Google search engine

“13 ተጨዋቾች ለቅቀውም የተቋቋምነው ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለሆነ ነው” “በየአመቱ ጠንክረው ብቅ የሚሉ ክለቦች ቢኖሩም እኛ ግን በየአመቱ መኖራችን ያኮራኛል” አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

ባለፉት ሁለት አመታት የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫን ያነሱት ፈረሰኞቹ አሁን ግን ከባድ ፈተና ገጥሟቸዋል…ሊጉ ሊጠናቀቅ 8 ጨዋታ በቀረበት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  በ7 ነጥብ በመቻል ደግሞ በ2 ነጥብ ተበልጠው ከባድ ትግል ገጥሟቸዋል….ለ3 ተከታታይ አመታት ሻምፒዮን ለመሆን ላቀዱት ጊዮርጊሶች ቀሪዎቹ ጨዋታዎች ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ ውድድሩ ገና ቢሆንም የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ  ዘሪሁን ሸንገታ ባለፉት ሁለት አመታት 15ቱን  ክለቦች ወደ ታች  ሲመለከት ቢቆይም አሁን ደግሞ ሁለት  ክለቦችን አንጋጦ የማየት  ተራ ደርሶታል….የሊጉ ዮሴፍ ከፈለኝ  በአጠቃላይ የሊጉ ፉክክር፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ የአሁን አቋምና ሌሎች እግርኳሳዊ ጉዳዮች ከፈረሰኞቹ አለቃ  አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጋር ያደረገው ቃለምልልስ የሚከተለውን ይመስላል..

ሊግ:-  የድሬዳዋ ቆይታችሁ ምን ይመስላ..?

ዘሪሁን:- በሁለት መንገድ እንየው.. የመጀመሪያው የትኛውም ቡድን ምክንያት የሚያቀርብበት ሜዳ አይይደለም..የድሬዳዋ ከንቲባ አቶ ከድርን አመሰግናለሁ… እንደሀገር ትልቅ ስራ ነው የሰራው  እንደዚህ አይነት ሜዳዎች ለእግርኳሱ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አለውና  ሁሉም  ቡድን ያለውን እንዲያሳይ የተሻለ ስራ እንዲሰራ ያደረገ በመሆኑ ሁሉም ክልልሎች ተመሳሳይ ጥራት ያላቸው ሜዳዎች እንዲሰሩ የድሬዳዋና የከንቲባዋ ተግባር  አርአያነት ሊወስዱ ይገባል..ስራው የሚያስመስግን ነው ጥሩ ጊዜ ነበረን በዚህ ደስተኛ ነበርኩ.. ከውጤት አንጻር ሰባት ጨዋታ ተጫውተን 3 አሸንፈን  2 ጊዜ አቻ ወጥተን  2 ጊዜ  ተሸንፈን  የድሬ ቆይታችንን ጨርሰናል ጥሩ የጨዋታ አቀራረብ ነበረን  የምንችለውን ሞክረናል ነገር ግን አቋማችን ሊዋዥቅ ችሏል..አንዳንድ የአጨራረስ ድክመት ነበረብን… ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደጋግመን ደርሰናል በአጨዋወት የቅዱስ ጊዮርጊስን ከለር አሳይተናል፡፡ ነገር ግን ግብ ማስቆጠር ሳንችል ዋጋ አስከፍሎናል እንደ ቡድን  በውጤቱ አልተደሰትንም አመርቂም አይደለም ከዚህ የተሻለ ብቃት ይፈለግብናል ብዬ አምናለሁ

ሊግ:- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነት  አያስፈራም..? ስጋት አይፈጥርም..?

ዘሪሁን:-  የምን ስጋት..? ለሰከንድም አስቤው አላውቅም… አምናና ካቻምና ዋንጫውን የወሰደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው  አሁን ገና 8 ጨዋታ ይቀራል  ጥሩ ፉክክር እየተደረገ ነው ዋናው እኛ የቱ ጋር ነን እነሱስ እንዴት መጡ የሚለውን ማየት ይጠበቃል። በርግጥ ማግኘት ካለብን 21 ነጥቦች ወደ 10 ነጥቦችን ጥለናል እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህ ውጤት ያበሳጫል አሁን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ7 ነጥብ እየመራን  ነው፡፡  ገና በመሆኑ ግን ስጋት የለብንም፡፡

ሊግ:- በሁለት የዋንጫ አመታቶችሁ  እንዲህ ተበልጠህ ታውቃለህ..?

ዘሪሁን:– አዎ ነበሩ የሆኑ ወረድ ደከም የምንልባቸው ጊዜያቶች ነበሩ አይረሱም በወቅቱ ግን የአሸናፊነት አዕምሮ ስለነበረን አልተረታንም አሁንም ገና 8 ጨዋታ ስለሚቀር የማስተካከያ ጨዋታ ይሆናል፡፡ ዋናው  የምንስታቸው እኛንም  የሚጎዱን እንዳይሆን ግን በቀሪ 8 ጨዋታዎች ጠንክረን መስራት አለብን ብዙ አጥቅተን ለፍተን የምንስትና ራሳችን ላይ አደጋ የምንፈጥር ከሆነ አደጋ አለው፡፡ ያንን ለማስተካከል ጠንክረን እንሰራለን ስለ እውነት ግን ጥሩ ስሜት አልተሰማኝም፡፡ ግን እግርኳስ ሂደት መሆኑን አውቃለሁ ማሸነፍ አቻና መሸነፍ አለ ሁሌም ዌንጫ መውሰድ ላይኖር ይችላል ያም ሆኖ የጨዋታ ዘይቤና አቅም ከቡድኑ  ስነልቡና ጋር ማቀናጀት ከተቻለ መስተካከሉ አይቀርም  የምንስታቸው ኳሶች ራሳችን ላይ አደጋ እየፈጠሩ ነው በዚያ ላይ ብዙ ተጨዋቾች  ከቡድናችን ለቀዋል ..ወደ 13 ተጨዋቾች ለቅቀው እንኳን የተቋቋምነው ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለሆነ ነው እንደ አጠቃላይ ውድድሩ አላለቀም ስጋትም የለብንም፡፡

ሊግ:- የውጤት መንገጫገጩ  የመጣው ተጋጣሚዎቹ ጠንካራ ሆነው ስለመጡ ወይስ  እናንተ ስለወረዳችሁ..?

ዘሪሁን:– መታወቅ ያለበት 15ቱም ክለቦች ከእኛ ጋር ሲጫወቱ  ጠንክረው ነው የሚቀርቡት ከእኛ ጋር ያለው ጨዋታ ሁሉም ከባድ ነው ለእኛ እያንዳንዱ ጨዋታ የዋንጫ ነው  ተፋልመውን ካላቸው አቅም በላይ ነው የሚያወጡትና  ጠንክረን መጠበቅ አለብን  እንደ አጠቃላይ እነሱ ከእኛ ጋር ሲመጡ ጠንክረው  ሊፋለሙን መሆኑና የእኛም  ስህተት ታክሎበት ነው የተሻለ ነገር ሰርተንም ሽንፈት ሲገጥመን ወይም አቻ ስንወጣ የሚገባንም ይሄ ነው፡፡

ሊግ:-  በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ደጋፊው ለሁለት መከፈሉ ከቦርዱ ጋር ያለው ክርክር ተጨዋቾቹ ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ  የለም…?

ዘሪሁን:-  ይኖራል እንጂ…መረጃውኮ ቀጥታ የሚሄደው አዕምሮ ላይ ነው..ከባድ ነው  ሳይኮሎጂ ከባድ ነው የኳሱ ስራኮ መነሻው በአዕምሮ ነው እናም ጉዳት ሊፈጥር ይችላል  ግን ይህን ሁሉ ለመቋቋም ነው የምንሰራው፡፡ እንደ ዘንድሮ ባይጋነንም አምናም ካቻምናም  ነበር  አዕምሯችን መጠበቅ አለብን የምንሰማው እኛን ወደኋላ ማስቀረት የለበትም እዚህ ላይ አስምሬ መናገር የምፈልገው፡፡  ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድነት መክሮ ክለቡን ወደተሻለ መንገድ ሊዪመጣ ይገባል እንጂ እንዲህ ልዩነት መፈጠር የለበትም፡፡ ሁሉም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ነው የሚጥረውና  ደጋፊውም ቡድኑም ተመሳሳይ አላማ ስላለን ቤታችንን ዘግተን  የውስጣችንን ገበና ይዘን መምከር አለብን የሚል እምነት አለኝ ለማንኛውም ሰው ነገሩ መነገር  መረጃው መውጣት የለበትም፡፡ ጉዳዩ የቅዱስ ጊዮርጊሳዊያን ብቻ ስለህነ ዘግተን ተጠባብቀን መነጋገር  አለብን  ቡድኑ ላይም ተጽዕኖ ቢኖረውም በጋራና በአንድነት  በህብረት ከእግዚአብሄር ጋር የምንወጣው ይሆናል፡፡

ሊግ:- ቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ አባጅፋር  ከታችችኛው ሊግ ባደጉበት አመት  ዋንጫ ወስደዋል ..አሁን ደግሞ በተመሳሳይ  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋንጫውን   ሊወስድ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ…እዚህ ላይ ምን ትላለህ..?

ዘሪሁን:– በርግጥ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትልቅ ቡድን ነው ይሄ አያከራራክርም ሊጉን እየመራሞ ነው በያዘው አቋም የሚቀጥል ከሆነ ዋንጫ የማያነሳበት ምክንያት የለውም  ግን ውድድሩ ገና  8 ጨዋታ አለው  ብዙ ነገር ሊፈጠሩ ይችላልና እገሌ የሚባለው ክለብ ዋንጫ ሊወስድ ነው አይደለም የሚለው የሚወራበት ጊዜ ነው ብዬ ግን አላስብም፡፡ ገና ነው፡፡ ወደ አራት አምስት ክለቦች የዋንጫ ማንሳት እድል አለን። በርግግም  በሰባት ነጥብ ርቆናል  ያም ሆኖ ተሻሽለን መቅረብ ይጠበቅብናል፡፡ እንደ አሰልጣኝ 16ቱም ክለቦች  አሪፍ ናቸው… ከላይ ያሉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መቻል ምርጥ ናቸው ለዋንጫና ለመቅረት የሚደረጉ ፉክክሮችን የምናይባቸው 8 ትንቅንቅ ያለባቸው ጨዋታዎች አሉ  እነሱን ሳላይ  መናገር አይቻልም፡፡

ሊግ:-  22 ሳምንት ጨዋታዎች  ተካሂደወል….  ከነዚህ ጨዋታዎች መሃል  በማሸነፍህ የተደሰትክበት የትኛው ጨዋታ ነው..?

ዘሪሁን:- ሁሉም ያሸነፍኳቸው ጨዋታዎች አስደስተውኛል ምክንያቱም  የምፈልገውን የጨዋታ ፕላን  የሚጫወቱበትና እንደ ጊዮርጊስ ተጨዋቾቼ ያሰብኩትን ፈጽመዋል አልፈጸሙም የሚለውን የማይባቸው ስለሆነ ነው ለኔ ይሄ ነው የሚያሳስበኝ … የምፈልገውን  አድርገዋል ወዳቀድኩት  መስመርስ ገብተዋል የሚለው ነው የሚያሳስበኝ ሁለም ቡድኖች ጠንክረው ስለሚመጡ ትንሽና ትልቅ የምለው ጨዋታ የለኝም፡፡ ለሁሉም ጨዋታዎች የምሰጠው ዋጋ ተመሳሳይ በመሆናቸው ለይቼ  ያሸነፍኩት የምለው የለኝም፡፡

ሊግ:- ፕሪሚየር ሊጉ ባለፉት 3 አመታት  ጠንካራ እየሆነ መጥቷል ማለት ይቻላል..?

ዘሪሁን:- አምናም ሆነ ካቻምና  ዘንድሮም ጨዋታዎቹ ከባዶች ናቸው  ሁሉም ጠንክሮ ነው የመጣው…. አምና ባህርዳርን ካቻምና ፋሲል ከነማን ትጠራለህ ዘንድሮ ኢትዮጵያ  ንግድ ባንከና መቻል አሉ ነገር ግን ደስታዬ ሁሉም ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ መኖሩ ነው በየአመቱ ጠንክረው ብቅ የሚሉ ክለቦች ቢኖሩም እኛ ግን  በየአመቱ  መኖራችን ያኮራኛል። ይሄ የሚያሳየው ስራችን በአግባቡ በትክክል የምንሰራ መሆናችንን ነው መሆን ያለበትን አድርገናል ወይስ የሚለው ነው ሁሌም የሚያሳስበኝ፡፡

ሊግ:- ዳኝነቱ ተመቸህ..?

ዘሪሁን:-ዳኝነት ሊመችም ላይመችም ይችላል ብዙ ስህተቶች ሊታዩ ይችላል ግን እንደ እኛ ሰው ናቸው  ማለፍ መታገስ አለብን በጸጋ መቀበል አለብን ብዬ አስባለሁ ስህተታቸው ዋጋ የሚያስከፍሉ ይሆናሉ ግን እኔም እነሱም ሰው ነን  ማንኛውም ሰው ሊሳሳት ይችላል እነሱም እንደዛው… ከስህተት ቶሎ ተምረው ጨዋታውን ውብ የማድረግ ሚናቸውን በቀጣዮቹ ጨዋታዎች እንደሚያሳዩ ተስፋ አደርጋለሁ …  ለነሱ ትልቅ ክብር አለኝ  እነሱ ላይ ጣቴን መቀሰር  አልሻም

ሊግ:– ባለፉት ሁለት አመታት 15ቱን ክለቦች ወደ ታች እያየህ ጨርሰሃል…አሁን ግን ንግድ ባንክና መቻልን ወደላይ አንጋጠህ እያየህ ነው… ይሄኝንስ እንዴት ትገልጸዋለህ..?

ዘሪሁን:-ጠንካራ ቡድኖች ሆነው ብቅ ብለዋል ግን ትኩረቴ አሀንም ስራዬ ጋር ነው ገና 24 ነጥቦች ያሉቧቸው ግጥሚያዎች አሉ ይሄ  አያሳስበኝም ትልቅ ፉክክር እንደሚኖረን አምናለሁ ሁለቱ ከላይ ያሉት ቡድኖች ብቻ ሳይሆን ከታችም ያሉት  ክለቦች ጠንካራ ናቸው ፉክክሩ ከብዷል የተሻለና ጥሩ ነጥብ የሰበሰበ ቡድን ዋንጫ ይወስዳል ያንን ለማድረግም እየሰራን ነው፡፡

ሊግ:– ለተጨዋቾችህ ሁሌ የምትላቸው ነገር ምንድነው..?

ዘሪሁን:– የቡድን መንፈስ እንዲጠብቁና ለእያንዳንዱ ጨዋታ ትኩረት ሰጥተው እንዲገቡ ሁሌ የማሳስበው ይህንን ነው

ሊግ:- ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር ሰላም ነው…?

ዘሪሁን:- ሁሉ አማን ሁሉ ሰላም ነው የሚገባንን ስራ በህብረት እየሰራን ነው ምንም አይነት ችግር የለም

ሊግ:- ከአንድ ተጨዋች ቋሚና ተጠባባቂ ይሁን ከሚል የሃሳብ መነሻ የተፈጠረ ክፍተት የለም..?

ዘሪሁን:– የለም በፍጹም አልተከሰተም  ሃሳባቸውን እሰማለሁ እንማከራለን  የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት መብቱ ግን የኔ ነው ይሄ በፍጹም አልተጣሰም ልዩነትም አልተፈጠረም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት የተፈጠረ ነገር የለም፡፡

ሊግ:- የቡድን መሪው አዳነ ግርማ  ጋርስ..?

ዘሪሁን:-  የምን ጸብ..? አልተፈጠረም አንደኛ የቡድን መሪ ነው ቡድኑ ጋር  የግድ ይኖራል… ደግሞም  የትም ሄዶ አያውቅም አንዴ ግን  መልበሻ ቤት እያለን ተናግሮት መሰለኝ  ኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ እቀጣዋለሁ ወደዚህ እንዳይመጣ ስላላለኝ እንዳይቀጣው ብዬ  ከመልበሻ ቤት አትውጣ ብዬው አውቃለሁ በቃ፡፡

ሊግ:– ጨረስኩ…የምትለው የመጨረሻ ቃል ካለህ….?

ዘሪሁን:– በቃ እኔም ጨርሻለሁ  አመሰግናለሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P