የሸገር ደርቢ ተጠባቂ ፍልሚያ
ኢትዮጵያ ቡና VS ቅ/ጊዮርጊስ
ረቡዕ 10፡00
በመሸሻ ወልዴ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ጨዋታ የፊታችን ረቡዕ በኢትዮጵያ ቡናና በቅ/ጊዮርጊስ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት
ጀምሮ ይካሄዳል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናና ቅ/ጊዮርጊስ በእዚህ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ለብዙ ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ በርካታ ጨዋታዎችን ያሸነፈ ሲሆን ቡና
ደግሞ የተወሰኑትን አሸንፏል፤ በአቻ ውጤት ያጠናቀቋቸውም ግጥሚያዎች አሉ፤ ሁለቱ ቡድኖች ሁሌም በሸገር ደርቢ ጨዋታ ሲገናኙ
ግጥሚያዎቹ በቡድኖቹ ደጋፊዎች፣ በተጨዋቾቹ በኮቺንግ ስታፍ አባላቶችና በሌሎችም የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ በከፍተኛ ጉጉት
የሚጠበቅ ሲሆን በጨዋታው ላይ በተለይ አንዱ ቡድን በአንዱ መሸነፍን ፈፅሞ የማይፈልግበት ሁኔታም ስላለ የእርስበርስ ግንኙነታቸው
ትኩረትን ይስባል፡፡
ከዛም ውጪ የሁለቱም ቡድን ደጋፊዎች በማናቸውም የውድድር አይነት ላይ ሲገናኙም የአዲስ አበባ ስቴድየም ላይ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው
በመታጀብ ለየክለቦቻቸው የሚሰጡት ድጋፍ ለስታድየሙ ውበትም ሆኖ ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሸገር ደርቢው ጨዋታ ላይ ሲገናኙ ዛሬ ቅዳሜ እና ነገ እሁድ ዕለት ያስመዘገቡትን ውጤት ሳይጨምር
ኢትዮጵያ ቡና 12 ነጥብን በመያዝ እና በ8ኛ ስፍራ ላይ በመገኘት ሲሆንቅ/ጊዮርጊስ ደግሞ 14 ነጥብን በመያዝ እና በ5ኛ ደረጃም ላይ
በመገኘት እና ከመሪው ክለብ መቐለ 70 እንደርታም ቡና በ7 ቅ/ጊዮርጊስ ደግሞ በ5 ነጥብ ተበልጠው በሚገኙበት ሁኔታ ነው፤
የሁለቱን የሀገሪቱ ትልቅ ቡድኖች ተጠባቂ የሸገር ደርቢ ጨዋታን አስመልክቶ እና ሌሎችን ጥያቄዎች በማንሳት ከኢትዮጵያ ቡናው
ተጨዋች አህመድ ረሺድ /ሺሪላ/ እና ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጨዋች ሙሉዓለም መስፍን /ዴኮ/ ጋር ቆይታ በማድረግ ተጨዋቾቹ
ለቀረበላቸው ጥያቄ ሁሉ ምላሽን ሰጥተዋል፤ መልካም የሸገር ደርቢ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች፡፡
“እንደሲቲ ካፑ ሁሉ በፕሪምየር ሊጉም ቡናን እናሸንፋለን”
ሙሉዓለም መስፍን(ዴኮ)
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ጅማሬው ውጤታማ መሆን አልቻለም፤ ወደ ክልል ለጨዋታ ሲወጣም ማሸነፍ
ተስኖታል፤ በዚህ ዙሪያ እያጋጠማችሁ የሚገኘው ነገር ምንድን ነው?
ሙሉአለም፡- በሊጉ ጨዋታ ቅ/ጊዮርጊስን ውጤታማ እንዳይሆንም ሆነ ወደ ክልል ተጉዞ እንዳያሸንፍ ያደረገው ዋንኛው ነገር የቡድናችን
የአጥቂ ስፍራ ተጨዋቾች ሳላህዲን ሰይድና ጌታነህ ከበደ ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያጋጥማቸው ጉዳት ሲሆን በተለይ ደግሞ ክልል ላይ
ሄደን ስንጫወት ጨዋታዎችን አሸንፈን እንዳንወጣ የእነሱ በመልካም ጤንነት ላይ ለመገኘት አለመቻል እና ከዛ በተረፈምደግሞ
የምናገኛቸውን የጎል ማስቆጠር እድሎችንም በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ስላልቻልን እነዚሁ ሁኔታዎች በጣሙን እየጎዱን ናቸው፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህርዳር ከተማን ነገ እሁድ ይፋለማል፤ የፊታችን ረቡዕ ደግሞ በሸገር ደርቢውጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር
ይፋለማል፤ እነዚህን ጨዋታዎች እንዴት ነው የምትጠብቋቸው፤ በተለይ የረቡዕን በጉጉት የሚጠበቀውን የሸገር ደርቢውን ጨዋታ?
ሙሉአለም፡- በአሁን ሰዓት ከሸገር ደርቢው ጨዋታ በፊት እኛ እያሰብንም ሆነ እየጠበቅነው የምንገኘው ግጥሚያ መጀመሪያም
የሚቀድመው ባህርዳር ከተማን የምንፋለምበት የነገው ጨዋታ ነውና ለዛ ነው ትኩረት ሰጥተነው ያለነው፤ ባህር ዳር ከተማን ካሸነፍን
ደግሞ ከቡና ጋር የሚኖረን የሸገር ደርቢ ጨዋታ ለእኛ ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆንልናል ብለን ስላሰብንምለረቡዕ ጨዋታ አሰልጣኛችን
ከእሁዱ ግጥሚያ ተነስቶ የሚያዘጋጀን ነገር አለና ሙሉ ትኩረታችንን ወደዛ ጨዋታ ላይ ነው የምንወስደው፤የእኛ ተጋጣሚ ኢትዮጵያ ቡናም
እንደእኛ ሁሉ ከሜዳ ውጭ ማሸነፍ አለመቻሉ ተመሳሳይ ችግር እየገጠመው ስለሆነም ለእዚህ ተጠባቂና ትልቅም ለሆነው የደርቢ
ጨዋታምለግጥሚያው በሚገባ ተዘጋጅተን እንመጣለንማ በጨዋታውም ልክ እንደሲቲ ካፑ ሁሉ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፈን ለመውጣትም
በጣሙን ዝግጁ ነን፡፡
ሊግ፡- በሸገር ደርቢው ጨዋታ መጫወትየተለየ ስሜትን ይሰጣል? ከእናንተስ የሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች ምን ምን ነገርን እንጠብቅ?
ሙሉአለም፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በሸገር ደርቢው ጨዋታ ላይ ብዙ ጊዜ ሲገናኙ በተጠበቀው መልኩ ጥሩ እንቅስቃሴን
ባያሳዩም በእነዚህ ምርጥ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ፊት ታጅበህ ይህንን ታላቅ የሀገሪቷን ግጥሚያ ስታደርግ በአንተ ውስጥ የተለየ እና
በጣም ደስ የሚል ስሜትን ይፈጥራል፤ ሁለቱ ሲጫወቱም ከጨዋታው ይልቅ የደጋፊዎቻቸው የአደጋገፍ ድባብም ነው ጎልቶና
ደምቆም የሚወጣውና የደጋፊዎቹ የድጋፍ ድባብ በሲቲ ካፑም ላይ እንደታየው ለክልል ቡድኖች በትምህርት ሰጪነቱና በመልካም ጎኑም
ሊታይና ምሳሌም ሊሆን ይገባዋልና በስፖርታዊ ጨዋነቱ ላይ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ለኳሱ ትልቅ ነገርን ነው ባለፈው ጊዜ የሰሩትና
እነዚህ ደጋፊዎች አሁንምቢሆን ያን መልካምና የበጎ ተግባር ስራቸውን ዳግምም ሊያስቀጥሉት ይገባል፡፡
በሜዳ ላይ ያለውን ነገር ደግሞ እኛ ተጨዋቾች ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ መልኩ ፉክክሩን ከፍ አድርገን ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት
መልኩ ለመጫወት ጥረትን እናደርጋለን፤ ጨዋታውንም በድል አድራጊነት ለማጠናቀቅ እንዘጋጃለን፡፡ የሁለታችን ጨዋታ ከመቼውም ጊዜ
በተሻለም በሜዳ ላይ ጥሩ ፉክክርንም እናሳይበታለን ብዬም አምናለው፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ ቡናም በቅዱስ ጊዮርጊስ መሸነፍን ፈፅሞ አይፈልጉም፤ ይህን ስሜት ታውቀዋለህ?
ሙሉአለም፡- አዎን በሚገባ፤ ደርቢ የሚባለውም ስሜት የመጣሁ ከዚሁ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ሁለቱም የአንድ ከተማ ትልልቅ
ቡድኖች ናቸውና አንዳቸው በአንዳቸው የመሸናነፍ ፍላጎት ፈፅሞ የላቸውም፤የሁለቱ ቡድን ደጋፊዎቻቸውም በስራ ቦታ ላይ ሲገናኙ፣ ከአንድ
ቤተሰብም ደግሞ ሁለቱንም ቡድኖች የሚደግፉ ሰዎችም ስላሉና የሚነቋቆሩበት እና የሚበሻሸቁበት ቡድኖቻቸውንም በከፍተኛ ሞራል
ላይ ሆነውም ለመደገፍ ገንዘባቸውን ጊዜያቸውን ጉልበታቸውን ሰጥተውም የሚመጡበት ነገር ስላለም ነው መሸነፍን የማይፈልጉት እና
በዚህ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ቡና ላይ የነበረውን የበላይነት እና ታላቅነት ይዞ ማስቀጠል ነው የሚፈልገው፤ ቡናም ደግሞ እዛ
ጋር ለመድረስ እየጣረ እና ታሪኩንም ለመቀየር የሚያደርጉት የትንቅንቅ ጨዋታ ስለሆነ የደርቢው ጨዋታ ስሜት የሚሆነው ከዛ አንፃር
ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- ለሸገር ደርቢው ጨዋታ የተለየ ስሜትን ሰጥተህ ነው ወደ ሜዳ የምትገባው? ልዩ ትውስታህስ ምንድነው?
ሙሉአለም፡- ለጨዋታው ሁሌም ቢሆን የተለየ ግምትን አልሰጥም፤ ስላለኝ ትውስታ ግን አንድ መናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር
በሁለታችን የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ እኔ በግምባሬ ገጭቼ ቡና ላይ የድል ጎልን አስቆጥሬባቸው አውቃለሁና ያን ደስታዬን መቼም ቢሆን
የምረሳው አይደለም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ አመት ውድድርን እንዴት እየተመለከትከው ነው? መቐለ 70 እንደርታ ሊጉን ከመምራቱ አንፃርስ
የምትፈራው ነገር አለ?
ሙሉአለም፡- መቐለ 70 እንደርታ የሊጉን ውድድር ከወዲሁ መምራቱን ማስፈራት በሚለው ደረጃ ላይ ባልወስደውም አካሄዳቸውን ግን
እንደቀላል አናየውም፤ ምክንያቱም እነሱ ጠንካራ ቡድን እና የዓምናም ሻምፒዮና ስለሆኑ ነው፤ በዛ ላይ አሰልጣኙ ልምድ ያለውና
ጨዋታዎችን እንዴት አድርጎ ማሸነፍም እንዳለበት የሚያውቅም ባለሙያ ነውና የሊጉ ጨዋታ በአሁን ሰዓት ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት
ከመሆኑ አንፃር እኛም ለእያንዳንዱ ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተንም በመግባት ነው እየተጫወትን የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪምየር ሊጉ ቀጣይ የውድድር ጉዞው በጣም ይሻሻላል ወይንስ….?
ሙሉአለም፡- ከባድ ጥያቄ ነው፤ ግን ቡድናችን አጥቂዎችን የሚያገኝ ከሆነና ወይንም ደግሞ ጉዳት ላይ ያሉት ልጆች ከጤንነታቸው ሙሉ
ለሙሉ አገግመው የሚመለሱ ከሆነ ይሻሻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እዛ ጋር ለመድረስ ግን የእነሱ ወደጤንነታቸው መመለስ ብቻ ሳይሆን
ብዙ ስራ ይጠበቅብናል፤ ያንን የምናደርግ ከሆነ እንለወጣለን፤ ግን መለወጡ ቀላል አይመስለኝም፤ አሁንም በጣም መሰራት ያለባቸው
ብዙ ነገሮች አሉና፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ……?
ሙሉአለም፡- የሸገር ደርቢውን ጨዋታን አስመልክቶ አንድ ነገርን ማለት እፈልጋለሁ፡፡ የእኛና የቡና ጨዋታ እንደ ሲቲ ካፑ ሁሉ
በደጋፊዎቻችን ዘንድ ኢትዮጵያዊነት የሚንፀባረቅበት እና አንድነታችን እና ወንድማማችነታችንን የምናሳይበት የጨዋታ መድረክ ይሆናል
ብዬ አስባለሁ፡፡
አህመድ ረሺድ (ሺሪላ)
ሊግ፡- የሸገር ደርቢው ጨዋታ ረቡዕ በ9 ሰዓት ይካሄዳል፤ ይህን ፍልሚያ እንዴት እየጠበቃችሁት ነው? ስለደርቢው ጨዋታ ያለህስ
ትውስታ?
አህመድ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም እንደሚያውቀው ትልቁ የደርቢ ጨዋታ የሃገሪቷ ትላልቅ ቡድኖች ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ
የሚያደርጉት የሸገር ደርቢው ጨዋታ ነው፤ ለእዚሁም ጨዋታ ቡድናችን በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፎ መውጣትን ስለማይፈልግ በጥሩ አቋም
ላይ ሆኖ ለመቅረብ በሚገባ ይዘጋጃል፤ ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣትም ጠንክሮ ይሰራል፡፡
በጨዋታው ከዚህ በፊት የነበረኝ እና የማልረሳው ትውስታ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ሆኜ በጊዜም ለጨዋታው ጠዋት 3 ሰአት ሄጄ ሜዳ
ያላገባሁበት አጋጣሚ ቢኖርም አሁን ላይ ግን ራሴ የቡና ተጨዋች ሆኜ ያለውን ድባብ ሳየው በዛ ልዩ ትውስታው አለኝ፡፡
ሊግ፡- የሸገር ደርቢው ጨዋታ አሸናፊ ማን ይሆናል?
አህመድ፡- ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን የሚያደርጉት የሸገር ደርቢው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በደረጃው ሰንጠረዥ አናት ላይ
ወይንም በመሪነት ማማው ላይ በሚገኙበት አይደለም፤ እኛ 8ኛ እና ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ 8ኛ ሆነን ነው ይህን ጨዋታ
የምናደርገውና አንዱ አንዱን የሚያሸንፍበት ውጤት ከተመዘገበ ያ ግጥሚያውን የደረጃ ለውጥ እንዲያመጣ ስለሚያደርገው ጨዋታውን
ተጠባቂ ያደርገዋልና የሁለታችን የደርቢ ጨዋታ በእኛ አሸናፊነት ይጠናቀቃል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስም በኢትዮጵያ ቡና መሸነፍን ፈፅሞ አይፈልጉም፤ ከዚህ አንፃርስ ጨዋታውን
ስትመለከተው?
አህመድ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ አይደለም በእንደዚህ አይነት የሃገሪቱ ትልቅ የደርቢ ጨዋታ ላይ በሌላም ፍልሚያ ላይ ቢሆን ማንም
ቡድን በየትኛውም ቡድን መሸነፍን አይፈልግም፤ ሁለታችን ስንገናኝ ደግሞ በደጋፊውም ሆነ በተጨዋቾች አህምሮ ውስጥ የውጤት
ማጣት ትልቅ ቀውስንም ነው የሚፈጥርብህና ለጨዋታው በደንብ ነው የምትዘጋጀው፤ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት እኛ ጋር ሽንፈትን
የሚጥሉ በርካታ ደጋፊዎች ነው ያሉን፤ ደጋፊዎቻችን ደረጃችን ጥሩ ሆነም አልሆነም ሁሌም እነሱን ማሸነፍ እና ማሸነፍንም ብቻ ነው
የሚፈልጉት፤ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ ትልቅ ደስታንም ነው የሚሰጣቸውና ሌላ ብዙ የሚያስጨንቃቸውም ነገር የለም፤ ስለዚህም
የረቡዕን ጨዋታ ለማሸነፍ ጠንክረን እየሰራን ነው የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- የሸገር ደርቢው ጨዋታ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲያልቅ የምታስተላልፈው መልዕክት ይኖርሃል?
አህመድ፡- አዎን፤ በእዚህ አጋጣሚ በዚህ ዙሪያ እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ ቅርብ
አመታት ጊዜ ድረስ በመጡበት መንገድ የሃገራችን ፉትቦል እርስ በርስ ንቁሪያ የነበረበት ነውና ያ ጊዜ አልፎ የዘንድሮው ውድድር በጥሩ
ሁኔታ መካሄድ መቻሉ መማሪያ ይሆናል፤ ይሄን ጥሩነትም ለማስቀጠል ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ሁለቱ ቡድኖች ናቸውና ይሄ
ይልመድባቸው እላለው፡፡ የሁለቱ ቡድኖች አመራሮች ለደጋፊዎቻቸውና ለተጨዋቾቻቸው አላስፈላጊ ነገር እንዳያደርጉም የስፖርታዊ
ጨዋነቱን አስቀጥለው እንዲሄዱም በሁለታችንም በኩል ትልቅ ነገር ይጠብቀብናል፤ በተለይ ደግም ከእኛ ተጨዋቾች ትልቅ ነገር
ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ደጋፊ ተጨዋች የሚያደርገውን አክት ተከትሎ ነው ሌላ ነገር ውስጥ የሚገባውና በቡናም በቅዱስ ጊዮርጊስም
በኩል ከአሁኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ሊግ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ የደርቢው ጨዋታ በፊት እሁድ ከወልዋሎ አዲግራት ጋር ትጫወታላችሁ፤ ስለ ደርቢው ብቻ አወራንና ይሄስ
ግጥሚያ ተረሳ እንዴ?
አህመድ፡- ኸረ በፍፀም አልተረሳም፤ ከወልዋሎ አዲግራት ጋር የምናደርገው ጨዋታ በጣም ትልቅ እና ተጠባቂም ነው፤ ለዛም ጨዋታ
ከፍተኛ ዝግጅትን ነው እያደረግን የምንገኘው፡፡ ይሄን ጨዋታም ተሸንፈን መጥተን ቅዱስ ጊዮርጊስን በሸገር ደርቢ መግጠም ትንሽ ከባድ
ሊልብን ስለሚችል የወልዋሎ ጨዋታን በአሸናፊነት ለመወጣትና በጥሩ ስነ-ልቦናም ለሸገር ደርቢው ጨዋታ ላይ ለመቅረብ እየተዘጋጀን
ነው የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አጠቃላይ ውድድሩን ከእናንተም ውጤታማ አለመሆን ጋር አዛምደህ እንዴትና በምን መልኩ ነው
እየተመለከትከው የምትገኘው?
አህመድ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን አዲስ አበባ ላይ አንድ እና ሁለት ጨዋታን ብቻ የመመልከት እድሉ ቢያጋጥመኝም አብዛኛው
ጨዋታን በራሴ እይታ ስመለከተው ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት ያለ ይመስለኛል፡፡ ቡናን አስመልክቶ ግን ውጤት የለውም የሚለውን ነገር
ለመግለፅ ቡድናችን የያዛቸው አብዛኛው የተጨዋቾች ስብስብ በአዲስ መልክ የተገነባ ነው፤ ከ90 ፐርሰንት በላይ ማለት ይቻላል አዲስ
ቡድንም ነው ሰርተን የመጣነው፡፡ አዲስ የጨዋታ ፍልስፍናንም ነው እየተከተልን የምንገኘው፤ ቡድናችን የሚከተለው ጨዋታም እንደ
ቡድን ብቻ ሳይሆን እንደሃገርም አዲስ ፍልስፍና እየተከተልን ስለሆነ ብዙዎች ቡድኖች ለመከለካል ሰርተውብን ነው የሚመጡት፤ ከቡና ጋር
የሚጫወቱትን ጨዋታም ከሌላ ጋር አይጫወቱትምና ያ ያ ውጤታችን ላይ ተፅህኖ ፈጥሮብናል፡፡ ቢሆንም ግን እስካሁን
የተሸነፍንባቸውም ሆነ አቻ የወጣንባቸውን ጨዋታዎች ስታይ ግን በሚገርም የጨዋታ ብልጫ ነውና ከሜዳ የወጣንባቸውና ይሄ ጨዋታ
ለነገ ለክለባችን ብቻ ሳይሆን ለብሄራዊ ቡድናችንም ትልቅ ግብአት ይሆናል፤ ቡና አሁን የያዘው አጨዋወት በጣም ያዋጣል፤ ይሄ ቡድን
በቀጣይ ጊዜያት አንድአንድ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች ጣል ሲያደርግ እና ለፍልስፍናውም የሚሆኑ ጥቂት ልጆችንንም ሲጨምር
ሻምፒዮና የማንሆንበት ምንም ምክንያት የለም፤ ዘንድሮም ስህተቶቻችንን ከቀነስንም ለሻምፒዮናነት የማንሄድበት ነገርም የለም፡፡
ሊግ፡- የመቐለ 70 እንደርታ ሊጉን መምራት ለእናንተ ስጋትን ፈጥሮባችኋል?
አህመድ፡- መቐለ 70 እንደርታ እንደ ቡድን ትልቅ ነው፤ ጠንካራም ቡድን አላቸው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ደካማ ጎንም አላቸው፤ ስለእነሱ
የምናገረው በሜዳቸው ላይ ተጫውተን ስላየዋቸው ነው፤ ያን ግጥሚያ አሸንፈን መምጣትም እየተገባን ነው ነጥብ ጥለን የነበረው፤
ሊጉን እነሱ ቢመሩም ያንን ያህል የሚያስፈሩን አይደሉም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር የተመለከትከው ለየት ያለ ነገር አለ?
አህመድ፡- አዎን፤ ዘንድሮ እንዳየሁት ለሃገራችን አዲስ የሆነን የጨዋታ ፍልስፍና ይዞ ነው የመጣው፤ ያልተለመደም አይነት አጨዋወት
ነው፡፡ ከዚህ በፊት ኳስ ትጀምራለህ፤ ትጠልዛለህ፤ አሁን ግን እየሰራንበት ያለው ነገር ከበረኛ ጀምሮ እስከ አጥቂ ድረስ ኳስ ተነካክቶ
በመሄድ ነው ጎል እንዲቆጠር የሚፈልገው፡፡ ከዚህ በፊት እኛ ወደ አፍሪካ ሀገር ሄደን እነሱን ስንገጥም በጉልበት ይበልጡናል፤ እኛ ደግሞ
እስከዛሬ ባለን ነገር እየተጠቀምንበት አልነበረም፤ በፊት በነበረው አጨዋወት የተወሰነ ውጤት ልናመጣ እንችል ነበር፤ ያ ግን ዘላቂ
አልነበረምና ነገ የተለየ እና ምንም ነገር ሳታይ ትሸነፍበታለህ፡፡ ስለዚህም አሁን በቅርቡ እንኳን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ያመጣነው ውጤት
የእዚያ አይነት ተፅዕኖ ያለበት ነውና የቡናው አሰልጣኝ አሁን ላይ የሚከተለውን አይነት አጨዋወት ሁሉም አሰልጣኝ ጠንክሮና በርትቶም
ሰርቶ ተከታይ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ከተፈጠረ በኳሱ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይቻላልና በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ ካሳዬ ይዞት
ለመጣው ነገር ሊበረታታ ይገባል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
አህመድ፡- የሸገር ደርቢ ጨዋታን አስመልክቶ ለጓደኞቼ የማስተላለፍው መልህክት ቢኖር ስፖርታዊ ጨዋነትን ከምንም እና ከምንም ነገር
በላይ አስቀድመን ደርቢ እንደመሆኑ መጠን ሁላችንም ለክለቦቻችን ታማኝ ሆነን ነው የምናገለግለው፡፡ ቢሆንም ጨዋታው ላይ
ላለመበጥበጥ ጠንክረን ልንስራ ይገባል፤ ድል ለኢትዮጵያ ቡና፡፡