎቻችን ስላሉ እነሱን ጭምር ነው በውጤት የምናስደስተው፡፡ ሊግ፡-በመጨረሻ….? ሳሙኤል፡- የመቀሌ 70 እንደርታ ክለብ ውስጥ በሚኖረኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ ዘንድሮ ጥሩ ብቃቴን ለማሳየት እና ቡድናችንን ለውጤቴ ለማብቃት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ራሴን ለውድድሩ አዘጋጅቼያለው፤ ከዛ ውጪ ማለት የምፈልገው እስካሁን ለደረስኩበት ደረጃ ከእኔ ጎን በመሆን የረዱኝን አካላቶች ማመስገን እፈልጋለው፤ ለዚህም የመጀመሪያው ተጠቃሽ ፈጣሪዬ ሲሆን በመቀጠል፣ እናትና አባቴን፤ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን፣ የወንጂ ተወላጅ እንደመሆኔ ልጅ ሆኜ ያሰለጠነኝን ፍፁም ረጋሳን በሼር ኢትዮጵያ ስጫወት አሁንም እንደቤተሰብ ጭምር የምንተያየውን አሰልጣኜ ሲሳይ ቱርባን እና በብዙ ነገር ሲደግፈኝ የነበረውን ጃፋር ያሲንና የመከላከያ ቡድን አመራሮችና የቡድን መሪውን ሻለቃ ሙሉ ባራኪንና የወንጂ ጓደኞቼን ማመስገን እፈልጋለው፡፡
“ለሻምፒዮንነት እንጂ መሐል ሰፋሪና ሊጉ ላይ ለመቆየት አንጫወትም” ሳሙኤል ሳሊሶ /መቐሌ 70 እንደርታ/
ተመሳሳይ ጽሁፎች