Google search engine

“የእኛ ጥያቄ ክለቡን በባለቤትነት እንረከብ የሚል ሳይሆን በጠቅላላ ጉባዬውና በውሳኔ ሰጪነት ላይ ያለን ሚናና ውክልና ከፍ ይበል የሚል ነው” አቶ ክፍሌ አማረ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት

በተለይ ለሊግ ስፖርት
“የእኛ ጥያቄ ክለቡን በባለቤትነት እንረከብ የሚል ሳይሆን በጠቅላላ ጉባዬውና በውሳኔ ሰጪነት ላይ ያለን ሚናና ውክልና ከፍ ይበል የሚል ነው”
አቶ ክፍሌ አማረ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት
በአለምሰገድ ሰይፉ
ቡናማዎቹ ህዳር 2/2011 ዓ/ም ደማቅ ድግስ ነበራቸው፤ “ለቡንዬ እሮጣለሁ” ሶስተኛው ዙር የክለቡ የቤተሰብ ሩጫ ደማቅ በሆነ ሁኔታ ያለአንዳች እንከን ተጠናቅቋል፤ ይህ ፋይዳው ሁለትዮሽ የሆነው የክለቡ ደጋፊዎች የጎዳና ላይ ሩጫ ወንድማማችነትን ከማጠናከርም ባሻገር ወፈር ያለ ገቢም ለኢትዮጵያ ቡና ማስገኘት ችሏል፡፡
ከ1995 ዓ/ም ጀምሮ በውስጡ ያለው ክለባዊ ደም አሁን ድረስ የዘለቀው የክለቡ ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ክፍሌ አማረ ደግሞ ከዚህ ዘመን ጀምሮ የግል ስራውን በመበደል ለኢትዮጵያ ቡና በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ አሁን ደግሞ አጥጋቢ ውጤት እያስመዘገበ በሚገኘው የደጋፊው ማህበር ውስጥ በፕሬዘዳንትነት እያገለገለ ነው፡፡ ወቅታዊ አጀንዳውን ተንተርሶ ፕሬዝዳነቱ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አለምሰገድ ሰይፉ ጋር በሚከተለው ሁኔታ አውግቷል፡፡
ሊግ፡- 3ተኛው ዙር “ለቡንዬ እሮጣለሁ” የደጋፊዎች ሩጫ በምን መልኩ ተጠናቀቀ?
አቶ ክፍሌ፡- እንዴት ተጠናቀቀ ከሚለው በፊት ክለባችን በ2007 ዓ/ም አላማ አድርጎ ሲነሳ ሶስት ነገሮችን ይዞ ነው፡፡ አንደኛው የክለቡ ደጋፊዎች ከስታዲየም ውጪም ትብብራቸው ቤተሰባዊ ስሜት እንዲኖረው ማስቻል ሲሆን ሌላው ደግሞ ክለቡ ያለውን ጥሩ ኢሜጅ የሚገነባበትና በዋናነት ደግሞ ክለቡ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበትን መንገድ መቀየስ ነው፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ በተከናወነው የ2011 ዓ/ም የሩጫ ፕሮግራም ወደ 28 ሺህ የሚጠጋ የቡና ቤተሰብ በሩጫው ላይ ተሳትፏል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ይሄን ያህል ሰፊ የሆነ ህዝብ በተሳተፈበት ውድድር ላይ ያለ አንዳች ኮሽታ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁ ሂደቱ ምን ያክል ስኬታማ እንደነበር ያሳያል፡፡
ሊግ፡- እቅዱና ስኬቱ ተጣጥመዋል ማለት ይቻላል?
አቶ ክፍሌ፡- አዎ፤ ስኬቱን የምንገልፀው ከያዝነው አላማ አንፃር ነው፡፡ በገቢ ረገድ ካየነው ከዚህ የተሻለ እመርታ ማስመዝገብ እንችል ነበር፤ ይህም ማለት በ3ተኛው ዙር የተሳተፉት ወደ 28 ሺህ የሚጠጋ ነው፡፡ የደጋፊው ጥያቄ ደግሞ አሃዙን ወደ 32ሺ ከፍ ያደርገዋል፤ ነገር ግን ውድድሩ የተካሄደበት ለቡ አካባቢ የመኖሪያ ቦታ በመሆኑና ለመሮጥም አመቺ ባለመሆኑ ለመገደብ ተገደናል፡፡ እንደዛም ሆኖ ክለባችን በዚህ የጎዳና ላይ ሩጫ ብቻ ከ6.5 ሚሊዮን የሚልቅ ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡
ሌላው የክለባችንን የቤተሰብ ሩጫ ስኬት የምትለካው ከሌሎች ታላላቅ የጎዳና ላይ ሩጫዎች አንፃር ነው፡፡ የእኛ ሩጫ ከተጀመረ ገና ሶስተኛ አመቱን ያስቆጠረ ሲሆን በአንፃሩ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ደግሞ በ18 አመት የውድድር ታሪክ ዘንድሮ 44ሺህ ተወዳዳሪዎች ነው የሚያሳትፈው፡፡ ቡና ደግሞ በሶስት አመት ውስጥ 30ሺህ ሯጮችን ማግኘት መቻሉ ውጤታማነታችን ምን ያክል ፈጣን እንደሆነ የሚያሳይ እውነታ ነው፡፡ በዛ ላይ ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ሳይሆን በበጎ ፈቃደኝነት በተሰራበት ሁኔታ ይሄን ያህል ስኬታማ መሆን ከቻልን ወደፊት አሰራሩን በፕሮፌሽናልነት ካዘመነው ከ5 አመታት በኋላ ታላቁ ሩጫ የያዘውን ሪከርድ እኛ የማንሰብርበት አንዳችም ምክንያት አይታየኝም፡፡
ሊግ፡- ከሩጫው ባሻገር ክለቡን በሌላ የፋይናንስ አቅም ለማገዝ የያዛችሁት እቅድ አለ?
አቶ ክፍሌ፡- ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልህ ይህ የሩጫ ውድድር ፋይዳው ብዙ ነው፤ ለክለቡ ተጨማሪ የገቢ አቅም ከመፍጠርም ባሻገር የዚህ አይነቱን ወንድማማችነት የበለጠ የሚያጠናክር ሁኔታ በመፍጠር ለሌሎች ክለቦችም አርአያ የሚሆን ተግባር ነው፤ እንደ ማህበርም ደጋፊዎቻችንን በማስተባበር በተለያየ ሁኔታ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ነው እየሰራን የምንገኘው፡፡ እንደ ምሳሌነትም በወርሃዊ መዋጮ፣ በማሊያ ሽያጭና በኮንሰርቶች ክለቡን የማገዙ እቅድ አለን፤ ከዚህ አንፃር ክለቡ ከስፖንሰርሺፕ ከሚያገኘው ገቢ ባልተናነሰ ሁኔታ ደጋፊ ማህበሩ ክለቡ ከሚያወጣው ወጪ ግማሹን ያህል ለመሸፈን እየቻለ ነው፡፡
ሊግ፡- ደጋፊውን በዘመናዊና ዲጂታል በሆነ ሁኔታ የመመዝገቡ ሂደት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ክፍሌ፡- እንደሚታወቀው ክለባችን ኢትዮጵያ ቡና በአገራችን ውስጥ ግዙፍና በርካታ ደጋፊዎች ካሏቸው ክለቦች በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ክለቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በአገራችን ካሉት ደጋፊዎች በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካ፣ በአረብ አገራት፣ በአሜሪካና በአውሮፓ እጅግ በርካታ የሆኑ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች አሉ፤ አንድ ገለልተኛ የሆነ ተቋም እንዳጣራውም ክለባችን ወደ 6 ሚሊየን የሚጠጉ ደጋፊዎች እንዳሉት ነው ጥናቱ ያረጋገጠው፡፡ እናም ይሄንን ደጋፊ የተመዘገበ እንዲሆን ከማድረግም ባሻገር ከምዝገባው የሚገኘው ገቢ ክለቡን የበለጠ ማገዝ ይችላል የሚለው ነጥብ የተለየ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ደጋፊዎችን መመዝገብ ማለት ማንኛውም ደጋፊ በያዘው ሞባይል የአባልነት ምዝገባ ማካሄድ የሚችልበት ዘመናዊ የምዝገባ ስርዓት ሲሆን አልያም አጠገቡ በሚገኙ ቅርንጫፎች በመመዝገብ የአባልነት ግዴታውንና በአንፃሩ ደግሞ ከክለቡ ማግኘት የሚገባውን ጠቀሜታን በዘመናዊነት የመተግበር አሰራር ነው፡፡ የዚህ አይነት አሰራርም እጅግ ዘመናዊና በሃገሪቱ የመጀመሪያ የሆነ አካሄድ ነው፡፡ ይህን አካሄድም እውን ለማድረግ ይቻል ዘንድ እልባት ቴክኖሎጂ ከሚባል ኩባንያ ጋር በጣምራ እየሰራን ነው ፡፡ እስካሁንም 100 የሚደርስ ወኪል ቅርንጫፎች አሉን፡፡ በዚህ አካሄድ ከቀጠልንም በሁለትና ሶስት አመታት ውስጥ በመቶ ሺህ ደረጃ የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን በዲጂታል መንገድ እንመዘግባለን ብለን እናስባለን፡፡
ሊግ፡- ደጋፊ ማህበሩ በተጨዋች ግዥ ላይ ለክለቡ የሚያደርገው ድጋፍ አለ?
አቶ ክፍሌ፡- የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች ማህበር ከክለቡ ጋር ያላው ቁርኝት ለየት ያለ ነው፤ ይሄንንም እውነታ ለየት የሚያደርገው የደጋፊ ማህበሩ አባላት በቦርድ ውስጥ ራሱን የቻለ የአመራርነት ሚና ይጫወት ዘንድ ቦታ ተሰጥቶናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም በቦርዱ ውስጥ የደጋፊ ማህበሩ ሁለት ቦታዎች አሉት፡፡ ዋናው አላማችንም አብረን በመሆን የምንወደውን ክለባችንን ማገዝ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ደጋፊ ማህበሩ ከሚያዘጋጀው የሩጫ ፕሮግራም ባሻገር የማሊያና ቁሳቁሶች ሽያጭ እንዲሁም ከአባላት ክፍያ የሚሰበሰበው ገንዘብ በብዙ ሚሊየን ደረጃ የሚቆጠር በመሆኑ ክለቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሱን ለማሳደግና በተጨዋቾች ጥራት የተሻለ ተሰላፊ ለማግኘት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በገንዘብ እንደግፋለን፡፡
ሊግ፡- ይህ እገዛችሁ የሚደገፍ ቢሆንም አንዳንዴ ደጋፊ ማህበሩ በተጨዋቾች ዝውውርና በአሰልጣኞች ቅጥር ላይ እጁን ያስገባል የሚል ቅሬታ ይቀርብባችኋል፤ ምን ያህል እውነት ነው?
አቶ ክፍሌ፡- ከአሁን በፊት በነበረው ሁኔታ በየጊዜው የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ሲገነባ የደጋፊው ሚና ከፍተኛ ነው፤ ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ተብሎ በአዲስ ስያሜ መጠራት ከጀመረበት 1987 ዓ/ም ጀምሮ ስም ያላቸው ተጨዋቾች ወደ ክለቡ እንዲመጡ ለማስቻል ደጋፊዎች ገንዘብ እያዋጡ ተጨዋቾችን ያስመጡ ነበር፡፡ ይህ አካሄድም እስከ 2003 ዓ/ም ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ ሆኖም ከዚህ ዘመን በኋላ ግን ክለቡ ራሱ ነው ለተጨዋቾች ዝውውር ክፍያ የሚፈፅመው፣ አሰልጣኝም የሚቀጥረው፤ ከ2004 ጀምሮ ደግሞ ደጋፊ ማህበሩ ተጨዋቾችን በማምጣቱ ረገድ ራሱን የቻለ ሚና ነበረው፤ ነገር ግን እገዛው አሰልጣኙ ፈቅዶና ወዶ በሚፈልገው መንገድ መንቀሳቀስ እንጂ ደጋፊው አንዱን ተጨዋች ስለወደደውና ስለፈለገው ብቻ እንዲመጣ ግፊት ማድረግ አይደለም፡፡ እናም አንተ ቀደም ብለህ እንደገለፅከው በደጋፊው ግፊት ተጨዋቾች የሚመጡበት ስርአት ነበር፡፡
ነገር ግን ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ የመጣው የደጋፊ ማህበር ቦርድ ውስጥ ባለው ቦታና ሃላፊነት ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ስራዎች ውስጥ አንዳችም ጣልቃ ገብነት እንዳይፈፀም ተብሎ በአሰልጣኙ ፍላጎትና ምርጫ ካልሆነ በስተቀር ደጋፊዎች ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት እንዳይፈፅሙ በመባሉ ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ወዲህ ማንኛውም ወገን በሙያተኛው ስራ ጣልቃ የሚገባበት አንዳችም ሁኔታ የለም፡፡
ሊግ፡- ብዙ ጊዜ እንደምንሰማው ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ በቦርድ አመራሩና በእናንተ በደጋፊ ማህበሩ አመራር መካከል አለመግባባቶች እንደሚፈጠሩ ይነገራል፤ የልዩነቱ ምክንያት ምንድነው? አሁን ያላችሁበት ሁኔታስ በምን ይገለፃል?
አቶ ክፍሌ፡- አዎ፤ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም አንድ መታወቅ ያለበት እውነታ ቢኖር የቦርድ አመራርም ሆነ የደጋፊ ማህበሩ ሃላፊዎች ተልዕኳቸው አንድና አንድ ነው፡፡ የእኛ ማህበር ህጋዊ እውቅና አግኝቶ የሚንቀሳቀስ ሲሆን በዚሁ ረገድ ደጋፊውን በማስተባበርና በማገዝ ጥያቄዎቻቸው በአግባቡ እንዲመለስ፣ ክለቡ ውጤታማ እንዲሆንና በአደረጃጀት ደረጃ ዘመናዊ ይዘት እንዲኖረው ይሻል፡፡ ከዚህ መነሻነትም አንተ እንዳልከው በተለያየ ጊዜ ልዩነቶች ይፈጠሩ ነበር፤ ሆኖም እነዚህ ልዩነቶች ጤናማና ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ ከመፈለግ ብቻ የመነጨ ነው፡፡
ደጋፊው የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አምናም ነበሩ፤ ዘንድሮም አሉ፤ ከዚህ መነሻነትም ከምንጊዜውም በተለየ ሁኔታ የክለቡ አመራሮች በተለየ ሁኔታ የክለቡ አመራሮች የደጋፊውን ጥያቄ ከልቦና በማድመጥና አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት ቆርጦ በመነሳቱ የደጋፊ ማህበሩ በቦርድ ውስጥ ያለው ውክልና ከፍ እንዲልና በአስተዳደር መዋቅሩ፣ ከዛ ከፍ ሲልም በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የተሻለ ውክልና እንዲኖረው ለማስቻል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ምናልባት ክለቡ በቅርቡ በህዳር ወር በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የደጋፊ አመራሩ የሚኖረው ቦታና የአመራሩ ሚና ከፍ በሚልበት ሁኔታ ላይ ክለቡ ጥሩ ውሳኔ ያስተላልፋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከዚህ በተረፈ የክለቡ ቦርድና የደጋፊ ማህበሩ አመራር ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እጅና ጓንት ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እንደማሳያነትም በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ፣ ከምንም በላይ ደግሞ የዘንድሮው የሩጫ ውድድር ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ለማስቻል በቅንጅትና በመናበብ የሰራናቸው ስራዎች ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከውጪ ሃገር በሚመጡት ማሊያዎችና ቁሳቁሶች አስመጥቶ በማከፋፈል ረገድ ቦርዱ በደጋፊ ማህበሩ ላይ ሙሉ እምነት አሳድረው መስራታችን ሲታይ ከልዩነት ባፈነገጠ ሁኔታ በመግባባትና በመደማመጥ ላይ ያተኮረ ስራዎችን እየፈፀምን መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ማለት ግን ደጋፊዎች የሚያነሱት ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ተመልሷል ማለት አይደለም፤ ሆኖም የሁላችንም የጋራ ራዕይ ኢትዮጵያ ቡናን ወደላቀ የእድገት ደረጃ ማሸጋገር በመሆኑ በሰከነ ሁኔታ የደጋፊዎቻችንን ጥያቄ እያቀረብን ምላሽ እንዲሰጥበት ለማስቻል በትጋት እየሰራን ነው፡፡
ሊግ፡- መፍትሔ ለማፈላለግ የተመረጠው ኮሚቴስ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
አቶ ክፍሌ፡- እንደሚታወቀው ክለባችን ከ2004 ዓ/ም የውድድር ዘመን አንስቶ በእጅጉ እየተዳከመ በመምጣቱ በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች በቦርዱ አመራር ላይ ቅሬታ አቅርበው ስለነበር ይህን ችግር ፈቶ ወደ መፍትሔ አቅጣጫ ማምጣት የሚችል አካል በታህሳስ 2010 ዓ/ም በመንገድ ትራንስፖርት አዳራሽ በተደረገው ስብሰባ አስር የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ተመርጠዋል፡፡ ከዚህ መነሻነትም የክለቡ የቦርድ ሃላፊዎች፣ የደጋፊ ማህበሩ አመራሮችና የተመረጠው መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አንድ ላይ በመሆን ክለቡ ካለበት ችግር እንዲላቀቅ ብዙ መክረናል፡፡ በዚህም ላይ የደጋፊ ማህበሩ በክለቡ የአመራር ሚና ውስጥ የአመራርነት ሚናው እንዲጨምር መደረግ አለበት የሚል ሃሳብ ቀርቦ ከሞላ ጎደል ሃሳቡን በመርህ ደረጃ የተቀበለው በመሆኑ ምናልባትም አሁን በቅርቡ በሚጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የደጋፊ ማህበሩ አሁን ካለው ሁለት የስራ አመራር ቦርድ ውስጥ ያለው የውሳኔ ሰጪነትና ውክልና ወደ አራት ከፍ ሊል የሚችልበትን አሰራር የስራ አመራር ቦርዱ በመርህ ደረጃ ተቀብሎት በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ለማፀደቅ ሂደት ላይ ነው፡፡ እንደተባለው ይህ አጀንዳ ከፀደቀ ደጋፊው በክለቡ ላይ ያለው የአመራርነት ሚና የሚጨምር በመሆኑ ደጋፊው ያነሳቸው ጥያቄዎችና መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ከሞላ ጎደል አጥጋቢ ምላሽ አግኝተዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሊግ፡- ደጋፊ ማህበሩ የክለቡን የባለቤትነት መብት ለመረከብ ይፈልጋል ስለሚባለውስ ነገር ምን ትላለህ?
አቶ ክፍሌ፡- ይሄ የምትለው ነገር ሁሌ የሚነሳ ጥያቄ ነው፤ በክለቡ ደረጃም የባለቤትነት ጥያቄ ልታነሱ አትችሉም ይባላል፤ አንዳንድ ደጋፊዎችም የዚህ አይነት ስሜት አላቸው፡፡ ግን የባለቤትነት ጉዳይ ሳይሆን ክለቡ ቀጣይነት ያለው ውጤታማ ቡድን እንዲኖረው፣ አሰራርና አደረጃጀቱ ዘመናዊነትን የተላበሰ እንዲሆን፣ እንደ ክለብ ፕሮፌሽናል መሆን እንዲችል፣ ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ የሚችልበትን አቅም ማጎልበትና ደጋፊ ማህበሩ በስራ አመራር ቦርዱና በጠቅላላ ጉባኤው በኩል ያለው የአመራር ሚና ከፍ እንዲል ለማስቻል እንጂ እንደሚባለው ክለቡን በባለቤትነት ደረጃ ወስደን ደጋፊው ያስተዳድረው የሚል አይነት ጥያቄ ፈፅሞ የለንም፡፡ ትልቁ ነገር በክለቡ መዋቅር ውስጥ ያለን ውክልና በቂ ስላልሆነ በቂ ውክልና ኖሮን በክለቡ የአመራር ስራ ውስጥ ተሳትፎ ይኑረን የሚል ነው እንጂ ክለቡን የማስተዳደር ጥያቄ ለማንሳት ህጋዊ አግባብነት የለንም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች በርካታ ከመሆናቸው አንፃር ማህበሩን በፕሬዝዳንትነት መምራት ትንሽ አይከብድም?
አቶ ክፍሌ፡- እኔ ይሄን ሃላፊነት የምወስደው አንድ ሃገርን በበላይነት ከመምራት ጋር ነው አነፃፅሬ የማየው፡፡ ስፖርት በራሱ ከስሜት ጋር ቀጥተኛ ዝምድና ያለው ከመሆኑ አንፃር ደስታና ሃዘን እየተፈራረቀ ስለሚመጣ ጫናውም የዛኑ ያህል ነው፡፡ ምክንያቱም ፕሮፌሽናል ሳይሆን አማተር በሆነ አሰራር ውስጥ ሆነንና እንደሰለጠነው ሃገር ሲስተም ባልዳበረበት ሁኔታ ጫናው እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ ሲስተሞች በበቂ ሁኔታ ተደራጅተው ጥያቄዎች በአግባቡ በማይመለሱበት አካሄድ ሁሉም ተጠያቂነት የሚያነጣጥሩት አመራሩ ጋር በመሆኑ የራስህን ህይወት ከመምራት አኳያና የግል ስራህን በፈለግከው ጊዜ ለመፈፀም በጣም ፈታኝ ነው፡፡ ነገር ግን ለምትወደው ነገር መስዋዕት መሆንና ስፖርት ክለባችንን የህይወታቸውን ያህል ለሚደግፉት ደጋፊዎች መስዋዕትነትን ለመክፈል ስትዘጋጅ እነዚህን ጫናዎች በፀጋ ተቀብሎ ከማገልገል ውጪ ሌላ አማራጭ አይታይህም፡፡
ሊግ፡- አንዳንዴ ጫናው በከፍተኛ ደረጃ ሲበዛብህ ምነው ይሄን ሃላፊነት ቢቀርብኝ ብለህ ያሰብክበት ጊዜ አለ?
አቶ ክፍሌ፡- እንግዲህ አንተም እንደምታስታውሰው ከ1995 ዓ/ም ጀምሮ በዚህ ክለብ ውስጥ በተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች አገልግያለሁ፡፡ በስራ አስፈፃሚነት፣ በፀሃፊነት፣ በምክትል እና በፕሬዝዳንትነት እስከ 2003 ዓ/ም አገልግያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ በድጋሚ ተመርጪ በደጋፊ ማህበሩ አመራር ውስጥ የላቀ ሚና ተወጥቻለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ባለው ሁኔታ ክለባችን ወደተሻለ ፕሮፌሽናልነት አደረጃጀት ከመጓዙ አንፃር ከአንድ ጠባብ ቢሮ ተላቆ ዘመናዊ የቢሮ አደረጃጀት በመፍጠር የሙሉ ጊዜ ሰራተኞች ከ7 እና 8 በላይ ቀጥሮ ማሰራት የተጀመረበት ሁኔታ መፈጠሩና ከ50 በላይ ደጋፊዎች የሚመዘገቡበት ዘመናዊ ቅርንጫፎች መከፈታቸውን ሳይ ሁሉንም ጫና ረስቼ የበለጠ ሌት ተቀን እንድተጋ ነው የሚያደርገኝ፡፡ በርግጥ አንተም እንዳልከው አንዳንድ ጊዜ እጅግ ሞራልህንና የግል ስብዕናህን የሚነኩ ነገሮች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ሆኖም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንደሚፈጠር አጋጣሚ ስለሚቆጠር በሂደቱ ብዙም አልከፋኝም፡፡
ሊግ፡- ስፖንሰርሺፕን በተመለከተ ኢትዮጵያ ቡና ከሃበሻ ቢራ ከተጠቀመው ይልቅ ሃበሻ ቢራ ከኢትዮጵያ ቡና የተጠቀመው ነገር ይልቃል የሚሉ ወገኖች አሉ፤ አንተ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
አቶ ክፍሌ፡- እኔ የዚህ አይነቱን የተሳሳተ አስተሳሰብና አመለለካከትን ፈፅሞ አልቀበለውም፡፡ ይሄን የምልበት በቂ ምክንያት አለኝ፡፡ ሃበሻ ቢራ ገና ምርት ማምረት ሳይጀምርና ወደገበያ ሳይገባ የፋብሪካ ግንባታ ላይ በነበረበት ጊዜ ጀምሮ ነው ለክለቡ ያለውን ቁርጠኛ አጋርነት ማረጋገጥ የጀመረው፡፡ በዛን ወቅት ምንም ማምረት ሳይጀምር ለክለቡ በየአመቱ አንድ ሚሊየን ብር ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የድጋፉን መጠን ከፍ አድርጎታል፡፡ እንደማርኬት ካየኸው ካምፓኒው መስራትና ማትረፍ መቻሉ ትክክል ነው፡፡ ሃበሻ ቢራ አትራፊ ተቋም እንጂ የቻሪቲ ድርጅት አይደለም፡፡ ማንኛውም ተቋም ስፖንሰር ሲያደርግ የራሱ የሆነ ታርጌት አለው፡፡ ሃበሻ ቢራ በዚህ ረገድ ለክለቡ ገንዘብ ይሰጣል እንጂ በማኔጅመንት እና በተጨዋች ግዥ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ አይችልም፡፡ እንደዛ ከሆነ ምናልባት ክለቡ ዋንጫ ቢያገኝ ኖሮ ከሃበሻ ቢራ ይልቅ ቡና ነው የተጠቀመው ልንል ነበር? በዚህ ረገድ ጥያቄው ገንዘብ አንሷል አላነሰም የሚል ከሆነ አንፃራዊ ነው፡፡ ሁሉን ነገር በመፈተሽና የሌሎች ተሞክሮ ምን ይመስላል? የሚለውን አካሄድ ባላየንበት ሁኔታ ተጠቅሟል፣ አልተጠቀመም የሚለው አባባል የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ በርግጥ በአቅርቦትና በሽያጭ በመቶ ሺህ እና በሚሊየን ደረጃ ምርቱን በማስተዋወቅ ተሸጦ ሊሆን ይችላል፡፡ ስፖርት ደግሞ መገለጫው ውጤት ነው፡፡ እናም ስፖርትን ከፍጆታ ጋር በማነፃፀር ወደ አልተፈለገ ድምዳሜ መድረስ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ሃበሻ ቢራ ከመነሻውም ትርፍና ኪሳራውን ሳያይ ከክለባችን ጎን የቆመ አጋራችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
እናም በእኔ አስተሳሰብ ቡና ተጎድቷል አልልም፡፡ ይህ እኮ የኮንትራት ጉዳይ ነው፡፡ ከተፈለገ እኮ ቡና አሊያም ሃበሻ በዚህ ረገድ ተጎጂ ከሆኑ አብረው የመሄድ ግዴታ የለባቸውም፡፡ በየአመቱና በየሁለት አመቱ የሚታደስ ውል ስላላቸው አንደኛው ያልተጠቀመው ወገን ውሉን ሊያፈርስ የሚችልበት ሁኔታ ስላለው ማድረግ ይቻላል፡፡ እንደእኔ እምነት ግን አሁን ባለው አካሄድ ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ ናቸው፡፡
ሊግ፡- የዘንድሮውን የክለባችሁን ስብስብ እንዴት አገኘኸው?
አቶ ክፍሌ፡- ብዙ ጊዜ አንተም እንደምታውቀው ቡና ውስጥ ቡድን ገንብቶ ማፍረስ የተለመደ ነው፡፡ ለዚህ ዋንኛው ምክንያት ደግሞ አሰልጣኞች በተደጋጋሚ ጊዜ ቡድናችንን ለቀው በመሄዳቸው ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ በዚህ አመት ግን ከምንም በላይ የተጨዋቾች ተነሳሽነት መኖር፣ እጅግ ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣት ተጨዋቾች ቡድናችን ውስጥ መካተታቸውና ከክለቡ አልፈው ለብሄራዊ ቡድን ጥሩ ግልጋሎት እየሰጡ የሚገኙ ሶስት ተጨዋቾች ቡድናችን ውስጥ መካተታቸውን ስታይ የዘንድሮው ስብስባችን ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደምታውቀው 16ቱም ተፎካካሪ ቡድኖች ለማሸነፍ ነው የሚጫወቱት፤ ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ ትንሽ የሚታየው የቅንጅት ችግር ከተስተካከለ ዘንድሮ የተሻለ ነገር መፍጠር እንችላለን፡፡
የቡና ስፖርት ክለብ ከከፍተኛ ዲቪዝዮን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ሁሌም በመጀመሪያው ዙር ስኬታማ ሲሆን አይታይም፤ በሰባት አመት ሂደት ያለውን ሁኔታ ብናይ እንኳን በሁለት ጨዋታዎች ከሶስት ነጥብ በላይ አግኝቶ አያውቅም ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ከሁለት ጨዋታዎች ሙሉ ስድስት ነጥብ ማሳካት መቻሉ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ስንቅ ሆኖት እስከመጨረሻው በውጤታማነት ይዘልቃል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሊግ፡- የሲቲ ካፑን ዋንጫ ከማንሳታችሁና ሁለቱን የሊግ ጨዋታ በድል ከማጠናቀቃችሁ አንፃር ዘንድሮ ለሻምፒዮናነት ነው የምትጠበቁት?
አቶ ክፍሌ፡- አዎ፤ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልህ ከአሁን በፊት የነበሩትን የውጤት ሪከርዶች ስታስበው ክለባችን በመጀመሪያው ዙር ነጥቦችን ሲጥል ነው የምናየው፡፡ በአንድ ወቅትም ከዘጠኝ ጨዋታ አስር ነጥብ ነው መሰብሰብ የቻልነው፡፡ አሁን ግን በሁለት ጨዋታ 6 ነጥብ ማግኘቱ ሲታይ በሰባት አመት ታሪክ ውስጥ ያልታየ በመሆኑ አዲስ ታሪክ ነው የተሰራው፡፡ ከወዲሁ በዚህ መልኩ ነጥብ ማሰብሰብ ከቻልንና የቡድኑ ተሰላፊዎች ተነሳሽነት በዚሁ ከቀጠለ ያለጥርጥር ቡድናችን ዘንድሮ የሚጫወተው ለሻምፒዮናነት ነው፡፡
ሊግ፡- ስለነበረን ቆይታ በሊግ ስፖርት ጋዜጣ አንባቢያን ስም አመሰግናለሁ?
አቶ ክፍሌ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P