Google search engine

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ከተቀላቀሉት ክለቦች መካከል የአዲስ አበባ ከተማው ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ እና የመከላከያው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ቴዎድሮስ ታፈሰ በቡድናቸው ስኬት ዙሪያ ይናገራሉ

“የአሰልጣኛችንን ታክቲክ ልንተገብር ስለቻልን ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ልናልፍ ችለናል”
ሳምሶን አሰፋ /አዲስ አበባ ከተማ/

“በልፋታችን ዋጋ ፕሪምየር ሊጉን ተቀላቅለናል”
ቴዎድሮስ ታፈሰ /መከላከያ/

#በመሸሻ_ወልዴ

በኢትዮጵያ ከፍተኛው ሊግ ይወዳደሩ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ ክለቦች አዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና የመከላከያ ክለቦች ከተደለደሉበት ምድብ ውስጥ ቀዳሚ ደረጃን በማስመዝገባቸው የመጪው ዘመንን የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን በቅድሚያ የተቀላቀሉ ክለቦች ሲሆኑ አርባምንጭ ከተማም ይህን እድል ለማግኘት ከመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡

የምድብ ሁለት ተወዳዳሪ የነበረው የአሰልጣኝ እስማኤል አቡበከሩ አዲስ አበባ ከተማ ፕሪምየር ሊጉን ሊቀላቀል የቻለው 12 ቡድኖች ተካፋይ በነበሩበት ውድድር ላይ  ኢኮስኮን 2-0 ያሸነፈበት ጨዋታ 48 ነጥብን እንዲያስመዘግብ አድርጎት ተከታዩ ሀምበሪቾ ከነማ ሊደርስበት በማይችልበት መንገድ ቀሪ ሁለት ጨዋታ እያለው ሊያልፍ የቻለ ሲሆን የምድብ አንድ ተካፋዩ እና የአሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌው መከላከያም 9 ቡድኖች ከሚሳተፉበት ምድብ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን 1-0 የረታበት ግጥሚያ 35 ነጥብ ላይ እንዲቀመጥ ስላስቻለው አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው ከወዲሁ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ሁሉ የመጪው ዘመን ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ መሆናቸውን ሊያውጁ ችለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማንና የመከላከያ ክለቦችን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማለፍን አስመልክተን ከሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች ማለትም ከአዲስ አበባ ከተማው ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ ጋርና ከመከላከያው አማካይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ጋር አጠር ያለ ቆይታን ያደረግን ሲሆን እነሱም ምላሻቸውን ሰጥተውናል፡፡

ከከፍተኛ ሊጉ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በመቀላቀላቸው ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማው እና የቀድሞ የመተሀራ፣ የኤሌክትሪክ፣ የድሬዳዋ ከተማ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስና የብሔራዊ ቡድናችን ግብ ጠባቂ የነበረው ሳምሶን አሰፋ ምላሹን ሲሰጥ

“አዲስ አበባ ከተማ ወደ ከፍተኛው ሊግ ውድድር ሲገባ የመጀመሪያ እቅዱ የነበረው በምድቡ ካሉት ክለቦች ጋር ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ምርጥ ቡድንን ለመገንባት ነበር፤ ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉም በፍጥነት እንገባለን ብለንም አልጠበቅንም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ውድድር ላይ ከገባን በኋላ በአሰልጣኛችን እስማሄል አቡበከር አማካኝነት እንደ ቡድን በደንብ ልንዋሃድ ስለቻልንና እሱ በሚሰጠን ጥሩ ስልጠናም እኛ የእሱን ታክቲክ በአግባቡ ልንተገብር ስለቻልን የቡድኑን የፕሪምየር ሊግ የመሳተፍ እልሙን ከ5 ዓመት በኋላ ልናሳካው ችለናል፤ ይህን ድልና ስኬት ስለተጎናፀፍን በጣምም ደስ ብሎናል”፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ክለብ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎ ለቡድኑ በምን ያህል ግጥሚያዎች ላይ ለመሳተፍ ቻልክ…ለሚለው ጥያቄም ምላሹን ሲሰጥ

“እስካሁን ካደረግናቸው 20 ጨዋታዎች ውስጥ በ18ቱ ላይ ተጫውቻለው፤ ሁለት ግጥሚያዎችን ብቻም ነው ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ሳልጫወት የቀሩት” ብሏል፡፡ አዲስ አበባ ከተማን ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያልፍ ካስቻሉት ጠንካራ ጎኖች ውስጥ የቱ በቀዳሚነት ይጠቀሳል በሚል ጠይቀነውም “ለእዚህ ውጤት እንድንበቃ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው አሰልጣኛችን እስማሄል ነው፤ እሱ ለየጨዋታው የራሱ የሆነ የማሰልጠን ፕላን ነበረው፤ እሱ ውጤታማ ሊያደርገን የሚችለውን ታክቲክ ይሰጠን ነበር፤ እኛ ደግሞ ያን ተቀብለንለት በሜዳ ላይ ስለምንተገብረው በዛ ነው ቤትኪንጉን ልንቀላቀል የቻልነው”፡፡ ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ ብዙዎች በድሬዳዋ ከተማ ግብ ጠባቂነትህ ነበር የሚያውቁህ፤ አንተ ግን አዲስ አበባ ከተማ ክለብ ውስጥ ተገኘክና ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያልፍ ካደረጉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ሆንክ፤ በዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ  ..

ቀደም ሲል ከነበርኩበት ቡድን ለቅቄ ወደዚህ የመጣሁት አሁን ላይ ልናገራቸው በማልፈልጋቸው ምክንያቶች ነው፤ ሁሉን ነገርንም ጊዜ ይፈታዋልም፤ በእዚህ ሁኔታ ላይ ሆኜና ወደ አዲስ አበባ መጥቼም ይህን ቡድን ለእዚህ ክብር ከጓደኞቼ ጋር እንዲበቃ ስላደርግኩት የተለየ የደስታ ስሜትም ተሰምቶኛል”፡፡
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ከመቀላቀላችሁ አኳያ በመጪው ዘመን ጠንካራ ተፎካካሪስ ትሆናላችሁ በሚልም ጥያቄን አቅርበንለት ሲመልስ “በዚህ ዙሪያ አሁን ላይ ሆኜ ብዙ ነገርን ለማለት ባልፈልግም በአሰልጣኝ እስማሄል አቡበከር የተገነባው ቡድን ግን ጠንካራና ምርጥ እንደዚሁም ደግሞ ጥሩ አቅም ያላቸው የተጨዋቾች ስብስብ ያሉበት እንደነበር አውቃለው፤ ይሄ ቡድን ከአንድ አንድ ክፍተት ቦታዎች በስተቀርም ክለቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ጥቂት ልጆችን ማምጣት እንጂ ብዙ ጥገናም  የሚያስፈልገው ስላልሆነ ጊዜው ባይደርስም ጥሩ ነገርን መጠበቄ ግን ከፍተኛ ምኞቴ ነው”፡፡

በከፍተኛ ሊግ ተሳትፎአችሁ የአዲስ አበባ ከተማ ቡድንን ምን ነገር የተለየ ያደርገዋል…

“ከሁሉም በላይ በምርጥ ተጨዋቾች የተገነባው ቡድናችን ታክቲካሊ ዲስፕሊን ሆኖ መጫወቱ ነው ከሌላዎቹ ቡድኖች እኛን ለየት ያደርገን የነበረው፤ በዚህ ውስጥ ስናልፍም ብዙ ጎሎችን እንዳናስቆጥርና ጥቂት ግብን ብቻ እንድናስተናግድ ከማድረጉ ባሻገር የመጀመሪያው ዙር ውድድር ሊጠናቀቅ የሶስት ሳምንት ሲቀረው ጀምሮ እስካሁን ድረስም አንድም ግብ ሳይቆጠርብንና ሶስት ጨዋታም እየቀረን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ስለገባን ይሄ ለእኛ ታሪካዊ ውጤትም ሆኖ ተመዝግቧል”፡፡

በመጨረሻ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ ብለንም ጠየቅነው፤ እሱም ይህን መለሰ “የአዲስ አበባ ከተማ ቡድናችን ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለማለፉ ከሁሉም በበለጠ ከፍተኛ ድርሻውን የሚወስደው አሰልጣኛችን እስማሄል አቡበከር ነው፤ የእዚህ ወጣት አሰልጣኝ በዚህ ደረጃ ውጤት ማምጣትም ለሌሎቹ ወጣት አሰልጣኞች በር የሚከፍትም ስለሆነ እሱን በቅድሚያ ላመሰግነው እፈልጋለው፤ ከእሱ በመቀጠል ደግሞ ከእስማሄል ጋር ሲሰሩ የነበሩት ረዳት አሰልጣኙ ደምስ እና ለቡድኑ እንደ ሳይኮሎጂስት /የስነ-ልቦና ባለሙያ እና ሽማግሌም ጭምር በመሆን ቡድናችንን በብዙ ነገር ይጠቅም የነበረው የግብ ጠባቂያችን አሰልጣኝ መሰረት ወልደ ማሪያም እንደዚሁም ደግሞ የቡድን መሪያችን ሲሳይ እና የቦርድ ሀላፊዎቹ በጋራ ተጣምረው ለውጤቱ መሳካት ትልቁን ሚና ተጫውተዋልና እነሱም ይመስገኑልኝ፤ ከዛ ውጪ ስማቸውን ልጠራቸው የምፈልጋቸው ሁሌም ከጎኔ አሉ፤ አንዷ የልጆቼ እናት ማህሌት ታምራት /ናቲ/ ናት፤ ሌላዋ እናቴ ብርሃኔ ማሞም ለእኔ ጊዜን ሰጥተውን አይዞንም ብለው እልሜን እንዳሳካና የቀድሞ ስምና ዝናዬንም በቀጣይነት ለመመለስ እንድችልም የሚያደርጉልኝ ጠቃሚ ነገር አለና ለእነሱም ምስጋና አለኝ”፡፡

የመከላከያ እግር ኳስ ቡድን ለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ መብቃቱን ተንተርሶ ሌላ ያነጋገርነው ተጨዋች ቴዎድሮስ ታፈሰም ለጥያቄዎቻችን መልስን ሰጥቷል፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ስለመቀላቀላቸው ተጨዋቹ ይህንን ብሏል “ቡድናችን በዘንድሮው የከፍተኛው ሊግ ውድድር ካለበት ምድብ ቀዳሚ ሆኖ ሊጉን ለመቀላቀል መቻሉ የሚገባው ውጤት ነው፤ በውድድር ዘመኑ ይህን ውጤት ለማግኘት ከየትኛውም ቡድን በፊት የፕሪ-ሲዝን ዝግጅትን የጀመርነው እኛ ነበርን፤ ብዙ ልፋት አድርገንም ነው ይህን የድል ስኬት ያገኘነው”፡፡

ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለማለፍ የእናንተ ጠንካራ ጎን ምን ነበር?

“አንድነታችን፤ ጥንካሬያችንና ፍቅራችን የተለየ ነበር፤ ሁሉም በአሰልጣኙ ዩሃንስ ሳህሌ የሚሰጠውን የታክቲክ ስራም እየለፋም ሲሰራ ነበር፤ ሀላፊነታችንን ልንወጣ ስለቻልንም ነው በዚህ ጥንካሬያችን ሊጉን ለመቀላቀል እና የልፋታችንንም ውጤት ልናገኝ የቻልነው”፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ከእናንተ ውጪ ኢትዮ-ኤሌክትሪክም የመራበት ጊዜ ነበር፤ ከእዛ የእናንተ ማለፍ ተረጋገጠ፤ ጠንካራ ውድድር ነበር ማለት ነው?

“አዎን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታችን ዝዋይ ላይ የተደረገ ነበር፤ በዛ ቆይታችንም ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የምድቡ መሪ ነበር፤ ከዛ ውድድሩ ወደ ሐዋሳ ሲመጣ የመጀመሪያ ጨዋታችንን እነሱን በማሸነፍ መሪነቱን ልንነጥቃቸው ቻልንና በስተመጨረሻም የእኛ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማለፍ እውን ሊሆን ቻለ፤ የከፍተኛ ሊጉ ውድድር በጣም ጠንካራ ነው፤ በዛ ውስጥ ተፈትነንም ነው ለዚህ ክብር የበቃነው”፡፡

መከላከያ እንደ ፕሪምየር ሊግ ቆይታው ጥሩ ኳስን እየተጫወተ ነበር የመጣው በሚልም ጠይቀነው

“የከፍተኛ ሊግ ውድድር እንደ ፕሪምየር ሊግ አይደለም፤ መጫወት ባለብን ሰዓት ጥሩ እንጫወታለን፤ ከዛ ውጪ ቀድሞ ጎል ያስቆጠረ ቡድን የውጤት ተጠቃሚም ይሆናልና ጨዋታችን ተለዋዋጭም ነበር”፡፡
የመከላከያን በታችኛው ሊግ መጫወት አስመልክቶ ቡድኑን ሊለቅ ተቃርቦ እንደነበር “መጀመሪያ ላይ ያለመግባባት ነበር፤ በዛ ሰዓት ላይም በስምምነት ለመልቀቅ ከጫፍ ደርሼም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ይሄ ቡድን ለእኔ ከስር ጀምሮ ያደረገልኝ ጥሩ ነገር ስለነበርና አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌም እኔን በጣም እንደሚፈልገኝ ስለነገረኝ ወደላይ ሄጄ ለመጫወት ከፍተኛ ጉጉት ባልነበረኝ ሁኔታ ለዚህ አሳዳጊዬ ቡድን ተጫውቼ ቡድኑን ወደ ነበረበት ፕሪምየር ሊግ ዳግም እንዲመለስ ከጓደኞቼ ጋር ጥረትን ስላደረግኩኝ በጣም ደስ ብሎኛል”፡፡

በመጨረሻ

  “መከላከያ ለእኔ ከምገልፀው በላይ ጥሩ የሆነልኝ ክለብ ነው፤ ይሄ ቡድን ወደታችኛው ሊግ ሲወርድም በጣም ቆጭቶኝ ነበር፤ አሁን ደግሞ ዳግም ይሄን ቡድን ወደነበረበት ስንመልሰው ደስታዬን የተለየ ነው ያደረገው፤ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ቆይታዬ ለዚህ ቡድን ሁሉም ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ 5 ያህል ግቦችን ለማስቆጠር ችያለው፤ ይሄ ቡድን በመጪው ዓመት ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎውም ላይ ጠንካራ ቡድንን ፈጥሮ እንደሚመጣ ስለማውቅ ያኔም ጥሩ ችሎታዬን አሳይቼ ቡድኔን ለውጤት ለማብቃትና ለሀገሬም ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ስለመጫወትም አስባለው፤ ይህንን ካልኩ ለዘንድሮ ቡድናችን ውጤት ማማር የአሰልጣኙ ዩሃንስ ሳህሌ ድርሻ ከፍ ያለ ነውና እሱን በመቀጠል ደግሞ የቡድናችንን ተጨዋቾችና እየመጡ ሲደግፉን የነበሩትን ደጋፊዎቻችንን ለማመስገን እወዳለው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P