በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘጠኝ ግቦችን ለክለቡ ሐዋሳ ከተማ አስቆጥሮ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር ውስጥ ይገኛል። ገና ወጣት ነው። ወደፊት ብዙ ስራዎች ይጠበቅበታል። የእሱ የኳስ እልም እንደ ቀድሞዎቹ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች አዳነ ግርማና ሌሎች መሰል ተጨዋቾች ስመ ጥር መሆንና ለሀገሩ ብሄራዊ ቡድን በመመረጥ መጫወትና እስከ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ መድረስ እንደሆነም አጥቂው ብሩክ በየነ ከሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር በነበረው ቆይታ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሊግ ስፖርት እና ብሩክ በየነ ያደረጉት ቆይታም ይህንን ይመስላል። መልካም ንባብ።
ስለ ቤትኪንግ ፕሪምየር የእስካሁን ጉዞአቸው
“በእስካሁኑ የውድድር ቆይታችን አሁን ባህርዳር ላይ እያደረግነው ካለው ጨዋታ በስተቀር በሌሎቹ ከተሞች ላይ የነበረን የጨዋታ ተሳትፎ በጣም ጥሩ ነበር። አበረታቾ ውጤትም ልናስመዘገብበት ችለናል”።
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከተቋረጠበት ሲቀጥል በምን መልኩ እንደሚቀርቡ
“ያን ጊዜ እረፍት አድርገን ስለምንመጣ ጉድለታችንን አስተካክለን የምንመጣበት ነው። በእዛ የውድድር ቆይታችንም ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ ቀድሞ አቋማችን እንመለሳለን”።
ሐዋሳ ከተማን ከሌሎቹ ቡድኖች ምን እንደሚለየው
“በታዳጊ እና በወጣት ተጨዋቾች የሚያምን ቡድን አለን፤ ይሄም ነው እኛን የሚለየን”።
ዘጠኝ ጎሎችን በማስቆጠር የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር ውስጥ ስለመግባቱ
“አጥቂ እስከሆንኩ ድረስ እዚህ ፉክክር ውስጥ እንደምገባ አስቀድሜ አውቅ ነበር። ቡድኔንም እየጠቀምኩት ነው። ሊጉ ደግሞ ገናም አላለቀም ተጨማሪ ጎሎችን በማስቆጠርም ተፎካካሪነቴን እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ አስቀጥለዋለሁ”።
በቤትኪንጉ ለአንተ ምርጥ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ተጨዋች ማን ነው?
“የቅ/ጊዮርጊሱ አቤል ያለው ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም ጥሩ የውድድር ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል”።
ቅ/ጊዮርጊስ ወይንስ ፋሲል ከነማ የሊጉን ዋንጫ ማን በበላይነት ያጠናቅቃል?
“በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት አምስት ነው። ቅ/ጊዮርጊስ ሊጉን ቢመራም ባህርዳር ላይ እየተቸገረ ያለበት ሁኔታ ስላለ እና ፋሲል ከነማ ደግሞ በነጥብ እየተጠጋው ስለሆነ አሁን ላይ ስለ ሻምፒዮናው ቡድን ማወቅ አይቻልም”።
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በምን ደረጃ ላይ ሆነው እንደሚያጠናቅቁ
“በደረጃው ሰንጠረዥ ሁለተኛ ወይንም እስከ ሶስተኛ ሆነን እናጠናቅቃለን”።
አሁን ያለህን የኳስ ብቃት የት ደረጃ ላይ ማስቀመጥ እንደሚፈልግ
“ከፍ ባለ ደረጃ ነዋ! ወደፊት ወደ ውጪ ሀገር ወጥቼ መጫወት እፈልጋለሁ። ከዛ ሌላ ደግሞ እንደ ቀድሞዎቹ እንደ እነ አዳነ ግርማ የሀገሪቱ ስመ ጥር ከሆኑት ተጨዋቾች አንዱ መሆንና የወቅቱም ምርጥ አጥቂ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ መሆንም እፈልጋለሁ”።
በውድድር ዘመኑ የነበረባችሁ ክፍተት
“አንደኛው ድክመት በጉዳት ተጨዋቾችን ማጣታችንና ይደርስብን የነበረው ቅጣት ነው። ያ ተጨዋቾችን በሜዳ ላይ አሳጥቶናል። በቀጣይነት እነዚህን ችግሮቻችንን ቀርፈን እንመጣለን”።
ካስቆጠርካቸው ግቦች ለአንተ ምርጧ
“ጅማ አባጅፋርን ስናሸንፍ ያስቆጠርኳት ለእኔ ምርጧ ግብ ነች”።
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በአንተ እይታ
“የዘንድሮ ከባድ ነው። ብዙ ቡድኖች በተቀራራቢ ነጥብ ላይም ይገኛሉ። ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክርም እየታየበት ነው”።
የእግር ኳስን ለምን ያህል ዓመት መጫወትን እንደሚያልም
“ጉልበቴ እስኪዝል ድረስ እግር ኳስን ለረጅም ዓመታት መጫወት እፈልጋለሁ”።
ማሻሻል አለብኝ የምትለው
“ብዙ ጎሎች እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። በተለይም ደግሞ በአንድ ጨዋታ ላይ ተደጋጋሚ ግቦችን ማስቆጠር ዋንኛው እልሜ ነው”።
ስለ ደጋፊዎቻቸው
“የሐዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በጣም ጨዋ ናቸው። በጥሩ ሁኔታ ይደግፉናል። ያበረታቱናልም። ለእዛም ሊመሰገኑ ይገባል”።
እናጠቃል
“የምታመሰግንልኝ ሰው አለ በኳስ ህይወቴ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ብዙ ነገሮችን አድርጎልኛል፤ ለእሱ የተለየ ቦታም አለኝ።