Google search engine

“ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፍ ብቻ እኛን ለሻምፒዮናነት አያበቃንም” በዛብህ መላዮ /ፋሲል ከነማ/

የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂው እና አጓጊው ጨዋታ
ኢትዮጵያ ቡና Vs ፋሲል ከነማ
ቀን፡- ቅዳሜ ጥር 27/2013
ሰዓት 4፡00

በመሸሻ ወልዴ

የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና የሁለተኛው ዙር የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከትናንትናው ዕለት አንስቶ መካሄድ የጀመረ ሲሆን ቀጣይ ጨዋታዎቹ ደግሞ ዛሬና ነገ ይደረጋሉ፤ በዛሬው ዕለት ከሚካሄዱት ጨዋታዎች መካከልም የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት የቀኑ 4 ሰዓት ላይ ጨዋታ ወሳኝና ተጠባቂም ሆኗል፤ የሁለቱ ቡድኖች የጨዋታ አሸናፊም ወይ የነጥብ ልዩነቱን ያሰፋዋል አልያም ያጠበዋል ተብሎም ስለሚጠበቅ ግጥሚያው በሁለቱም ቡድን ተጨዋቾችና ደጋፊዎቻቸው ዙሪያም ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል፡፡

ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በ32 ነጥብ እየመራ ባለው ፋሲል ከነማ እና በ5 ነጥብ ልዩነት ተበልጦ እየተከተለ በሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና መካከል ስለሚደረገው የዛሬ ጨዋታ፣ ስለ ራሳቸው እና ስለ ቡድኖቻቸው አስመልክተን ከሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች ውስጥ በአማካይ ስፍራ ላይ በጥሩ መልኩ የሚጫወቱትን የኢትዮጵያ ቡናውን ሬድዋን ናስርን እና የፋሲል ከነማውን በዛብህ መላዮን አናግረናቸዋል፤ ተጨዋቾቹም ምላሻቸውን ሰጥተውናል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፍ ብቻ እኛን ለሻምፒዮናነት አያበቃንም” በዛብህ መላዮ /ፋሲል ከነማ/

ስለ ፋሲል ከነማ ወቅታዊ አቋም

“ፋሲል ከነማ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ የውድድር ተሳትፎው ራሱን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እያሻሻለ በመምጣት የአሁን ሰዓት ላይ በመሪነት ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ተከታዮቹንም ቡድኖች በአምስት ነጥብ እና ከዛ በላይም በሆነ ልዩነት በመብለጥ አስፈሪ ቡድንነቱን እያስመለከተን ይገኛል፤ ፋሲል ከነማ በእዚህ የሊጉ ተሳትፎ ሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ጠንካራ ቡድኖች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፤ የዘንድሮ ቡድኑም በጥሩ የአሸናፊነት መንፈስ በመጓዝ ላይም ነውና ይሄንን ጥንካሬያችንን እናስቀጥለዋለን”፡፡

በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተከታያቸውን ኢትዮጵያ ቡናን ስለሚፋለሙበት የዛሬ ጨዋታ

“ፋሲል ከነማ ሁሌም ለሻምፒዮናነት የሚጫወት ቡድን ነው፤ ይሄን ደግሞ አይደለንም እኛ ማንኛውም ሰውም ያውቃል፤ ያ ስለሆነም በእንደዚህ አይነት መልኩ በተለይም ደግሞ በ5 ነጥብ ከምትበልጠው ከተከታይህ ቡድን ጋር የምታደርገው ጨዋታ በወሳኝነቱ አቻ የማታገኝለት ስለሆነ የዛሬውን ጨዋታ በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን ልናሰፋው በሚገባ ተዘጋጅተናል”፡፡

በፋሲል ከነማ እና በኢትዮጵያ ቡና ክለቦች መካከል በእንቅስቃሴ ደረጃ ሜዳ ላይ ይኖራል ተብሎ ስለሚጠብቀው የጨዋታ ፉክክር

“ይሄ የሁለታችን ቡድኖች ጨዋታ እኛ ለሻምፒዮናነት ከመጫወታችን አኳያ ግጥሚያውን አሸንፈን ነጥባችንን ለማስፋት የምንፈልግበት ቡናዎች ደግሞ ነጥቡን አጥበው እኛን ለመቀራረብ የምናደርገው ፍልሚያ ስለሆነ ግጥሚያው የሚከብድ እና ጥሩ ፉክክርንም የምናሳይበት ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ”፡፡

ስለ ነገ ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና

“በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎ ኢትዮጵያ ቡና ጥሩ ቡድን ነው፤ ኳስን ይዞና በደንብ አንሸራሽሮም የሚጫወት ቡድን አላቸው፤ ወደፊትም አጥቅተውም ነው የሚጫወቱት፤ በዚህ ዙሪያ ዘንድሮ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ለየት ብለውብኛል”፡፡

ከቅ/ጊዮርጊስ ስላደረጉት እና በመጨረሻው ደቂቃም ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥረው ስላሸነፉበት ጨዋታ

“ባሳለፍነው እሁድ የነበረው የእኛና የእነሱ ፍልሚያ አንዳችን አንዳችንን አሸንፈን ከሜዳ ለመውጣት ያደረግነው ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ ሲሆን መጨረሻም ላይ የእነሱ ተከላካይ አስቻለው ታመነ በሰራው ጥፋትም እኛ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተን በግጥሚያው አሸናፊ የሆንበት ነው፤ የፍፁም ቅጣት ምቱን በተመለከተ ዳኛው የወሰነው ውሳኔ ተገቢ ነው፤ ይሄን በቪዲዮ ላይ ደጋግሞ ማየትም ይቻላል፤ የዕለቱ ዳኛም በዛ ባለቀ ሰዓት ላይ ይህን መወሰኑም ቆራጥነቱን ያሳየንም ነው፤ ከዛ ውጪም ይህን ውሳኔ አስመልክቶም ከእነሱ ተጨዋቾች ውስጥ ያመኑም አሉና የጨዋታው አሸናፊነታችን ተገቢ ነው”፡፡

ፋሲል ከነማ የዛሬው ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን መርታት ከቻለ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ በእርግጠኝነት ያነሳል ስለመባሉ

“ይሄን በሚመለከት እኛም ከአንድአንዶች አንደበት ብዙ ነገሮችን እየሰማን ይገኛል፤ ያም ሆኖ ግን የሊጉ ጨዋታ ገና 11 ጨዋታዎች የሚቀሩት ስለሆነ ቡድናችን የዛሬው ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፍ መቻሉ ብቻ እኛን ለሻምፒዮናነት ያበቃናል ብለን አናስብም፤ ፋሲልን ሻምፒዮና የሚያደርገው ቡናን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እያሸነፈ የሚጓዝ ከሆነ ብቻ ነው”፡፡

ለፋሲል ከነማ እየሰጠ ስላለው ግልጋሎት

“ፋሲል ከነማ በሚያደርጋቸው እያንዳንዱ ጨዋታዎች ሁሌም ቡድኔን በጥሩ መልኩ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፤ ለዛ ጠንክሬ እየሰራውም ነው የምገኘውና በቀጣይ የቡድኖቻችን ጨዋታዎች ላይ ያለኝን አቅም አውጥቼ በመጫወት ከጓደኞቼ እርዳታ ጋር ቡድኔን በውጤታማነት ማማው ላይ ለማስቀጠል ተዘጋጅቻለው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P