Google search engine

“ፈታኝ ግጥሚያዎች ቢጠብቁንም ኢትዮጵያ ቡናን ለኮንፌዴሬሽን ካፑ ልናሳልፈው ይገባል”ፍቅረየሱስ ተወልደ ብርሃን /ኢትዮጵያ ቡና/

ኢትዮጵያ ቡና ከጅማ አባጅፋር ያደረገውን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ ሳምንት ጨዋታውን 0-0 በሆነ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን በዚሁ ውጤት መሰረትም ግጥሚያውን በአቻ ውጤት ማጠናቀቁን ተከትሎም ነጥቡን 34 በማድረስ ሁለተኝነቱን እንዳስጠበቀ ይገኛል።
በጭቃማው እና ለኳስ ቅብብልም አስቸጋሪ በነበረው በድሬዳዋ ስታድየም ሜዳ ላይ ቡናዎች ከተጋጣሚያቸው በሚሻል መልኩ ጥሩ እንቅስቃሴን ያደረጉ ቢሆንም እነሱም ሆኑ ተጋጣሚያቸው ኳስን ከመረብ ላይ ማሳረፍን አልቻሉም። ከዚህ ጨዋታ በፊት የኢትዮጵያ ቡናው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ፍቅረየሱስ ተወልደ ብርሃን /ችምስ/ በቡድኑ አጠቃላይ የቤትኪንግ ተሳትፎና በራሱ አቋም ዙሪያ እንደዚሁም ደግሞ ከዚህ ጨዋታ በኋላ ቡድናቸው ምን ውጤት ሊያጋጥመው እንደሚችል አስተያየቱን ሊሰጠን ችሏል፤ ተከታተሉት።

 

ሊግ፡- የፋሲካ በዓል በመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እሁድ ይከበራል፤ እንኳን አደረሰህ?
ፍቅረየሱስ፡- አመሰግናለሁ፤ እኔም ለእናንተ እና ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ እንዲሆንላችሁም እመኛለሁ፡፡
ሊግ፡- የብርሃነ ትንሳሄ /የፋሲካ በዓልን/ ከዚህ ቀደም እንዴት ነበር የምታሳልፈው? ዘንድሮስ?
ፍቅረየሱስ፡- ይህን በዓል ብቻ ሳይሆን ገናን ጨምሮ ልጅ ከነበርኩበት ዕድሜ አንስቶ እነዚህን በዓላቶች ሳከብር እና ሳሳልፍ የነበርኩት ከቤተሰቦቼ ጋር ነበር፤ ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ ካመራው በኋላ ግን ብዙውን ጊዜ በስራ ማለትም ወደ ክልል ጭምር በመውጣት የሊግ ጨዋታዎቻችንን የምናደርግበት እና በሙያዬም የተሰጠኝንም ሀላፊነት የምወጣባቸው ሁኔታዎች ስላሉ እኔም ሁንኩኝ ሌሎች ተጨዋቾች በዓሉን ከቤተሰብ ጋር አሳልፈን አናውቅም፡፡ የዘንድሮ በዓልን በተመለከተም ለረቡዕ የሐዋሳ ከተማ ላይ ቀጣይ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎቻችን የበዓሉ ቀን ጉዞን ስለምናደርግ እኛ ተጨዋቾች በዓሉን በጋራ ሆነን ነው በደስታ እና ፍቅር በተሞላበት ሁኔታም የምናሳልፈው፡፡
ሊግ፡- ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እናምራና፤ ፋሲል ከነማ የሻምፒዮናነቱን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ሊያነሳ አንድ ነጥብን አልያም ደግሞ ያን ነጥብ እስከመጨረሻው ጨዋታ ድረስ ካላሳካ በአንድ ጨዋታ ላይ የተከታዩን ቡድን ነጥብ መጣል ብቻ ይጠብቃል፤ ከዚህ አኳያ ስለ እነሱ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎ ምን ማለት ይቻላል? /ቃለ-ምልልሱን ያደረግነው ረቡዕ ጠዋት ነው/፡፡
ፍቅረየሱስ፡- ፋሲል ከነማ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎው እንዳለው ጥንካሬና ምርጥ ቡድንነቱ የእዚህን ዓመት ዋንጫ ከወዲሁ አንስቶታል ማለት ይቻላል፤ አሁን ይሄ ቡድን ከተከታዮቹ ጋር ያለው የነጥብ ርቀት በጣም ሰፊ ነው፤ በእኛ ቡድን በመጀመሪያው ዙር ከመሸነፍ ውጪ በሌሎቹ ግጥሚያዎች ላይ ለማንም ያልተንበረከከ ቡድን ስለሆነ ከሰራቸው የጠንካራ ስራዎች አንፃር የሊጉ ዋንጫ ለቡድኑ የሚገባው ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናስ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዘንድሮ በምን መልኩ አሳለፈ?
ፍቅረየሱስ፡- የእዚህ ዓመት የእስካሁን ተሳትፎአችን ከሞላ ጎደል በጣም ጥሩ የነበረ ቢሆንም በአንድአንድ ጨዋታዎቻችን ላይ የጣልናቸው ነጥቦች እኛን ወደ ሻምፒዮናነቱ ጉዞ እንዳናመራ ዋጋ ሊያስከፍሉን ችለዋል፤ ከዚህ መነሻነትም የእኛ አካሄድ እንደ ፋሲሎች ዘላቂ ስላልነበርም ዋንጫው ሊርቀን ችሏል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ዋንጫው ጉዞ እንዳያመራ ዋጋ አስከፍሎታል ብለህ የምትጠቅሳቸው ግጥሚያዎች የትኞቹ ናቸው? ዘንድሮ ግን ዋንጫ የማንሳት እድሉ ይኖራችሁ ነበር?
ፍቅረየሱስ፡- አዎ! እድሉማ ነበረን፤ ሻምፒዮናነቱም በእኛ እጅ ይወድቅም ነበር፤ ያን ባለማድረጋችን ያስቆጨናል፤ ፈጣሪ ካልፈቀደ በስተቀር ብትቆጭም ባትቆጭም ምንም ነገርን የምታመጣው ነገር የለምና አሁን ላይ ለሌላ ለክለቡ ጥቅም ለሚያስገኘው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ለማለፍ ወሳኝ ለሚባሉት የቀጣይ ጊዜ ጨዋታዎቻችን ከፍተኛ ትኩረትን በመስጠት እየተዘጋጀንበት ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናን በዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎው ነጥቦችን በመጣል ወደ መሪው ፋሲል ከነማ በነጥብ እንዳይቃረብና የሻምፒዮናነቱን ፉክክርም እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ እንዳይፋለም አድርጎት ዋጋ ያስከፈሉት ግጥሚያዎች ከሐዋሳ ከተማ፣ ከወላይታ ድቻ፣ ከሀድያ ሆሳዕናና በቅርቡ ደግሞ በሸገር ደርቢ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ነጥብ መጣል ሳይገባውና ከመጫወቻ ሜዳ አኳያም በእንቅስቃሴው የሚፈልገውን ውጤት ይዞ እንዳይወጣ ያደረጉት ምክንያቶች ስለነበሩ ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና መጣል የሌለበትን ነጥብ ጥሏል እያልከን ነው?
ፍቅረየሱስ፡- አዎን፤ ያላሰብናቸውን እና መጣል የሌለብንን ነጥብ ጥለን ነው ከመሪው ቡድን ፋሲል ከነማ ጋር በብዙ ነጥብ ልንርቅ የቻልነው፡፡
ሊግ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስላደረጋችሁት እና ሽንፈትን ስላስተናገዳችሁበት የቅርቡ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ምን አልክ?
ፍቅረየሱስ፡- የሜዳው መጨቅየትና ለጨዋታውም ምቹ አለመሆን የእኛን ቡድን ከሚከተለው የጨዋታ ፍልስፍና አንፃር በጣም ጎድቶታል፤ ሜዳው ደረቅ ቢሆን ኖሮ እኛ ነበርን የውጤት ተጠቃሚ የምንሆነው፤ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ የእኛ ቡድን ጥሩ ይጫወት ነበር፤ ውጤቱ ጨዋታውን አይገልፀውምና የሜዳው ሁኔታ ለእነሱ ጠቅሞአቸው አሸናፊ ሊሆኑ ችለዋል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ከእነዚህ ከጣላቸው ነጥቦች አኳያ ታዲያ ከስህተቱ ይማራል?
ፍቅረየሱስ፡- በጣም እንጂ የአሁኑ ቡና ከስህተቱ በጣም የሚማር ቡድን ነው፤ ካለፈው ዓመት አኳያ ዘንድሮ በብዙ ነገሮች ተሻሽለናል፤ የእዚህ ዓመት ስህተቶቻችንና ክፍተቶቻችንም የሚታረሙ ናቸውና ለቀጣዩ ዓመት ቡድኑ በብዙ ነገሮች ተስተካክሎ ይመጣል፡፡
ሊግ፡- እንደ አንተ ምልከታ ኢትዮጵያ ቡናን ዘንድሮ ምርጥ ነው ማለት ይቻላል?
ፍቅረየሱስ፡- ከሚገባው በላይ ጥሩ ጎኑ ስለሚበዛ አዎን ምርጥ ቡድን ነው የነበረን፤ የተወሰኑ ክፍተቶች ነበሩ እነሱ የሚስተካካሉ ናቸው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎው ከሌሎች ክለቦች አንፃር ምን ለየት ያደርገዋል?
ፍቅረየሱስ፡- የመጀመሪያው የእግር ኳስን በዚህ መንገድ እጫወታለው ማለቱ፤ ሲቀጥል ደግሞ አንድ ቡድን በምን መልኩ መጫወት እንዳለበት የራሱ የሆነ “የታክቲክ ሀሳብ” አለው እና ያ ነው እሱን ከሌሎች ቡድኖች አኳያ ለየት የሚያደርገው፤ ሌሎች ቡድኖች የራሳቸው የሆነ አጨዋወትና ቅርፅ ብዙ ጊዜ ስለሌላቸው ምን ሊጫወቱ እንደሚፈልጉ ላታውቅ ትችላለህ፤ ቡና ይዞት የመጣው ግን የራሴ የሚለው አጨዋወት አለውና ሌሎቹ ቡድኖች ከእኛ ጋር ሲጫወቱ ይዘን ለመጣነው የጨዋታ ሀሳብ ሲዘጋጁም ነው የሚከርሙትና ይሄ ነው የቡናና የሌሎች ቡድኖች ዋናው ልዩነት፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና የዘንድሮ የውድድር ዘመን ቆይታህ በቋሚነት ሳትሰለፍ በምትቀርባቸው ጊዜያቶች ያሉህ ስሜቶች ምንድን ነው የሚመስሉት? አኩራፊ ተጨዋችስ ነህ?

ፍቅረየሱስ፡- እኔ ደስተኛ እንጂ አኩራፊ የምባል ተጨዋች አይደለሁም፤ ደስተኛ ስለሆንኩም ነው ተቀይሬ በምገባባቸው ጨዋታዎች ላይ ለቡድኔ ጥሩ በመንቀሳቀስ ክለቤን ስጠቅም የምታየውም፤ ከዛ ውጪ በኢትዮጵያ ቡና የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ዘንድሮም ሆነ ከዚህ በፊት በቋሚነት በማልሰለፍባቸው ጨዋታዎች ላይ ብዙ ጊዜ ከመታገስና ከማየት ውጪ ብዙም የማዝን አይነት ሰዋች አይደለሁም፤ ለቡድኑ ተሰለፍኩም አልተሰለፍኩም ሁሌም ነገን ሌላ ቀን ነው ብዬ በማሰብ ክለቡን በሚገባ ለመጥቀም የምተጋና የምለፋም ተጨዋችም ነኝ፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና በቋሚ ተሰላፊነት ያለመጫወትህ ምክንያት ምንድን ነው?
ፍቅረየሱስ፡- አስቀድሞ የመጫወት ዕድሉን ያገኘሁበት አጋጣሚው ነበረኝ፤ ከጉዳት ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ግን ያን የመሰለፍ እድል አጣው፤ ስለዚህም ይሄ የአሰልጣኝ ውሳኔ ስለሆነም የግድ የምቀበለው ነው፤ በዚህ በኩል አልተሰለፍኩም ብዬም ብዙ የሚያሳስበኝ ነገርም አይኖርም፡፡
ሊግ፡- ከፋሲል ከነማ ስር ያለው የእናንተውን ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ ሌሎች ጥቂት ቡድኖች ከዚህ በኋላ ሁለተኛ ወጥቶ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ለማለፍ የምትጫወቱበት ፉክክር ነው የሚኖረው፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
ፍቅረየሱስ፡- የዘንድሮ የሁለተኝነት ደረጃ ጥሩ ዕድልን ነው ሻምፒዮና ለማይሆኑ ክለቦች ይዞ የመጣላቸውና ይሄን ለመጠቀም ሁሉም እድሉ ያለው ቡድን በሚገባ እየተዘጋጀበት ነው የሚገኘው፤ አሁን የዋንጫው ነገር ያከተመ ይመስላል፤ ስለዚህም ትኩረቶች ሁሉ ወደዛ አምርተዋል፤ ሻምፒዮናው ፋሲል ያለምንም ተፎካካሪ አስቀድሞ በሰፊ የነጥብ ልዩነት ርቆ ቢሄድም ከዚህ በኋላ ሁለተኝነቱን ለማግኘት የሚኖረው የጨዋታ ፉክክር በጣም ምርጥ ይሆናልና በደረጃው ሰንጠረዥ ከእኛ ስር ያሉት ቡድኖች አሁን ወደላይ በነጥብ እየተጠጉ ከመሆኑ አኳያ ይህን ደረጃ ለማሳካት የግድ ከፊትህ ያሉትን ሁሉንም ጨዋታዎች እያሸነፍክ ልትጓዝና በበላይነትም ውድድሩን ልታጠናቅቅ ይገባል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ይህን እድል የሚጠቀምበት ይመስልሃል?
ፍቅረየሱስ፡- ፈታኝ ግጥሚያዎች ከፊታችን እንደሚጠብቀን እናውቃለን፤ ያንን በደንብ ስለተረዳንና ይህን በአፍሪካ ክለቦች የኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ መሳተፍ ደግሞ ለቡድናችንና ለደጋፊዎቻችንም ክብር ስንል በጣም አስፈላጊያችንም ስለሆነ ይሄን አጋጣሚ በሜዳ ላይ ካለን አቅምና ብቃት አኳያ የምንጠቀምበት ይመስለኛል፤ ይሄን እድል ከፈጣሪ እርዳታም ጋር ለማግኘት የራሳችንን የቤት ስራ እስከመጨረሻው ጨዋታ ድረስም በደንብ አድርገን ልንሰራም ይገባል፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለአንተህ ምርጡ እና የተለየ ነበር የምትለው ተጨዋች ማንን ነው?
ፍቅረየሱስ፡- እንደ ራሴ የኳስ ምልከታ በሊጉ በጣም ነጥሮብኝ እና አቋሙም ሳይዋዥቅ ጎልቶ የወጣብኝ ተጨዋች አቡበከር ናስርና አሁንም ስሙን ደግሜ ደጋግሜው ልጠራው እፈልጋለሁ አቡበከር ናስር ብቻ ነው፤ እንደ ቡድን ደግሞ ምንም እንኳን ሙጂብ ቃሲም ለቡድኑ የሚያደርገው ጥሩ ነገር ቢኖርም ፋሲል ከነማ ጎልቶ የወጣ ቡድን ነው፡፡
ሊግ፡- በፕሪምየር ሊጉ ላለፉት 6 እና 7 ዓመታት ያህል ቆይታን እያደረግህ ነው፤ አሁን ላይ ካለህ ልምድ ተነስተህ እንደ አቡበከር ላሉና ለሌሎች ተጨዋቾች ልምድህን የምታካፍልበት ሁኔታ አለ?
ፍቅረየሱስ፡- አዎን፤ ብዙዎች እኔን በዚህ ደረጃ የሚያውቁኝ አሉ፤ ልምዴን ለማካፈል ምንም አይነት ችግርም የለብኝም፡፡
ሊግ፡- የትዳር ዓለምህ በምን መልኩ እየተጓዘ ነው? ለባለቤትህም አንድ ነገርን በል?
ፍቅረየሱስ፡- የትዳር ህይወቴ እስካሁን በጣም አሪፍና በጥሩ መልኩም እየሄደልኝ ነው፤ መልካሟ ባለቤቴም ረድሄት ተሾመ ይህን ህይወት የበለጠ ጣፋጭ ለማድረግ ብዙ ነገሮችን ከእኔ ጋር በመመካከር እያደረገችም ነው የምትገኘውና ለእሷ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለኝ መናገር እፈልጋለሁ፤ ከዛ በተረፈም የእኔ ቆንጆን እንኳን ለፋሲካ በዓል አደረሰሽ ልላትም እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- ቤቴኪንግ ፕሪምየር ሊጋችን በዲ.ኤስ.ቲቪ ስለመታየቱ ምን አልክ?
ፍቅረየሱስ፡- ይሄ እድል መምጣቱ ለእኛ ሀገር ተጨዋቾች በጣም ጥሩ ነው፤ ከዚህ በፊት ፀብና ዳኛ ከበባ በስፋት ይታይ ነበር፤ አሁን ይህ ነገር እየቀረ መጥቷል፤ ብዙ ተጨዋች ችሎታቸውን ለማሳየትም ሲጥሩ ይታያልና ይሄ ለእግር ኳሳችን ለውጥ ሊረዳን ይችላል፡፡
ሊግ፡- በምን እናጠቃል?
ፍቅረየሱስ፡- የፋሲካ በዓል አይደል፤ ከላይ በእንኳን አደረሳችሁ ምኞቴን የገለፅኩላቸው ነበሩ፤ አሁን ደግሞ መቼም ቢሆን ለማልረሳቸው ቤተሰቦቼ እንደዚሁም ደግሞ ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ጭምር በዓሉ የሰላም፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆንላችሁ እየተመኘው፤ ቡናን ደግሞ ለኮንፌዴሬሽን ካፑ ውድድር ለማሳለፍ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ እንደተዘጋጀን ነው፤ ለሁላችሁም መልካም በዓል ይሁንላችሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P