ፋሲል ከነማ በዝውውር መስኮቱ ካስፈረማቸው የሊጉ ስኬታማ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የደደቢቱ ሽመክት ጉግሳ በእዚህ ዓመት በሊጉ የሚጫወትበትን ክለብ ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በመሆን ለውጤት እንደሚያበቃው አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ የፋሲል ከነማ ክለብ በሊጉ የሁለት ሳምንታት ጨዋታዎቹ የመጀመሪያውን ግጥሚያ በሲዳማ ቡና ተሸንፎ ሁለተኛውን ጨዋታው ሐዋሳ ከነማን በመርታት ለድል የበቃ ሲሆን ከዚህ በኋላ በሚኖሩት የሊጉ ጨዋታዎች ቡድናችን ለተከታታይ ስኬቶች ከመብቃት ባሻገር ለዋንጫ ባለቤትነት የሚጫወት ቡድን ነውም ሲል ሀሳቡን አክሎ ሰጥቷል፡፡ የፋሲል ከነማው አዲሱ ፈራሚ ሽመክት ጉግሳ በሊጉ የተጨዋችነት ቆይታው ባለው ጥንካሬና ፍጥነት አይድከሜነቱና ጥሩ ችሎታው የሚታወቅ ሲሆን የእዚህ ዓመት ላይ ብዙ ጎሎችንም ለክለቡ ለማስቆጠርም እቅድን ይዟል፤ ይህን ተጨዋች አጠር ባለ ሁኔታ ስለ አዲሱ ቡድኑና ስለ ሊጉ የጅማሬ ጨዋታዎቻቸው አናግረነው የሚከተለውን ምላሹን ሰጥቶናል፡፡ ስለ አዲሱ ክለቡ ፋሲል ከነማ “የክረምቱ የዝውውር መስኮት ላይ የተቀላቀልኩት አዲሱ ክለቤ ፋሲል ከነማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለእኔ ጥሩ የሆነልኝና በጣምም የወደድኩት ነው፤ ቡድኑ በአዲሱ አሰልጣኝ ሊከተል ያሰበውም የጨዋታ እንቅስቃሴ እኔ የምፈልገው አይነት ስለሆነልኝም በቡድኑ ተመችቶኝ
ነው እየተጫወትኩ ያለሁት”፡፡ ስለ ፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸው “ከሲዳማ ቡና ያደረግነው የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታችን ጥሩ ቢሆንም የአጨራረስ ችግር እኛን ጎድቶናል፤ ውጤታማም እንዳንሆን አድርጎናል፤ ያን ዕለት አራት ያህል ኳስም ነው ብረት እየገጨብን እና እየተመለሰብን የነበርነው፤ በዛ እለት ጨዋታ እድለኛም አልነበርንምና ግጥሚያውን መሸነፋችን የሚገባን አልነበረም”፡፡ስለ ተጋጣሚያቸው “ሲዳማ ቡናዎች በጨዋታው ሲያጠቁ ጥሩ ነበሩ፤ ሲከላከሉ ደግሞ ክፍተቱ ነበረባቸውና እንቅስቃሴያቸውን የተመለከትኩት በእዚሁ መልኩ ነው”፡፡ የሐዋሳ ከነማን በሁለተኛው ሳምንት ድል ስላደረጉበት የሊጉ ጨዋታ እና ዘንድሮ ሊያሳኩት ስላሰቡት ውጤት “የፋሲል ከነማ ክለብ በእዚህ ዓመት ሊጉ ላይ ለማምጣት ያሰበው ውጤት ከዚህ ቀደም ካስመዘገባቸው ውጤቶች የተሻለ እና የሚጫወተውም የውድድሩ ሻምፒየና ለመሆን ነው፤ በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታችን የተሸነፍንበትን ውጤት በቀጣዩ ግጥሚያ በማሸነፍ ማካካስ እና ደጋፊዎቻችንም በውጤት ልንክስ ችለናል፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ ቡድናችን የአሰልጣኙ እምነት በሆነው ኳስን ተቆጣጥሮና ፖሰስ አድርጎ ከሚከተለው የታክቲክ ፍልስፍና ጋር የበለጠ እየተዋሃደ ስለሚሄድ ካለፉት ዓመታቶች አንፃር ፋሲል የእዚህ ዓመት ላይ የተሻለ ውጤት ያመጣል ብዬ አስባለው፤ የሐዋሳ ከነማ ጋር የነበረንን ጨዋታ ያሸነፍነው እኛ በሁሉም መልኩ ጥሩ ስለነበርን ነው፤ ግጥሚያውን አሸንፈንም ከሳምንት በፊት የተከፉብንን ደጋፊዎቻችን ልናስደስት ችለናል”፡፡ በፋሲል ከነማ ቆይታ ዘንድሮ ከአንተ ምን ይጠበቅ? “ፋሲል ከነማን በክረምቱ ወራት ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ የቡድኑ
ቆይታዬ ላይ አንድ የራሴ የሆነን አሻራ ለማስቀመጥ አለብኝ ብዬ ስላሰብኩ ዘንድሮ ቡድኑ ከእኔ ጥሩ ነገር ይጠብቅ፤ ከዚህ ቀደም በነበረኝ የሊጉ ተሳትፎዬ ጥሩ መንቀሳቀስ ብችልም፣ ኳሶችን ለአጥቂዎች ባቀብልም፤ ብዙ ጎሎችን አላስቆጥርም ነበር፤ የእዚህ ዓመት ላይ ግን ብዛት ያላቸው የድል ጎሎችንም ለክለቤ ለማስቆጠር ተዘጋጅቻለው፤ የሊጉ ጅማሬዬ ላይም ከወዲሁ የድል ግብ በሐዋሳ ከነማ ላይ ማስቆጠሬም በጣም ሊያስደሰተኝ የቻለም ሁኔታ ነው”፡፡
“በሲዳማ መሸነፋችን ባይገባንም ሐዋሳን ድል አድርገን ደጋፊውን ክሰናል፤ ድሉም ይቀጥላል” ሽመክት ጉግሳ (ፋሲል ከነማ)
ተመሳሳይ ጽሁፎች