የባህር ዳር ከተማ ክለብ ጋር የነበረውን የውል ጊዜ ካጠናቀቀ በኋላ በድጋሚ ውሉን በማራዘም በክለቡ ደስተኛ እንደሆነ የሚናገረው የአማካይ ስፍራ ተጨዋቹ ሳምሶን ጥላሁን የመጪው ዓመት የሊጉ ተሳትፎአቸው ለዋንጫው ባለቤትነት መፎካከር እንደሆነ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር በነበረው ቆይታ አስተያየቱን ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥቷል፡፡
የባህር ዳር ከተማውን አማካይ በእዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለጋዜጣው የሰጠውን ምልልስም በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል፡፡
በባህር ዳር ከተማ ስለነበረው የተጨዋችነት ቆይታ
“ባህር ዳር ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ክልል ወጥቼ የተጫወትኩበት ክለቤ ነው፤ በእዚህ ክለብ ቆይታዬም ጥሩ ጊዜን ለማሳለፍ ችያለሁ፤ በተለይ ደግሞ ወደ ክለቡ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ በደጋፊዎቹ፣ በአሰልጣኙ ፋሲል ተካልኝ እና በሁሉም የክለቡ አባላት ማለት ይቻላል ተወድጄ እና እኔም በጣም ወድጄያቸው የፕሪምየር ሊጉ ውድድር በኮቪድ 19 እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ መልካም ጊዜን ያሳለፍኩበት ክለብ ስለነበር ደስተኛ ሆኜ ነው ኳሱን በመጫወት ከክለቡ ጋር ያሳለፍኩት”፡፡
ባህር ዳር ከተማ ፕሪምየር ሊጉ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ዓመቱን በምን መልኩ እንዳሳለፈ
“በኮቪድ 19 የፕሪምየር ሊጉ ውድድር እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ክለባችን የነበረው አቋም ከፍተኛ መሻሻልን እያሳየን የነበርንበት ወቅት ላይ ስለነበርን ለእኛ ብዙ ነገሮች ጥሩ ሆኖልን ነበር፤ ከእነዛ መካከልም ክለባችን የመጀመሪያው ዙር ላይ ከነበሩበት ችግሮች መካከል ብዙ ጎሎችን ቢያስቆጥርም በራሱ ላይ ጎል የሚቆጠርበትም አጋጣሚዎች ስላሉ እነዛን ችግሮች የሁለተኛው ዙር ላይ ልንቀርፋቸው ችለናል፤ ብዙ ነገሮችንም አስተካክለናል፤ ሊጉ ባይቋረጥ ኖሮም ስህተቶቻችን የቀነስንባቸው ሁኔታዎች ስለነበሩ እስከ ዋንጫ ተፎካካሪነት መጓዛችን የማይቀርም ነበር”፡፡
ኮቪድ የፕሪምየር ሊጉን ውድድር ባያቋርጠው ኖሮ እስከ ዋንጫው ተፎካካሪነት ለመጓዝ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ያላቸው እንደሆነ
“አዎን በመሪነት ደረጃ ላይም ሆነ በቅርብ ርቀት ላይ ካሉት ክለቦች ውጤት አንፃር በሂሳብ ስሌት እኛ ያለንበትን ስፍራ ስመለከተው በሊጉ ፉክክራችን እስከ ዋንጫው ብሎም ደግሞ ጠንካራ ተፎካካሪ እስከመሆን የሚያስችል ሁኔታ ላይ ነበር የምንገኘው፤ በተለይ ደግሞ ሊጉ የተቋረጠው ከመሪው ፋሲል ከነማ እና በወራጅ ቀጠናው ላይ ይገኝ ከነበረው ሀድያ ሆሳህና ጋር በሜዳችን ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ልናደርግ በተዘጋጀንበት ወቅት ላይም ስለነበር እነዛ ግጥሚያዎችን ማሸነፍ ደረጃችንን ወደላይ ከመውሰድ ባሻገር ነጥባችንንም በጣም እንድናጠብም ያደርገን ነበርና ይሄን ሀሳቤን ነው ልጨምርልህ የቻልኩት”፡፡
የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ላይ ስለነበራቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎን
“ባህር ዳር ከተማ በእዚህ ዓመት የሊጉ ተሳትፎው ጠንካራ ጎኑ ከወገብ በላይ አሪፍ ለመሆን መቻሉ ነበር፤ በእዚህ ቦታ በተለይ ደግሞ በሜዳችን ላይ ስንጫወት ተደጋጋሚ እና ብዙ ጎሎችንም እናስቆጥር ነበር፤ በድክመት ደረጃ የማነሳው ደግሞ የሁለተኛው ዙር ላይ መሻሻል መጣ እንጂ በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ጨዋታዎቻችን ላይ በመከላከሉ ክፍሉ የመናበብ ችግር ነበር፤ ብዙ ጎሎች ለማስቆጠር ብንችልም ግቦች በቀላሉ ይቆጠርብንም ነበርና እነዚህ ናቸው ክፍተቶቻችን”፡፡
ወደ ባህር ዳር አምርተህ ከመጫወትህ አኳያ በክለባችሁ የተመለከትከው ለየት ያለ ነገር
“የባህር ዳር ከተማ ክለብን ለመቀላቀል የቻልኩት ዘንድሮ ነው፤ ወደዛ አምርቼም መጫወት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ በክለቡ ያየሁት የተለየ የሚባል ነገር ቢኖር ደጋፊዎቻችን ልክ በአዲስ አበባ እንደሚገኙት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች ሁሉ እነሱም ለክለባችን የሚሰጡት ጥልቅ የሆነ ድጋፍ እና በስታድየሙ ውስጥም የሚያሳዩት የአደጋገፍ ድባብ የአማረ መሆኑን ነው፤ ይሄን ድጋፍ ደግሞ ለክለባችን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ሲጫወት ጭምር በተደጋጋሚ ጊዜም አሳይተዋል፤ ከዛ ውጪም ከአደጋገፋቸው ምርጥነት ባሻገር ክለባቸውን ከልብ የሚወዱበትንም ሁኔታዎች እንድታደንቅላቸው ያደርግሃል”፡፡
ለቅ/ጊዮርጊስ፣ ለደደቢት፣ ለኢትዮጵያ ቡና ተጫወትክና ነው ወደ ባህር ዳር ከተማ ያመራኸው፤ ስለ ክለብ መቀያየርህ
“የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ከክለብ ወደ ክለብ የምትዘዋወርበት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው፤ እነዛም ከነበርክበት ቡድን ጋር በፊርማ እና በደመወዝ ክፍያ ሳትስማማ ስትቀር፣ ከሚያሰለጥንህ አሰልጣኝ ጋር ሳትግባባ ስትቀር፣ በራስህ የሆኑ ግላዊ ሁኔታዎችና ሌላው ደግሞ ቡድንህ በችሎታ ማነስ ሳይፈልግህ ቀርቶ ሲቀንስህና ሌሎችም በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉና እነዚህ እግር ኳሱ ውስጥ ያሉ ባህሪያቶች ናቸውና በዚህ ተጨዋቾች ከክለብ ወደ ክለብ ሊዘዋወሩ የነበሩበትንም ክለብ ሊቀይሩ ይችላሉ፤ በተጨዋችነት ዘመኔ እኔም ብሆን ከክለብ ወደ ክለብ በማምራት የተለያየ ቡድን ውስጥ ስጫወት ያያችሁኝ ሁኔታዎች ቢኖርም ቅያሪ ያደረግኩባቸው ምክንያቶች ግን በራሴ ውሳኔዎች እና የውል ዘመኔን ከመጨረስ ጋርም ተያይዞ ወደ ሌላ ቡድን የማምራት እድሉንም አግኝቼ ነው፤ ስለዚህም በኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ከክለብ ወደ ክለብ መዘዋወር የሚያጋጥም ነው፤ ዋናው ነገር ይህ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ለምትጫወትበት ቡድን አቅምህ በሚችለው መጠን ሁሉ በቋሚነት የመሰለፍ እድሉን አግኝተህ ጥሩ ግልጋሎትህን መስጠት ነው”፡፡
የእግር ኳስ ተጨዋቾች ከክለብ ወደ ክለብ ሲዘዋወሩ የተረጋጋ የኳስ ህይወት የላቸውም ይባላል፤ ለአራት ክለቦች ከመጫወትህ አንፃር የአንተም እንደዛ ነው ማለት ይቻላል?
“በፍፁም፤ አንድ ተጨዋች የተረጋጋ የኳስ ህይወት የለውም የሚባለው ለሚጫወትባቸው ክለቦች ምንም አይነት ጠቃሚ ግልጋሎትን ሳይሰጥ ቀርቶ ከአንዱ ክለብ ወደ አንዱ ክለብ በማምራት እና በየዓመቱም ወደተለያዩ ቡድኖች በመዘዋወር በርካታ ቡድኖችን ሲያዳርስ እንጂ በሚቆይባቸው ቡድኖች ውስጥ ከአንድ ለበለጡ ዓመታቶች ቆይቶ መልካም የሚባል እንቅስቃሴን ለማሳየት ከቻለ ያ የተረጋጋ የኳስ ህይወት አልነበረውም ማለት አይቻልምና እኔ ነገሮችን የምመለከተው በእዚሁ መልኩ ነው፤ ለእዚህም ነው እኔን በተመለከተ ያለኝ የኳስ ህይወት የተረጋጋ ነው ማለትን የፈለግኩት፤ ምክንያቱም በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትኩት ላሳደገኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ነው፤ በእዚህ ቡድንም ለሶስት ዓመታት ቆይቻለው፤ በቆይታዬም ምንም እንኳን በተደጋጋሚ ጊዜ በቋሚ ተሰላፊነት የመጫወት እድልን ባለገኝም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ግን ለማሳየትም ችያለው፤ ከክለቡ ጋር ለሁለት የፕሪምየር ሊግ የዋንጫ ድልና ለሌሎች ስኬቶችም ልበቃ ችያለው፤ ያም ሆኖ ግን ከክለቡ ጋር የተለያየሁት የቋሚ ተሰላፊነትን ዕድል በተደጋጋሚ ጊዜ ካለማግኘት እና ሜዳ ላይም ገብቶ ከመጫወት ጋር በተያያዘ ስለሆነና ያኔም ከወጣትነቴ አንፃር የራሴን አቅምም ማሳየት አለብኝ በሚል ወደ ደደቢት ክለብ ላመራ ችያለው፤ በደደቢት የአራት ዓመታት ቆይታዬ ደግሞ ከቡድኑ ጋር የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ለማንሳት እና ጥሩ የውድድር ጊዜንም ለማሳለፍ ችያለው፤ በኢትዮጵያ ቡናም ለሁለት ዓመታት ያህል ቆይታን አድርጌና በምችለው መልኩም ጥሩ እንቅስቃሴን አድርጌ ነው የውል ጊዜዬ ከመጠናቀቁ ጋር በተያያዘ ከክለቡ ጋር የምቀጥልበት ሁኔታ ስላልነበር ወደ አዲሱ ቡድኔ ባህር ዳር ከተማ አምርቼ ዘንድሮ ከክለቡ ጋር ጥሩ የውድድር ጊዜን ያሳለፍኩት፤ ይሄ ክለብም በሜዳ ላይ ለቡድኑ ያበረከትኩትን መልካም የሚባል እንቅስቃሴዎቼን ተመልክቶና አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝም ለቡድኑ አስፈላጊ ተጨዋች መሆኔን ተረድቶም አሁንም ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውሌን በማደስ ከክለቡ ጋር የምቀጥልበት ሁኔታዎች ስለተመቻቹልኝ እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው በተረጋጋ የኳስ ህይወት ውስጥ እንዳለሁኝ የሚያመላክቱት”፡፡
ከባህር ዳር ከተማ ጋር ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ለመቀጠል ውልህን አራዝመሃል፤ በክለቡ ተፈላጊነትህ ጨምሯል ማለት ነው?….ወደ ሌላ ቡድን ስለማምራትስ አላሰብክም ነበር?
“በባህር ዳር የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ የውል ጊዜዬን ለሁለት ዓመታት በማራዘም በድጋሚ ከቡድኑ ጋር ልቀጥል የቻልኩበት ዋንኛው ምክንያት ወደ ሌሎች ቡድኖች የማምራት እድሉን ላገኝ ብችልም ለእኔ ግን ጥሩ ነገር መስሎኝ የታየኝ በሁሉም መልኩ እኔን በሚያውቀኝ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ዳግመኛ ብሰለጥን የተሻለ ነው ብዬ ስላሰብኩና በቡድኑ ተፈላጊም ተጨዋች ስለሆንኩ፤ ፋሲልም እንደ አሰልጣኝነቱ የእኔን ከክለቡ ጋር መቀጠልን ለሚገነባው ቡድን አስፈላጊ ተጨዋች እንደሆንኩ ስላስረዳኝ ከክለቡ ጋር ተስማምቼ ውሌን ላድስ ችያለሁ”፡፡
ባህር ዳር ከተማን በአዲሱ ዓመት የፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎው እንዴት እና በምን መልኩ እንጠብቀው?
“ክለባችን በአሁን ሰዓት ያለው የተጨዋቾች ስብስብ በጣም ጥሩ ነው፤ ሌሎች እኛን የሚያጠናክሩልን ልጆችም ወደ ቡድናችን ለመምጣት መቻላቸውም ለእኛ እንደ መልካም ዜና ነው፤ ይህን ካልኩ በእዚህ ስብስብ ላይ አሰልጣኛችን ፋሲል ተካልኝም ቡድን የመስራት ምንም አይነት ችግር ስለሌለበት እና ይህንንም ደግሞ በዘንድሮው የባህር ዳር ከተማ ቡድን የአሰልጣኝነት ቆይታው ላይ ምርጥ ቡድንን ሰርቶ በተግባር ለማሳየት ስለቻለ ከዛ ውጪም በሚጎሉን ነገሮች ላይም የምንሰራቸው ስራዎችም ስላሉ የመጪው ዓመት የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ክለባችንን የምንጠብቀው ለዋንጫው ባለቤትነት ነው”፡፡
ብዙዎች በእግር ኳስ ካለህ ችሎታ አንፃር መድረስ ያለብህ ስፍራ ላይ አልደረስክም ይሉሃል..
“በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ወደ ውጪ ሀገር ወጥቶ ከመጫወት አኳያ ከሆነ ልክ ናቸው፤ በእኛ ሀገር ደረጃም ያን ካላሳካክ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ጊዜ መባላቸው የማይቀር ነው፤ ይሄን አስቀድሞ ባሳብኩት መልኩም እስካሁን ድረስ አላሳካሁትም፤ ከዛ በዘለለ ግን በሀገር ውስጥ በተጫወትኩባቸው ጊዜያቶቼ መድረስ የነበሩብኝ ስፍራዎች ላይ ተገኝቼ ኳሱን እየተጫወትኩ ነው የምገኘው፤ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ባይሆንም ተጫውቼ አሳልፌያለው፤ ባለ ድልም ሆኛለው፤ በደደቢትም ምርጥ የሚባል የጨዋታ ጊዜን ከላይ እንዳስቀመጥኩትም ለማሳለፍ በቅቻለው፤ በቡናም አሁን ደግሞ በባህር ዳር ከተማ ቆይታዬ ጥሩ የጨዋታ ጊዜን ያሳለፍኩባቸው ወቅቶች ስለነበሩና በብሔራዊ ቡድን ውስጥም ተመርጬ ቆይታን ያደረግኩባቸው ጊዜያቶች ስለነበሩ በሀገር ውስጥ ደረጃ መገኘት ያለብኝ የኳስ ደረጃ ላይ ነው ልደርስ የቻልኩት”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ መዝናናትን በጣም ያበዛል ስለመባልህ
“መቼም የሰው ፍጡር ነኝና አልዝናናም አልልህም፤ አልዝናናም ብዬም መዋሸትን አልፈልግም፤ ሁለት አይነት መዝናናትም ስለሌለ ከስራ ውጪ ባሉኝ ጊዜያቶቼ ራሴን ጠብቄ በደንብ እዝናናለው፤ ከዛ ውጪ ያለውን ጊዜ ደግሞ እግር ኳስን መጫወት ባለብኝ ሰዓት ሜዳ ገብቼ ኳስን እጫወታለው”፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዳግመኛ ስለመመረጥ
“በባህር ዳር ከተማ ክለብ የእዚህ ዓመት የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ላይ ብሔራዊ ቡድናችን ከኮትዲቭዋር ጋር ያደረገውን ጨዋታ እንደተመለከትኩ በጣም ከመጓጓቴ አንፃር የእውነት ይሄን ቡድን ዳግመኛ ስለመቀላቀሉ በጣም ነበር ሀሳቡ የነበረኝ፤ ምክንያቱም በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የተመራው ቡድን እግር ኳስን በጥሩ መልኩ የሚጫወትና እኔም ደግሞ ልጫወትበት የምፈልገው አይነት እንቅስቃሴም በመሆኑ ነው፤ ይሄ ቡድን ከዛ ውጪም ሜዳ ላይ የነበረው የመጫወት ነፃነት የሚያስገርም ነበር፤ ያለ ምንም አይነት ጫናም ነበር ኳሱን በጥሩ የራስ መተማመን ስሜት ላይ ሆነውና በውስጣቸው ያለውንም እምቅ አቅምም ጭምር በማውጣት ሲጫወቱ የነበሩትና አሁን ላይ ካለኝ የወጣትነት እድሜ አንፃርና ኳስንም ገና ጠግቤ ያልተጫወትኩ ከመሆኔ አኳያ ይሄን ቡድን ዳግም ስለመቀላቀል እያሰብኩ ነው”፡፡
በኮቪድ 19 ከእግር ኳሱ ከተራቀ አሁን ወደ 6ኛው ወር እያመራን ይገኛል፤ ይሄ እንደ ተጨዋችነትህ በአንተ እይታ ሲታይ….?
“ከኳስ ለእዚህን ያህል ጊዜ ከሜዳ መራቅ በጣም ይከብዳል፤ ምክንያቱም ኳስ ጨዋታ ብዙዎች የሚዝናኑበት እና የደስታ ስሜትንም የሚያገኙበት ስፖርት ስለሆነ፤ ከዛም ባሻገር ለስፖርተኛውም ከመዝናናት በተጨማሪ ኳሱ የገቢ ምንጩም በመሆኑ ያለዛ መቆየት መቻል እኛን ተጨዋቾች ብቻ ሳይሆን ተመልካቾችን እና ኳስን የማይጫወቱትን ጭምር ድብርት ውስጥ እንዲገቡም ያደርጋቸዋልና በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘው፤ ስለዚህም ወደ ኳስ ጨዋታው ተመልሶ መምጣት አሁን ላይ በጣም ናፍቆኛልና ወደዛ ስለምናመራበት ነገሮች ነው ማሰብ የሚኖርብን፤ ለእዚህ ደግሞ ራሳችንን ከአስከፊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሚገባ በመጠበቅና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከመንግስትም የሚወጡ መመሪያዎችን በማክበር ጭምር ፈጣሪ ረድቶን ጥሩውን ነገር እንዲያመጣልን ነው የምመኘው”፡፡
በመጨረሻ..?
“በቅርቡ በህዳሴ ግድቡ ሙሌት ሀገራችን ወደ ላይ ከፍ ያለችበትን ነገር እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለመመልከት በመቻሌ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ለእዚህ ግድብ ሙሌት እንደዜግነቴም በ8100 ኤ ቦንድ በመግዛት ጭምርም ሀላፊነቴን እየተወጣሁ ይገኛል፤ ለሁላችንም ሀብታችን ለሆነው ለእዚህ ግድብ በቀጣይነትም ሁላችንም ከፍተኛ ድጋፍን እንድናደርግም መልህክቴን አስተላልፋለው፤ ከዛ ውጪ ማለት የምፈልገው ኮቪድን ፈጣሪ አጥፍቶልን በፍጥነት ወደ ምንወደው እና ወደ ናፈቀን እግር ኳስ እንድንመለስ እና በደጋፊዎቻችን ጭምርም እንድንጫወት እሱ ይርዳንም ነው የምለው”፡፡
“ፕሪምየር ሊጉ ባይቋረጥ እስከ ዋንጫ ተፋላሚነት እንደርስ ነበር” ሳምሶን ጥላሁን (ባህር ዳር ከተማ)
ተመሳሳይ ጽሁፎች