Google search engine

“የካሳዬ አራጌ የጨዋታ ፍልስፍና ብቻውን ቡናን ውጤታማ አያደርገውም”ሮቤል ተክለሚካኤል /ኢትዮጵያ ቡና/

“ስለ ዋንጫ ካሰብን እንደ ቅ/ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ የስኳድ ጥልቀት ሊኖረን ይገባል”

በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ጥሩና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን እያሳየ ይገኛል። ለቡድኑ ጥሩ ጥቅምን በመስጠት በኩልም ወደ ደጋፊው ልብ ውስጥ በመግባት ላይ ይገኛል። ይሄ ተጨዋች ለኤርትራ ብሄራዊ ቡድን ሲጫወት ታይቶና ተመልምሎ ወደ ቡና የተቀላቀለው ሮቤል ተክለሚካኤል ሲሆን ተጨዋቹን ኢትዮጵያ ቡና ሰበታ ከተማን በእሱና በአቡበከር ናስር ሁለት ግቦች 2-0 ካሸነፈ በኋላ ተጨዋቹን በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ የሊግ ስፖርቱ ድህረ-ገፅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርቦለት ምላሽን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶታል። ተከታተሉት።
በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ምርጥ እና ታሪካዊ ግብ ስለማስቆጠሩ

“እንዴ! ግቧ ታሪካዊ ነው እንዴ የምትባለው?”።
አዎን።

በ1990ዎቹ ጅማሬ አንዳርጋቸው ሰለሞን እንዲህ ያለ ግብ አስቆጥሮ ነበር።

“ያ ከሆነ በጣም ደስ ይላል”።

ከቅ/ጊዮርጊስ ሽንፈት መልስ ሰበታ ከተማን ስለረቱበት ጨዋታ

“ከእዚህ ግጥሚያ በፊት መሸነፋችን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ እንድንገባ ስላደረገንና በጨዋታው ላይም ስለተነጋገርንበት ነው ጠንከረን ወደ ሜዳ ለመግባት በመቻላችን አሸናፊ ለመሆን የቻልነው። በእዚህ ጨዋታ ሰበታ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ጫና እየፈጠሩ ነበር። ከእረፍት በኋላ ደግሞ ቡድናችን በእንቅስቃሴ ደረጃ እየተስተካከለ መጥቶ ውጤቱ ለእኛ አሪፍ ሊሆን ቻለ”።

ድሉ ለእናንተ ይገባችኋል?

“አሆዋ፤ እንዴ! ለምንድን ነው የማይገባን። ስለተገባንም ነው ጨዋታውን ያሸነፍነው”።
በጨዋታው እናንተ የተሻላችሁ ነበራችሁ?
“አዎን በሚገባ! ምክንያቱም እነሱ ወደ እኛ ክልል ቢመጡም የመከላከል ክፍሉ ላይ በምንሰራው ጥቃቅን ስህተት ነው የግብ ሙከራን ሲያደርጉብን የነበሩት። የእኛ ሙከራ እና የግብ ማስቆጠር ብቃታችንን የፈጠርነው ግን በጨዋታ መስርተነው በመጣነው ነገር ስለነበር እኛ ልንሻል ችለናል”።

ሰበታ ከተማን ለማሸነፍ ስላስቻላቸው ጠንካራ ጎንና ከእነሱ ተጨዋቾች ውስጥ ስላደነቀው

“ጠንካራው ጎናችን የነበረው በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ውጤት አጥተን ስለነበር ይሄን ግጥሚያ ለማሸነፍ ከበረኛችን አንስቶ እስከ አጥቂው ክፍል ድረስ ወደ ሜዳ በወኔ መግባታችንና የማሸነፍ ግዴታ ውስጥም መግባት እንዳለብን ስለተነጋገርንበት እና በጥሩ መልኩም ልንንቀሳቀስ ስለቻልን ነው ። ከሰበታ ከተማ ተጨዋቾች ውስጥ ደግሞ ያደነቅኩት አጥቂዎቻቸውን ነው። ጥሩ ነበሩ፤ በተለይም ደግሞ 2 ቁጥራቸው፤ ከእሱ ውጪም 16 እና 7 ቁጥሩም ይለዩ ነበር”።

በሸገር ደርቢው በቅ/ጊዮርጊስ በቅርቡ በሰፊ ግብ ሲሸነፉ ስለተፈጠረባቸው ስሜትና የሽንፈቱ ምክንያት

“በእዚህ ጨዋታ ላይ አራት ግቦች ተቆጥሮብን መሸነፋችን ያልጠበቅኩትና ያልተቀበልኩት ነው። ግቡም ብዙ ነው። ያም ሆኖ ግን ቅ/ጊዮርጊስ ወደ ሻምፒዮናነቱ ግስጋሴ እየሄደ ያለና ከበረኛም አንስቶ እስከ አጥቂው ክፍል ድረስ ከእኛ በተሻለ በጣም ጠንካራ ክለብ ስለሆነ እና እኛ ላይ ደግሞ ትንሽ የጨዋታ ድካምም ስለነበረና የመበረታታትና ወኔም ስላልነበረን በእዚህ ሁኔታ ተሸንፈናል”።

በሽንፈቱ ደጋፊዎቻቸው ስለማዘናቸው

“ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት ደጋፊዎቻችን በጣም ብዙ ሆነው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። ከቅ/ጊዮርጊስ በቁጥር ደረጃም ይበልጡ ነበርና ጨዋታውን ስንሸነፍ በጣምም ነው ያዘኑትና የተናደዱት ለእዛም እነሱን ይቅርታ ልንል እንፈልጋለን። የደጋፊው ነገር በሚመለከት በሰበታው ቀን ጨዋታ በቅ/ጊዮርጊስ የደረሰብንን ሽንፈት መነሻ አድርገው አዝነው የቀሩ ደጋፊዎች ነበሩ። እነዚህ ደጋፊዎችም ቡድኑን በጣም ስለሚወዱት በቀጣዩ ጨዋታዎቻችን በእርግጠኝነት ይመጣሉ ብዬም ነው የማስበው”።

ከመሪው ክለብ ቅ/ጊዮርጊስ በበርካታ ነጥቦች ስለመራቃቸው እና የዘንድሮን ውድድር በምን ውጤት እንደሚያጠናቅቁ

“እኛ ከዚህ በኋላ ስለ ሌላው ቡድን ማሸነፍና መሸነፍ ላይ ሳናተኩር ነው እያንዳንዱን ጨዋታዎች ለማሸነፍ የምንጫወተው። ለእዛም ጠንክረን እየሰራን ነው። አንደኛ ከወጣን እሰየው ነው የሚባለው። ነገር ግን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነን ሊጉን ለመጨረስም እነ ወላይታ ድቻን እንዲሁም ሌሎቹን በእሱ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙትን ቡድኖችም በነጥብ መብለጥ አለብንና ለኮንፌዴሬሽኑም ካፕ ለማለፍ ጥረትን እያደረግንም ነው”።

ኢትዮጵያ ቡና ለወደፊቱ የዋንጫ ባለቤት እንዲሆን መስራት ስላለበት

“ስለ ዋንጫ ካሰብን በቅድሚያ በቅ/ጊዮርጊስ እና በፋሲል ከነማ አይነትና ተመሳሳይነት ደረጃ የስኳድ ጥራት ሊኖረን ይገባል። ግብ ጠባቂው፣ ተከላካዩ፣ አማካዩና የአጥቂው ክፍልን እንደ እነሱ ተጨዋቾች ልናደርግና ቡድኑን በእዛ መልኩም ገንብተን ልንሰራበት ይገባል። በእዛ መንገድ ለመሄድ ካልቻልን ግን የእኔ ሮቤል ወይንም ደግሞ የሌላ ተጨዋች የካሳዬ አራጌን ልምምድ መስራት ብቻ ቡናን ተጠቃሚ አያደርገውም። ቡናን ተጠቃሚ የሚያደርገው
የካሳዬ አራጌ ስራ ብቻ አይደለም። እኛን ለውጤት የሚያበቃን የካሳዬ አራጌ የአጨዋወት ፍልስፍናው እንዳለ ሆኖ ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ ሲኖረንና እኛም ተጨዋቾች በግልም በቡድንም ልምምዳችንን ጠንክረን ስንሰራም ነው። የተጨዋቾችን ጥራት በተመለከተ ኢትዮጵያ ቡና 11 ቋሚ ተሰላፊ ተጨዋቾች ቢኖሩትም ተቀይረው የሚገቡት ልጆች ልምድ የሌላቸው ናቸው። ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስታመራ ደግሞ ተቀይረው የሚገቡት ልጆች ካላቸው ልምድ አንፃር ልዩነትም መፍጠር የሚችሉ ናቸውና ይሄን ነው ለማለት የምፈልገው”።

በሰበታ ከተማ ላይ ያስቆጠራትን ግብ ከእዚህ ቀደም አግብቷት እንደሆነ

“በአስመራ ሳለው በግራ እግሬ መትቼ እንዲህ ያለ ግብ ከፔናሊቲ ሳጥን ክልል ውጪ አግብቻለው። በባህርማዶዎቹ ቀን አቆጣጠርም በ2019 ላይ ደግሞ ኤርትራና ኬኒያ ሲጫወቱ በረኛቸው በተደጋጋሚ ይወጣ ነበርና ሌላ ተጨዋች ያስቆጠረበትን ጊዜ አስታውሳለው፤ የእኔ ተመሳሳይ ግብ ግን አንድ ናት ያገባሁት። እሷም ለቀይ ባህር ስጫወት ማይተመናይ በሚባል ቡድን ላይም ነው ያስቆጠርኩት”።

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን እንዴት አገኘኸው?

“ካላቸው የተጨዋቾች ስብስብ እና ጥንካሬያቸው አንፃር ታምር ካልተፈጠረ በስተቀር ቅ/ጊዮርጊስ ዋንጫውን የሚያነሳ ይመስለኛል”።
በኢትዮጵያ ቡና ቆይታህ ደስተኛ ነህ?
“አዎን፤ በጣም ደስተኛ ነኝ”።

ደጋፊዎቻቸው እሱን እያወደሱት ከመሆኑ አንፃር ሲገልፃቸው

“ስለ ቡና ደጋፊ ማውራት ቃላት ያጥረኛል፤ በደረጃው ሰንጠረዥ አይደለም አሁን በምንገኝበት ደረጃ እታች በ10ኛው ስፍራ ላይ ሆነን እንኳን በእዚህ ደረጃ እንደ ቡና አይነት ደጋፊ ክለብን የሚያበረታታ ደጋፊ በህይወቴ አይቼ አላውቅምና እነሱ ይለያሉ ነው የምለው”።

አጠቃላይ የቤትኪንግ ፉክክሩ ለአንተ ምን ይመስላል?

“አስመራ ላይ ሆኜ ስጫወት ይኸው ፍክክር እንዲህ ጠንካራና ጥሩ ይሆናል ብዬ የምናገር አልመሰለኝም ነበር። ሊጉ ቀላልም ነው የመሰለኝ። አሁን ግን በጣም ሌላ ነገርን ነው እየተመለከትን የምንገኘው። እንደ ሰበታ እና ጅማ አባጅፋር ያሉት ቡድኖች በደረጃው ሰንጠረዥ እታች ሆነው ምን አይነት ጨዋታን ተጫወቱ የሚለውን ስመለከት እኔ ራሴ ገርሞኛል። ሁሉም ቡድን ጠንካራ ነው። ሊጉ ከጨዋታው ባሻገር በበጀቱና ጨዋታዎቹ በዲ ኤስ ቲቪ እየተላለፈም ስለሆነ ጥሩነቱን አሳይቶናል። ከዛ ውጪም እኔ አሁን የገረመኝ በአስመራ እያለው ያገባሁት ግብ የለም። በቪዲዮ ደረጃ አይቼውም አላውቅም። በሰበታ ላይ ያገባዋት ግብ ግን እዚህ በቪዲዮ አለ። ሴቭ አድርገህም ታስቀምጠዋለህ። ለእኔ ጥሩ ማስታወሻም ይሆናል። ከእዛም በተጨማሪ ወደፊት ወደ ውጪ ሄደህ ለመጫወትም ለኤጀንትህም ትሰጣለህና ይሄን ነው ልል የምፈልገው”።

ስለ ቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቱ

“በኢትዮጵያ ቡና ቆይታዬ ጥሩ ስራን ሰርቼ ወደ ውጪ ሀገር በመውጣት መጫወትን ነው የምፈልገው”።

በመጨረሻ…?

“መጀመሪያ ሁሉ ነገርን ላደረገልኝ ፈጣሪዬ ትልቅ ምስጋና አለኝ። ከእሱ በታች ደግሞ ቤተሰቦቼ እኔን ስላበረታቱኝና ስለደገፉኝ። እንዲሁም ከእነሱ ውጪ በኤርትራ ላሉ ደጋፊዎቼና ሁሌም አንደኛ ናቸው የምላቸውንን የቡና ደጋፊዎችን ማመስገን እፈልጋለው”።

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P