በባህር ዳር ከነማ ክለብ ውስጥ በቅድሚያ በከፍተኛ ሊጉ በመቀጠል ደግሞ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕና በፕሪምየር ሊጉ የጅማሬ ጨዋታዎች ላይ በመሀል ተከላካይነት ስፍራ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ ተመልክተነዋል፤ ተጨዋቹ በሜዳ ላይ ባሳየው ብቃትም ብዙዎቹ የተመለከቱት የስፖርት አፍቃሪዎች ለወጣቱ ተጨዋች ከወዲሁ ከፍተኛ አድናቆትን እየሰጡት ይገኛል፤ ይሄ ተጨዋች ወንድሜነህ ደረጄ ሲባል የተከላካይ ስፍራው ላይ ምንም አይነት ድንጋጤ ሳይታይበት ኳሱን ይዞ የሚጫወትበት መንገድ ከአቅሙ በላይ ከሆነበት ደግሞ የሚያገኘውን ኳስ ከአደጋ ክልሉ እንዲወጣ ያደረገበት አጨዋወቱ ይበል የሚያሳኝ ሊሆንለት ችሏል፡፡ የባህር ዳር ከነማ ክለብ በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታው ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን በወሰኑ ዓሊ ብቸኛ ግብ 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለውንና የቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋቾችንም ባለው የአህምሮ ፍጥነቱ ተጠቅሞ ሊያቆማቸው የቻለውን ይህን ተጨዋች በኳስ ሕይወቱ ዙሪያና ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርበንለት የሰጠን ምላሽ በሚከጸላ መልኩ ቀርቧል፡፡ ሊግ፡- የፕሪምየር ሊጉን ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪኩ በተቀላቀላችሁበት የመክፈቻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ ችላችኋል፤ ይሄን ውጤት እንዴትና በምን መልኩ አሳካችሁት? ወንድሜነህ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ ያሸነፍነው የእኛ ቡድን ተጨዋቾች በከፍተኛ ፍላጎትና ወኔ ስለተጫወቱ ነው፤ ስለሊጉ ካለማየታችን የተነሳ ብዙ አናቅም ነበር፤ ኳስን በፍላጎት መጫወት ግን ውጤታማ ያደርጋልና እኛ በእዛ ተጠቃሚ ሆነን ጨዋታውን አሸንፈናል፡፡ ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን ያሸነፋችሁበት ጨዋታ ላይ በሁለታችሁ መካከል የነበረው የእንቅስቃሴ ልዩነት ምን ነበር? ጨዋታውን በማሸነፋችሁስ ምን ስሜት ተፈጠረባችሁ? ወንድሜነህ፡- በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ላይ በእኛና በቅዱስ ጊዮርጊሶች መካከል የነበረው የኳስ ልዩነት እነሱ ረጅም ኳስ ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴን ነበር የሚከተሉት፤ ይሄ አጨዋወታቸውም ለእኛ ኳስን ይዘን ለመጫወት የሞከርንበት ሁኔታ ስላለ ለማሸነፋችን ጠቅሞናል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፋችን ቡድኑ ትልቅ እና በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የሚጫወት ከመሆኑ አንፃር በጣም አስደስቶናል፡፡ ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን ከማሸነፋችሁ አንፃር አንዳንዶች ለእነሱ ብቻ እንደተዘጋጃችሁ እና በቀጣይ ጨዋታዎች ደግሞ ይሄን ድል እንደማትደግሙት ሲናገሩ ይሰማልና ከእዚህ አንፃር የአንተ ምላሽ የሚሆነው ምንድን ነው? ወንድሜነህ፡- በሊጉ እኛ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ አልተዘጋጀንም፤ ያንን ያሰቡ ካሉም ስህተት ነው፤ በውድድሩ ቆይታችን ዘንድሮ ማንንም አቅልለን አናይም፤ ማንንም ከፍ አድርገንም ሰማይ ላይ አንሰቅልም፤ ለሁሉም ቡድኖች እኩል ግምትም ሰጥተን ነው በየጨዋታዎቹ ሜዳ ላይ የምንቀርበውና እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ሁሉ ሌሎችንም ጨዋታዎች ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው፤ በዚህ ዓመትም ጥሩ ነገር ይኖረናል፡፡ ሊግ፡- የባህር ዳር ከተማ የእዚህ አመት ግቡ የት ድረስ ነው? ወንድሜነህ፡- የፕሪምየር ሊጉን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀልነው ዘንድሮ ስለሆነ እና ለውድድሩም ቡድናችን አዲስ ስለሆነ የእኛ የእዚህ ዓመት ዋናው ግብ ሊጉ ላይ መቆየት ነው፤ ለእዚያም የቤት ስራችንን ከወዲሁ በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስንም የረታንበት የመጀመሪያ ጨዋታም ለቀጣይ ፍልሚያዎቻችን ከፍተኛ መነሳሳትን ይፈጥርልናልም ብዬ አስባለሁ፡፡ ሊግ፡- የባህር ዳር ከነማ የተጨዋቾች ስብስብ በአንተ አንደበት እንዴት ይገለፃል? ስብስባችሁስ ሊጉን መቋቋም ይችላል? ወንድሜነህ፡- በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎአችን በአሁን ሰአት ላይ የያዝነው የተጨዋቾች ስብስብ በአብዛኛው ወጣትና ኳስን በከፍተኛ ፍላጎት መጫወት የሚችሉትን ነው፤ ልምድ ያለው ተጨዋች ብዙም የለንም፡፡ ከሁለትም አይበልጡም፤ ያም ሆኖ ግን በስብስቡ እንደሌሎች በርካታ ቡድኖች እውቅ የሆኑ ተጨዋቾችና ባንይዝም የእኛ ልጆች ወጣቶች ከመሆናቸው አኳያ ራሳቸውን ሊጉ ላይ ለማሳየት ስለሚጫወቱ ያለን ስብስብ ጥሩ ነው፤ ስብስባችንም ሊጉን በደንብ ተቋቁመን እንድናጫወትም ያደርገናል፡፡ ሊግ፡- የባህር ዳር ከነማ ክለብ ውስጥ በተከላካይ ስፍራው ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረግክ ነው ይህንን
ብቃትህን በሜዳ ላይ እንዴት ልትወጣው ቻልክ? ወንድሜነህ፡- አሁን ላይ በሜዳ ውስጥ የማሳየው አበረታች ብቃት ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም፤ ከልጅነት እድሜዬ አንስቶ ለኳሱ ከነበረኝ ፍቅር አንፃር ጠንክሬ ስለሰራሁ ነው እዚህ ደረጃ ላይ ልገኝና ጥሩም አቋሜን ላሳይ የቻልኩት፤ ለዚህ ለመብቃቴም የህፃንነት እድሜዬ ላይ በአሰልጣኝ ተሻለ ምንዳዬ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ሰልጥኜ ማለፌና ለመርካቶ ዩኒየን መጫወቴ፤ በከፍተኛ ሊጉም በአሰልጣኝ ሀብተወልድ ደስታ ይመራ በነበረው የልደታ ክፍለ ከተማ ቡድን ውስጥ እና እንደዚሁም ደግሞ በአራዳ ክፍለ ከተማ እና በአሠልጣኝ ታደሰ ጥላሁን በሚመራው የሱሉልታ ከነማ ቡድን ውስጥ መጫወቴና ጥሩ ልምድንም አካብቼ በመምጣቴ ነው ኳሱን በጥሩ ሁኔታ እየተጫወትኩ ያለሁት፡፡ ሊግ፡- የባህር ዳር ከነማ ክለብ ውስጥ የመሃል ተከላካይ ሆነህ ነው የምትጫወተው፤ በኳስ ህይወትህ በእዚህ ስፍራ ብቻ ነው የተጫወትከው? ወንድሜነህ፡- አይደለም፤ ኳስን ተከላካይ ሆኜ ብጀምርም በስኪመር ስፍራና ስቶፐር ሆኜም ተጫውቼ አሳልፌያለሁ፡፡ ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን በተፋለማችሁበት ጨዋታ ምንም እንኳን ያለህ የሰውነት አቋም ግዙፍ ባይሆንም በአነስተኛ ተክለ ሰውነትህ አጥቂዎቹን አላፈናፍንም ብለህ ነበር፤ በግጥሚያው ያንን እንዴት ልታሳካው ቻልክ? ወንድሜነህ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ላይ ግዙፉን የእነሱን አጥቂም ሆነ ጌታነህ ከበደ በነበረበት ጨዋታ ላይ ጎል እንዳያስቆጥሩብን በመከላከሉ ላይ አላፈናፍን ያልኳቸው ዋናው ምክንያት አሁን ላይ የምጫወትበት የእድሜ ደረጃ ወጣት መሆኑና ከምንም በላይ ደግሞ ልብ ያለኝ ተከላካይ ስለሆንኩ ነው፤ ለአጥቂዎቹ ትኩረት ሰጥቼ መጫወቴ ሊጠቀመኝ ችሏል፤ በእዚሁ አጋጣሚ ግን ጌታነህ ከበደን ሃገራችን ውስጥ ካሉ ተጨዋቾች በጣም እንደማደንቀውም መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ሊግ፡- የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር የአንተ ተምሳሌት ሮል ሞዴልህ የነበረው ተጨዋች ማን ነበር? ወንድሜነህ፡- ሙሉአለም ረጋሳ ነዋ! የሊጉን ጨዋታዎች ስከታተል መጀመሪያ ያደንቅኩት እሱን ነው፤ ከውጪዎቹ ደግሞ ሊዮኔል ሜሲ የእኔ ሮል ሞዴሌ ነው፡፡ ሊግ፡- የወደፊት ምኞትህ? ወንድሜነህ፡- የእግር ኳስን የሚጫወት ማንኛውም ተጨዋች ክለብ ውስጥ ከገባ በኋላ ቀጣይ ምኞቱ ለሀገሩ ብሄራዊ ቡድን መጫወት ነው፤ ይሄንን ህልሜን በቅድሚያ ማሳካት እፈልጋለሁ ቀጥሎ ደግሞ ፕሮፌሽናል ተጨዋች መሆን ህልሜና ግቤ ነው፡፡ ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን መመረጥህን ሰማን፤ አሁን ደግሞ ከቡድኑ ጋር የለህም ምክንያቱ ምንድን ነው? ወንድሜነህ፡- አዎን፤ ለኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን እኔና ግብ ጠባቂያችን ተመርጠን ነበር፡፡ እድሉን ሳገኝም በጣም ተደሰትኩ፤ ያም ሆኖ ግን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድንን በተፋለምንበት የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ቡድኔ እኔንም ግብ ጠባቂያችንንም በእዚያ እለት ለነበረው ጨዋታ ካለብን የስኳድ ጥበት አንፃር ቡድናችን ምን እንደሚገጥመው ስለሚያውቅ እኛን ሊያጫውተን በመቻሉ እና የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ደግሞ ማንም ተጨዋች ለብሄራዊ ቡድን ከተጠራ በኋላ ለክለቡ መጫወት የለበትም የሚል ትዕዛዝን በማስተላለፉበእዚሁ ከክለባችን ጋር መስማማት ሳይቻል ቀርቶ ከብሄራዊ ቡድኑ ውጪ ልሆን ችያለሁና በአሁኑ ቡድን ባይሳካልኝም በቀጣዩ ጊዜ የብሄራዊ ቡድን ምርጫ ላይ ለሀገሬ በድጋሚ በመመረጥ እንደምጫወት ተስፋ አድርጋለው፡፡ ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን ባሸነፋችሁበት ጨዋታ የእነሱን አቋም እንዴት ተመለከትከው፤ ውጤቱስ ይገባችዋል? ወንድሜነህ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን ዋንጫ ለረጅም አመታት ያነሳ እና ትልቅ ቡድን ቢሆንም ያን እለት በነበረው ጨዋታ ግን እኛ ለእነሱ አቋም ትኩረትን ሰጥተናቸው ስለነበር እንደነበረን ብቃት ማሸነፋችን ይገባናል፤ የእነሱን አቋም በተመለከተ እንደ በፊቱ ሆነው አላገኘዋቸውም፤ እኛን አክብደውንም ነው የገቡት፤ አስፈሪ ቡድንም አልነበራቸውም፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ? ወንድሜነህ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በተቀላቀልኩበት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዬ ላይ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ስለቻልኩ በጣም ደስ ብሎኛል፤ የኳስ ህይወቴን ገና አሁን ነው መጫወት የጀመርኩት፤ አበረታች የሆነ ብቃትን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየሁ ነው፡፡ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃም ከእኔ ጎኔ ሆነው የረዱኝን ሁሉ ለማመስገን እፈልጋለሁ፤ ለእዚህም የመጀመሪያ ተጠቃሽ የምትሆነው ኪዳነ ምህረት ነች፤ እሷ የምጠይቃትን ሳይገባኝ ጠይቄያት ትሰጠኛለች፤ ከእሷ ውጪም ብዙ ነገር ያደረገችልኝ ወላጅ እናቴ እማሆይ ስፈርን፤ ልጅ ሆኜ ያሰለጠኑኝ ደረጄ ሽፈራው እና ተሻለ ምንዳዬን እንደዚሁም ደግሞ በእኔ ላይ ከፍተኛ እምነት ጥሎ የባህር ዳር ከነማ ክለብ ውስጥ እያጫወተኝ ያለውን አሰልጣኜን ጳውሎስ ጌታቸው / ማንጎ/ እና እኔ ጥሩ ደረጃ ላይ እንድደርስ ሁሌም የሚያበረታቱኝን የሰፈሬን የአህያ በር ልጆችን ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
“ቅ.ጊዮርጊስን ያሸነፍነው ለእነሱ ብቻ ተዘጋጅተን አይደለም”ወንድሜነህ ደረጄ (ባህርዳር ከነማ)
ተመሳሳይ ጽሁፎች