Google search engine

“የክለቤ አመራሮች ለግብጹ ክለብ 40 ሚሊዮን ብር ጠይቀው ዝውውሩ ባለመሳካቱ ከፍቶኛል” ዮሴፍ ታረቀኝ /አዳማ ከተማ/

 

የ2015 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስፋ የተጣለበት ወጣት ኮከብ ተብሎ ተመርጧል… አዳማ ከተማዎች አሉኝ ከሚሏቸው ኮከቦች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል…  ድፍረቱ በዝቶ በራስ መተማመኑ በጣም ጨምሮ እብሪተኛ አድርጎታል የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም ወጣቱ ተስፈኛ ዮሴፍ ታረቀኝ ግን አባባሉ እኔን አይገልጽም ሲልም ይናገራል …

ለግብጹ አረብ ኮንትራክተር ሊፈርም ከጫፍ ደርሶ ሳይሳካለት ቀርቷል… ለምን ..? ምክንያቱስ ..? ከሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቃለምልልስ  ያደረገው ተስፈኛው የመቂ ልጅ ዮሴፍ ታረቀኝ ስለ አጠቃላይ እግርኳሳዊ ጉዳይ ዙሪያ ለቀረበለት ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል…

ሊግ:- አመሰግናለሁ ለቃለምልልሱ ላሳየኸው ፈቃደኝነትህ…….የውጪ ዕድል አግኝተህ ነበር እንዴት ሆነ…..?

ዮሴፍ:- ለ15 ቀን የሙከራ ዕድል ሰጥተውኝ ነበር የሄድኩት… ኮንትራቱ ለ3 አመት እንዲሆን ፈልገው እኔ ሁለት አመት እንዲሆን ጠይቄ ተስማምተው ነበር፡፡ በኋላ ግን በአዳማ ከተማ ውል ስላለኝ አዳማዎች ለዝውውሩ ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቃቸው ሳይሳካ ቀርቷል… በዚህም በጣም ተከፍቻለሁ….

ሊግ :- ከፍተኛ ገንዘብ ማለት …?

ዮሴፍ:- ለግብጹ ክለብ አረብ ኮንትራክተር ከፈለጋችሁት 40 ሚሊዮን ብር  ክፈሉ አሏቸው፡፡ የአዳማ ክለብ  አመራሮች ግን ይህን ጥያቄ ሲጠይቁ የጠሩትን ብር እንደማላወጣ ከፍተኛ ገንዘብ መሆኑንም ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ የግብጹም ክለብ  የተጠየቀውን ብር መክፈል አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ዝውውሩ ሳይሳካ ቀርቷል… የክለቤ አመራሮችም ለግብጹ ክለብ 40 ሚሊዮን ጠይቀው ዝውውሩ ባለመሳካቱ ከፍቶኛል… እንዲቀንሱ ብዙ ጥሬያለሁ፡፡ እምቢ አሉኝ  ይሄን መሰል እድል ብዙ ጊዜኮ አይገኝም፡፡ አሁን ሄጄ ቢሆን ኖሮ የተሻለ አቅም እፈጥር ነበር፡፡

ሊግ:- ምናልባት ወሳኝ ተጨዋች በመሆንህ እንዳትሄድ አስበው ይሆን …?

ዮሴፍ:- አዎ እንዳልሄድ ስለፈለጉ ነው የሚመስለኝ፡፡ የዝውውር መስኮቱ ተዘግቶ ስለመጣሁ ማንንም አላናገርኩም፡፡  ትርጉም አልነበረውም ተመልሼ እንደማልሄድ በማረጋገጤ ዝም ነው ያልኩት፡፡ ግን የኔን እድል አበላሽተውብኝ ከፍቶኛል፡፡ ተመሳሳይ እድል ሌላ ጊዜ ቢመጣ እንደገና እንደማይከለክሉኝ ምን ዋስትና አለኝ..?  ነገ ሌላ እድል ሊመጣ ይቻል አይቻል የማውቀው ነገር የለም፡፡ ያገኘሁትን መጠቀም ላይ ትኩረት የምሰጥ ሰው ነኝ፡፡ ስለነገ አላውቅም የእውነት ከፍቶኛል… አሁን ግን እየረሳሁት ነው ማስታወስ አልፈልግም፡፡ የማይተው የማይረሳ ነገር የለም…

ሊግ:- የስንት አመት ውል አለህ ..?

ዮሴፍ:- በአዲሱ ውል ሁለት አመት አድርገውልኛል …. ቢዚ ሆነው ነው ያልጸደቀው፡፡ ሰሞኑን ሄደን እናጸድቀዋለን፡፡

ሊግ:- 40 ሚሊዮን ብር የተጠራበት የመጀመሪያው ተጨዋች ዮሴፍ ታረቀኝ ሲባል ታሪካዊ የመሆን ስሜት አልፈጠረብህም …?

ዮሴፍ:- /ሳቅ/ በለው … /ሳቅ በሳቅ/ ለኔ ታሪክ ይሄ አይደለማ…. 40 ሚሊዮን ብር ስሙ ምን ያደርግልኛል… መጫወት ስችል ነው በነጻም ይሁን በ1 ሚሊዮን ስራዬን ወጥሬ መስራቴ አይቀርም፡፡ እንዲህ ተብሎለት ነበር  መባሉ ምንም አይጠቅመኝምኮ፡፡

ሊግ:- የዓረብ ኮንትራክተር በር ተዘጋ አበቃ ማለት ነው ..?

ዮሴፍ:- እድሉማ አለ.. በሩም አልተዘጋም፡፡ አሁን በቀጥታ ሄጄ መፈረም እችላለሁ፡፡ ግን ይለቁኛል አይለቁኝም የሚለው ነው ዋናው ..

ሊግ:- እስቲ ወደ ሊጉ እንመለስ…. አመቱ እንዴት ተጀመረ …ሊጉን እንዴት አገኘኸው..?

ዮሴፍ:- ምንም ለውጥ የለውም፡፡ ከአምና የቀጠለ ነውኮ፡፡ ብዙም ለውጥ አላየሁም፡፡ 2015 ላይ የነበረውን 2016 ላይ ነው የተደገመው፡፡ የተሻለ ውጤት እንደሚኖረን ግን ርግጠኛ ነኝ፡፡

ሊግ:– አዳማ ከተማኮ በሶስት ጨዋታ 5 ነጥብ ይዞ  6ኛ ነው… እንዴት አየኧው….?

ዮሴፍ:- ገና ሶስት ጨዋታ ነው ያደረግነው፡፡ ቡድናችን ለማሸነፍ የሚጥር ቡድን ነው የሚስተካከል ነው፡፡ በተቻለ መጠን ውጤታማ ለመሆን እንጥራለን… አዲስ ስብስብ ነው፡፡ ነባሮቹ ከመልቀቃቸው አንጻር አዲሱ ቡድን ሲጠናከር የተሻለ ውጤት እናስመዘግባለን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሊግ:- የጆሲ አቋም እንዴት ነው  ባለበት ነው አድጓል ወይስ…?

ዮሴፍ:- ሊጉ ከመጀመሩ በፊት ከአምበሪቾ ዱራሜ ጋር በነበረን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ላይ ተጋጭቼ ጉዳት ስለገጠመኝ ገና እያገገምኩ ነው፡፡ በገባሁባቸው ጨዋታዎች ጥሩ ነበርኩ፡፡ ዋናው ብቃቴ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ በእስካሁኖቹ 3 ጨዋታዎችኮ 90 ደቂቃ አልተሰለፍኩም.. በመጀመሪያው ጨዋታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተቀይሬ ወጣሁ፡፡ ሁለተኛው ጨዋታ ላይ ጭራሽ የለሁበትም ተሰላፊ አልነበርኩም፡፡ ሶስተኛው ላይ ከአምበሪቾ ጋር ስንጫወት ተቀይሬ ገብቼ  ግብ በማስቆጠሬ አቻ ተለያየን፡፡ በቀጣይ በአራተኛ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሚኖረን ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ በቋሚነት የምሰለፍ ይመስለኛል አሁን ጥሩ ስሜት እየተሰማኝ ነው …

/ቃለምልልሱን የሰራነው ማክሰኞ ምሽት ነው/

ሊግ:- ከአምበሪቾ ዱራሜ ጋር አቻ ተለያያችሁ… ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋርስ..?

ዮሴፍ:-  አምበሪቾዎች በወዳጅነት ጨዋታ መተውኝ ሊጉ ጨዋታ ላይ እንዳልደርስ ፈልገው የነበረ ቢሆንም ደርሼ አገባሁባቸው …./ሳቅ በሳቅ/ ስቀልድ ነው ባክህ፡፡ የነጥብ ጨዋታ ላይ እንጂ የወዳጅነት ጨዋታ ላይ እንኳን ብዙም የሚነካ የለም… ከአምበሪቾ ጋር ጥሩ ነበርን፡፡ ንቀናቸው ሳይሆን ቀድመን ስላገባን የትኩረት ማነስ ገጠመን፡፡ የምናሸንፋቸው ያህል ተሰማን.. እንደዛም ሆኖ ከአቻው ውጤት በጣም ተምረናል፡፡ በቀጣይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጠንካራ ጨዋታ አለን። በጥሩ ሁኔታ ውጤት ለማግኘት የምንገባ ይሆናል፡፡ በእኛ በኩል ከፍ ዝቅ የምናደርገው ክለብ የለም 3 ነጥቡን ለማግኘት ጠንክረን እንጫወታለን፡፡

ሊግ:- የአመቱ ተስፋ የተጣለበት ኮከብ ተጨዋች ተብለህ የተመረጥክበት ሽልማት እጅህ ገባ..? ወይስ ..?

ዮሴፍ:- /ሳቅ/ ማቀዴማ አይቀርም፡፡ ያን ያህል ጓጉቼ አልጠበኩትም፡፡ ግን ለምን አዘገዩት እስካሁንኮ አልሰጡንም… ሽልማትኮ ደስ ይላል ያበረታታል… ያው ገንዘብ ስታገኝ የምታደርግበት ነገር አይጠፋምና ቶሎ ቢሰጡን ጥሩ ነው../ሳቅ/

ሊግ:– የበጎ አድራጎት ስራ ላይ የመሳተፍ ራዕዩ አለህ..?

ዮሴፍ:- ዋናው የማስበውና የማቅደው ይህን ነው… የበጎ አድራጎት ስራ ያስደስታል፡፡ ለሰው መድረስ መስጠት ጥሩ ስሜት ይፈጥራል.. አሁንም ቢሆን የምችለውን የምረዳቸው ሰዎች አሉ፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ በቀጣዮቹ አመታት ጥሩ የፋይናንስ አቅም ስፈጥር የበጎ አድራጎት ዋነኛ ትኩረቴ መሆኑ አይቀርም፡፡ ትተነው ለምንሄደው ለተቸገሩ ወገኖቻችን መድረስ ያኮራልና በዚህ ላይ ትልቅ ህልም አለኝ፡፡

ሊግ :- የተወለድከው መቂ ነው ….የመቂ አምባሳደር አድርገህ ራስህን ትቆጥራለህ…?

ዮሴፍ:– አዎ…የወጣቶች አርአያ መሆኔ ይሰማኛል… መቂን በውጤታማነቴ ለማስጠራት እጥራለሁ፡፡ በዚህም ሃላፊነቴ ደስተኛ ነኝ… ለወጣቶች አርአያ የመሆን ግዴታዬን እንደምወጣ ርግጠኛ ነኝ፡፡ መቂ ከፈቀደችና አምባሳደር ካደረገችኝ ደግሞ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡

ሊግ:- ዮሴፍ ታረቀኝ እብሪተኛ ነው ወይስ በራሱ የሚተማመን….የቱ ይገልጽሃል ..?

ዮሴፍ:– እብሪተኛ አይደለሁም …አስቸጋሪም አይደለሁም፡፡ በአልሸነፍ ባይነት ስታገል ለሚፈጠረው ቅሬታ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ይሄ ባህሪዬ ነው ያልሆነ ስም እያሰጠኝ ያለው… ከሜዳ ውጪ ከማንም ጋር አልነካካም ሜዳ ውስጥ ባለኝ ታጋይነት የተጋጣሚ  ቡድኖች  ደጋፊዎች ቅር ሊሰኙ ይችላሉ ምንም ባለማድረጌ ግን አዝናለሁ፡፡

ሊግ:-  ለአዳማ ደጋፊ የምትለው ነገር አለ…?

ዮሴፍ:- ለደጋፊዎቻችንም የምለው ነገር አለኝ፡፡ እብሪተኛ አይደለሁም ማንንም አልሰማም የምል አይደለሁም፡፡ ግን ጎል አስቆጥሬ ጣቴን ጆሮዬ ላይ አድርጌ ስጨፍር ደጋፊ አልሰማም እያለ ነው እየተባለ የሚሰጠው ትርጉም ልክ አይደለም… ቀርበው አውቀውኝ ቢናገሩ እመርጣለሁ፡፡ አብዛኛው ደጋፊ ይረዳኛል። ሳያውቁኝ የሚሳደቡ ደጋፊዎችን ግን አሁንም አልሰማም ቅረቡና አውቃችሁ ተቹ አመስግኑ፡፡ በግሌ አቋሜ ሲወርድ የሚተቹኝ ጥሩ ስሆን የሚያወድሱኝ ደጋፊዎቻችንን አመሰግናለሁ…

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P