Google search engine

ያሬድ ሀሰን /አዲስ አበባ ከተማ/ “ብዙዎች ወደነበርንበት  ሊግ እንደምንመለስ ቢያስቡንም እኛ ግን ሁኔታውን ቀይረን ጠንካራ ተፎካካሪ እየሆንን ነው”

 

አዲስ አበባ ከተማ ከሐዋሳ ከተማ ያደረገውን የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ  1-1 በሆነ ውጤት አጠናቋል፡፡  በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ መቀዝቀዝ በታየበት በእዚህ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለአዲስ አበባ ከተማ ጋናዊው ተጨዋች  ሪችሞንድ ኦዶንግ ከእንዳለ ከበደ  ከግራ መስመር የተላለፈለትን  ረጅም ኳስ በግንባሩ  ቦታ አይቶ  ግቧን ሲያስቆጥር ለሐዋሳ ከተማ ደግሞ በጥሩ የኳስ አካሄድ  ብሩክ በየነ ለመስፍን ታፈሰ  ከሰጠው በኋላ መስፍን ለኤፍሬም አሻሞ  አቀብሎት ኤፍሬም ግቧን ሊያስቆጥር ችሏል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የዚህን የጨዋታ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎም  በ7ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ያደረገው ሲሆን  ቡድኑ ስላደረገው ጨዋታ፣ በእዚህ ዓመት ስላላቸው አቋም፣ ከራሱ ወቅታዊ ብቃት ጋር በተያያዘ እና ስለ ዘንድሮ የውድድር ዘመን እቅዳቸው በአሁን ሰዓት ለክለቡ ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት ላይ የሚገኘውን ያሬድ ሀሰንን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አናግሮት ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶታል፤ ተከታተሉት፡፡

ሊግ፦ ሐዋሳ ከተማን ገጥማችሁ የ1-1 ውጤት አስመዝግባችኃል፤ ግጥሚያውን እንዴት አገኘኸው?

ያሬድ፦ ይህን ጨዋታ ያደረግነው ከተሸናፊነት መጥተንና ዳግም ደግሞ ውጤቱን ላለማጣትም ስለነበር ጥንቃቄ በተሞላበትና በስነ-ልቦናው ደረጃም  በተቸገርንበት ሁኔታ  ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን እኛ ጨዋታውን ማሸነፍ የምንችልበትን ኳስ ለማግኘት ብንችልም በጥቃቅን ስህተት ግጥሚያውን በአቻ ውጤት ልናጠናቅቅ ችለናል፤ ውጤቱንም በፀጋ ልንቀበል ችለናል፡፡

ሊግ፦ ስለተጋጣሚያችሁ ሐዋሳ ከተማ አቋም ምን ትላለህ?

ያሬድ፦ ባለፈው ግጥሚያ አሸንፈው ከመምጣታቸው አንፃር ጥሩ ስነ-ልቦና ኖሯቸው ብንመለከትም ጨዋታው ላይ ያንን ያህል የከበዱን አልነበሩም፤  በተወሰነ መልኩ እንደሁም እኛ ከእነሱ የተሻልን ነበርን፡፡

ሊግ፦ በተጋጣሚያችሁ ላይ ያስቆጠራችሁትን ግብ በሚመለከት ምን አልክ?

ያሬድ፦ እኛ ያስቆጠርነውን የመሪነት ግብ ማስጠበቅ አልቻልንም እንጂ በመስመር ላይና በአጥቂ  ስፍራ ላይ የሚገኙት ተጨዋቾችን የሚያገናኝ የልምምድ ሜዳ ከመስመር ላይ የሚመጡ ኳሶችን በምን መልኩ መጠቀም እንዳለብን የሚያሳይ ስራ ነው፤ ያንንም ተጠቀምንበት፡፡

ሊግ፦  የአቻነቷን ግብ ያስተናገዳችሁበት ሁኔታስ?

ያሬድ፦ የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታችንን ባገባነው  ግብ  አስጠብቀን ለመውጣት በማሰብ ወደ ኃላ ማፈግፈግ ይታይብን ነበር፤ በእዛም ሁኔታ መዘናጋት ስለታየብንም በፈጠርነው ስህተት ግብ ሊቆጠርብን ችሏል፡፡

ሊግ፦ የእስካሁኑ የቡድናችሁ ጉዞ በአንተ እይታ እንዴት ይገለፃል?

ያሬድ፦ የእኛ ቡድን እንደ አዲስ የተዋቀረና ብዙ አዳዲስ ተጨዋቾችንም የያዘ ከመሆኑ አኳያ አሁን ላይ የመጣንበት መንገድ ጥሩ ነው፤ መሻሻሎች ይታዩብናል፤ በእዛ ላይ ከታችኛው ሊግ ስለመጣንና  አጠር ያለ የዝግጅት ጊዜን ስለሰራንም  የተሰጠን  ግምት ነበር ያንን የሰዎች ሀሳብ ማስቀየርም ችለናል፤ ከእዚህ በኋላም ወደ ላይ ከፍ  የምንልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

ሊግ፦  በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለእናንተ የተሰጣችሁ ግምት ምን ነበር? እናንተስ ምን ውጤትን ለማምጣት ነው እቅድን የያዛችሁት?

ያሬድ፦ የእዚህ ዓመት የውድድር ተሳትፎአችንን በተመለከተ ለእኛ በሶሻል ሚዲያው ላይም  ሆነ በሰዎች ዘንድ የተሰጠን ግምት አዲስ አበባ ከታች  እንደመጣ ተመልሶ ይወርዳል፤ ነጥቦች ማግኘት ይናፍቀዋል፤ ብዙ ጎሎችም ይቆጠርበታል የሚል ነው፤ አሁን እየታየ ያለው ግን በተቃራኒው ስለሆነና በወገብ ደረጃም ላይ ስላለን የእዚህ ዓመት ውድድራችንን በጥሩ ተፎካካሪነት በመጫወት ሊጉ ላይ  ለመቆየት ነው እቅድን የያዝነው፡፡

ሊግ፦ ቤትኪንጉን ስትጀምሩ በሽንፈት ነበር፤  አሁን አሁን ላይ  ደግሞ ወደ ውጤታማነት እየመጣችሁ ነው፤ የእዚህ የለውጥ ሚስጥር ምንድን ነው?

ያሬድ፦  የዘንድሮ  ውድድራችንን ስንጀምር ከሌሎች ክለቦች አንፃር  የእኛ የዝግጅት ጊዜና  ቀን በጣም አናሳ  ስለነበር   በሲቲ ካፑም ላይ ሆነ  ቀደም ሲል በተደረጉት ሁለቱ  የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታዎቻችን ላይ  ውጤት ማምጣቱ ላይ ተቸግረን ነበር፤ በኋላ ላይ ቡድኑ በጥሩ ሁኔታ እየተሰራ ሲመጣና ወደ መናበቡና መቀናጀቱ ላይ ስንመጣ ግን መከላከያን በሰፊ  ግብ ማሸነፍ ጀምረን የአምናውን ሻምፒዮናም ለማሸነፍ ችለናልና ይሄ መሆን መቻሉ የቡድናችንን መቀየርና ጥንካሬያችንን ያሳየን ሆኗል፡፡

ሊግ፦ የአዲስ አበባን የተጨዋቾች ስብስብ በተመለከተ ምን አልክ?

ያሬድ፦ ብዙዎች ስብስቡን በጥሩ መልኩ አላዩትም ነበር፡፡ በመናቅ አይነት ስሜትም ነበር የተመለከቱን በሜዳ ላይ ግን ተቃራኒ ነገር ነው  እያየን የሚገኘው፡፡ አዲስ አበባ የያዛቸው ተጨዋቾች በጣም አቅም ያላቸውና ብዙ ነገሮችንም መስራት የሚችሉ ናቸው፡፡

ሊግ፦  አሁን ላይ የእናንተ ጥንካሬና ክፍተት ጎን ምንድን ነው?

ያሬድ፦ እንደ ግል ሳይሆን እንደ ቡድን መጫወት መቻላችንና  ከተጠባባቂ ወንበር የሚነሳው ተጨዋችም አንዱ የአንዱን ስፍራ ተክቶ መጫወት መቻሉ ጥንካሬያችን ሲሆን  በክፍተት ደረጃ ማረም ያለብን ደግሞ ብዙ ነገር አለ፤ ከእነዛ መካከልም  ጎል ላይ ኳሶችን እናባክናለን፤  በጥቃቅን ስህተት በመዘናጋትም ጎል ይቆጠርብናልና እዛ ላይ እየሰራን ነው፡፡

ሊግ፦ የራስህን ወቅታዊ አቋም በተመለከተስ ምን አልክ?

ያሬድ፦  አሁን ላይ  ሙሉ ለሙሉ ፐርፌክት በሚባል ደረጃ ላይ  እገኛለው ባልልም ከፈጣሪ እርዳታ ጋር  ግን  ከፍተኛ ለውጦችን  እየተመለከትኩኝ ነው፡፡ ለእዚህ ለውጥም ባለፈው ጊዜ የነበረኝንና ያሳለፍኩትን የኳስ ወቅት ወደ ኃላ ቆም ብዬ መመልከቴና በአሁኑ  ቡድኔ ውስጥ የተሰጠኝ የመጫወት ነፃነት እንደዚሁም ደግሞ ከአጠገቤ የሚገኙት ተጨዋቾችም ለእኔ ጥሩ ሆነው  አቋሜን እንዳሳድግም በጠንካራና ደካማ ጎኔ ላይ ተነስተው  የሚነግሩኝ  የጠቀመኝ ሁኔታ አለና ከዚህ በኋላም የተሻሉ ነገሮችን በመስራት  ቡድኔን ለውጤት ማብቃትም እፈልጋለውኝ፡፡

ሊግ፦ በዘንድሮው የሊጉ ጨዋታችሁ ያስደሰተክና ያስከፋ ግጥሚያ የቱ ነው?

ያሬድ፦ በጣም ያስደሰተኝ ጨዋታ  ለእኛ ከተሰጠን አነስተኛ ግምት አንፃር ብዙዎቹ ባልጠበቁን መልኩ የአምናውን ሻምፒዮና  እንደዚሁም ከእኛ ጋር እስኪጫወቱ ድረስ ጥሩ ጉዞ ያደረጉትን  ፋሲል ከነማዎችን ብዙ ያገቡባችዋል ተብሎ ተጠብቆ ያሸነፍንበት ሲሆን ያስቆጨኝ ግጥሚያ ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር የነበረንን ፍልሚያ ከመራን በኋላ በመጨረሻው ደቂቃ ግብ ተቆጥሮብን አቻ የተለያየንበትን ነው፡፡

ሊግ፦ በመጨረሻ?

ያሬድ፦ በቅድሚያ አገራችንን ሰላም ያድርግልን እያልኩ በኳሱ ላይ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ስለምፈልግና ቡድኔንም ለውጤት ማብቃትም ዋንኛው ግቤ ስለሆነ ለእዛ በበቂ ሁኔታ እየተዘጋጀው ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P